የአፋር ሕዝቦች በመካከላቸው የሚፈጠሩ ግጭቶችን የሚፈቱት በባህላዊና ልማዳዊ ሕጎቻቸው እንዲሁም በዳኝነት ሥርዓታቸው በመጠቀም ነው። ለችግሮቻቸው መፍትሔ በመስጠት እና ግጭቶችን በመቆጣጠር በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰላምን በማስፈን የዕለት ከዕለት ኑሮአቸውን በሰላምና በነፃነት ያከናውናሉ።
ለዘመናት ከኖሩበት የአኗኗር ዘይቤያቸው፣ ወግ እና ልማዳቸው ከሃይማኖታቸው ጋር የተሳሰሩ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልትና ዘዴዎችን በተግባር ላይ በማዋል በውስጣቸው በተለያየ መልክና ሁኔታ ለሚከሰቱ ግጭቶች እልባት በመስጠት በሕዝባቸው ውስጥ ሰላማዊ ማህበራዊ ግንኙነት ለመፍጠር አንድነታቸውን ጠብቀው መኖር አስችሏቸዋል። የዳኝነት ሥርዓታቸውም ከማህበረሰባቸው ውስጥ ባላቸው እውቀት፣ ችሎታ፣ ክህሎት፣ ኅብረተሰቡ በሚሰጣቸው የአክብሮት ደረጃ፣ ብስለት እና ተሰሚነት አንጻር በሚመረጡ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች አማካይነት ይከናወናል።
በአፋር ሕዝቦች ውስጥ ለሚፈጠሩ አስተዳደ ራዊና የፍትህ ጉዳዮች በበላይነት የሚመራው እና የሚያስፈጽመው የሱልጣኔት የፍትህ ተቋም ነው። አልፎ አልፎ የሼሪያ ሕግ ከእስልምና ሃይማኖት አንጻር ከሚያያቸው ጉዳዮች በስተቀር እንደ ጉዳዩ ትልቅነት እና አስፈላጊነት እየታየ ውሳኔው በተለያየ ደረጃ ላይ ባሉ የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ሊፈጸም ይችላል። የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባወጣው መረጃ በባህላዊ ሕጉ የነፍስ ማጥፋት ጉዳይ ወይም የደም ካሳ እስከ መቶ ግመሎች የሚደርስ ወይም ከዚህ ጋር እኩል ዋጋ ባለው ሌላ ቅጣት እንደሚጣልበት ያትታል። በመሆኑም እንደ ወንጀሉ ዓይነትና የአፈጻጸም ሁኔታ እየታየ ለሁሉም የጥፋት ዓይነቶች በዝርዝር የተቀመጡ የቅጣት፣ የክፍያ፣ የካሳ መጠን አሏቸው።
ከአፋር እሴቶች መካከል «ፈኢማ» አንዱ ነው። «ፈኢማ» የብርቱ ወንዶች ስብስብ የቡድን ስም ሲሆን የፈኢማ አባላት ሰላምና ፀጥታን የማስከበር፣ ፍርድን የማስፈፀም፣ የታመመን የመርዳት፣ እንግዳን የማስተናገድ በሠርግና በመሰል በዓላት ሥራ የማገዝ፣ በቀብር ወቅት መቃብሩን የማዘጋጀትና ሥርዓቱን የማስፈፀም …ወዘተ ተግባራትን ያከናውናሉ። በእያንዳንዱ ጎሣ በብርታታቸውና ንቃታቸው የተመረጡ ወንድ ወጣቶችና ጎልማሶች ተውጣጥተው «ፈኢማ» ይመሠርታሉ።
«ፈኢማ» በመባል የሚታወቀው የአፋር ብሔረሰብ ማኅበራዊ የቡድን አደረጃጀት በአንድ ሰው አቅም የማይከናወኑ ሥራዎችን ተጋግዞ ለማቃለል የብሔረሰቡ አባላት የሚጠቀሙበት ባህላዊ የማኅበራዊ ቡድን አደረጃጀት ነው። ለሥራ ተሳታፊዎች ከሥራ በኋላ ባንድ ላይ መብላትና መጠጣትም ያለ ባህል ነው። ከብሔረሰቡ ባህላዊ ማኅበራት መረዳዳት፣ በችግር ጊዜ የሚፈለገውን በማዋጣት የተለያዩ ችግሮችን ለማቃለል በገንዘብ፣ በጉልበትና በምክር ድጋፎች ማድረግን ያጠቃልላል። ለመጥቀስ ያህልም ከብሔረሰቡ እጅግ ድሃ ወይም አቅመ ደካማ የሆነውን መልሶ ለማቋቋም በገንዘብና በዓይነት ድጎማ ማድረግን፣ በሠርግ ወቅትም ቢሆን ለጋብቻ የሚዘጋጀው ሰው ለሚገጥመው ችግር ቡድኑ ገንዘብ በማዋጣት ችግሩን ለመፍታት የሚያገለግል ነው። ሴቶችም በተመሳሳይ ፈኢማ ይመሰርታሉ። ይህ የሴቶች ፈኢማ ሴቶች ያለባቸውን የቤት ውስጥ ዕቃና የገንዘብ ችግር ለማቃለል አባላቱ ገንዘብ በማዋጣት እንደ ችግራቸው ቅድሚያ እየተሰጣጡ ሁሉንም በየተራ የሚረዳዱበት ዘዴ ነው።
«ፈኢማ» የዕድር መንፈስ ቢኖረውም የአፋር ብሔረሰብ የመረዳዳት ባህል ከሌሎቹ ብሔረሰቦች ለየት ይላል። የራሱ ባህልና ወግም አለው። በአፋር ብሔረሰብ ውስጥ ፈኢማ ሲባል ወንድና ሴት አይቀላቀልም፤ ወንዶች የራሳቸው ፈኢማ ሲኖራቸው ሴቶችም እንዲሁ። እስከ ዛሬ ድረስ የአፋር ብሔረሰብን ባህል ዕድሜ የሰጠው ከጥንት አያትና ቅድመ አያቶች ጀምሮ እየተወራረሰ የመጣው የፈኢማ ባህል እንደሆነ የብሔረሰቡ ነዋሪዎች ይገልጻሉ። «ፈኢማ» በአጠቃላይ ጽንሰ ሀሳቡ በመረዳዳት ላይ በመመርኮዝ ችግሮች ሲከሰቱ የሚከናወን ነው። ፈኢማ በአባላቱ ዕውቅና የተሰጠው አለቃ (ሰብሳቢ) ይኖረዋል። በሰብሳቢው አማካይነት ሥርዓቱን ያልተከተለ አባል ይቀጣል። ስለዚህ አባላት ለሥርዓቱ ተገዥ ይሆናሉ። በአፋር ብሔረሰብ ብዛት ያላቸው ፈኢማዎች ሲኖሩ ማንኛውም የብሔረሰቡ አባል በመረጠው ፈኢማ የመግባት መብት አለው። ነገር ግን ከነበረበት ፈኢማ ወጥቶ ወደ ሌላ ፈኢማ ለመግባት ከመጀመ ሪያው ለምን እንደወጣ በቂ ምክንያት ካላቀረበ ሌላኛው ለአባልነት አይቀበለውም። ቀደም ሲል እንደተገለፀው ፈኢማዎች የወንድና የሴት ከመሆናቸውም ሌላ አንዱን ፈኢማ ከሌላው የሚለይበት ሁኔታ የለም። ሴቶች የራሳቸው ደንብ አላቸው ወንዶችም በተመሳሳይ።
የሴቶች ፈኢማ በሠርግና በለቅሶ ጊዜ ምን መልክ እንዳለው ስንመለከት ሰው በሚሞትበት ጊዜ «ፈኢማ» ይጠራል። በዚህም ጊዜ የተለየ የአለባበስ ባህል አለ፤ ወደ ለቅሶ የሚመጡ ሴቶች ሁሉ ፀጉራቸው
ላይ ሻሽ ያስራሉ፣ ባዶ እጃቸውን አይመጡም። ይህም የሚደረገው ኀዘንተኛውም ሆነ ዘመዶቹ ምንም ዓይነት ወጪ እንዳያወጡና ፈኢማው ከጎናቸው መሆኑን ለማሳወቅ ነው። ሠርግንም በተመለከተ በፈኢማዎች በኩል ጥሪ ይደረጋል። በሠርግ ጊዜ ብቻ የሚዘፈን ባህላዊ ጨዋታ ይጫወታሉ። በጭፈራውም ወቅት ፈኢማው ቀድሞ ሳይጫወት ሌላ ሰው መጫወት አይችልም። ቀድሞ የሚጫወት ካለ ይቀጣል። ጨፍረው ከዘመድ አዝማድ የሚገኘውን ሽልማት ከፊሉን ለሙሽራው ወይም ለሙሽራዋ እናት ይሰጣሉ። ከዚህ በተጨማሪ «ፈኢማ» ከፍተኛ ክብር ስላለው በድግሱ ወቅት ለአባላት የሚዘጋጅላቸው ምግብ የተለየ ነው።
የሴቶች ፈኢማ ባህልን ከማስጠበቅ አኳያ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ማንኛውም የአፋር ብሔረሰብ እናት ይቀርበኛል ወይም ይስማማኛል በሚሉት ፈኢማ ይደራጃሉ። ይሄ የአፋር ብሔረሰብን ያስተ ሳሰረና የማንነቱ መግለጫ ስለመሆኑ አብዛኛው የብሔረሰቡ አባላት ይናገራሉ። ታዲያ ይህ አኩሪ የሆነው ባህላቸው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ባለፉ ቁጥር ባህሉ ሳይጓደል ለተተኪው ትውልድ እንዴት ነው የሚተላለፈው የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በሂደትም የመዘንጋት ወይም የመበረዝ አደጋ እንዳይገጥመው «በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል» ነውና የሚመለከታቸው አካላት ሊያስቡበት ይገባል መልዕክታችን ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
አብርሃም ተወልደ