ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ናት፡፡ በየዘመናቱ የሀገሬን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር አላስደፍርም ያሉ ጀግኖች ልጆቿ እምቢ ለሀገሬ በማለት አጥንታቸውን ከስክሰው፤ደማቸውን አፍስሰውና ህይወታቸውን መስዋዕት አድርገው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስጠብቀዋል፤ ለተተኪው ትውልድም ነጻነትንና ኩራትን አስረክበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታሪካዊት ሀገር፤ ሕዝቧም የዚህ ታላቅ ጀብዱ ባለቤት ነው፡፡ ይህ ጀግና ሕዝብ የብሔር፤ የሃይማኖት፡ የጾታ እና ሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ሳይበግሩት በአንድነት በዓድዋ፤በመተማና በካራማራ ቅኝ ገዢዎችን እና ወራሪዎችን አሳፍሮ መልሷል፡፡ ለሉዓላዊነቱና ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትናንት በዓድዋ ሀገሩ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ልትወድቅ መሆኑን በሰማበት ቅጽበት ቀፎው እንደተነካበት ንብ ከአራቱም ማዕዘናት በአንድነት ተሰባስቦ ሀገሩን ታድጓል፤ ታሪክ ጽፏል፤ ለመላው ጥቁር ሕዝቦችም መከታ ሆኗል፡፡
ከዓድዋ ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን በየካቲት ወር ከሚያከብሯቸው ድሎች አንዱ የሆነው የካራማራ ድል 46ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡ ሕዝቡን በማስተባበር ታጠቅ ተብሎ በተሰየመው ማሰልጠኛ 300 ሺህ ሚሊሻ በሶስት ወራት በማሰልጠን የእብሪተኛውን የዚያድ ባሬ ጦር ካራማራ ላይ ድል በማድረጉ የኢትዮጵያ አሸናፊነት በአደባባይ የታወጀበት ታሪካዊ ድል ነው።
ከጣሊያንና ከእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ነፃነቷን በ1952 ዓ.ም ያገኘችው ሶማሊያ በነጻነቷ ማግሥት ሶማሊያን ለ21 ዓመታት ያስተዳደሩት ዚያድባሬ፤ ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመስረት በሚል “ድንበራችን እስከ አዋሽ ይደርሳል” እያሉ በመዛት የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽመዋል።
ሆኖም እስከ ድሬዳዋ ድረስ የዘለቀውን ወራሪ ኃይል አሳፍሮ በመመለስና ብሎም ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዲደርስበት በማድረግ ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር መሆኗን ያስመሰከሩ በርካታ ጀብዱዎች ተፈጽመዋል፡፡ ሀገሬ ስትደፈር ከምመለከት ህይወቴ ቢያልፍ እመርጣለሁ ያሉ በርካታ ጀግኖች በአውደ ውጊያው መስዋዕት ሆነው የሀገራችንን ሉአላዊነት አስከብረዋል፡፡ ሆኖም ይህ አኩሪ ድላቸውና መስዋዕትነታቸው በታሪክ ዘላለም ሲዘከር ይኖራል፡፡
እኛ የዛሬ ትውልዶችም ልንቀስመው የሚገባ ትምህርት አለ፡፡ለሀገር ሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ውለታ የሚመለሰው የሰላምና የልማት አርበኛ መሆን ስንችል ነው፡፡ በተለይም ሰላም ለራቃት ሀገራችን የሰላም አምባሳደር በመሆን የአባቶቻችንን መስዋዕትነት ከንቱ እንዳይሆን የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባል፡፡
የግጭት፣ የጦርነት፣ ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ እሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል።
በአባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎ ያገኘነው ኩራትና ነጻነታችን ሙሉ እንዲሆን ሀገሪቱን በልማት ማበልጸግና ኢትዮጵያን በሚመጥናት ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ትውልድ ታላቁን የዓባይ ግድብ ሰርቶ እያገባደደ ነው፡፡ ይህን የሀገር ኩራት የሆነ ግድብ አጠናቆ ለሀገር ብሎም ለአፍሪካ ብርሃን ማጎናጸፍ የዚህ ትውልድ አንዱ አደራ ነው፡፡
በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ የተገኘውን አኩሪ እንቅስቃሴ ዘላቂ ማድረግና ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካን መመገብ ሌላው የዚህ ትውልድ አሻራ ሊሆን ይገባል፡፡ አረንጓዴ አሻራ በማኖር ረገድ ኢትዮጵያውን ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ አኩሪ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት የማይወዱ አካላት ሊያጣጥሉት ቢሞክሩም ተግባሩ የሚደበቅ አይደለምና ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው መድረኮች ሁሉ በውጤታማነቱ እየተወሳ ይገኛል፡፡ ስለዚህም ትውልዱ ይህንን አንጸባራቂ እንቅስቃሴ ከዳር ማድረስና ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን አረንጓዴ ማልበስ ቀጣይ የቤት ሥራው ሊያደርግ ይገባል፡፡
በተለይም ወቅቱ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያ ልክ እንደ ዓድዋና ካራማራ በዓለም መድረክ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ወጣቱ ትውልድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ክህሎት በመታጠቅ የሀገሩን ልማት ወደፊት ሊያራምድ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል በዓድዋም ሆነ በካራማራና በሌሎችም የጦር አውድማዎች የሀገርን ዳር ድንበር አላስደፍርም በማለት ደማቸውን በማፍሰስ፤ አጥንታቸውን በመከስከስ ውድ ህይወታቸውን መስዋዕት ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድም የሀገሩን ዳርድንበርና ሉአላዊነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን በሰላም እና በልማቱም መስክ ሀገሪቱን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚያስችሉ ተግባራትን በመፈጸም መስዋዕት የከፈሉ ቀደምት አባቶችን ፈለግ ሊከተል ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ነው የአባቶች መስዋዕትነት ተገቢውን ዋጋ ሊያገኝ የሚችለው!
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2016 ዓ.ም