አምራች ዘርፉን ያነቃቃው -‹‹ኢትዮጵያ ታምርት››

መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ ርምጃዎች መካከል ከአንድ ዓመት በፊት፣ ሚያዝያ 2014 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው፡፡ የሀገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው፡፡

ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሠራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ንቅናቄው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርቶ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሻግር ተግባር ነው፡፡ ሀገሪቷ ያላትን ትልቅ የዘርፉን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር የተጀመረው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ዋና ዋና ምሰሶዎቹ ባለድርሻ አካላትን ማሣተፍ፣ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ለዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እና የሀገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ ናቸው፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችና በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡

የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ተዋንያን በሆኑ በበርካታ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚተገበር ቢሆንም ንቅናቄውን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡ የሚኒስቴሩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በንቅናቄው ትግበራ ለአምራች ዘርፉ ችግሮች መቃለል መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ንቅናቄው በተጀመረበት ዓመት ከ50ሺ በላይ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በማሳተፍ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ባለሀብቱንና አመራሩን ለማቀራረብ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ በዚህም ዘርፉ እንዲነቃቃ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል፡፡ ከሶስት መቶ ሃምሳ ሁለት በላይ ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል፡፡ ስድስት መቶ ሰላሳ አምስት አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል፡፡ አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈቃድ ወስደዋል፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት በንቅናቄው በተከናወኑ ሥራዎች፣ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እና የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 55 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚኖረው ውጤታማነት ትልቅ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉትና ቀልጣፋ አሠራርን ለማስፈን የሚረዱት የአንድ መስኮት አገልግሎት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ይይዙት ከነበረው የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ማቅረቢያ በጀት በላይ ተጨማሪ በጀት በመያዝ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የሼድ ግንባታና የመሬት አቅርቦት ድጋፎች ተሻሽለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች ምን ዓይነት ምርቶችን ያመርቱ እንደነበርና ለሌሎች ፋብሪካዎች ምን ያህል ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክት መረጃ አልነበረም። ንቅናቄው ይህ መረጃ እንዲታወቅ በማስቻሉ በአምራቾችና በገዢዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪዎች መካከል የተሻለ ትስስር እንዲፈጠር አግዟል። በሀገሪቱ በአምራች ዘርፍ የተሠማሩ በርካታ ተቋማት በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ እቅዶች ላይ ተመሥርተው ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ሲሆን፣ ንቅናቄው ቀደም ሲል ጀምሮ የነበሩባቸውን ችግሮች ለመፍታት እገዛ እያደረገላቸው ይገኛል።

ባለፉት ስድስት ወራት በንቅናቄው በኢንዱስትሪ ደረጃ ከተለዩ 2167 ችግሮች (የግብዓት፣ የመሠረተ ልማት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ የመሥሪያና የማስፋፊያ ቦታ ዝግጅት፣ የጉምሩክና የሎጂስቲክስ አገልግሎት …) መካከል፣ 1034 የሚሆኑት መፍትሔ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በቀሪዎቹ 1133 ላይ ደግሞ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፤ ችግሮቻቸው ከተፈቱላቸው አምራቾች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ አምራቾች ናቸው፡፡

የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የመጀመሪያው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ ሚሊኒየም አዳራሽ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ለአምስት ቀናት የተካሄደው ኤክስፖ ከ450 በላይ ተጋባዥ እንግዶች፣ ከ25 በላይ መገናኛ ብዙኃንና ከ53ሺ በላይ ጎብኚዎች የተሳተፉበት እና ከ125 በላይ የንግድ ስምምቶች የተፈረሙበት እንዲሁም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት የተፈፀመበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዘንድሮም ሁለተኛው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ኤክስፖ ይካሄዳል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደሚገልጹት፣ ኤክስፖው ኢትዮጵያ የአምራች ዘርፉን ተወዳዳሪነት፣ የምርት ጥራትና ብዝሀነት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በመጨመር የኢንዱስትሪ ዘርፉ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ያላት ቁርጠኝነት ማሳያ ነው፡፡ ኤክስፖው በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶችን ለዓለም አቀፍ ሸማቾች የማስተዋወቅና የገበያ ተደራሽነታቸውን የማስፋት፣ የውጭ ቴክኖሎጂዎችንና ኢንቨስትመንቶችን ወደ ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመሳብ እንዲሁም አምራችና የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ውስጥ ባሉ ባለድርሻ አካላት መካከል ትብብርን የመፍጠር ዓላማዎች አሉት፡፡

‹‹በኤክስፖው አምራቾች ምርቶቻቸውን የሚያሳዩበት መድረክ ይመቻቻል፡፡ ገዢ ሊሆኑ ከሚችሉ ባለሀብቶች ጋር ትስስር ይፈጥራሉ፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት ውይይትና የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ፡፡ በዘንድሮው ኤክስፖ በመጀመሪያው ኤክስፖ ከተሳተፉ ባለሀብቶች የበለጠ ቁጥር ያላቸው አምራቾች ምርቶቻቸውን ያስተዋውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል›› ይላሉ፡፡

እንደአቶ መላኩ ማብራሪያ፣ ኤክስፖው ለፋይናንስ አቅራቢዎችም አዋጭ የኢንቨስትመንት እድሎችንና የተሻሉ ተበዳሪዎችን ለመለየት ያግዛል፡፡ የሀገር ውስጥ ምርቶች የተሻለ እውቅና እንዲያገኙ እና የሀገር ውስጥ የምርትና የንግድ ሥራዎችን ለመደገፍ እድል ይፈጥራል፡፡ ሸማቾች አዳዲስ ምርቶችን እንዲያውቁ እና ዋጋዎችንና የግዢ ውሳኔዎችን እንዲያወዳድሩ ይረዳቸዋል፡፡ በተጨማሪም ለፖሊሲ አውጭዎች መረጃ በመስጠት ያልተፈቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡

የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የኢኮኖሚ ነፃነትና የሀገር ሉዓላዊነት ተልዕኮዎች ያሉት ነው፡፡ የሚሉት አቶ መላኩ፣ ኤክስፖው ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለሀገር እድገትና ህልውና ካለው ሚና አንፃር የተቀረፀ መርሃ ግብር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሁሉም ሀገራት ያሉ አምባሳደሮች ስለመርሃ ግብሩ እንዲያስተዋውቁ በመደረጉ አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ የሚገኙ ባለሀብቶች አሉ፡፡ ስለሆነም በዘንድሮው ኤክስፖ የውጭ ገዢዎችም ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አቶ መላኩ፣ በመጀመሪያው ኤክስፖ ላይ ምርቶችን በሚገባ በማስተዋወቅ ረገድ ክፍተቶች እንደነበሩ አስታውሰው፣ በዘንድሮው ኤክስፖው ጥራቱን የጠበቀ፣ የሀገርን ገፅታ የሚገነባ እና ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ማቅረብ እንደሚገባ ይናገራሉ። ‹‹ምርትን በተገቢው መንገድ በማስተዋወቅ ረገድ ሁሉም ድርጅት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት አለበት። የምርት ጥራት ግምገማ እናደርጋለን። ምርትን የሚያስተዋውቁ ሰዎች ስልጠና ወስደው በተገቢው መንገድ ማስተዋወቅ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ተግባር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ ያደርጋል›› ይላሉ፡፡

በሀገሪቱ በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ተቋማት በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ እቅዶች ላይ ተመስርተው ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ሲሆን ንቅናቄው ቀደም ሲል ጀምሮ የነበሩባቸውን ችግሮች ለመፍታት እገዛ እያደረገላቸው እንደሚገኝና በትግበራውም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ከፍተኛ ጥራትና ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸውን የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርተው የ‹‹ኬርኤዢ ኢትዮጵያ›› ሌዘር ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም መርዓዊ፣ ድርጅታቸው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ትግበራ ተጠቃሚ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ንቅናቄው ተጨማሪ የገበያ እድሎችንና የልምድ ልውውጥ እድሎችን ፈጥሮላቸዋል። በዚህም ተጨማሪ የሥራ እድሎችን መፍጠርና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ችለዋል፡፡

አቶ ዘላለም ‹‹ንቅናቄው አምራች ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የህልውና መሠረት መሆኑን ያሳየ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የተካሄደው ኤክስፖ በርካታ የተደበቁና እስከዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚመረቱ የማናውቃቸውን ምርቶች ያየንበት መድረክ ነው፡፡ በንቅናቄው ትግበራ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የቆዳ ውጤቶችን ለበርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አቅርበናል፡፡

ምርቶቻችን ‹በኢትዮጵያ የተመረቱ (Made in Ethiopia)› ተብለው ለሀገራት መሪዎች፣ ቀዳማዊት እመቤቶች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች የሚበረከቱ መሆን ችለዋል፡፡ በዚህም ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ችለናል›› በማለት ንቅናቄው ስላስገኘላቸው ጥቅም ያስረዳሉ፡፡ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባባር ኤክስፖውን ዓለም አቀፍ በማድረግ ገዢዎችን መሳብ እንዲሁም ምርቶችን ወደ አፍሪካ ሀገራት መላክ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አቶ ዘላለም ‹‹ኬርኤዢ ኢትዮጵያ›› ባለፉት አምስት ዓመታት ከስድስት ሚሊዮን በላይ በኢትዮጵያ የተመረቱ የቆዳ ውጤቶችን አምርቶ በመላው ዓለም ለሚገኙ ገበያዎች ማዳረሱን ጠቁመው፣ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የተገኙ ልምዶችን አጠናክሮ በማስቀጠል በዘርፉ ያለውን ውጤታማነት ለማሳደግ እንደሚተጋ ይገልፃሉ፡፡

የ‹‹ቡልኮ›› ቴክስታይል አክስዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ በበኩላቸው፣ በንቅናቄው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ተጠሪ ተቋማትና የልማት አጋሮች ለድርጅቱ ያደረጉት ድጋፍ፣ ድርጅቱ በተሻለ ፍጥነት የምርት ሥራዎችን እንዲያከናውን እንዳስቻለው ያስረዳሉ፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት፣ ቀደም ሲል ‹‹አይካ አዲስ›› በመባል ይታወቅ የነበረውን አምራች ድርጅት በግሉ ዘርፍና በመንግሥት ሽርክና (Pub­lic-Private Partnership) እንደገና በማደራጀት የተቋቋመው ‹‹ቡልኮ›› ቴክስታይል አክስዮን ማኅበር፣ ንቅናቄው ከሌሎች ተቋማት ጋር ትስስር ፈጥሮ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮለታል። የንቅናቄው ትግበራ ያስገኛቸውን ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አጠናክሮ በማስቀጠል ድርጅቱ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በተኪ ምርት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኝም አቶ ሲሳይ ይገልፃሉ፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን የካቲት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You