የሀገር ካስማ… ሴት

ሴትነትን ስናነሳ እህት፤ ልጅ፤ ሚስት ከሚለው በላይ እናትነት በብዙኃኑ ልብ ላይ ገዝፎ ይታያል። በምድር ላይ እናቱን የማይወድ ፍጡር አለ ቢባል የመልካም ልብ ባለቤት አልያም ሰዋዊ ስሜትን የተላበሰ ነው ለማለት ያስቸግራል። እናላችሁ የምድር ሚዛን ጠባቂ የሆነችው ሴት ዓለም ካላት ሃብት እኩል ተጠቃሚ እንድትሆን አለማድረጉ ንፉግነት አይመስላችሁም?

የሃገር ካስማ ሴት ሆና ሳለች ስለሃገር ወጥታ ስትናገር አድማጭ የምታጣበት እና ተዓማኒ የማትሆንበት ጉዳይ አሁንም ለምን የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ዘመናዊ የተባሉት የዓለም ክፍሎች ላይ ሳይቀር እስካሁን የሴትን ልጅ እኩል ተጠቃሚነት ሙሉ በሙሉ ሳያረጋግጡ ቆይተዋል። ለውሳኔ ሰጪነት እሷን ወደ ኋላ ከማስቀረት ይልቅ ለእሷ የታያት በቂ ነው ብሎ መቀበሉስ ምኑ ላይ ነው ክፋቱ ብዬ እጠይቃለሁ። ሴት ቢያውቅ… በወንድ ያልቅ የሚለው የሀገራችን ብሂል ሴቶች ለብቻቸው አይወስኑም አይችሉም ወደሚል አንድምታ ሲወስዱት ይታያል። ዓለምም በዚሁ መርሕ እየተመራች ስለመሆኗ በተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እስካሁን በየትኛውም ሀገር ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ አለመቻሉ ታላቅ ማሳያ ነው።

እስከዛሬ በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎች የተነሳ ጉልህ ለውጦች አሉ። ዓለምም በወንዶች ብቻ የነበረውን ሥርዓቷን ቀይራ ሴቶች ያላቸውን አቅም እና ሰብዓዊ መብታቸውን እንዲያረጋግጡ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ። ነገር ግን አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ የፆታ እኩልነትን ለማስመዝገብ ታላቅ ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ በመቀጠል ላይ ነው። ሴቶች ውሳኔ ሰጪነትን በሚጠይቁ ቦታዎች ላይ የመቀመጣቸው ነገር የማይዋጥላቸው ሰዎች አሉ። ይህንንም የሚያያይዙት ባላት ሩህሩህ የሆነው ተፈጥሯዊ ባሕሪዋ ነው። ነገር ግን ደግሞ በተለያየ ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሴቶች ደግሞ ሥራቸውን እጅግ በቁርጠኝነት እና ችላ ባለማለት ጥንቅቅ አድርገው የተሰጣቸውን ሥራ ኃላፊነት እንደሚወጡ ደግሞ ብዙዎች የሚመሰክሩት ጉዳይ ጭምር ነው ።

አሁንም ድረስ ግን ሴቶች በመሪነት የተቀመጡባቸው ቦታዎች ላይ በተለያዩ የዓለም ሀገራት መድልዎ፣ ጥቃት፣ የትምህርትና የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት ውስንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ልዩነቶች ይደርስባቸዋል። የዚህን ችግር መጠን ለማሳየት በተለያዩ ዓለማቀፍ ጥናቶች የተደገፉ አኃዛዊ መረጃዎችን እንመልከት።

በሴቶች እና በወንዶች ያለውን የኢኮኖሚ ልዩነት ስንመለከት፤ ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በአማካይ ከወንዶች በ23 በመቶ ያነሰ ገቢ ያገኛሉ ይህ በጉልበት ሥራ ላይ የተሰማሩ እና በጉልበታቸው ብቻ በሚመዘኑ የሥራ መስኮች ላይ ብቻ ሳይሆን እኩል የትምህርት ዝግጅት ያላቸው እና እኩል የመመረቂያ ነጥብ ይዘው በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ ያሉ ሲሆን ነገር ግን የሚከፈላቸው ክፍያ ከወንድ የሥራ ባልደረቦቻቸው ያነሰ መሆኑ ነው። ሴቶች በአመራር ቦታዎች ላይ ያላቸው ውክልና ፣ ተሳታፊነት ሲታይም ዝቅተኛ ነው። በፓርላማ ውስጥም መቀመጫ ማግኘት የቻሉት 24 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ብቻ ናቸው።

በትምህርት ላይም የልጃገረዶች የትምህርት ተደራሽነት የተሻሻለ ቢሆንም በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሟቸው ይገኛል። ከነዚህም ውስጥ እንደ ያለ አቻ ጋብቻ እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ያሉ የተለያዩ ባሕሎች ምክንያት ሴቶች የመማር እድላቸው ላይ መሰናክል ሆኖባቸዋል። እነኝህን በመሳሰሉ ችግሮችም በዓለም ዙሪያ በግምት ከ130 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች ከትምህርት ቤት ውጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሦስት ሴቶች አንዷ በሕይወት ዘመኗ አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት ይደርስባታል። በሴት ልጅ ግርዛት እና ያለአቻ ጋብቻ ባሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሁንም በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ልጃገረዶች ይጎዳሉ። ይህም በትምህርት እራሳቸውን ከፍ አድርገው እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ጉዞ በአጭሩ የሚያስቀር ነው።

አሁን ላይ በየሀገራቱ የሴቶችን ተሳትፎ ለመጨመር በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ችግሩን ከስሩ ለመንቀልና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በዋናነት የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎች ሊደረጉ ይገባል። መንግሥታት የፆታ እኩልነትን የሚያረጋግጡ እና የሴቶችን መብት የሚያስጠብቁ ሕጎችን አውጥተው ማስተግበርም ይገባቸዋል። በሕጎችም ሴቶች እንደ ወንዶች ሁሉ ለሚሠሯቸው ተመሳሳይ ሥራዎች እኩል ክፍያ እንዲያገኙ የሚያስገድድ፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና በሁሉም ዘርፍ የሚደርሱ አድሎዓዊ ጉዳዮችን መፍታት የሚችል መሆንም አለበት ።

የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ፆታ ተኮር የሆኑ ፖሊሲዎች መተግበር አለባቸው፤ ከእነዚህም መካከል ሴቶች እኩል ክፍያ፣ ብድር የማግኘት ዕድል እና የሥራ ፈጠራ ድጋፎችን እንዲሁ ሊያገኙ ይገባል። የግል ሴክተሩም የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን እንዲያበረታታ እና አድሎዓዊ ድርጊቶችን እንዲያስወግድ ማበረታታት አስፈላጊ ነው ።

በጤና እና ደህንነት ዘርፉም መንግሥታት እና ድርጅቶች ለሴቶች ጤና ቅድሚያ መስጠት አለባቸው። ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ማረጋገጥ እንዲሁ ሊሠራበት የሚገባ ዘርፍ ነው። በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመፍታት መሥራትም አለባቸው። ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ለመቅረፍም ለሴቶች የተለያዩ የድጋፍ አገልግሎቶችን መስጠት፣ አካባቢዎች ደህንነታቸው የተጠበቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ እና የሕግ ጥበቃን እና ከለላን መስጠት ወሳኝ ነው። ሴቶች በሚደርስባቸው ጥቃቶች በሕግ የተደነገጉ ውሳኔዎች አለማክበር ከተጠቂዎች እና ጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ አካላት በተደጋጋሚ የሚቀርብ አቤቱታ በመሆኑ በወረቀት ላይ ተጽፈው የሚገኙ ሕጎችን ከማስፈጸም ባሻገር፣ ሴቶች የሚደርሰውን ጥቃት ለመቀነስም ሆነ ለማስቀረት ጥብቅ የሆኑ ሕጎችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ሴቶች በሥራ ቦታቸውም ሆነ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ደህንነት እንዳይሰማቸው የሚያደርግ በመሆኑ ሕጎች ተግባራዊ መደረጋቸው ስጋት የተሞላበትን እንቅስቃሴ የማስቀረት አስተዋፅዖ አለው። በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት ደርሶባቸው ጥቃት አድራሹ አካል ውሳኔ ቢሰጠውም እንኳን ውሳኔው በተገቢው መንገድ አለመተግበር፣ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊትም ሆነ በኋላ ባጠቃቸው አካል ተደጋጋሚ የሆነ ጥቃት የሚደርስባቸው በመሆኑ ጥቃት የደረሰባው ሴቶች ሪፖርት ከማድረግ እንዲቆጠቡ እና በስጋት እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል በመሆኑም ጥቃት ላደረሰው አካል ሳይሆን ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ከለላ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ።

በዓለም አቀፍ ትብብር በኩልም እንዲሁ በመንግሥታት፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና በሲቪል ማኅበረሰብ መካከል ያለው ትብብር የዓለም አቀፍ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው። ሴቶችን ብቁ በማድረግ እና እድል በመስጠት ፣ ሴቶች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ተገቢውን ቅጣት የሚሰጡ እና መሰል ፆታዊ ጥቃቶች እንዳይስፋፉ የሚሠሩ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን እና ግብዓቶችን መጋራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እድገትን ለማፋጠን ሚናው የላቀ ነው።

ለሴቶች ተጠቃሚነት ሌሎች አካላትን ከመጠበቅ ይልቅም እራሳቸው የጉዳዩ ባለቤቶች ሴቶች ወደፊት የሚወጡበትን ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ራሳቸውን በኢኮኖሚም ሆነ በእውቀት እኩል ተወዳዳሪ ለማድረግ ተግተው መሥራት ይኖርባቸዋል። ለዓለም በርካታ ነገሮችን የሚሰጡት ሴቶች ከሰጪነት አልፎ ራሳቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚተጉ መሆን ይገባቸዋል።

በተጨማሪም ዕድሉን አግኝተው በተለየ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሴት መሪዎችም ሴቶች ያላቸውን አቅምም ሆነ ችግር ለመረዳት የሚችሉ በመሆናቸው በተሰጣቸው ኃላፊነት ሕጉን በተከተለ መልኩ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሠሩ እና ዕድል ላላገኙ እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች ድምፅ መሆን ይገባቸዋል። ሴት እናት፤ ሚስት፤ እህት፤ በአጠቃላይ የዓለም ሚዛን ጠባቂ የሆኑት ሴቶች የመሪነት ሚናቸውን ለመወጣት ዓለም ባላት ተፈጥሮ እኩል ተጠቃሚ ለመሆን የራሳቸውም ሆነ የሌሎች ኃላፊነት በጉልህ እንደሚጠበቅ ልብ ያለው ልብ ይበል ብዬ አበቃሁ።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016  ዓ.ም

Recommended For You