ጸሐፊው ይፃፍ፤ ሰዓሊውም ይሳል፤ ሙዚቀኛውም ያንጎራጉር:: ያልወጣ የታፈነ የተዳፈነው ሁሉ ይገለጥ:: ልቡን የሚያነፃ እና የልቦና አይኑን የሚከፍት በውበት ውስጥ የሕይወትን ታላቅ ፀጋ ይጎናፀፋል፤ ብሎም ይከውናል:: ለእነዚህ የጥበብ ሰዎች ደግሞ የሀሳብ መገኛ ስለሆኑ ውበት እና ፍቅር ለዘላለም ይኑሩ::
ውበት እንደ ተመልካቹ ነው! ሁሉም ሰው ስለ ውበት የራሱ የሆነ መግለጫ አለው ሁሉም ሰው ውበትን በራሱ ሚዛን ይለካል፤አንዱንም ከአንዱ ያስበልጣል ። በመልካም ስብዕና ላይ ማራኪ ገጽታ የሚቸራቸው ደግሞ ይለያሉ።
ታዲያ ለዛሬ እንዲህ ያለ የተሟላ ውበት የተላበሰች አገሯን በዓለም መድረክ ያስተዋወቀች እንስት ጋብዘናል። የክብር ዶክትሬት በናይጀሪያ ከተማ ላይ ተበርክቶላታል። በሙያዋ ዓለም አቀፍ የፋሽን ዲዛይነርና ሞዴሊስት ነች።ይቺ አገር ወዳድ በአገሯ መልካም ስራ ላይ ተሰማርታለች። በተለይም ስራ አጥነትን ለመቀነስ የምታደርገው ጥረት ከእሷ አልፎ ተርፎ ጣሊያኖች አይናቸውን እንዲከፍቱ ምክንያት ሆናለች የዛሬው የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› አምድ እንግዳችን ዲዛይነርና ሞዴሊስቷ ሰናይት ማሪዮ። ከእሷ ብዙ የምንማረው አለና እስኪ አጫውቺን ብለናታል፤ መልካም ንባብ!
“የዳቤ” ልጅነት
ሰናይት እንደዛሬው ሞዴልነት ላይ የሚያደርስ ቅርጽ አልነበራትም። በጣም ወፍራም ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በወላይትኛ ዳቤ በአማርኛው ደግሞ ዳቦ የሚለው ቅጽል ስም ወጥቶላት ነበር። እናም በዚህ ስሟ የአካባቢው ሰውም ሆነ ቤተሰቦቿ ይጠሯታል። በወቅቱ በትምህርቷ ጎበዝ ስለነበረች ዶክተርና ፓይለት የመሆን ምኞት እንደነበራት ትናገራለች።
በልጅነቷ ተጨዋች፣ ታዛዥና በቤት ውስጥ ብዙ ስራ የምትሰራ እንስት እንደነበረች የምትገልጸው ዲዛይነር ሰናይት፤ የማትሞክረው የቤት ውስጥ ሥራ እንዳልነበረና ሥራውን የምትሰራው ከጫና አንጻር ሳይሆን ስራ እንድትለምድ ተብሎ እንደነበር ታነሳለች።
ሰናይት የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ነች። ይህም በአባቷ በጣም እንድትወደድ አድርጓታል። ከቀረቤታቸው አንጻርም አባቷን የምታየው እንደ ጓደኛ ነው። ይህ ቀረቤታቸው ሁሉን ነገር በነጻነት እንድትከውን እንዳገዛት ትናገራለች።
የወላይታ ሶዶ እንቁዋ ዲዛይነር ሰናይት «ዋሞራ» ተብላ በምትጠራው የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው የተወለደችው። እድገቷ ደግሞ ለሶዶ ቅርብ በሆነችው «አሮጌው አራዳ» ተብላ በምትጠራ ከተማ ውስጥ ነው። ዛሬ ይህቺ ገጠር ከተማ ሰፍታ ወላይታ ሶዶን ተቀላቅላለች። ስለዚህም ከዞኑ ሳትወጣ የልጅነት ጊዜዋን አሳልፋለች።
‹‹ለስኬት መስራት ከልጅነት ጀምሮ ያደገ ባህሪዬ ነው። ወድቆ መነሳት ለእኔ ቀላል ነው። አልችለውም የምለው ነገርም እንዳይኖርም እድል ሰጥቶኛል።» የምትለው የትናንቷ ህጻን የዛሬዋ ወጣት ዲዛይነር ሰናይት፤ በልጅነቷ የጀመረችው ማንኛውም ሥራ በሌላ አካል ከተደናቀፈ የበኩሏን እንዳደረገች ስለሚሰማት ወደፊት መጓዝን ብቻ እንደምትመርጥ ትናገራለች።
የእነሰናይት ቤተሰብ ብዙዎች የሚያድጉበትና ለቁምነገር የሚበቁበት ነው። በዚህ ደግሞ ሰናይት ቤተሰቡን ለመመገብ ሲባል ብዙ ስራዎችን ታከናውናለች። ነገር ግን የጥናት ጊዜዋን በምንም መልኩ እንዲነካባት አትፈልግም። ቤተሰቦቿም ቢሆኑ ፕሮግራም በማውጣትና በማስጠናት ያግዟታል። በእርግጥ «የተማረ ይግደለኝ» አይደል የሚባለው ቤተሰቦቿ ማለትም እናትና አቧቷ የትምህርትን ጥቅም ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በምትፈልገው ነገር ሊደራደሯት አይፈልጉም።
ሌላው የዲዛይነር ሰናይት የልጅነት አቅም ረጅም ጉዞ ማድረጓ ሲሆን፤ በቀን ውስጥ ከአምስት ኪሎሜትር በላይ ትጓዛለች። ይህ ደግሞ ለዛሬ ቅርጿ መምጣት መሰረት ሳይሆን እንዳልቀረ ትናገራለች።
ከወላይታ እስከ …
«የደረጃ ተማሪ አለመሆን በእኛ ጊዜ ያስቀጣ ነበር» የምትለው ዲዛይነርና ሞዴሊስቷ ሰናይት፤ የሁለተኛም ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን እስክታጠናቅቅ ድረስ ከ1ኛ እስከ 3 ኛ ደረጃ ነበር የምትወጣው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው በአደገችበት ከተማ በሚገኘው ትግል ፍሬ ትምህርት ቤት ነው።
ቀጣዩን ትምህርቷን ደግሞ ሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች። የአስራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት ሲመጣ ግን ወላይታን መልቀቅ ግድ ሆነባት። ሐዋሳ መምህራን ኮሌጅ ገባች። በኮሌጁ ቋንቋ አጥንታ በዲፕሎማ ተመርቃለች።
የትምህርት ጥማቷን ያላረካችው ዲዛይነር ሰናይት፤ ለስራ አዲስ አበባ ሄዳ እንኳን አላረፈችም። ቀን እያስተማረች ማታ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት መማር ጀምራ ነበር። ሆኖም ይህንን ትምህርት አላጠናቀቀችውም። ምክንያቱ ደግሞ የበለጠ የመማር እድል ማግኘቷ ነው።የውጪ የትምህርት እድል በኬኒያ መንግስት ተሰጣት። እናም ወደ ዩጋንዳ ሄደች። በዚያም የሶሾሎጂ ትምህርት አጥንታ በዲግሪ ተመረቀች።
በሙያዋ አገሯን በማገልገል ላይ ሳለች መማር የሁልጊዜ ፍላጎቷ ነውና በትዳር ወደ ጣሊያን አመራች። ይህ መሆኑ ደግሞ ሁለት እድሎችን እንዳቀዳጃት ትናገራለች። የመጀመሪያው ዛሬ የምትሰራበትን ሙያ ማለትም ሞዴሊስትነቱንና ዲዛይነርነቱን ሰጥቷታል። ሁለተኛው ደግሞ በአለም እንድትታወቅ አስችሏታል። ለዚህ መንስኤው ደግሞ ጣሊያን አገር በሚገባ ተግባብታ መኖር ስላለባት ጣሊያንኛ ቋንቋን ለመማር ከዩጋንዳ ናይሮቢ መመላለሷ ነው። እናም በዚህም የሞዴሊስትና የዲዛይን ትምህርት በቀረበላት ጥያቄ መሰረት ተቀብላ መማር ችላለች።
ወደ ባለቤቷ ጣሊያን አገር ስትመለስም ቢሆን መማርን አላቆመችም። የተማረችውን ትምህርት እየሰራ ችበት ሁለተኛ ዲግሪዋን በሳይንስ ኦፍ አግሪካልቸር ጀምራለች። አሁን የመመረቂያ ጽሁፍ ብቻ እንደቀራትም አጫውታናለች። «ትምህርት የሚቆም ተግባር አይደለም» የምትለው ሞዴሊስት ሰናይት፤ ሦስተኛ ዲግሪዋንም ለመቀጠል እንዳሰበችና በተለይም በዲዛይን ሙያ አገርን የሚያስጠራ ሥራ የመስራት ራዕይ ሰንቃለች።
የፓርኩ ላይ ጉዞ
ኬኒያ ናይሮቢ ላይ ነበር ይህ የሆነው። በፓርኩ መካከል እየተጓዘች ሳለ አንድ ድምጽ ከኋላዋ አቃጨለ። ለእርሷ የቀረበ ጥሪ ነበር። መለስ ስትልም የምታደንቃት ኢማኒ የተባለች ዓለምአቀፍ ሞዴሊስትና ዲዛይነር ነች። የራሷ የሆነ የሞዴሊንግ ኤጀንሲ፣ የሞዴሊንግ ትምህርት ቤት አላት። ቀረብ ብላም ሞዴሊስት መሆን እንደምትችል ነገረቻት፤ አጨቻት። የተለያዩ ስልጠናዎችንም እንድትወስድ አመቻቸችላት። ከዚያማ ሜዳውም ፈረሱም ከተገኘ ውጤቱን ለእኔ ተይው ብላ ተዋቂነቱን ተቆናጠጠች።
ይህ እድል ሲሰጣት ዲግሪዋን በኬንያ እየተማረች እንደነበር የምትገልጸው ዲዛይነር ሰናይት፤ «የመጀመሪያ ውድድሩ አለማቀፋዊ ነበር፤ የለበስኩት ደግሞ የዋና ልብስ ነው። የመጀመሪያዬ ስለነበር በጣም አስፈርቶኛል። ሆኖም እርሷን ማሳፈር ስለሌለብኝና እኔም እድሉን መጠቀም ስለነበረብኝ አድርጌዋለሁ። በወቅቱ ግን ያገኘሁት ምላሽ ያልጠበኩት ነበር። ስኬታማ አድርጎኛል» ትላለች። በዲዛይነርነት ሙያዋም ብዙ ሳትለፋ በዚህ ባገኘችው እድል ታዋቂነትን እንዳተረፈችም ትናገራለች።
ሞዴሊስትም ሆነ ዲዛይነር መሆንን መቼም አስባው እንደማታውቅ ነገር ግን ሀሳቡና ተግባሩ ለእርሷ ስኬታማነት እንደሚጠቅም በጊዜው የተረዳችው ሰናይት፤ ሞዴል ማለት ምሳሌ መሆን ነው ትላለች። በልብስና በተክለ ቁመና ብቻ የሚገለጥ እንዳልሆነ ከዚያ በላይ ሀይል እንዳለው ትናገራለች። ሞዴሊስት መሆን የውጪ ገጽታ የሚታይበት ብቻ ሳይሆን የውስጥ ውበትም ማሳያ ጭምር መሆኑን ትናገራለች። በዚያ ማለፍ የሚችሉ ትክክለኛውን ሞዴሎችንም ለማፍራት እየሰራች መሆኑንም ታስረዳለች።
ሞዴሊንግ በራሱ ሙያ ነው። ሆኖም ማህበረሰባችን የሚሰጠው ምልከታ ትክክለኛ አረዳድን የተከተለ አይደለም የምትለው ዲዛይነሯ፤ ያለንን የተፈጥሮ ውበት ለማሳየት ሁኔታው መስተካከል አለበት ባይ ነች። ሥራው የሚፈለገው ነገር ላይ እንዳይደርስ ፣ ተክለ ቁመናዋ ያማረ ብቻ ሞዴል ትሁን የሚለው እንዲገዝፍ፤ የተዛባ ግንዛቤን በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲኖር ያደረገው ሙያነቱን መቀበል ስላልተቻለ ነው። በተለይ ከጸባይ ጋር በተያያዘ ሁሉንም በአንድ የመጨፍለቅና ባለጌ ብሎ የመፈረጅ ሁኔታ በመግዘፉ ዓለም በሥራችን እንዳያውቀን አድርጎናል። እናም ራሳቸውን አስከብረው ሙያውን የሚያገኑ ሰዎች መኖራቸውን በማሰብ ይህንን ማረም ያስፈልጋል። ውበትን ከአርአያነት አንጻር ማየትና ለሙያው ክብር መስጠትም ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም አካል መረባረብ አለባት ባይ ናት።
አርአያዎቼ
አርአያ የማደርጋቸው ሁለት ሰዎች አሉኝ ትላለች፤ አንደኛው አባቷ ናቸው።” አባቴ በስራዬ ሁልጊዜ ደስተኛ መሆን እንዳለብኝ፤ ስራ እንደሚያስከብር፣ ለአገር መኖር ከምንም በላይ ክብር እንደሆነ፣ መለወጥ፣ መደሰትና ለስኬት መብቃት የሚቻለው በስራ ብቻ መሆኑን አስተምሮኛል” ትላለች።
ሁለተኛዋ በአርአያነት የጠቀሰችውና ለዚህ ያበቃችኝ የምትላት ሊያ ከበደን ነው። ብዙ ሰዎችም ሲያገኙዋት ከእርሷ ጋር እንደሚያመሳስሏት ትናገራለች። እናም ሊያ ከበደ ማን ናት የሚለውን ለማወቅ ጥረት አድርጋለች። ተሳክቶላትም ከእርሷ ጋር መተዋወቋንና የተለያዩ ስራዎችንም አብራ መስራቷን ትናገራለች።
ሊያ በየትኛውም ፋሽን ሾዎ ላይ ጎልታ የምትወጣ ኢትዮጵያዊ ሴት ናት። በዚህም እርሷ ካደረገችው ለምን እኔስ የሚል ወኔ ውስጥ እንደገባችና ስኬታማ እንደሆነችም ታስረዳለች። በተለይም «ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ» እንደሚባለው ኢትዮጵያን በአለም ደረጃ ለማስተዋወቅ ሁለተኛ መሆንንም እንደምትሻ ትገልጻለች።
ባለታሪኳ እንደምትለው፤ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዊ ሞዴሊስቶች ቢኖሩም ከራሳቸው ያለፈ ስራ አልሰሩም፤ አገራቸውንም ለማስጠራት በቂ ጥረት አላደረጉም። ሊያ ግን ለአገሯ ብዙ ስራዎችን ሰርታለች። ስለዚህም ከእርሷ ይህንን መማር ያስፈልጋል። ለእኔ ብርታትና ለአገሬ እንድሰራ መምህሬ እንደሆነች ሁሉ ሌሎችም አርአያቸው በማድረግ ለአገራቸው መስራት አለባቸው ትላለች።
የሥራ ቆይታ
የሶሾሎጂን ትምህርት በወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ባሉ ኮሌጆች ውስጥ ለዓመታት አስተምራለች። በአፍሪካ ትልልቅ የሚባሉ የሞድሊንግ ስራዎች ላይም ተሳትፋለች። ከዚያ ልጅ ሲወለድ ቅርጿ መቀየሩ አገዳትና ከሙያው ላለመራቅ የዲዛይኒግ ትምህርት በመማር በዲዛይነርነት እንድትሰራ ሆናለች። በዚህ ደግሞ በዓለም ደረጃ ታውቃበታለች። የክብር ዶክትሬት የተቸረችውም በዚህ ሥራዋ እንደነበር ታስታውሳለች። ከአፍሪካ ወጥታ አውሮፓንም በሞዴሊንጉም ሆነ በዲዛይኑ አዳርሳለች። ሚላኖ ፋሽን፣ ሮም ፋሽን፣ ስላይ ለንደን እየተባለ እስከ አሜሪካ ዘልቃለች።
በዲዛይን ሙያ ውስጥ ሳለች ለመጀመሪያ ጊዜ በዲዛይን ስራ አገሯን በማስተዋወቋ ብዙዎች አመስግነዋታል። የልብሶቿ እውቅናም ይበልጥ የገነነው ጣሊያኑን በማልበሷ ነበር። ከኢትዮጵያ አልባሳት ውስጥ የወላይታን በመምረጥ ጣሊያን እንስቶችን እንዲለብሱ ማድረጓ ደግሞ ይበልጥ መልዕክቷን ያለገደብ እንድታስተላልፍ እድል ሰጥቷት ነበር። በወቅቱ ሁሉም ሚዲያ ተቀባብሎት ትልቅ ስኬትንም አጎናጽፏታል። በዚህም በሁሉም ቦታ እውቅናን አግኝታለች።
ዛሬ በአለም ደረጃ የሚታዩት የዲዛይንና የሞዴሊንግ ሥራዎችን ትሰራለች። አነሳሷ በዓለም ደረጃ የሚቀርቡ ማንኛውም የዲዛይን ሥራዎች በቀለም ምርጫዎችም ሆነ በዲዛይናቸው አፍሪካንና ኢትዮጵያን የሚያሳዩ አለመሆናቸው አስቆጭቷት ነው። በተለይም ዲዛይናቸው ከባህላችን የወጡ መሆናቸው ለምን ያሰኛት ነበር። በተጨማሪም መቶ በመቶ ተፈጥሯዊ ከሆኑ ጥሬ እቃዎች የሚመረቱ ምርቶች በቀላል ዋጋ ተወስደው መልሰው በዶላር ሲመጡ ማየቷ እጅግ ያበሳጫት ነበር። ይህንን ቁጭቷን ለመበቀል እንደገባችበት ትናገራለች።
«በማንኛውም ሥራዬ ውስጥ ሌሎች እንዲኖሩና እንዲጠቀሙ እፈልጋለሁ» የምት ለው እንግዳችን፤ የስራ እድል ለመፍጠርና ማህበረሰቡም ከስራው እንዲያገኝ በማሰብ የተለያዩ ዝግጅቶችን ወደ አገር ውስጥ እንደምታመጣ፤ በተለይም የዕደ ጥበብ ባለ ሙያው የልፋቱን እንዲያገኝ ማድረግ ላይ እየሰ ራች መሆኑን አስታውቃለች።
እንግዳችን ለአገሯ ዲፕሎማትም ናት፤ አገራት ከአገራት የሚገናኙበት ድልድይ በመሆን ጭምር እያገለገለች ነው። አለምአቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ወላይታ ሶዶ ከተማን ከጣሊያን አገር ብሪቻኖ ከተማ ጋር የእህትማማችነት ፊርማ አፈራርማለች። ይህ ደግሞ በልማቱ ዘርፍ በከተሞቹ መካከል ትልቅ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል። ለእደጥበብ ባለሙያውና በቅርብ ላሉ ነጋዴዎችም ብዙ የሥራ እድል ይፈጥራል። ማህበረሰቡም ቢሆን ከተጠቃሚነቱ ባሻገር ባህሉን አድናቂና ወዳድ እንዲሆን ያደርገዋል።
በሚሊኒየም አዳራሽ ባለፈው ዓመት በተዘጋጀው ኢንተርናሽናል አፍሪካን ፋሽን ላይ እንደተሳተፈች የምትናገረው ዲዛይነር ሰናይት፤ አርባምንጭ ላይ እንዲሁ ዝግጅቶችን አድርጋ ነበር። ሞዴሊስቶቹ ደግሞ የአካባቢው ወጣቶች እንዲሆኑ እድል ያመቻቸችና ከተዋቂ ሞዴሌስቶች የልምድ ልውውጥ እንዲኖራቸው በር የከፈተችም ናት። ዛሬም ቢሆን ለአገሯ የምትሰራቸው በርካታ ትልልቅ እቅዶች እንዳሏትም አጫውታናለች።
«ዋን ፒስ» በማለት የተለያዩ የማስታወቂያና የዲዛይኒግ ሥራዎችን በሁለቱ አገራት ላይ እየሰራች የምትገኘው ዲዛይነር ሰናይት፤ ዋን ፒስ ከስያሜው ጀምሮ ብዙ ታሪክ ያለው ነው። በመካከላችን አለመግባ ባት ሲፈጠር ልዩነቱ እንዲጠፋ ለማድረግ ወደ ሳቅ የለወጥንበት መጠሪያ ነው። አንድነት ሰላም ነው ለማለት ስለፈለግን ነው ዋን ፒስ ያልነውም ትላለች። ዋን ፒስ በኢትዮጵያ ወላይታ ሶዶና በጣሊያን አገር ውስጥ የሚሰራ ድርጅት ሲሆን፤ በወላይታ ሶዶ የማስታወቂያ ሥራ በጣሊያን አገር ደግሞ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ይሰራል ብላናለች።
ይገባሻል …
የተለያዩ የምስክር ወረቀቶ ችና ዋንጫዎች እንዲሁም ሜዳሊያዎች ከተለያዩ አካላት ተበርክ ተውላታል። ይሁንና እንደእርሷ ገለጻ፤ «ለእኔ ትልቅ ሽልማቴ የአገሬ ሰዎች የሰጡኝ ክብር ነው።”ትላለች። ሶስቱ ትል ልቅ ሽልማቶችም ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ታነሳለች። የመጀ መሪያው ከ40 አፍሪካ ሴቶች ውስጥ አንዷ በመሆን እኤአ በ2017 ”የማይስ አለማቀፍ የፋሽን ኢቨንት“ ላይ ያገኘችው ሽልማት ነው። ሽልማቱም የተከና ወነው ደግሞ ጋና ላይ በመሆኑ ጋናውያን በትልቁ እንዳከበሯት ታስታውሳለች።
ሌላው ሽልማቷ አሜሪካ ላይ የተበረከተላት ነው፤ በሰብአዊነት ላይ በሰራቻቸው ስራዎች ያገኘችው ነው። ሞዴል ሰናይት በጣም አበር ትቶኛል፤ ወደፊት የምጓዝበትን መንገድ የጠረገልኝ ነው የምትለው ሽልማት ደግሞ የክብር ዶክትሬት ያገኘችበትን ሲሆን፤ በናይጀሪያ ከተማ በስቴይ አፕ አቬሽን ድርጅት አማካኝነት የክብር ዶክትሬት ተበርክቶላታል። ሽልማቱ «አፍሪካን በቱሪዝሙ ዘርፍ በማስተዋወቋ የላቀች» በሚል የተሰጣት ነው። ምርጫውን ያከናወነችውና ያረጋገጠችው አሜሪካ እንደነበረችም አጫውታናለች።
ውሃ አጣጭ
አባቷ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ የትምህርት አስተባባሪ ናቸው። ከውጪ ሀገር ዜጎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚው አላቸው። በዚህም በርካታ ሰዎችን ያውቁ ነበር። ይህ ሁኔታ ደግሞ አገር ተሻግራ ጓደኛ እንድታፈራ ዕድል ከፈተላት። በአባቷ ጓደኛ አማካይነት የዛሬውን የትዳር አጋሯንም ተዋወቀች። የሰናይት ባለቤትን ጁሶፔ ላዞሮቲ ይባላል። እርሱ ስለኢትዮጵያ ከአ ገሩ በላይ ይናገራል፤ ያስተዋውቃልም። ኢትዮዽያን መውደዱና ማክበሩ የማረካት አገር ወዳዷ ሰናይትም ለቀረበላት የትዳር ጥያቄ ሳታንገራግር ምላሽ የሰጠችው ከዚህ አንጻር እንደሆነ ትናገራለች።
በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የፍቅር ህይወት ከስድስት ዓመት በኋላ በጋብቻ እንደታሰረ የምትገልጸው ባለታሪኳ፤ የበለጠ ተምሮ ለመስራትና አገሯን ለማገዝ ስትል በጣሊያኑ ባለቤቷ አማካኝነት ኢትዮጵያን ለቃ ጣሊያን ገባች።
«ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን በይበልጥ እንዳስተዋ ውቃት የሚጎተጉተኝ ባለቤቴ ነው። የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ጭምር ስለጣሊያን ሳወራ ኢትዮጵያን ሳልናገር እንዳልወርድ ያደርገኛል። ይህ ደግሞ ምን ያህል ለአገሬ ቦታ እንዳለው የሚያሳይ ነው» ትላለች ስለባለቤቷና ኢትዮጵያ ትስስር ስታነሳ።
የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ዲዛይነር ሰናይት፤ ‹‹ልጄ በቀለሙ አባቱን ቢመስልም በባህሉ ግን የሁለቱም እንዲሆን ማድረግ ላይ ተጋግዘን እየሰራን ነው። በይበልጥ አባቱ የእናቱን አገርና ባህል እንዲያውቅ ይፈልጋል። ምክንያቱ ደግሞ የጣሊያኑን እየኖረበት ስለሆነ በቀላሉ ይረዳዋል ብሎ ስለሚያምን ነው። ከሁለት ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ መጥቶ የተለያዩ ቦታዎችን እንዲጎበኝም እድሉን ያመቻቸለት እርሱ ነው።›› ብላለች።
‹‹ ለልጆቻችን የምንነግረው ነገር አግባብ ያለውና በህይወት ሊኖሩት የሚችል መሆን አለበት›› ብላ የምታምነው ዲዛይነር ሰናይት፤ ባለቤቷ ወላጅ አልባ ህጻናትን እንደሚያግዝና 42 ህጻናትን አሳድጎ ለቁምነገር እንዳበቃ ትናገራለች። ዩኒቨርሲቲም የሚያስተምራቸው ልጆች መኖራቸውን፤ በየዓመቱ እየመጣ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኝም አጫውታናለች።
መልዕክተ ሰናይት
«ኢትዮጵያዊነት ሁሉ ነገር መሆኑን ያወኩት በመንገድ ስጓዝ ከርቀት ምን ያህል እንደሚማርክ ሳስብ ነው። ውብ ቀለምና ቁመና አለን፤ ተፈጥሮ በሁሉ ነገርም አጎናጽፋናለች ብዬ እንዳምን ሆኛለሁ። ምክንያቱም ማንም ከርቀት ታይቶ ሲመረጥና ሞዴሊስት ሲሆን አላየሁም። እናም ኢትዮጵያውያን ይህንን ያህል አቅም ካለን ለምን አንሰራበትም?» ስትል ትጠይቃለች። ቀጥላም የተሰጠን መጠቀም ላይ ክፍተት አለብንና እንፍጠን ስትል ምክሯን ትለግሳለች።
በፋሽኑ ኢንዱስትሪ ባህልን ማስተዋወቅ የእርሷ ዋነኛ አላማ እንደሆነ የምትናገረው ዲዛይነር ሰናይት፤ ለአገር ከሚጠቅመው አንጻር ስራዎችን መስራት ትወዳለች። ሆኖም በየቢሮው ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግር እስከዛሬ ሊያሰሯት እንዳልቻሉ ትገልጻለች። ሶዶ ላይ አጋጣሚውን በማግኘቷ ግን ደስተኛ እንደሆነች ታነሳለች። እናም አጋጣሚውን ያላገኙ ግን በርካቶች መኖራቸውን በመጠቆም ፍላጎትና አቅርቦት መመጣጠን አለባቸው ትላለች።
የመልካም አስተዳደር እጦት(ቢሮክራሲ) ማብዛት አገርን አያሳድግም። ማገዝ ያለበትን ሰው ራሱን ካወጣ በቂ ነው ብሎ እንዲያስብ እና ሌሎችን እንዳያግዝ ያደርጋል እንጂ። ባለሀብቱም ሆነ ሙያተኛው ለአገሩ የሚሰራበትን መንገድ መጥረግ መጀመር አለበት። ለአገሩ ብዙ ነገር ማበርከት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ በውጪው አለም ሞልቷል። አገር ውስጥ ሲገባ የሚሰጠው ምላሽ ግን ተስፋ አስቆራጭ ነው። እናም በተለይ የመንግስት አካላት ይህንን ሊያዩ ይገባል ትላለች።
«በባህሪዬ ቁጭት የለብኝም። አንድ ነገር አልሳካ ካለኝ እተወውና ሊሳካልኝ የሚችለው ላይ እሰማራለሁ። ኢትዮጵያውያን በየትኛውም መስክ ላይ መለያቸው ተስፋ አለመቁረጥ ነው። ስለዚህ አንድነታችንን በተስፋ በመደገፍ ለአገራችን እንስራም» መልዕክቷ ነው።
ለአገር ስራ በአንድነት የመተግበሩ ሁኔታ የጎላ አይደለምና ዛሬ መንቃት አለብንም ትላለች። በተለይ ውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ ብዙ እውቅና ኖሮት ለአገሩ ላይ መስራት እየቻለ አይደለምና ዛሬ ሊነቃ ይገባልም ባይ ነች። እኛም መልዕክቷ ይድረሳችሁና ለአገራችሁ የበኩላችሁን አድርጉ በማለት ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው