‹‹የሽግግር ፍትህ የተረጋጋች ሀገርን ይፈጥራል›› አቶ ጠገነኝ ትርፌ  የሽግግር ፍትህ ባለሙያዎች ቡድን አባል

የሽግግር ፍትህ ዓላማው የተሟላ ሰላምን ማስፈን ከእርስ በእርስ ጦርነት፣ ግጭት እና ጭቆና በመውጣት፣ በፖለቲካና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትርጉም ያለው ሽግግር ማድረግ ነው። የሽግግር ፍትህ ሥርዓት መዘርጋቱ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅ እና ፍትህ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በሌላ ጎኑ ደግሞ በሽግግር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ ከነበረበት ሁኔታ ሲወጣ ወይም ለመውጣት በሚደረግ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመው ፈተና በግጭት፣ በጦርነት ወይም ጨቋኝ ሥርዓት በነበረበት ወቅት ለተፈፀመ ጥቃት፣ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና በደል የተሟላ መፍትሔ መስጠት አለመቻል ተጠቃሾች ናቸው።

ለመሆኑ የሽግግር ፍትህን ለማስፈን ከማን ምን ይጠበቃል፤ ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ ምን ዓይነት ጉዳዮችን ሊመለከት ይችላል በሚሉት ላይ በፍትህ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠናቀቅ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግና በሽግግር ፍትህ ባለሙያዎች ቡድን አባል ከሆኑት ከአቶ ጠገነኝ ትርፌ ጋር ቆይታን አድርገናል::

 አዲስ ዘመን፦ የሽግግር ፍትህ ማለት ምን ማለት ነው?

አቶ ጠገነኝ፦ የሽግግር ፍትህ ጽንሰ ሃሳቡ በዋናነት የምናገኘው በሽግግር ላይ ካሉ ሀገራት ወይም ማህበረሰቦች ሲሆን ሽግግሩ ከየት ወዴት ነው ሲባል ደግሞ ከእርስ በእርስ ጦርነት አልያም ማህበረሰብ አቀፍ ከሆኑ መገፋፋቶች ከአምባገነን ሥርዓቶች ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሁኔታዎች ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሻገር የሚተገበር የፍትህ ማስፈኛ አንድ ስልት ነው። በዋናነት የሽግግር ፍትህ ሥርዓት መተግበር የጀመረውም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ ወዲህ ሲሆን በዚህም በጀርመን ናዚና በጃፓን የጦር ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አመራሮችን በወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ ሥራ ጋር ተያይዞ የተጀመረ ነው። በነገራችን ላይ በ1980 ዎቹ የነበረውም አረዳድ ላለፉት ችግሮች መፍትሔ መስጠት አያስፈልግም፤ ዝም ብሎ አዳፍኖ ስለቀጣዩ ነገር ማሰብና ማተኮር ነው የሚያስፈልገው የሚል ጽንሰ ሃሳብ ነበር።

ነገር ግን ከ1980 መጨረሻ ወዲህ ይህ ሃሳብ እየተቀየረ መጥቶ የወንጀል ተጠያቂነትን ብቻ በማስፈን ያለፉ ችግሮችን ዝም ብሎ ማለፍ ለቀጣይ እንቅፋት ያመጣል ብሎም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትና የሕግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ያለፉትን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ሁሉን ባቀፈና ባሳተፈ መልኩ መፍታት ያስፈልጋል የሚል ጽንሰ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየዳበረ መጣ።ከላይ እንዳልኩት የጀርመንና የጃፓን ጦርነቶች በተለይም ጀርመኖች በጁዊሾች ላይ የፈጸሙት የዘር ጭፍጨፋ ላይ የተሳተፉ አመራሮች ላይ የሞት ፍርድ እስከማስፈረድ ድረስ (ኑርምበርግ ትሪሙናል) ተፈጽሟል። ጃፓንም በተመሳሳይ ይህ ሂደት ተከናውኗል።

ነገር ግን ይህ ይፈጸም እንጂ በሀገሮቹ ላይ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አላመጣም። ከዛም ሃሳቡ እየተቀየረ መጥቶ የሽግግር ፍትህ በማለት ነገሮችን ሰፋ አድርጎ የማየት ሥራ መሠራት እንዳለበትና ሰዎች ባጠፉት ጥፋት የወንጀል ተጠያቂ መሆናቸው አንድ ነገር ሆኖ ነገር ግን  ለተጎጂዎች ደግሞ ማካካሻ እርቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ተቋማዊ ለውጥና ማሻሻያ ማድረግና ሌሎች የሽግግር ፍትህ የሚያጠቃልላቸውን ነገሮች ምህረትን ጨምሮ እውነት ማፈላለግና ይፋ ማውጣት ተጨምረውበት የሽግግር ፍትህን በተሟላ ሁኔታ መተግበር ያስፈልጋል በሚል ተቀባይነት እያገኘ መጥቶ ብዙ ሀገራት ከሞላ ጎደል የተሳካ የሽግግር ፍትህን እየተገበሩ የመጡት ሁኔታ ተስተውሏል።

አዲስ ዘመን፦ እንደ ሀገር የሽግግር ፍትህ ያስፈልገናለ ስንል ከምን ተነስተን ነው?

አቶ ጠገነኝ፦ የሽግግር ፍትህ ከእርስ በእርስ ጦርነት ከግጭት ካለመተማመንና ከአምባገነናዊ ሥርዓት የመውጪያ አንድ ስልት እንደመሆኑ በሀገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስናየው ለረጅም ጊዜ የቆዩና አሁንም የሚታዩ አለመረጋጋቶች፤ ጦርነቶች ፤ አለመተማመንና እርስ በእርስ የመገፋፋት ሁኔታ አለ፤ ሕዝብ ከሕዝብ እንዲሁም ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ያለመተማመንም ችግሮች አሉ። ከዚህ አንጻር ከቀደምት ጊዜ ጀምሮ የመጡ አሁንም የቀጠሉ እንዲሁም ስር የሰደዱ ችግሮችንና አለመረጋጋቶችን ጦርነቶችን መገፋፋቶችን ለማስወገድ በዘላቂነትም ለመፍታት የሽግግር ፍትህ አስፈልጓል።

የሽግግር ፍትህን መተግበርም ችግሮቹን ከመፍታት ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሕግ የበላይነትን አረጋግጦ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ሁነኛ መሳሪያ ይሆናል ተብሎ ታምኗል፤ በነገራችን ላይ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን ወደማርቀቅ ሥራው ከመኬዱ በፊት በዘርፉ ምሁራን ጥናቶች ተደርጓል፤ በዚህም በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሽግግር ፍትህን አስፈላጊነት የሚጠይቅ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ተደርሷል። በዚህ መነሻነትም ፍትህ ሚኒስቴር የባለሙያዎች ቡድን አቋቁሞ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ቀረጻ ውስጥ ገብቷል።

አዲስ ዘመን፦ የሽግግር ፍትህ ዘላቂ ሰላም እርቅና ፍትህ ከማስፈን አንጻር ሚናው የጎላ ነው ካልን፤ ይህንን አካሄድ ተጠቅመው ውጤት ያመጡ ሀገራት ተሞክሮስ ምን መልክ አለው?

 አቶ ጠገነኝ፦ አንድ ሀገር ላይ ተሞክሮ ውጤት ያመጣ የሽግግር ፍትህ አካሄድ ሌላው ሀገር ላይ በተመሳሳይ ውጤታማ ይሆናል ለማለት ያስቸግራል። ወጥ የሆነ የሽግግር ፍትህ አሰራር ሂደትም ላይኖር ይችላል። እንደ ሀገራዊ ሁኔታው እየታየ የሚተገበር ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣቸው ሰነዶች ላይም ሆነ የአፍሪካ ህብረት ባወጣው የሽግግር ፍትህ ሰነድ አተገባበር ላይ እንደተገለጸው ፖሊሲው የሀገር የሕዝብን ባህል ወግ ባከበረና ነባራዊ ሁኔታውን በሚያሳይ መልኩ መተግበር አለበት ነው የሚለው። በመሆኑም የሀገራቱ ተሞክሮም በልዩነትም በጥንካሬም የሚነሱ ጉዳዮች ይኖራሉ።

ለምሳሌ ሩዋንዳ በእኛ አቆጣጠር በ1980ዎቹ አካባቢ ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ ባደረጉት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ምክንያት ከ8 መቶ ሺ እስከ 1 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸውን በ3 ወር ውስጥ አጥተዋል። ከዚህ ዘግናኝ ሁኔታ በኋላም የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ አድርገዋል። ድክመትና ጥንካሬው እንዳለ ሆኖ እንደጠቅላላው ግን ምን አስገኘ የሚለውን ስንመለከት የተሻለ መረጋጋትና ሰላም ላይ አድርሷቸዋል። በመሆኑም እንደዚህ ያሉ ዘግናኝና ወጣ ያሉ ጭፍጨፋዎች ከተፈጸሙ በኋላ የሽግግር ፍትህን መተግበር የተሻለ ውጤትን እንደሚያመጣ ማሳያ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ሴራሊዮን ብንመለከት በተመሳሳይ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች። የሽግግር ፍትህ ሂደትን ተከትሎ ግን ሙሉ በሙሉ የተዋጣለት ዘላቂ ሰላም ላይ ደርሳለች ማለት ቢያስቸግርም አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ከእርስ በእርስ ጦርነት ለመውጣት ችላለች። ኬንያም በተመሳሳይ እኤአ 2007 የነበረውን ምርጫ ተከትሎ የተከሰተባትን አለመረጋጋት የፈታችው በዚሁ የሽግግር ፍትህ ሂደት ነው። በጠቅላላው ግን የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት ድክመት እና ጥንካሬው እንዳለ ሆኖ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል። ይህም የተሻለ ተሞክሮ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፦ የእነዚህን ሀገራት ተሞክሮ በመቀመሩ በኩል እየሄድንበት ያለው ርቀት ምን ይመስላል?

አቶ ጠገነኝ፦ ረቂቅ ፖሊሲውን ከማዘጋጀታችን በፊት ሴራሊዮን በመሄድ ለመጎብኘትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ችለናል። በዚህም ለሴራሊዮን ጦርነት መነሻው ምን ነበር? ሂደቱስ ምን ይመስል ነበር? የሽግግር ፍትህ ሂደቱስ እንዴት ተተገበረ? ምን ዓይነት ተቋማት ተቋቋሙ? የሚሉትን ሁሉ አይተን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማቀናጀት ተሞክሯል። በመቀጠል ደግሞ ወደ አተገባበሩ ስንገባ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ አስፈላጊ ከሆነ እሱን የመቀመር ሥራውም ይሰራል። ዞሮ ዞሮ ከሌሎች ሀገሮች ክፍተቶቹንም ጥንካሬዎቹንም ተምሮ መልካም የትግበራ ሂደት ተከትሎ ውጤታማ ለመሆን ልምድን መቀመሩ መልካም ነው ።

አዲስ ዘመን፦ የሽግግር ፍትህ ምን ምን ዓይነት ጉዳዮችን ነው የሚመለከተው?

አቶ ጠገነኝ፦ የሽግግር ፍትህ ሲባል ብዙ ጉዳዮችን የሚዳስስ ቢሆንም በዋናነነት ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የትኩረት አቅጣጫዎቹ ናቸው። በዚህም ከአሁን በፊት ተፈጽመው ያለፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያተኩራል። ይህ ደግሞ ከዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ በሰፈረው መሠረት የሲቪል የፖለቲካ የባህል መብቶች እንዲጠበቁ ያዛል። በሀገራችንም በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የፖለቲካም ሆነ የሲቪል መብቶች ጥሰት የሰብዓዊ መብቶች ጋር የሚገናኝ በመሆኑ አተገባበሩም በሥራው ልክ ሰፊ ተደርጎ ነው የሚታየው።

አዲስ ዘመን፦ በደል የደረሰባቸው አካላት እንዲካሱ ይቅርታ እንዲጠየቁ የእርስ በእርስ ማህበራዊ አንድነታቸው እንዲመለስ ማድረግ ከሆነ ዓላማው እኛም በዚህ ችግር ውስጥ ያለን ሕዝቦች ነንና ለእኛ ጥቅሙ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ጠገነኝ፦ የሽግግር ፍትህ ዋና ዓላማው ያለፉ በደሎችን ቁርሾዎችን አለመተማመኖችን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፍታት ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ በማድረግ በቀጣይም ሰላም፤ መረጋጋትን አንድነትን የመብት መከበርንና ፍትህ እንዲሰፍን ማድረግ ነው።

ከዚህ አኳያ የሽግግር ፍትህ ሂደቶች መካከል አንዱ ማካካሻ (ካሳ) ሲሆን ይህ እንዴት ይተገበራል? እውነት ማፈላላግና ይፋ ማድረግ እንዴት ነው የሚሰራው? እውነት ሲወጣ በዳይም ተበዳይም ይታወቃሉ። ከዚህ አንጻር እርቅ አንዱ የሽግግር ፍትህ አካል በመሆኑ እንዴት ይተግበር? ምህረት ሌላው ነውና እነዚህን አንድ ላይ አድርገን ብንመለከታቸው እንኳን ተጎጂ ተኮር ሆነው ሰዎች ብሶታቸውን የደረሰባቸው እንዲገልጹ ይሆናል። በዳዮችም ይቅርታ ይጠይቃሉ። የተበደሉ ሰዎችም ካሳ የሚያገኙበት መንግሥትም ከሆነ በዳዩ ለበደላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ካሳ የሚከፍልበት ሁኔታ ይፈጠራል።

የግለሰብ በዳዮችም ከሆኑ ይቅርታ የሚጠይቁበት ካሳ የሚከፍሉበት ሥርዓት ይመቻቻል። በጠቅላላው ግን የሽግግር ፍትህ መነሻው እውነት ማወጣት ነው። ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ በዳዩ መንግሥትም ይሁን ግለሰብ በደል ላደረሰበት አካል እንዳስፈላጊነቱ ከገንዘብ ካሳ ጀምሮ መልሶ ማቋቋም የጠፉ ንብረቶችን መተካት ሥነ ልቦና ድጋፍ የሕክምና ድጋፍ ማድረግን ቤተሰብ ለሞተባቸው መታሰቢያ ማቆምን ጨምሮ የሚከናወኑ የመካካሻ ሥራዎች ይከናወናሉ።

አዲስ ዘመን፦ የሽግግር ፍትህ አተገባበር የጊዜ ገደብስ ይኖረው ይሆን?

አቶ ጠገነኝ፦ የሽግግር ፍትህ ሂደት እንደመሆኑ መጠን በዛ ውስጥ የሚከናወኑ የሚሟሉ ነገሮችና በርካታ የሚሰሩ ሥራዎች ይኖራሉ። ከዚህ እስከዚህ ይተገበራል ብሎም ቁርጥ ያለ ቀንን ማስቀመጥም አያስፈልግም። በመሆኑም የጊዜውን ሁኔታ የሚወስኑት የሥራው ባህርያት ናቸው።

አሁን በእኛ ደረጃ የሽግግር ፍትህን ለማስፈን ጥናት አድርገናል። የባለሙያዎችን ቡድን የማቋቋም ሥራዎች ተሰርተዋል። የሽግግር ፍትህ መሠረታዊ መርህ የሚባለውን የሕዝብ ውይይት በሀገር አቀፍ ደረጃ 78 ያህል መድረኮች ተዘጋጅተው ምክክሮች ተደርገዋል። ከሕዝብም ግብዓት ተሰብስቦ ለፖሊሲው ቀረጻ ውሏል። ከዚያ በኋላም የመተግበሪያ መመሪያዎች ሕጎች ስትራቴጂዎች ያስፈልጉ ስለነበር የሚቋቋሙ አዳዲስ ተቋማት ስለነበሩ እነዚህን የሚመለከት ሥራም ይሰራል።

ወደ ትግበራው ሲገባ ደግሞ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓትን የመመልከት ጉዳይንም ስለሚጠይቅ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። አንዳንድ ሀገራት ከአምስት እስከ አስርና ከዚያ በላይ ዓመትን በቅድመ ዝግጀት ብቻ የፈጁ አሉ። ይህ ለመሆኑ ዋናው ምክንያት ደግሞ ከበጀት ጀምሮ ሰፋፊ ሥራዎችን የሚጠይቅ መሆኑ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ፖሊሲው ከመረቀቁ በፊት የነበሩ በደሎችንስ የማየት አጋጣሚው ይኖር ይሆን?

አቶ ጠገነኝ፦ አንደኛ በሽግግር ፍትህ ሂደት ውስጥ ምክክሮች ሲደረጉ አሳታፊ አካታች እንዲሁም ተጎጂ ተኮር መሆን አለባቸው። የእኛ የቅድመ ፖሊሲ ማርቀቅ ሂደቶች ምን ይመስላሉ ካልን በሂደቱ መጀመሪያ መስፈርቶች ናቸው የወጡት። በዚህም የሚሳተፉ አካላት ምን ዓይነት መሆን አለባቸው? ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች አካተው በተለይም ተጎጂዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማድረግ ስለሚያስፈልግ እሱን በተቻለ መጠን ለማድረግ ችለናል።

አሁን ደግሞ ድረ ፖሊሲ ረቂቅ በሚል ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው እነዚህ አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉበት ይደረጋል። ወደፊትም ቢሆን አጠቃላይ የትግበራ ሂደቱ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ የሚከናወን ነው የሚሆነው። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር በሽግግር ፍትህ ትግበራ ላይ ሙሉ በሙሉ ሕዝቡ በተለይም ተጎጆዎች ይሳተፋሉ እንጂ መንግሥት ይህንን አድርጉ አታድርጉ የሚለው ብቻ አይደለም፣ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ሕዝቡ አምኖበት የእኔን ችግር ይፈታል ብሎ ሲቀበለው ብቻ ውጤት እንደሚመጣ ማመን ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፦ የሽግግር ፍትህን ለማስፈን ከማን ምን ይጠበቃል?

አቶ ጠገነኝ፦ ከመንግሥት ጀምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከትና የሁሉንም የነቃና የቀና ተሳትፎን የሚጠይቅ ነው። ከመንግሥት ብንጀምር መጀመሪያ የሚጠበቅበት ቁርጠኝነት ነው። በመቀጠል ባለሙያዎችን አደራጅቶ ጥናት አድርጎ የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ ቀረጻው እንዲካሄድ ማድረጉ ቁርጠኝነቱን ካየንባቸው መንገዶች መካከል ይጠቀሳል።

ነገር ግን ቁርጠኝነቱ በዚህ መወሰን ስለሌለበት ፖሊሲው ወደተግባር እንዲገባ በማድረግ የትግበራ ሂደቱን የሚያውኩ ነገሮችን በማጥራት ተገቢውን ከለላ በመስጠት፤ ጸጥታን በማስፈን፤ ሕዝቡ የራሴ ነው ይጠቅመኛል ብሎ እንዲቀበለው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራን በመሥራት በጀት መመደብ ሁሉ ከመንግሥት የሚጠበቁ ተሳትፎዎች ናቸው።

ሕዝቡ ደግሞ ግንዛቤውን አዳብሮ ችግሬን ለመፍታት፤ እንባዬን ለማበስ የተዘጋጀ ፖሊሲ ነው ብሎ ማመን ይገባዋል። በመቀጠልም በውይይት መድረኮች መሳተፍ በትግበራ ሂደቱ ላይ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ በየአካባቢያቸው ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች በመጠቆም ለመንግሥት በማሳወቅ በተቃራኒውም የሕዝብን ሰብዓዊ መብት ሲጥሱ የነበሩ ሰዎችን ነቅሶ በማውጣት መሳተፍ ይኖርባቸዋል።

የመገናኛ ብዙኃንም የሕዝቡን ግንዛቤ በማስፋት መረጃዎችን በመስጠት ስለ ሽግግር ፍትህ ምንነት እና አተገባበር ለሕዝብ ምን ያስገኛል የሚለውን በማስረዳት በኩል ሰፊ ሚና ሊጫወቱ ይገባል። በተጨማሪም የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላቱም የሕዝብ ተወካይ እንደመሆናቸው መጠን ሕዝቡን የማብቃት ሥራ መሥራት ይገባቸዋል። አጋር አካላትም በገንዝብ፤ በእውቀት፤ በክህሎት በኩል የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።

በጠቅላላው የሽግግር ፍትህ ማለት ካሉብን ችግሮች ሁሉ ተላቀን ሰላም አንድነትና አብሮነትን ለማስፈን የመጨረሻው አማራጫችን በመሆኑ ሁሉም በየደረጃው የነቃ ተሳትፎን የሚያደርግበት ሂደት እንዲሆን ይጠበቃል።

አዲስ ዘመን፦ የሽግግር ፍትህ አሁናዊ ቁመና ምን ይመስላል ? እርስዎ እንደባለሙያ የሚያስተላልፉት መልዕክትስ ምንድን ነው?

አቶ ጠገነኝ፦ እስከ አሁን የሽግግር ፍትህ ሂደቱ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለውን ባለሙያዎችን በማሰባሰብ በርካታ ጥናቶች እንዲደረጉ ሆኗል። ውጤቱም ያስፈልጋል የሚለው ላይ ስላደረሰን በሽግግር ፍትህ ላይ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎችን ከየሙያ ዘርፉ በማደራጀትና ቡድን በማዋቀር ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል።

ሌላው ሀገር አቀፍ ቅድመ ፖሊሲ ምክክሮችን ማካሄድ አንዱ እቅዳችን ነበር። እሱንም ሕዝብን ታሳቢ ያደረገ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች የተካተቱበት የተሳታፊዎች ምርጫ ተደርጎ ቦታዎችም ተለይተው እስከ ዞን ድረስ ምክክሮች ተደርገዋል። በዚህም የሕዝቡ ፍላጎትን የመለየት የትኞቹ ጥፋቶች ያስጠይቃሉ ማካካሻና ምህረት እንዲሁም እርቆች ምን መልክ መያዝ አለባቸው የሚለውን ጠለቅ ባለ መልኩ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

እነዚህ ግብዓቶችና የሽግግር ፍትህ መርሆዎችና የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ተደርጎ ፖሊሲው በረቂቅ ደረጃ ተቀርጾ ተጠናቋል። ከዚህ በኋላ ደግሞ ድረ ረቂቅ ውይይቶች ስለሚዘጋጁ እነሱን በማካሄድና ግብዓቶቹን በመጨመር ረቂቁ እንዲዳበር ይደረጋል። ከዛ በኋላ የመጨረሻው ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚቀረብ ይሆናል። ከጸደቀ በኋላም ወደትግበራ ይኬዳል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

እስከ አሁን ባለው ሂደት የሕዝቡም ሆነ የአጋር አካላት ድጋፍ ጥሩ የነበር፤ በቀጣይም ላለው ሥራ ተመሳሳይ እገዛዎች እንዲደረጉና ለውጤታማነቱ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አደራ ማለት ያስፈልጋል። መንግሥትም የእስከ አሁኑን ቁርጠኝነቱን አጠናክሮ በመቀጠል ለውጤታማነቱ እንዲተጋ አደራ እንላለን።

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::

አቶ ጠገነኝ፦ እኔም አመሰግናለሁ

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን የካቲት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You