ለግብርናው ምርታማነት ግብዓቶችን በወቅቱ የማቅረብ መልካም ጅምር ተጠናክሮ ይቀጥል!

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ተሸክመው ከሚያስጉዙ ዘርፎች አንዱና ቀዳሚው ግብርና ነው። ግብርናው በዘመናት ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ የዘለቀ፤ አሁንም በዛው ልክ የሚገለጽ ነው። ይሄ ሲባል ያለምክንያት አይደለም፤ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ዜጋ ኑሮውን የመሰረተው በዚሁ ዘርፍ ላይ ነው።

በሥራ እድል ፈጠራውም ቢሆን ድርሻው የጎላ ነው፤ በወጪ ንግድና በኢንዱስትሪ ግብዓት ምርቶችን በማስገኘት ረገድም ድርሻው ተኪ የለውም። ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ያቀፈ፣ የቀጣይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሻገር የሚያስችል ዘርፍም ነው። ዘርፉ በቀጣይ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የሚገለጽ ሚና እንዲኖረውም ይጠበቃል።

ከዚህ አኳያ ዘርፉን የማሳደግ፣ የማዘመንና የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት ማድረግ የተገባ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ይሄን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፤ ለአብነት በሰብል ልማት ዘርፉ የተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት አምጥተዋል።

በዚህ ረገድ የስንዴ ልማት ስራው ተጠቃሽ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ከመግዛት ወደ መሸጥ እንድትሸጋገር አድርጓታል። በሩዝና ሌሎችም ምርቶች የተጀመረው ሥራም አበረታች ውጤት እያሳየ ይገኛል።

ይሄ ውጤት እንዲገኝ ደግሞ በአንድ በኩል በዝናብ ላይ የተንጠለጠለው ግብርና በመስኖ ሥራ እንዲደገፍ መደረጉ ሲሆን፤ በዚህም በመኸርና በልግ ተወስኖ የሚከወነው ግብርና በበጋም በመስኖ ታግዞ መልማት እንዲችል ሆኗል። ይሄ በዓመት ሦስቴና ከዛ በላይ እንዲመረት የማድረግ ሂደቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የሚታረስ መሬት ምጣኔንም ከፍ ማድረግ ተችሏል።

በሌላ በኩል ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶች በወቅቱ ለአርሶአደሩ እንዲደርሱ ለማድረግ የተሰራ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ እንደ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የፀረ ተባይና አረም መድኃኒቶችን የመሳሰሉ ግብዓቶች በወቅቱ ለአርሶ አደሩ የማይደርሱበትን አሰራር መቀየር የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል። ከዚህ አኳያ በተለይ በዚህ ዓመት የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ በትኩረት እየተሠራ መሆኑም መመልከት ተችሏል።

በዓመት የማምረት ድግግሞሽን ከማሳደግ እና በሰብል የሚሸፈንን መሬት ከማስፋት አኳያ፤ በ2015/16 የመኸር ሰብል ልማት 17ሚሊዮን 390ሺህ 818 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ፤ 17ሚሊዮን 548ሺህ 694 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል። ከዚህም 496ሚሊዮን 917ሺህ 52 ኩንታል ምርት ተገኝቷል።

በዳግም ሰብል የማምረት ሂደትም 963ሺህ118 ሄክታር መሬት ላይ ከተዘራው ሰብል ዘጠኝ ሚሊዮን 929ሺህ 769 ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን፤ በዚህም ከመኸር ሰብል በአጠቃላይ 506ሚሊዮን 846ሺህ 821 ኩንታል ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የመስኖ ስንዴ ልማትን በተመለከተም፣ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስ እና 120 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፤ እስከ 22/06/2016 ዓ.ም ድረስ ሁለት ሚሊዮን 971ሺህ 544 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል። በሂደቱም በ515ሺህ 39 ሄክታር መሬት ላይ ያለ ሰብል ተሰብስቦ 12 ሚሊዮን 293ሺህ 851 ኩንታል ምርት መገኘቱን ነው የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላከተው።

የበልግ እርሻ ሁኔታን በተመለከተም፤ በበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ሦስት ሚሊዮን 123ሺህ 797 ሄክታር መሬት ለማልማት እና 81ሚሊዮን 852ሺህ 93 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፤ እስከ 22/06/2016 ዓ.ም ድረስ አንድ ሚሊዮን 715ሺህ 915 ሄክታር መሬት ታርሶ 200ሺህ 673 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል።

በዚህ መልኩ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚከናወነው የመኸር፣ የዳግም ዘር፣ የመስኖና የበልግ እርሻ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ምርታማነቱን ከፍ ለማድረግ የሚያግዙ የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱ የማቅረብ ሥራም በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል። በዚህ ረገድ ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየው የአፈር ማዳበሪያ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ይሄን ችግር ለመፍታት በምርት ዘመኑ በተወሰደ ርምጃ ለቀጣይ የምርት ጊዜ የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ ሳይቀር ቀድሞ እየገባ እየተደረገ ይገኛል።

ለምሳሌ፣ ለ2016/17 የምርት ዘመን ከውጭ ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ሰሞኑን ጂቡቲ ወደብ ከደረሰው 510 ሺህ ኩንታል ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ጨምሮ፣ እስከ አሁን ዘጠኝ ሚሊዮን 395 ሺህ 606 ኩንታል ማዳበሪያ ወደብ ደርሷል። ከዚህ ውስጥም ስምንት ሚሊዮን 731 ሺህ 403 ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል።

ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖም በሁለት ሳምንታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን 274 ሺህ ኩንታል ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርስ ይጠበቃል። ይሄን መሰል ተግባር ደግሞ በተለይ በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል፤ አርሶአደሩም በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራው እንዲገባ የሚያደርገው ነው።

ይሁን እንጂ አሁንም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የፀረ አረምና ተባይ መድኃኒቶችን የመሳሰሉ ግብዓቶች ከወዲሁ ታስቦባቸው ችግሮቹን ሊፈቱ በሚያስችል አግባብ ሊሰራባቸው ይገባል። ከዚህ ባሻገርም የአፈር ማዳበሪያው በወቅቱ ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት ባሻገር በተሳካና በተሳለጠ አግባብ ለአርሶአደሩ እንዲደርሱ ማድረግ ይጠበቃል። በመሆኑም ለግብርናው ምርታማነት አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችን በተቀላጠፈ መልኩ የማቅረብ መልካም ጅማሮ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!

አዲስ ዘመን የካቲት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You