ሕጻናትን ከጎዳና ሕይወት ለመታደግ

ዓለም በተቃርኖዎች የተሞላች ነች፡፡ እነኝህ ተቃርኖዎች ጥሩ እና መጥፎ ውጤቶችን ያስከትላሉ። ከዚህ አኳያ ማርክሲስቶች ተቃርኖዎችን በሁለት ይከፍሏቸዋል፡፡ አንደኛው ተፃራሪ ተቃርኖ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የማይጻረሩ ተቃርኖዎች ይሉታል፡፡

የማይጻረሩ ተቃርኖዎች የጋራ ጥቅም ባላቸው መደቦች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚፈጠር ነው፡፡ ይህ ማለት በዚህ ተቃርኖ ውስጥ ያሉ አካላት ወደ ግጭት አያመሩም፡፡ ይልቁንም ተቃርኖውን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የሀገራቸውን እና የሕዝባቸውን የኑሮ ሁኔታ ያሻሽሉበታል፡፡

በአንጻሩ ብዝበዛ እና ጭቆና በበዛበት ኅብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ቅራኔዎች ደግሞ ተፃራሪ ተቃርኖዎች ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ማህበራዊ ቀውስን የሚያመጣ ሲሆን፤ በእንደዚህ አይነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የምትንከላወስ ሀገር ደግሞ ዜጎቿ በከፍተኛ ችግር እንዲማቅቁ የተፈረደባቸው ናቸው፡፡ በርካታ ሰዎችም ለጎዳና ህይወት እና ለስደት ይጋለጣሉ፡፡

ስለተቃርኖዎች እንዳነሳ ያስገደደኝ አብይ ምክንያትም የማርክሲዝምን ፍልስፍና ለመዘርዘር ስለፈለኩ አይደለም፡፡ አሁን አሁን በሀገራችን ብሎም በዓለም ሀገራት እየተስፋፋ ያለውን መጠነ ሰፊ ስደት እና የጎዳና ህይወት አሳሳቢነት ለመግለጽ ስለፈለኩ ነው፡፡

በሀገራችን እንኳን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ ወላጅ ወይም አሳዳጊ ያጡ ሕፃናትን እና በቤት እጦት በየጎዳናው ለመኖር የተገደዱ ዜጎችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ በጎዳናው ላይ የሚኖሩ ሕፃናት አንጀታቸው ታጥፎ፤ ከንፈራቸው ደርቆ ፤ እግሮቻቸው በጸሐዩ ግለትና በአቧራው ቆስለው፤ በወላጅ ፍቅር ልባቸው ተሰብሮ በየጥጋጥጉ ተኮራምተው፤ በክረምት ዝናቡ በበጋ ፀሐዩ ሲፈራረቅባቸው ማየትም አዲሳችን አይደለም፡፡

በተለይ በክረምት! ባልበላ አንጀታቸው ዝናብ ሲቀጠቅጣቸው መስተዋሉ እጅግ አንጀት ይበላል፡፡ ሌሎች አጋዥ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ቢሆንም፣ በጎዳና ሕፃናት የሚስተዋለው ከልካይ እና ወሰን የሌለው ነጻነት ደግሞ ወደ ሱስ እንዲያመሩ አድርጓቸዋል፡፡

ጠዋት ሲነሱ ምን እንደሚያደርጉ፣ ምን እንደሚበሉና እንደሚጠጡ የሚያስብላቸው፤ ስለእነርሱ የሚሟገትና አለኝ የሚሉት ደራሽ ወገን የላቸውም፡፡ ብዙዎቹ ጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት ስለ ነገ አያውቁም፡፡ ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ተማምነውት የሚነሱት ፈጣሪያቸውንና ለእርዳታ እጆቻቸውን የሚዘረጉላቸውን ደጋግ ሰዎች ብቻ ነው። ካልቀናቸውም ጎዳናውን መሸሸጊያ አድርገው ጦማቸውን ውለው ያድራሉ፡፡

“ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም” እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 2021 ባወጣው ሪፖርት በአለማችን 150 ሚሊዮን የሚሆኑ ቤት አልባ ሰዎች መኖሪያቸውን በጎዳና ላይ አድርገዋል፡፡ ቢዝነስ ኢን ሳይደር አፍሪካ እ.አ.አ በ2023 ባወጣው ሪፖርት መሠረት ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለት ነጥብ 6 ሚሊዮን ያህል ሰው ጎዳና ላይ በማኖር ከአፍሪካ ሀገራት በስድስተኛነት ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

በ2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተደረገ ጥናትን ዋቢ በማድረግ ለአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ማብራሪያው በከተማዋ 66 ሺህ 575 የሚጠጉ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚገኙ አመላክቷል፡፡

ከዚህ ቁጥር ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት ከ10 እስከ 40 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ናቸው። በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህ ቁጥር ወደ 100 ሺህ ከፍ ሊል እንደሚችል ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ይህ እድሜ ደግሞ በአመዛኙ አምራች የሚባለው የዕድሜ ክልል በመሆኑ እንደ ሀገርም ብዙ እያጣን መሆናችንን ይጠቁማል፡፡

ስለቁጥሯዊ መረጃው ይህንን ያክል ያልኳችሁ የችግሩን አሳሳቢነት ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ነው። በየትኛውም የዓለም ሀገር የጎዳና ተዳዳሪዎች ያሉ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በየሀገሩ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር እና አኗኗር የተለያየ ነው፡፡ ሰዎችን ወደ ጎዳና እንዲወጡ የሚያደርጉና በጥናት የተመላከቱ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡

ከእነኝህ መካከል ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት እጦት ቀዳሚው ነው፡፡ ቤተሰባዊ ጉዳዮችም ሌላ ገፊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የቤተሰብ መፍረስ፣ የቤት ውስጥ ፀብ እና የድጋፍ እጦት ሕፃናትን ወደ ጎዳና የሚያስወጣ አብይ ምክንያት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም ሰዎችን ወደ ጎዳና ከሚያስወጣ አስገዳጅ ምክንያቶች መካከል ነው፡፡ የአዕምሮ ጤና ችግር እና አደንዛዥ ንጥረ ነገሮችን አላግባብ በመጠቀምም ሰዎች ወደጎዳና እንዲወጡ ሊያደርግ ይችላል፡፡

በእኛ ሀገር ለሚስተዋለው የጎዳና ህይወት መፈጠር ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም ዲሞክራቲክ ዋህድነት በሀገራችን አለማደጉ ዋነኛው ምክንያት ይመስለኛል። ዲሞክራቲክ ዋህድነት ከፍተኛ አመራሩ እና ዝቅተኛ አመራሩ በሀገሪቱ ያለውን ችግር ከሪፖርት ባለፈ በጥናት ላይ በተመሰረተ ትንታኔ የጋራ ምክክር አድርገው አንዳቸው ያዳቸውን ክፍተት ሞልተው የሕዝባቸውን ኑሮ የሚያሻሽሉበት ነው፡፡

ይሁን እንጂ የበላይ አመራሩ እና የበታች አመራሩ ተናቦ እና ተደማምጦ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ባህሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በሀገራችን የሚስተዋለውን የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር ለመቀነስ እንደ ሀገር ዲሞክራቲክ ዋህድነት (Democratic Centralism) ሊፈጠር ይገባል፡፡

ምክንያቱም ሰዎች ወደ ጎዳና ሲወጡ በሀገራት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ከማሳደሩም ባሻገር፤ በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ አሉታዊ ጥላ ያጠላል። በርካቶች በጎዳና ላይ ሲኖሩ ጉዳቱ ጎዳና ላይ ከወጡት ሰዎች ባሻገር ለሀገር እና ማህበረሰብም ነው፡፡ የጎዳና ላይ ኑሮ የሕዝብ ሀብትን ይጎዳል፣ የጤና አጠባበቅ ወጪዎችን ይጨምራል፣ ለአጠቃላይ የህይወት ጥራት ማሽቆልቆል አስተዋፅኦ ያደርጋል።

በአንጻሩ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎች ሲደገፉ የሚጠቀሙት ጎዳናውን መኖሪያቸው ያደረጉ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥት እና ሕዝብ ጭምር ነው። እናም መንሥት የተረጋጋ ሀገርን ለመምራት ካሰበ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎችን ቁጥር ሊቀንስ ይገባል፡፡ ምክንያቱም በርካታ ሀገርን ወደለየለት የትርምስ ቀጣና ለመውሰድ የሚፈልጉ ኃይላት በቀላሉ ጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን እና ወጣቶችን ይጠቀማሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ለሕፃናቱ ኃላፊነት ወስዶ ክፉውን ከደጉ እንዲለዩ የሚያደርግ ቤተሰብ አለመኖሩ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ሰዎችን ከጎዳና በማንሳት ወደ ማገገሚያ ማዕከል እንዲገቡ ሲያደርግ ቆይቷል። አስገብቷቸው ከነበሩ ዜጎች ውስጥ 513 አጋዥ የሌላቸውን ዜጎች በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ እንደዚህ አይነቶቹ በጎ ጅምሮች ያሉ ቢሆንም ችግሩ በሀገራችን ካለው አሳሳቢት አኳያ በቂ ስላልሆነ በስፋት ሊሰራበት ይገባል፡፡

የሕፃናት ጉዳይ የሴቶች ፣ ሕፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሥራ ብቻ ሳይሆን እንደ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እንዲሁም እንደ ሀገር ሁሉም ሊሠራበት የሚገባው ነው፡፡ የጎዳና ልጆችን ህይወት መቀየርም ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን፤ ማህበረሰቡ እና ባለሀብት ግለሰቦችን የወል ተግባር የሚሻ ነው፡፡ በመሆኑም ሕፃናትን ከጎዳና መታደግ የዛሬም፣ የሁሉም የቤት ሥራና ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን የካቲት 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You