አዲስ ዘመን ድሮ

አዲስ ዘመን ጋዜጣ እለታዊ ኩነቶችን እየዘገበ በርካታ ጉዳዮችን በትውስታ ማህደሩ በማኖር ታሪክን ለትውልድ ሲያሻግር ኖሯል።

ከዘመን ዘመን አድማሱን እያሰፋ ዛሬን በደረሰበት መንገድ፤ የሚያስታውሰን ብዙ አለ። ለዛሬ መለስ ብለን ከቃኘናቸው ርእሰ ጉዳዮች በቁጥር ከፍ ያሉት ወንጀል ነክ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሆነው እናገኛቸዋለን። አንደኛው ርእሰ ጉዳይ ወህኒ ቤት ገቡ ይለናል፤ ለመሆኑ የገቡት ማናቸው? የግብጹን ፕሬዚዳንት በአዲስ አበባ ለመግደል የወጡት ሦስቱ አሸባሪዎች የመጨረሻው እጣ ፈንታቸው ሞት ሆኗል። ደራሲው ማሞ ውድነህ “ዋሻ ይሠራሉ” ሲል እኛስ ለምን? በማለት ከሚመጣው የጦርነት ቅኝቱ ያካፍለናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከአንባቢው የጥያቄና የሀሳብ ድግሶች መሐከል ጥቂቱን በ”አንድ ጥያቄ አለኝ” ስር ከጳውሎስ ኞኞ ምላሾች ጋር ሰፍረዋል።

ወህኒ ቤት ገቡ

በአንዲት የሞተች ጥጃ ምክንያት በተነሣው የወንጀል ክርክር አንዲት የ30 ዓመት ሴት ዘጠኝ ልጆቻቸውን ጥለው ወህኒ ቤት መግባታቸውን ከአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተገኘው ዜና ታውቋል ።

እመት እልፍነሽ ወልደየስ የተባሉት የልጆች እናት ወህኒ ቤት ለመግባት ዋና ምክንያት የሆነባቸው አንዲት ጥጃ ገዝተው አርደዋል ተብለው ተከሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ነው።

በተከሳሿ ላይ የቀረበው የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመለክተው፤ ጥጃዋ ከታረደች በኋላ ተደርሶበት የቀረቡት ምስክሮች ቆዳዋ የተገኘው ጥጃ እመት ጌጤ የተባሉትን ሴት ጥጃ ትመስላለች በማለት ምስክሮች ባሰሙት ቃል ብቻ መሆኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ይገልጣል ።

እመት እልፍነሽ ፤በሞተች ጥጃ ምክንያት ተከሰው አዲስ አበባ አውራጃ ፍርድ ቤት ቀርበው በ፫ ወር እሥራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸው ወህኒ ቤት መግባታቸውን የተከሳሿ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የይግባኝ ማመልከቻ ገልጠዋል ።

(አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 1965 ዓ.ም)

ተቆጣጣሪ በመምሰል ያጭበረበረው ተቀጣ

ደሴ፣ ኢዜአ በደሴ ከተማ ውስጥ ምንም አይነት ሥልጣን ሳይኖረው የአሥር አለቃ ነኝ በማለት ከገጠር ወደ ከተማ የሚገባውንና የሚወጣውን እህል፣ ስኳርና ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በመፈተሽ ሲያወናብድ የተገኘው ዓሊ መሐመድ በ3 ወር እስራት እንዲቀጣ የ04-01-01 ቀበሌ ማኅበር የፍርድ ሸንጎ ከትናንት በስቲያ ወስኖበታል።

በተከሳሹ ላይ የእስራት ቅጣት ሊወሰንበት የቻለው ባልተሰጠው ሥልጣን በመንገድ ላይ እየጠበቀ ስኳርና ሸቀጥ ጭነው ወደ ገጠር የሚወጡትንና እህል ጭነው ወደ ከተማ የሚገቡትን መኪናዎች እያስቆመ በመፈተሽ የተመቸውን ጥቅም በመቀበል ሲለቅ ያልተመቸውን ደግሞ ወደ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በማቅረብ አወናብዶ ለማስቀጣት ሞክሮ እንደነበር በማረጋገጡ ነው።

(አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 1969ዓ.ም)

በሦስቱ አሸባሪዎች ላይ የሞት ቅጣት ተበየነ

(ኢ.ዜ.አ) የግብጹን ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክን አዲስ አበባ ላይ ለመግደል የሞከሩና ሁለት ኢትዮጵያውያንን ገድለው ሶስቱን ያቆሰሉ አሸባሪዎች በሞት እንዲቀጡ ትናንት ያስቻለው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ። የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ እንዳስታወቀው ሰውፊት ሃሰን፣ አብዱል ቃኒ፣ አብዱል ከሪም አብዱልናዲና አልአረብ ሳዲቅ ሃፊዝ በተባሉ ግብጻውያን ላይ ቅጣቱ የተበየነው አቃቤ ህግ ያቀረበባቸው ማስረጃ በዝግ ችሎት ላይ ሲመለከት በነበረው ፍርድ ቤት በመረጋገጡ ነው።

(አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 1989ዓ/ም)

ዋሻ ይሠራሉ

በዛሬው በዚህ በሚያሰጋው ጊዜ ድንገት አንዱን ቀን የሚፈራው የ3ኛው የዓለም ጦርነት የተነሣ እንደሆን ሽማግሌዎች፤ አሮጊቶች፤ ሕጻናቶች ከተቻለም ቁስለኞች የሚገቡበት ዋሻ በየቦታው እየተሠራ ነው። ይህንንም ዋሻ የሚሠሩት ሰዎች በትርፍ ጊዜያቸው ፈቃደኛ የሆኑት ናቸው። ዋሻው ከሚቆፈርበት ቦታ ድረስ የሚሄዱት መኪና ያላቸው በራሳቸው መኪና ሲሆን፤ የሌላቸው ደግሞ የሚሄዱት በነጋዴዎችና በልዩ ልዩ ማኅበር ሥር በሚያገለግሉት አውቶቡሶች ትላልቅ መኪናዎችና በታናናሽ የቤት አውቶሞቢሎች ነው ። ይህም ሥራ የሚሠራው በሌላ ሀገር ነው እንጂ በኛ ሀገር መስሏችሁ ውሸት ነው እንዳትሉኝ ሌላዎቹ ሀገሮች ይህን ሲሠሩ እኛስ ምነው?

ማሞ ውድነህ(ዋግ ድሃና)

አንድ ጥያቄ አለኝ

-አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

*የወንድሜ ጥርስ ሁለቱ ከወለቀ ሦስት ዓመቱ ነው። ከዛሬ ነገ ይበቅላል ስንል ምንም አላወጣም። ጥርሱ የሚወጣው በስንት ዓመቱ ነው?

እመቤት ሽፈራው

-አሁን ዕድሜው ስንት ነው? ድዳም ሆኖ እናዳይቀር ከጥርስ ሐኪም ዘንድ ወስዶ ማሳየቱ ያስፈልጋል። ያለዚያ ሊበላሽ ይችላል።

*በጥንት ጊዜ ዝንጀሮ ሰው ነበር የሰው ገንዘብ ተበድሮ በልቶ የሚከፍለው ስላጣ በብረት ምጣድ ተቃጥሎ ወደ ዝንጀሮነት ተለወጠ ይላሉ ። እውነት ነው ወይንስ አፈታሪክ ነው?

ወ/ት ቀለመወርቅ በላይ

-ያፍ ታሪክ ነው።

*ከሥራ ወጥቼ እስከ ምሽቱ 6 ሰዓት ድረስ ለማምሸት እፈልጋለሁ። ከጓደኞቼ ጋር መጫወት እፈልጋለሁ። ግን ሚስቴ ከሥራ ወጥተህ እንደ ዶሮ መስፈር አለብህ ትላለች፤ ትጨቀጭቀኛለች። ብመክር ባስመክር አልሰማ አለች። ልፍታት?

-እንደሱ አይደለም ጌታው እኔንም አይቆጡኝና ሚስትዎን በድለዋል። ክሰው ከቤትዎ ማምሸት ይልመዱ። እንደራስዎ ይዩት። ነገሩ ተገላብጦ ሚስትዎ ከውጭ እያመሹ እርስዎ ቤት እንዲጠብቁ ቢደረግ ይወዳሉ ? ተናደው የቤቱን ሳህን ሁሉ ይፈጁ ነበር። የሚያስመሽዎ ጓደኞችዎም መጥፎዎች ናቸውና ይሽሹ። ጨዋ አባወራ ይሁኑ እንጂ ሚስትዎን አይፍቱ። ለመሆኑ እንዲያው ግን ለመሆኑ አመልዎን ሳያስተካክሉ ለምን ሚስት አገቡ?

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 12 ቀን 1958ዓ.ም)

 

አዲሙሉጌታ ብርሃኑ

ስ ዘመን  የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You