በሀገሪቱ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ የመዝናኛ ዝግጅቶች አዲስ ቅርፅና ይዘት ተላብሰው መቅረብ ጀምረዋል።በተለይም በኮሜዲው ዘርፍ በሀገር ደረጃ እንደ አዲስ ብቅ ያለውና በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመቅረብ ላይ ያሉት “ሲትኮም“ ኮሜዲዎች ለዚህ አንድ ማሳያ ናቸው።
ሲትኮም ኮሜዲ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ኪናዊ በሆነ ጥበቡ እያሳቀ ፣እያዝናና ቁም ነገር አዘል መልዕክቶችና ጉሸማዎችን አዋዝቶ ለታዳሚው የሚያቀርብ ነው።
በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በርክተው የሚገኙት እነዚህ ሲትኮም ኮሜዲ ድራማዎች ይዘው የመጡት አዲስ አቀራረብ ተቀባይነታቸውን ከፍ ቢያደርገውም አልፎ አልፎ በሚያቀርቡት ይዘት ደካማነትና በሚያነሱት ርዕሰ ጉዳይ ትችትን ማስተናገዳቸው አልቀረም። ድራማዎቹ ከሚነሳባቸው አሉታዊ አስተያየቶች መካከልም የሰውን ስብዕናና መብትን በሚነካ መልኩ ገፀ ባህሪይ በመሳል ያቀርባሉ፤ የሚያነስዋቸው ርዕሰ ጉዳዮች ስሱ ከመሆናቸው የተነሳ በማህበረሰብ ደረጃ ቁጣን ይቀሰቅሳሉ፤ የአብዛኞቹ ይዘት ተመሳ ሳይነት ያለው ነው። በአጠቃላይ አቀራረቡ ሙያዊ ስነ ምግባርን የጠበቀ አይደሉም የሚል ናቸው።
የመዝናኛ ዝግጅቶቹ አቀራረብ ከተለመደና አሰልቺ ከነበረበት መላቀቃቸው እሰይ የሚያሰኝ ቢሆኑም አንዳንድ መዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ሲትኮም ኮሜዲ ድራማዎች ማህበራዊ ሃላፊነታ ቸውን የዘነጉ ይመስላል።ስራውን አውቀው፣ የሙያ ስነምግባሩን አክብረው እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች በቁጥር አነስተኛ ናቸው። በስነምግባር ውስጥ አለማለፋቸው “ጠንካራ” ሲትኮሞች አብረው እንዲወቀጡ አድርጓቸዋል።ያም ሆኖ አንዳንድ የተዋጣላቸው ሲትኮም ኮሜዲ ድራማዎች ሳይበገሩ ስራቸውን ቀጥለዋል። በተለይም አንዳንዶቹ መነጋገሪያ ከመሆን አልፈው ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉበት ሁኔታም ይታያል።
በመዝናኛ ዝግጅቶች ላይ የሚቀርቡት አብዛኛዎቹ ሲትኮም ድራማዎች ውለው ሲያድሩ የተነሱበትን ሀገራዊ ሃላፊነት በመዘንጋት ወይም የዜጎችን በጎ ስብዕናን የመቅረፅ አላማ በመርሳት የግለሰቦችን ክብር ማንኳሰስ፣ የማህበረሰብን ወግና ባህል ማጉደፍና መዳፈር፣ ያልተጨበጡ አሉባልታዎችን በማናፈስ ለእርስ በእርስ ቅራኔ መንስኤ በመሆን ሃላፊነታቸውን በመዘንጋት ላይ ይገኛሉ። በተለይ በኮሜዲው ዘርፍ የማስተማር ሳይሆን አንዱ አንዱን የማንኳሰሻ አንዱ ሌላውን የማጥላላት ዘመቻና ነቆራ እየተለመደ መምጣቱን የሚናገሩት የዘርፉ ባለሙያዎች ናቸው።
ለሶስት ተከታታይ ወራት ለዕይታ የበቃው “ትንሽዋ ፓርላማ” ሲትኮም ድራማ ደራሲና አዘጋጅ ተስፋ ንዳ ሲትኮም ድራማ በሌሎች ዓለማት የቆየ ቢሆንም በሀገር ደረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣ አዲስ ዘውግ መሆኑን ይናገራል። ዘርፉ በደንብ ከተሰራበት በማህበረሰቡ የሚነሱ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በማንሳት ሃሳብን በማንሸራሸር ማህበረሰባዊ ህፀፆችን ማረሚያ ማድረግ እንደሚቻል ማስረጃዎችን ያቀርባል።
አርቲስት ተስፋ በፅሁፍ እና በዝግጅት የሚሳተፍበት ትንሽዋ ፓርላማ ሲድኮም ድራማ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚናፈሱ የተለያዩ ጉዳዮች በማንሳት ስህተቶች እንዲታረሙ፤ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን ማህበረሰቡ በትክክልና ለበጎ አላማ ሊያውለው እንደሚገባ በማዝናናት ማስተማርን መርሁ ያደረገ መሆኑን ይናገራል። ሲትኮም ኮሜዲ ድራማው ወቅታዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ለውይይት በር መክፈት እንደቻለ ከተመልካች የሚቀርብላቸው አስተያየት መነሻ አድርጎ ያስረዳል።
በትንሿ ፓርላማ ሲትኮም ድራማ ላይ በፕሮዲዩሰርነትና በአዘጋጅነት የሚሳተፈው አርቲስት ጥላሁን ሺነበርክ፤ ሲትኮም ድራማ የሙያው ሥነ ምግባር በጠበቀ መልኩ ከተሰራበ ትና ካደገ ሀገራዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ይናገራል። ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ከማህበረሰቡ ተቀድቶ በቀልድ እየተዋዛ መልሶ ለማህበረሰቡ
በማቅረብ ትክክለኛና መልካም የሆነ እሳቤን መፍጠር ያስችላል የሚል እምነት አለው። እንዲህ አይነት ድራማዎች በአዲስ መልኩ በቁጥርም በአይነትም መበራከታቸው የሚበረታታ መሆኑን ገልፆ ጥራትና ይዘታቸው ላይ ግን ሊሰራ ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ መጠን በማህበረ ሰቡ ብዥታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚገልፀው ደራሲና አዘጋጅ ተስፋ በሚያዘጋጀው ትንሿ ፓርላማ ሲትኮም ድራማ ላይ የሚሰጡ አስተያየቶች በአመዘኙ መልካም መሆኑና ለዚህም የድራማው ይዘት ላይ ለአንድ አመት ያህል ጊዜ ጥናት አድርገው እንዳዘጋጁት ይናገራል። ይህም ከተመልካች ጥሩ ተቀባይነትን ማግኘት ያስቻላ ቸው ምክንያት መሆኑን ያስረዳል። ሲትኮም ድራማ ተዘጋጅቶ ለህብረተሰቡ በመገናኛ ብዙኃን ከመቅረባቸው በፊት በጥንቃቄ ይዘታቸው መፈ ተሽ እንዳለበትና ግለሰቦችን ሳይሆን ሃሳብ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ተናግሯል።
“የምን ልታዘዝ” ድራማ ደራሲ አዘጋጅና ፕሮዲዩሰር የሆነው በሀይሉ ዋሴ (ዋጄ) ድራማው የሚያነሳቸው ማህበራዊ ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉና የመገናኛ ብዙሃን ህግና ደንብ ያከበረ እንደሆነ ያስረዳል።“ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ ምን ልታዘዝ ሙሉ ለሙሉ ከስህተት የራቀ ነው ማለት አይቻልም።” ያለው አርቲስት በሀይሉ በይዘትና በታሪክ ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የራሱን ድራማ ዋቢ በማድረግ ያስረዳል።
በሲትኮም ኮሜዲ ድራማም ሆነ በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል ዘርፉ ያለበትን የሙያ እውቀትና የገንዘብ ችግር መቅረፍ ቀዳሚ መፍትሄ እንደሆነ ገልጿል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበብ መምህር አቶ ምንያህል በንቲ በአሁኑ ሰዓት “ሲትኮም” ድራማዎች ቢበራከቱም የሲትኮም ኮሜዲን ባህሪ የሚያሟሉ አለመሆናቸውን ይናገራሉ። በአቀራረብና በይዘት ረገድም በአብ ዛኛው የሙያውን መርህ ያልተከተሉና የተሳሳተ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። የሚያነሱት ርዕሰ ጉዳይ ጥንካሬና እውነት የጎደለው ስለመሆኑ፣ከማሳቅ ባለፈ ታዳሚው ቁም ነገር ማስጨበጥ ላይ ትኩረት አለማድረጋቸው፣ በጣም ስሱ እና የማይደፈሩ ጉዳዮች (ብሄረሰብ እና እምነት) ነክ ጉዳዮች ላይ ተገቢ ያልሆነ አገላለፅ እንደሚጠቀሙ ታዝበ ዋል። ይሄ ደግሞ ሙያውን እጅግ የሚጎዳው ተግባር መሆኑን ነው በአስተያየታቸው የጠቀ ሱት። በተጨማሪም ግለሰቦችንና ቡድኖችን በመፈረጅ የራሳቸውን አቋም በተቃርኖ ከማቅረብ በዘለለ አስተማሪ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ላይ የሲትኮም ድራማዎቹ ችግር አለባቸው ሲሉ ይጠቅሳሉ።
ሲትኮም ኮሜዲ ድራማ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚነሱ ጉዳዮችን ከመፈረጅ ይልቅ የተሻሉ ሃሳቦችን በማፍለቅ በቀላሉ ችግሮቹን መፍቻ መንገድ፣ መፍትሄ ማሳያ መሳሪያ ማድረግ እንደሚቻል አቶ ምንያህል ይገልጻሉ። በአዲስ መልክ እየተሰሩ የሚቀርቡት ሲትኮም ድራማዎች የማህበረሰቡን ባህልና ወግ ጠብቀው መዘጋጀት እንዳለባቸውና የሙያውን ስነምግባር ሊከተሉ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ። ይሁን እንጂ አሁን እየታዩ ያሉት ድራማዎች ግን ከሙያው ስነምግባር ያፈነገጡ ናቸው ለማለት ይቻላል።
ሲትኮም ኮሜዲ ድራማ እንደ ሀገር መላመድ የጀመረ አዲስ ድራማ እንደመሆኑ መጠን ብዙ የሚቀረው ስለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል። የተሻሉ ናቸው የሚባሉትም ቢሆኑ አንድ ሲትኮም ድራማ ሊያሟላው ይገባል ተብሎ በሙያው የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ አለመሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እዚህ ላይ ግን ከሞላጎደል ስራቸውን በትክክል ሰርተው የማህበረሰቡን ጉዳዮች በመዳሰስ የተሻለ አዎንታዊ ሚና የሚጫወቱ ሲትኮም ድራማዎች እስካሁን አልተሰሩም ወይም አሁንም የሉም ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል። በአዲስ አቀራረብ፣ ጠንካራ የታሪክ አወቃቀርና ባልተለመደ መልኩ ስራዎችን አቅርበው ተቀባይነትን በማግኘት ተወዳጅ ሆነው የዘለቁ ሲትኮም ኮሜዲ ድራማ ዎች ከነውስንነቶቻቸው መኖራቸው የማይካድ ሀቅ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
ተገኝ ብሩ