ዘመናችን የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የኤሌክትሮኒክስና የሕትመት ሚዲያው ኋላቀር ተብሎ የተፈረጀበትና ፌስቡክ፤ ትዊተር፤ ቴሌግራም፤ ቲክቶክ እና የመሳሰሉት በዘመናዊነት ተፈርጀው ሰፊ ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡ የብዙዎችም ምርጫ ሆነዋል፡፡
አሁን ዘመኑ የደረሰበት የኢንተርኔት አገልግሎትን በመጠቀም ማንኛውም ሰው የፈለገውን መረጃ በፈለገው ሰዓት ከቤቱ ሆኖ ያገኛል። ከመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ይልቅም የማኅበራዊ ሚዲያ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ ሆነዋል። በተለይም ስማርት ስልኮች ከተፈጠሩ ወዲህ የማኅበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀም በእጅጉን መጨመሩ የሚታይ እውነት ነው።
የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ባላቸው ሰፊ ተደራሽነትና ተሳትፎ ሳቢያ በጎም ሆኑ አሉታዊ መልዕክቶች በቀላሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩና በዓለም ዙሪያ ላሉ ሰዎች ለማዳረስ ያስችላሉ። ይህም በሰዎች ላይ ጉዳትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ይዘቶች በቁጥጥር አድራጊ አካላት ዕይታ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በርካቶች ዘንድ ስለሚደርሱ አሉታዊ ውጤታቸው በአጭር ጊዜው ውስጥ ሊታይ ይችላል።
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በሚንጣቸው ሀገራት ውስጥ ማኅበራዊ ሚዲያን ለአሉታዊ ዓላማ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖች እጅግ በርካታ ናቸው። አሁን አሁን ማኅበራዊ ሚዲያው ከሚታወቅባቸው ገጽታዎቹ የጥላቻ ንግግር አንዱ ነው፡፡ “የጥላቻ ንግግር” ማለት በአንድ ሰው ወይም የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሔርን፣ ብሔረሰብንና ሕዝብን፣ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሠረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው። በዚህም በግለሰቦች፣ በማኅበረሰቦች እና በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያለውን ግንኙነት በማበላሸት ለግጭትና ለጥቃት መሳሪያ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። ከዚህ አንጻር በሀገራችን ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየታየ ከሚገኘው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለጠፉ ሃሳቦች ጥላቻ አዘል፣ ግለሰብን ወይንም ቡድንን በብሔር እና በሃይማኖት የሚፈርጁና ብጥብጥ እና ሁከትን የሚሰብኩ ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 120 ሚሊዮን ገደማ እንደሆነ ይገመታል። ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት 24 በመቶ ያክሉ ከ13 እስከ 24 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው።
ከኢትዮ ቴሌኮም በተገኘው መረጃ መሠረት 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች ናቸው። በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎችም ቁጥር ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው፡፡ የቢቢሲ አማርኛ ክፍል በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰራው ዘገባም ፌስቡክ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትን የሚያበረታቱ መልዕክቶችን መቆጣጠር አልቻለም የሚል ከባድ ወቀሳ እንደሚደርስበት አትቷል።
የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የፌስቡክ ሠራተኞች ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ተመልክተው ለበላዮቻቸው ቢያሳውቁም ድርጅቱ ርምጃ አልወሰደም የሚል ይፋዊ ክስ ቀርቦበታል። ፌስቡክ፤ ኢትዮጵያን የግጭት አደጋ ካንዣበባቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል ቢመድባትም የድርጅቱ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች መቆጣጠሪያ ክንፍ የድርሻውን አልተወጣም በሚል ተደጋጋሚ ትችት ይሰነዘርበታል።
ዎልስትሪት ጆርናል ጋዜጣ መስከረም 2014 ባስነበበው ጽሑፍም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች ጭካኔ የተሞላቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ያለከልካይ ፌስቡክ ላይ ሲለጥፉ ነበር ብሏል። ሜታ ለተሰኘው የፌስቡክ ባለቤት ኩባንያ ይሠሩ የነበሩት ፍራንሲስ ሃውግን ፌስቡክ እንደ ኢትዮጵያና ምያንማር ያሉ ሀገራትን እያፈራረሰ ነው ሲሉ መረጃ ማሾለካቸው ይታወሳል። ለማርክዙከርበርግ ድርጅት ይሠሩት የነበሩት መረጃ አጋላጯ በአሜሪካ ሴኔት ፊት ቀርበው ነው ይህን ያሉት። ይህ ዜና በበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከተዘገበ በኋላ ፌስቡክ ርምጃ መውሰድ ጀምሬያለሁ ብሎ ነበር። ሆኖም ብዙ ለውጦች የሉም፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክቶች ጉዳት ከደረሰባቸውና ወላጆቻቸውን ከተነጠቁ ሰዎች መሃል አብርሃም አንዱ ነው፡፡ አብርሃም በማኅበራዊ ሚዲያዎች በተሰራጩ መልዕክቶች ምክንያት አባቱን አጥቷል፡፡ የአብርሃም አባት ፕ/ር ማዕረግ አማረ አብርሃ ከሚያስተምሩበት ዩኒቨርሲቲ ወጥተው ወደ ቤታቸው እየተጓዙ ሳለ በሞተር የመጡ ታጣቂዎች ተኩሰው ገድለዋቸዋል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ግለሰቦች በአካባቢው የሚተላለፉ ሰዎች ፕ/ር ማዕረግን እንዳይረዷቸው ስላስጠነቀቁ ማንም ሰው ሊያተርፋቸው አልሞከረም። ከተተኮሰባቸው ከሰባት ሰዓታት በኋላ ሕይወታቸው አልፏል። ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ፌስቡክ ላይ ስለ አባቱ መረጃዎች እየተለጠፉ እንደነበር አብርሃም ይናገራል። በተላለፉት የጥላቻ መልዕክቶች የተነሳም የአባቱ ሕይወት መጥፋቱን ገልጿል፡፡
ለፌስቡክ በተደጋጋሚ ስለእነዚህ ጽሑፎች ጥቆማ ቢያደርጉም “ፌስቡክ ግን እነዚህን ጽሑፎች በፍጥነት አላጠፋም” ሲል ያክላል። በዚሁ ምክንያትም ስሙን ከፌስ ቡክ ወደ ሜታ የለወጠው ድርጅት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ጥላቻ እና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ይዘቶችን በማሰራጨት የ2 ቢሊየን ዶላር ክስ ቀርቦበት እንደነበር የሚታወስ ነው።
ሌላው ከማኅበራዊ ሚዲያው ጋር ሰርክ የሚነሳው ብሔርና ሃይማኖትን ተገን በማድረግ የሚነዙ የጥላቻ ዘመቻዎች ናቸው፡፡ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳ አንዱ ሃይማኖት ሌላው ላይ እንዲዘምት የሚነዙ የጥላቻ ወሬዎች ማኅበራዊ ሚዲያውን የሚያጨናንቁበት ወቅት የበዛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሥነ ምግባሩም የተመሰገነና ለዘመናት የዘለቀ አብሮነት ያለው በመሆኑ እንጂ ዘወትር እንደሚነዙት የጥላቻ ዘመቻዎች ሀገርና ሕዝብ ባልኖረ ነበር፡፡
ክፉና የተዛባ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ግለሰቦች በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻቸው አንድን አካል በመነጠል ችግሩን እንደፈጠረ አድርገው አብዛኛው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ አድርገዋል፡፡ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የተፈጸሙ አሰቃቂ ግድያዎችን ሆን ብለው በማቀነባበር በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲሰራጩ በማድረግ ኅበረተሰቡን አደናግረዋል፡፡ ተጠቂ ነን ብለው ያሰቡ ግለሰቦችና ቡድኖችም አጸፋዊ ርምጃ እንዲወስዱ የሚነሳሱ መልዕክቶችም በስፋት ሲሰራጩ ቆይተዋል፡፡ ግጭቶችን በተመለከተ ጥናት የሚያከናውን ተቋም ይፋ እንዳደረገውም ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ያሉት ዓመታት ከባድ ግጭቶች የተከሰቱባቸው ዓመታት ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ፣ ለቢቢሲ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል ይፋ እንዳደረጉትም ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ ግጭቶች በከፍተኛ ደረጃ ጨምረዋል ይላሉ።
የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ላይ ያተኮረው እና አንድ ዓመት ከመንፈቅ ገደማ የፈጀው ጥናት፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ 5,300 የሚሆኑ ግጭቶች መከሰታቸውን ለይቷል። ይህም ከ1992 እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ዓመታት ካጋጠሙ ግጭቶች መካከል 58 በመቶዎቹ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከሰቱ ናቸው ተብሏል።
እነዚህ በአምስት ዓመቱ ውስጥ በሀገሪቱ ያጋጠሙት ግጭቶች ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ሕይወት መጥፋት እና ለከባድ የንብረት ውድመት ምክንያት ሆነው አሁንም እንደቀጠሉ ይገኛሉ። ይህ አሃዝ ወደ አምስቱ ዓመታት ሲካፈል በየዓመቱ 1,060 ግጭቶች የተከሰቱ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለወራት ሲከፋፈል በአምስቱ ዓመታት ውስጥ ባሉት 60 ወራት ውስጥ በየወሩ ከ80 በላይ ግጭቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ አጋጥመዋል።
እነዚህ ግጭቶችም ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ከመራገባቸውም በላይ አንዳንድ ጊዜም ማኅበራዊ ሚዲያው የፈጠራቸው ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከግጭቶቹ ስፋትና በተለይም ግጭቶቹን በማባባስና የብሔርና የሃይማኖት መልክ በማላበስ የተሰራጩበት መንገድ ሀገር እስከመበተን የሚያደርሱ ነበሩ፡፡
ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ሕዝብ በመሆኑ ብዙዎች ሩዋንዳ ዓይነት እልቂት እንዲፈጠር ቢሞክሩም ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ከምትታወቅባቸው ባህሎች መካከል የሃይማኖት መቻቻልን ያክል ግዝፈት ያለው አኩሪ ባህል ያለ አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያ አይሁድን፤ ክርስትናንና እስልምናን ከውጭ የተቀበለችና ለዘመናትም ተቻችለውና ተከባብረው እንዲኖሩ ያደረገች ድንቅ ሀገር ነች፡፡ ይህም አኩሪ ባህሏ በውጭው ዓለም ዘንድ በምሳሌነት ሰርክ የሚነሳና ብዙዎችም የሚቀኑበትና የሚመኙት ሕዝቦችዋ የአብሮነት መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ማኅበራዊ የትስስር ድረ ገጾችን ለሐሰተኛ መረጃና ለጥላቻ ንግግር ማስተላለፊያነት የሚጠቀሙ ሰዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ ማውጣቷ የሚዘነጋ አይደለም።
በአዋጁ ከተካተቱ ሕግጋት መካከል የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በሕትመት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ወይንም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎችን በመጠቀም ያስተላለፈ እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራትና በ100 ሺህ ብር ይቀጣል የሚል ይገኝበታል።
በተላለፈው የጥላቻ ንግግር ምክንያት በግለሰብ አሊያም በቡድን ላይ ጥቃት ከደረሰ አልፎም መረጃው ከ5 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት ገጽ ከተላለፈ ቅጣቱ እስከ 5 ዓመት ሊደርስ እንደሚችል አዋጁ ያትታል። ሆኖም ብዙዎች እንደሚስማሙበት አዋጁ ከወጣ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም የጥላቻ ንግግርን እንደልባቸው የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖችን ተከታትሎ በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ አኳያ ብዙ ርቀት መጓዝ አልተቻለም፡፡ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር የተቋቋሙ አካላት ኃላፊነታቸውን በምን ያህል ደረጃ እየተወጡ መሆኑን እራሳቸውን ቢፈትሹ የተሻለ ይሆናል፡፡
በዋነኝነት ግን ኅብረተሰቡ የሚመለከታቸውን እና የሚከታተላቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክቶች መምረጥ ይኖርበታል፡፡ ምን ዓይነት እውቀትና መረጃ የማይሰጡ ወይም የማያዝናኑ እና አልፎ ተርፎም ግጭትና ሁከትን በማባባስ ጭንቀትን ከሚፈጥሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እራስን መቆጠብ ብልህነት ነው፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያውን በአግባቡ ከተጠቀምንበት የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት፤ ለመደጋገፍና በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መረጃ ለመለዋወጠ ከማስቻሉም በላይ ለሀገር ግንባታም የማይተረካ ሚና መጫወት ይችላል። ስለሆነም የምንጠቀመውን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ መምረጥና በጎ በጎዎቹን ማበረታታት የዜግነት ግዴታን መወጣት መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
እንደ ኅብረተሰቡ ሁሉ ሌላው ኃላፊነት መውሰድ የሚገባቸው አካላት ገቢያቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያደረጉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ናቸው፡፡ ገቢ ለማግኘት ሲባል ብቻ የማኅበረሰቡን እሴትና ባህል እንዲሁም አብሮነት የሚሸረሽሩ መልዕክቶችን ማስተላለፍ የኋላ ኋላ መዘዙ ለሁሉም የሚትርፍ መሆኑን ሊረዱ ይገባል፡፡
አብዛኞቹ ማኅበራዊ ሚዲያውን መሠረት አድርገው ገቢ የሚሰበስቡ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚመለከቱት የሚያገኙትን ጥቅም ብቻ ነው፡፡ ግጭትን እና ሁከትን በማጋነን፤ ከሚያቀራርቡ ጉዳዮች ይልቅ የሚራርቁ ሃሳቦችን በማሰራጨት፤ አንዱን ብሔር በሌላው ላይ በማነሳሳት፤ አንዱን ሃይማኖት በሌላው ላይ እንዲሸፍት በማግባባት ጭምር የሚታሙ ናቸው፡፡ ከመታማትም አልፎ አንዳንዶቹ ለፍርድም ቀርበዋል፡፡ ስለሆነም ሕዝብን አጋጭቶና ሀገርን አፍርሶ የሚገኝ ጥቅም የለም አያደርስምና ቆም ብሎ ማሰቡ ብልህነት ነው፡፡
ይህንን ጉዳይ ስናነሳ ኮሚዲያን እሸቱን ሳናመስግን ማለፍ አንችልም፡፡ ከሞዲያን እሸቱ በዩቱብ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ሕዝብን ከሕዝብ የሚያለያዩና በሂደትም ሀገር የሚያፈርሱ መሆናቸውን በመረዳት ለዩቲበሮች በራስ ተነሳሽነት ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹ሕዝብን የሚጠቅምና ሀገርን የሚያሳድግ መልዕክት አስተላልፎ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ይቻላል›› የሚል አቋም በመያዝም እስካሁን በአራት ዙሮች መልካም ስብዕና ያላቸውን ዩቲበሮች ለመቅረጽ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው፤ ሌሎችም በዚሁ መንገድ ሊጓዙ ይገባል፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያውን የሚያስተዳድሩ አካላትም ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ኢንስታግራም፣ ፌስቡክን እና ዋትስአፕን የሚያስተዳድረው ሜታ ትልቁን የማኅበራዊ ሚዲያ ባለድርሻ በመሆኑ ሐሰተኛና የጥላቻ ንግግሮች ወደ ሕዝብ ከመድረሳቸው በፊት የሚቆጣጠርባቸውን ሥርዓቶች ሊያበጅ ይገባል፡፡ ለዓመታት ሲከተል የነበረውንም አካሄድንም ቆም ብሎ የሚያጤንበት ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎችን መልክ በማስያዝ በኩል የተጣለበትን ኃላፊት ሊወጣ ይገባል። ኢትዮጵያ በጥላቻ ንግግርና ሆን ተብለው በሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች በብዙ እየተጎዳች መሆኑ በመረዳት ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄድ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት ሊያበጅ ይገባል፡፡
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2016 ዓ.ም