ኢትዮጵያ ቡና አምራች ሀገር እንደመሆኗ ለውጭ ምንዛሬ ግኝቷ ቡና ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ከዚህም ባለፈ ቡና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የመኖር ዋስትና ነው፡፡ ይህ በሀገሪቱ የገቢ ምንጭና በአርሶ አደሩ ሕይወት ላይ ትልቅ ድርሻ ያለው ቡና ታዲያ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ መንግሥትም የባለሥልጣኑን ጥረት በመደገፍ ለዘርፉ ዕድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶት እየሠራ ነው፡፡
ባለሥልጣኑ በምርትና ምርታማነት እንዲሁም በግብይት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚያርጋቸው ጥረቶች ሁሉ የመንግሥት ድርሻ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ በተለይም ከግብይት ጋር በተያያዘ በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ውስብስብ አሠራሮችን በማስወገድ የተሻለ የግብይት ሥርዓት በመዘርጋት ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ በተጨማሪም የግብይት ሥርዓቱን ይበልጥ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ የቡና መገኛና አምራች ሀገር እንደመሆኗ ከዘርፉ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወደ ውጭ ገበያ ስትልክ የነበረው የቡና መጠን በዓመት በአማካኝ 200ሺ ቶን ነው፡፡ ከዚሁ ቡናም ሲገኝ የነበረው ገቢም በዓመት በአማካኝ ከ600 እስከ 700 ዶላር ነበር። ይህ እውነታ ከሌሎች ቡና አምራች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የቡና መጠን እዚህ ግባ የማይባል አይደለም፡፡
አሁን ላይ ሮቡስካ ቡናን ጨምሮ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው የቡና መጠን ከ173 ሚሊዮን ኬሻ በላይ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አዱኛ፤ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው 173 ሚሊዮን ኬሻ ቡና ውስጥ ደግሞ ከ100 ሚሊዮን ኬሻ በላይ የሚሆነው አረቢካ ቡና እንደሆነ ጠቅሰው ከዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ የምታቀርበው ሶስት ሚሊዮን መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህንንም ከአረቢካ ቡና ኤክስፖርት አንጻር ሲታይ ከሶስት በመቶ በታች እንደሆነና ኢትዮጵያ የቡና መገኛና አምራች ሀገር እንደመሆኗ አጠቃላይ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ ያነሳሉ።
‹‹ኢትዮጵያ የተለያየ ዓይነት ጣዕምና ጥራት ያላቸውን አረቢካ ቡና እያመረተች የገበያው ተጠቃሚ ያልሆነችበት ምክንያት ምንድነው ተብሎ ሲፈተሽ፤ አንደኛ የግብይት ሥርዓቱ የተንዛዛ መሆኑ ነው›› የሚሉት ዶክተር አዱኛ፤ ቡና ከአርሶ አደሩ ተነስቶ ቡና ላኪው ጋር እስኪደርስ ሰንሰለቱ የረዘመ ነው። በዚህም አርሶ አደሩ ቡናውን ማሳው ላይ ብቻ ለመሸጥ መገደዱን ያመለክታሉ፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ አርሶ አደሩ ቡናውን ማሳው ላይ ሲሸጥ ዋጋ መወሰን እንደማይችል፤ ይልቁንም ዋጋ የሚወስነው ሰብሳቢው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ አርሶ አደሩ ሰብሳቢው በሰጠው ዋጋ ቡናውን እንዲሸጥ የሚገደድ በመሆኑ በገዛ ቡናው የመደራደር አቅም አይኖረውም ይላሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ቡና ሰብሳቢ የሚባለውም እንዲሁ ከዚህም ከዚያም ዱካውን መከተል የማይቻል ሰብስቦ ለአቅራቢው የሚያቀርብ ሲሆን፤ አቅራቢው ደግሞ ቡናውን በሁለት መንገድ አዘጋጅቶ ለዓለም ገበያ ይልካል፡፡ አንደኛው የታጠበ ቡና ሲሆን፤ እሸት ቡናው በተሰበሰበበት ወቅት የሚታጠብ ይሆናል፡፡ አቅራቢው ቡና ማጠቢያ ማሽን ከሌለው ደግሞ ቡናውን አድርቆ ደረቅ ቡና ይሸጣል፡፡ የሚሸጠውም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ (በኢሲኤክስ) በኩል ሲሆን፤ አቅራቢው ዋጋ መደራደርም ሆነ መወሰን አይችልም፡፡ ቡናውን የሚሸጥለት ባለ ወንበር የሚባለው ወኪል ነው፡፡ ይህ ወኪልም የቡናውን ደረጃና ዋጋ የሚወስን ሆኖ ቡና አቅራቢው የተሰጠውን ዋጋ ብቻ የሚወስድበት ሁኔታ ነበር፡፡
ቡና ላኪውም እንዲሁ በኢሲኤክስ ውስጥ መግባት የማይችል በመሆኑ እሱም ባለ ወንበር የሚባል ወኪል ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ በአቅራቢውና በላኪው በኩል ያሉ ባለ ወንበሮች ቡናውን ተደራድረው ይሸጣሉ፡፡ ቡናውን የሚገዛው አካልም የጅማ፣ የሊሙ፣ የጉጂ ብሎ ከገዛ የገዛውን ቡና በትክክል ላያገኝ ይችላል፡፡ ደረጃ አንድ ብሎ ደረጃ ሰባት ሊደርሰው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ገዢው እራሱ ገብቶ ቀምሶና ተከታትሎ መግዛት አይችልም፡፡ ሌላው ዱካውን የተከተለ ምርት ማግኘት የሚችልበት ዕድልም አይኖርም፡፡ በማለት ገበያው ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ሲፈጥር መቆየቱን ያነሳሉ፡፡
ቡና ላኪው ቡና የሚገዛው አስቀድሞ ከውጭ ገዢዎች ጋር በገባው ኮንትራት መሠረት ነው፡፡ ይሁንና ከኢሲኤክስ ቡና ሲገዛ የሚፈልገውን የቡና ዓይነት አያገኝም፡፡ ይህም ኮንትራቱን ማሟላት የሚያስችለው አይሆንም፡፡ በመሆኑም የገዛውን ቡና አስቀምጦ ሌላ ኮንትራቱን ሊያሟላለት የሚችል ቡና ፈልጎ ይገዛል፡፡ የገዛውን ለመሸጥም እንዲሁ ሌላ ኮንትራት ይፈልጋል፡፡ በዚህ የግብት ሥርዓት በርካታ ችግሮች ተፈጥረው እንደ ሀገር ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው ቡና በመጠንና በገቢ እጅግ የቀነሰ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው የቡና መጠን እንዲሁም የገቢ መጠን በመቀነሱ ምክንያት ከኢሲኤክስ ውጭ ያሉ የግብይት አማራጮችን ማየት የግድ በመሆኑ በፖሊሲ ደረጃ ሪፎርም መደረጉን ያነሱት ዶክተር አዱኛ፤ ፖሊሲው ከዚህ ቀደም የነበረውን ብቸኛ የገበያ አማራጭ ወደ ስድስት አማራጮች ከፍ ማድረግ እንደቻለ ያመለክታሉ፡፡ ኢሲኤክስ የተባለው የገበያ አማራጭ እንዳለ የራሱን አሠራር ይዞ እንዲቀጥል በማድረግ የተለያዩ የገበያ አማራጮችን የመጠቀም ዕድል መመቻቸቱንም ያነሳሉ፡፡
እንደ ዶክተር አዱኛ ማብራሪያ፤ ከተለያዩ የገበያ አማራጮች መካከል አንደኛው አርሶ አደሩ በቀጥታ ቡናውን መሸጥ የሚችልበት መንገድ ነው፡፡ ይህም ቡናውን ማሳው ላይ ብቻ እንዲሸጥ የተደረገው አርሶ አደር ሁለት ሄክታር እና ከዛ በላይ መሬት ካለው በቂ ምርት ማምረት ይችላል ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህ አቅም እንዲኖረው በማድረግ በማሰልጠንና ከገበያ ጋር በማገናኘት ቡናውን በቀጥታ ኤክስፖርት ማድረግ የሚችልበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ሁለተኛው አርሶ አደሩ አቅም ከሌለው መሀል ላይ ያሉ ደላሎች ወጥተው ከአቅራቢው ጋር በዋጋ ተደራድሮ ለአቅራቢው ማቅረብ እንዲችል ሆኗል፡፡ ይህም ማሳው ላይ ብቻ ሲሸጥ የነበረው አርሶ አደር ከአቅራቢ ጋር እየተነጋገረ ለአቅራቢው ምርቱን ማቅረብ የሚችልበት የገበያ አማራጭ ነው፡፡
አቅራቢውም እንዲሁ ምርቱን ኢሲኤክስ ሳያስገባ በቀጥታ ከላኪው ጋር ተደራድሮ ቡናውን የሚሸጥበት ዕድል ተመቻችቶለታል፡፡ በእነዚህ የገበያ አማራጮችም አርሶ አደር ኤክስፖርተር ነው። ለአቅራቢም ይሸጣል፡፡ አቅራቢው ደግሞ ለላኪ ይሸጣል፡፡ ይህም ቀጥታ የገበያ ትስስር ይባላል፡፡ ይህ ቀጥታ የገበያ ትስስርም ኢሲኤክስ ላይ ሲፈጠር የነበረውን ችግር ሙሉ ለሙሉ መፍታት የቻለና ገዢው ቡናውን አይቶ፣ አሽትቶና ቀምሶ መግዛት እንዲችል አድርጎታል፡፡
ሌላው የግብይት አማራጭ አቅራቢው ምርቱን ከአርሶ አደሩ ብቻ ገዝቶ ለላኪው ከሚያቀርብ ይልቅ ወደ ልማቱ በመግባት አምራችም ላኪም መሆን የሚችልበት መሆኑን ያነሳሉ፡፡ አቅራቢው ወደ ልማቱ ገብቶ ያለማውን ቡና እንደ አቅራቢም እንደ ላኪም ሆኖ መሥራት እንዲችል አማራጭ ተቀምጧል። በዚህ አቅራቢ ላኪ በሚባል የገበያ አማራጭ አቅራቢው ልማቱንና ዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታውን የማወቅ ዕድል ተፈጥሮለታል ነው ያሉት፡፡
‹‹በቡና ገበያ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተዋናዮች ሴቶች ናቸው›› የሚሉት ዶክተር አዱኛ፤ ሴቶችን በማበረታታት ሴት ቡና አምራቾችን በቀጥታ ወደ ኤክስፖርት እንዲገቡ ማድረግም ሌላኛው የግብይት አማራጭ ሆኖ መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡ አብዛኛው ሴቶች ምርት ላይ ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን ያባክናሉ፡፡ ነገር ግን በድካማቸው ልክ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ‘Women in Coffee ‘ በሚለው የገበያ አማራጭ ሴቶች ቡና አምርተው በቀጥታ መላክ እንዲችሉ አልያም በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ገብተው በቀጥታ መላክ የሚችሉበት የገበያ አማራጭ መመቻቸቱን ይናገራሉ፡፡
ሌላው ቡና ቆይዎች ከዚህ ቀደም በነበረው ፖሊሲ ቡና መግዛት የሚችሉት ከኢሲኤክስ ብቻ የነበረ መሆኑን ያነሱት ዶክተር አዱኛ፤ ከኢሲኤክስ ሲገዙ የነበረው ቡናም ተረፈ ምርት ወይም ደረጃው ዝቅ ያለና ጥራት የሌለው ምርት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በመሆኑም ቡና ቆይዎች ከኢሲኤክስ ወጥተው የተሻለ ጥራት ያለው ቡና ከአምራቹ አልያም ከአቅራቢው በቀጥታ መግዛት የሚችሉበት የገበያ አማራጭ ማምጣት ተችሏል፡፡ እነዚህንና መሰል የገበያ አማራጮቹን ማስፋት በመቻሉም በግብይት ሥርዓት ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን መፍታት መቻሉን ያብራራሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ በአሁን ወቅት ሀገሪቷ ወደ ውጭ ገበያ ከምትልከው ቡና ከ80 እስከ 90 በመቶ ያህሉ አቅራቢውና ላኪው ተስማምተው የሚረካከቡት የግብይት ሥርዓት ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም የተጀመረው ይህ የቀጥታ ትስስር፤ በወቅቱ ወደ ውጭ ገበያ ሲላክ ከነበረው 200ሺ ቶን ቡና 20 በመቶ ያህሉ በቀጥታ ትስስር 80 በመቶው በኢሲኤክስ ይገበያይ ነበር፡፡ በአሁን ወቅት ግን ቀጥታ የገበያ ትስስርን አጠናክሮ በመቀጠል የተሻለ ውጤት ማስመዝግብ ተችሏል፡፡ በመሆኑም ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው የቡና መጠንና የሚገኘው የገቢ መጠን እንዲሁም የጥራት ደረጃው ከፍ እያለ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የቻለችው በ2014 ዓ.ም መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር አዱኛ፤ በወቅቱ 1 ነጥብ 42 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ይናገራሉ። ውጤቱ የተገኘውም በ2013 ዓ.ም የተጀመረው የቀጥታ ትስስር የገበያ አማራጭ በ2014 ዓ.ም በስፋት የተኬደበት ሲሆን፤ የኢሲኤክስ ድርሻ እየቀነሰ ሄዷል፡፡ አብዛኛው ቡና አምራች፣ አቅራቢና ላኪም ወደ ቀጥታ ትስስር በመግባት የተሻለ ጥራት ያለው ቡና ለዓለም ገበያ ማቅረብ የተቻለ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
‹‹ይህን የግብይት አማራጭ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ በኋላ በቡና ኤክስፖርት ላይ ተጨባጭ የሆኑ ለውጦች ታይተዋል›› የሚሉት ዶክተር አዱኛ፤ በ2015 ዓ.ም የዓለም የገበያ ዋጋ በ32 በመቶ መውረዱን ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ግን አቅራቢው ከአምራቹ በጥራት የሰበሰበውን ቡና ለላኪው ሲያቀብል በጥራት በመሆኑ የጥራት ደረጃው ከፍ ብሏል፡፡ በወቅቱ ለዓለም ገበያ የሚላከው የኢትዮጵያ የቡና መጠን በቶን በ18 በመቶ ጨምሯል፡፡ ይህም ማለት በ2014 አንድ ቶን ቡና በአራት ሺ ዘጠኝ መቶ ዶላር ሲሸጥ የነበረው ቡና በ2015 አንድ ቶን ቡና በአምስት ሺ አራት መቶ ዶላር መሸጥ ተችሏል፡፡ ይህም በቀጥታ የገበያ ትስስር የተገኘ ውጤት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
‹‹በቀጥታ የገበያ ትስስር የተገኘው ውጤት ዘርፈ ብዙ ነው›› የሚሉት ዶክተር አዱኛ፤ በሀገር ደረጃ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ብቻ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በ2013 ዓ.ም አንድ አርሶ አደር አንድ ኪሎ እሸት ቀይ ቡና ከ10 እስከ 12 ብር ይሸጥ እንደነበር አስታውሰው በ2014 ዓ.ም ወደ 50 እና 60 ብር ከፍ ማለቱን ያመለክታሉ፡፡ እንዲሁም በ2015 ዓ.ም ከዓለም የገበያ ዋጋ ጋር በመናበብ በኪሎ እስከ 40 ብር ድረስ ሲሸጥ ነበር፡፡
ይህም አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም ከቡና የሚያገኘው ገቢ ለቡና የሚያወጣውን ወጪ የሚመልስለት ባለመሆኑ ቡናን ከማምረት ተቆጥቦ ቡናውን በመንቀል በምትኩ ባህር ዛፍና ጫት ይተክል እንደነበር ይገልፃሉ። ይሁንና ካለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ አርሶ አደሩ ቡናን መልሶ የመትከል ሥራ እያሰፋ የመጣና አበረታች ውጤትም እያስመዘገበ የሚገኝ መሆኑን አመላክተው፤ ለዚህም ቀጥታ የገበያ ትስስር ትልቅ ድርሻ አለው ነው ያሉት፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2016 ዓ.ም