ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረጉ ጉዞ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ዲጂታላይዜሽንን ማስፋፋትና ማሳለጥ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችም እየተሠሩ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን ወደ ዲጂታል መቀየር፣ የክፍያ ሥርዓቶችን በኤሌክትሮኒክ እንዲሆኑ ማስቻል እና ለዲጂታል ሥራዎች አጋዥ የሆኑ የተለያዩ መተግበሪያዎች በልጸገው በተግባር ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውን መጥቀስ ይቻላል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረጉን ሥራ በበላይነት የሚመራው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም በቴሌኮም የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በሲስተሞች ልማት፣ በአስቻይ ምህዳር ፈጠራ እና በሰው ሀብት ልማት ረገድ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ መደላድል የሚሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ውጤቶች እንዲመዘገቡ እያደረገ ይገኛል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በባለፈው ሳምንትም በዲጂታል ረገድ የተሠሩ ሥራዎች በማስተዋወቅ ኅብረተሰቡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለመጨመር የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀቱ ይታወሳል። በመሆኑም የመጀመሪያው ‹‹የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት›› ‹‹የጋራ ጥረታችን ለዲጂታል ኢትዮጵያችን›› በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 18 እስከ የካቲት 22 ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በማዘጋጀት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲያካሄድ ቆይቷል ።

በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የመጀመሪያው ዲጂታል ሳምንት ለተከታታይ አምስት ቀናት መካሄዱ ማኅበረሰቡ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች እንዲያውቅና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው ። ሳምንቱም እንደ ሀገር በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)ና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ሲሰሩ የነበሩ ሥራዎችን ኅብረተሰቡ እንዲያወቃቸው ለማድረግ ያስቻለ ነው።

በሳምንቱ በተከናወኑ መርሃ ግብሮች በየክልሉ የሚገኙ የቴክኖሎጂና የአይሲቲ ዘርፉን ለሚመሩ አመራሮች፣ ለአጋር አካላትና ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ የተቻለበት እንደሆነም አመላክተዋል ። በመሆኑም በየእለቱ የተለያዩ ፕሮግራሞች የቀረቡ መሆኑን አስታውሰው፤ የመጀመሪያ ቀን ከክልል አመራሮች ጋር በዲጂታል ዘርፉ ላይ ልምድ ልውውጥ መድረጉን አንስተዋል ። ከዚህ በተጨማሪም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) በተመለከተ የተሠሩ ሥራዎች መጎብኘታቸውን ተናግረዋል ።

በሁለተኛውና በሦስተኛው ቀናትም የኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ እና ኢንተርፕራይዝ አርክቴክቸር በተመለከተ የተዘጋጁ ሰነዶች ቀረበው ውይይት ተካሄዶባቸዋል። በተለይ የኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ ለቀጣይ አምስት ዓመት የሚመራበት ስትራቴጂ ለማጽደቅ እንዲቻል የመጨረሻው ግብዓት ለማሰባሰብ የሚያስችል ውይይት የተካሄደበት እንደነበር ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰዋል።

በቀጣዮቹ ቀናትም እንዲሁ በዲጂታል ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ በርካታ ሥራዎች የቀረቡበት እንደሆነ የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በእነዚህ ቀናት በግሉ ዘርፍ እና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰሩ የተለያዩ ሥራዎች የቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህ ሥራዎች በዲጂታል ዘርፍ ያለውን ሀገራዊ አቅሞችን መገምገምና ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚያስችሉ ሥራዎች የተሰሩበት ነው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ በመርሃ ግብሩ አጠቃላይ በሀገር ደረጃ በዲጂታልና በአይሲቲ የተሰሩ ሥራዎች ሀገራዊ የዲጂታል አቅም የታየበት ነው ። በተለይ ሀገር በቀል በሆኑ እውቀቶች መጠቀም እንደሚገባ ያለንን አቅም እንድናይ የሚያደርገን ነው ። ሀገር በቀል አቅምን ስንጠቀም ደግሞ የጊዜ ብክነት ያስቀራል፤ የሰው ኃይል በአግባቡ እንድንጠቀም ያስችላል ። በተጨማሪም በሀገራችን የተሰሩ ኦፕሬቲንግ ሲስተም እና የራሳችን የሆነ ምርቶች መጠቀም ከደህነትም አንጻር ብዙ ፋይዳ አለው ። ምክንያቱም የሌሎች ሀገራት የተሰሩ ምርቶችን መጠቀም ከደህንነትም ሆነ ከውጭ ምንዛሪ ወጪ አንጻር ሲታይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ። በራሳችን የተሠሩ ውጤታማ የሆኑ ሥራዎችን ሲኖሩ የወደፊቱ ትውልድ ተስፋ አድርጎ የበለጠ ሥራ እንዲሰራ ያስችላሉ።

‹‹በዲጂታል ሳምንቱ የተሠሩ ሥራዎች በሀገር ደረጃ በዲጂታልና በአይሲቲ ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎች እየተገመገሙ ማኅበረሰቡ በእነዚህ ሥራዎች በመጠቀም የዲጂታል ሥራዎች እንዲሰራና የዲጂታል ሥራው እንዲቀላጠፍ ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ለማስገባት ከዲጂታል ቴክኖሎጂ እውን የሚያደርጉ ውጤታማ ሥራዎችን በመሥራት እንደሆነ ያስረዳሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በዋናነት መሠራት አለባቸው የተባሉት ተግባራት በግልጽ የተቀመጡ ናቸው። የመጀመሪያ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ነው። ይህ ሲባል በዋናነት የኤሌክትሪክ ኃይልና እና የኢንተርኔት ኔትወርክን እስከታችኛው ማኅበረሰብ ድረስ ማስፋትና ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው። እንዲሁም የዳታ ማዕከላትን መገንባት እና ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች መገንባትንም የሚጠይቅ ነው።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን እንዲሆን ማስቻል በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ብቻ የሚፈጸም ተግባር ሳይሆን የሁሉንም የመንግሥት ተቋማት አብሮ መሥራት የሚጠይቅ ነው ያሉት ዴኤታው፤ ለአብነት የኤሌክትሪክ ኃይልና እና የኢንተርኔት ተደራሽነት ስንል እነዚህ አገልግሎቶች ከተቋሙ ውጭ የሚሰሩ ስለሆነ እነዚህ ሥራዎች ለመሥራት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር አንድ ላይ በመቀናጀት መሠረተ ልማቱን በአብሮ የሚሰራ የሚያስፈልግ መሆኑን ያስረዳሉ።

‹‹በተጨማሪ አስቻይ ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል ። ዲጂታልን ስናነሳ የዲጂታል ግብይቶች ይኖራሉ ። ከሌሎች ጋር በዲጂታል መንገድ ግንኙነት ስናደርግ የዲጂታል ሲስተም ውስጥ መታወቅ አለብን ። ይህ ስናደርግ ደግሞ በዲጂታል መታወቂያ( አይዴ) አማካይነት ነው። እንዲሁም እንደ ቴሌ ብር፣ ኤምፔሳ እና ሌሎችም የዲጂታል ክፍያ ፕላትፎርሞችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል›› ነው ያሉት።

‹‹ዲጂታል የራሱ የደህንነት ስጋቶች ያሉት፤ ለዚህም የሳይበር ደህንነት ምህዳርን ማጠናከር ያስፈልጋል›› የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም በተቋም ደረጃ ተዋቅሮ እየተሰራ እንደሆነና በዲጂታል ፕላትፎርሞች ላይ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው ያስረዱት ። ለዚህም የመንግሥት አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ የማድረግ፣ ኢኮሜርስ ፕላትፎርሞች ያሉ ሲሆን፣ በእነዚህ ፕላትፎርሞች የንግድ ሥራዎችን እና የመንግሥት አገልግሎቶችንም በዲጂታል እንዲሳለጡ መደረጋቸውን ያነሳሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ የዲጂታል ሥነ ምዳሩን መገንባት ያስፈልጋል ። ምክንያቱም ለዲጂታል ዘርፉ ፋይናንስ ማዘጋጀት፣ በዘርፉ በቂ የሰው ኃይል ማፍራት እና በአጠቃላይ ኢኮሲስተሙን የሚያሳልጥ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ እንደሆነ ነው የገለጹት ። ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ እነዚህ ዋና ተግባራት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሪ ሆኖ ከሁሉም ተቋማት ጋር በአንድ ላይ የሚሰሩ ሥራዎች መሆናቸው ገልጸው፤ የግሉ ዘርፍንም ተሳትፎ የሚጠይቁ መሆኑን አብራርተዋል ።

እንደ ሚኒስቴር ዴኤታው ማብራሪያ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ በፍጥነት እውን እንዲሆን በመንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው አራት ዘርፎችም የግብርና፣ የቱሪዝም፣ የማኑፋክቸሪንግ እና አጠቃላይ አገልግሎቶችን በአይሲቲ ሲስተሞች እንዲሆኑ ማድረግ ናቸው። በተለይ ሲስተሞችን በአይሲቲ እንዲሆን ማድረግ፤ ሌሎች ሲሰተሞች ላይ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመሥራት እና የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያግዝ ነው።

እንደ ሀገር ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በሀገር አቅም የተሰሩ ሁለት ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ተናግረዋል ። ‹‹እነዚህ ፕሮጀክቶች ሀገራችን ያላትን እምቅ አቅም ለማየት ያስቻሉ ናቸው›› ብለዋል ። እነዚህ ፕሮጀክቶችም የሀገራዊ ኔትወርክ ማሳለጫ /National Network Exchange of Ethiopia/ እና የኢትዮኑክስ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ሥርጭት Ethionux Operating System Distribution ናቸው ብለዋል።

በሀገር አቅም የተሰሩ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የናሽናል ኔትወርክ ፕሮጀክት መሪ አቶ ዳንኤል አድነው እንዳሉት፤ አሁን ላይ በሀገራችን የምትጠቀምበት የኢንተርኔትና የኔትወርክ ፕሮቶኮል አሮጌ ነው። ሌሎች ሀገራት የሚጠቀሙት የኢንተርኔት ዓይነት ለመጠቀም የሚያስችል አይደለም። በመሆኑም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ለማሻሻል የሚያስችል የመጀመሪያ የኢንተርኔትና የኔትወርክ ፕሮቶኮል መሥራት ተችሏል ።

አሁን የተሰሩ እነዚህ ሥራዎች ሌሎች ሀገራት የሚጠቀሙበት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ግን እስካሁን መሥራት ሳይቻል መቅረቱን አንስተዋል። እስካሁን በሌሎች ሀገራት በሰሩት የኔትወርክ ማሳለጫ እየተጠቀምን እንደሆነ ጠቅሰው፤ የተሰሩት ፕሮጀክቶች ይህን ችግር የሚፈታና ሀገሪቷ ያላትን አቅም የሚያሳዩ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

የፕሮጀክቶቹ ሥራ ተጠናቅቆ የሚቀረው በተግባር ላይ ማዋል እንደሆነ የሚጠቁሙት አቶ ዳንኤል፤ ፕሮጀክቶቹ ተግባራዊ ሲደረጉ አሁን ላይ እያጋጠመ ያለው የኢንተርኔት መጨናነቅም አይኖርም ። ተጠቃሚ ለሚሆኑ አካላት ቴክኒካዊ ድጋፍ መስጠት፣ ፖሊሲ እንዲወጣ እና የተለያዩ ስትራቴጂዎች ወጥተው በሀገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን በከፍተኛ ፍጥነት ለመጓዝ ያስችላል ይላሉ።

‹‹በሌሎች ሀገራት (ሱማሊያ፣ ጂቡቲ እና ኬንያ) ይህን የኢንተርኔት ዓይነት እየተጠቀሙ እኛ የማንጠቀምበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም›› ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ይህ ፕሮጀክት ሀገሪቱ ሌሎች ሀገራት የሚጠቀሙት ዓይነት ኢንተርኔት ለመጠቀም የሚያስችል አቅም እንዳላትና ከዚህ በላይ መሥራት እንደሚቻል በተግባር ለማሳየት ያስቻለ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።

አሁን ላይ በሀገሪቱ የኢንተርኔት ኮኔክቲቪቲ ችግር እንዳለ ጠቅሰው፤ ችግሩም ምንድነው፣ የጎደለውስ ምንድነው፣ አገልግሎቶቹ ኖረውም አገልግሎት የማይሰጡትስ በምን ምክንያት ነው፤ የሚለውን በመለየትና ጥናት በማድረግ ይህን ፕሮጀክት መሥራት እንደተቻለ ይገልጻሉ ። ይህ ፕሮጀክትም እነዚህን ችግሮች የሚቀርፍ ሲሆን፤ በቀጣይም ይህን ለማሻሻል የሚያስችል ሀገራዊ የኔትወርክ ማሳለጫ (National network Exchange) አምስት ቦታዎች ላይ እንዲኖር በማድረግ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል ። ይህም ተግባራዊ ሲሆን የሳይበር ደህንነት ስጋት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ እንደሚያስችል ነው አቶ ዳንኤል የሚናገሩት ።

‹‹እስካሁን ባለው አሠራር በሀገራችንን ኢንተርኔት ለመጠቀም ሆነ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገራት በመውጣት ተመልሰን መግባትን የሚጠይቅ ነው›› ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ይህ ሲሆን ደግሞ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሚዳርግ መሆኑን አመላክተዋል ። በተለይ የሳይበር ደህንነት ስጋቶች ተጋላጭ የመሆን እድሉን ሊያሰፋው የሚችል መሆኑን አብራርተዋል ።

እሳቸው እንዳሉት፤ በሀገራዊ አቅም የተሰራ የኔትወርክ ማሳለጫ የኢንተርኔት ፍሰቱን 80 በመቶ ያህል በማሳደግ የሳይበር ደህንነት የሚቀንስ ነው ። ለዚህ አገልግሎት የሚወጣውን ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ፕሮጀክቱ ሀገሪቱ ለኢንተርኔት ማሳለጫ በዓመት ታወጣው የነበረውን ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚያስቀር ነው።

ይህን ማሳለጫ መሥራት ባለመቻሉ ሀገሪቷ እስካሁን ለኢንተርኔት ብቻ ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣ እንደነበር ያነሱት አቶ ዳንኤል፤ ይህ ፕሮጀክት እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶችን በሀገር ውስጥ መሥራት የሚቻል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ይላሉ። ፕሮጀክቱንም በቅርቡ በተግባር ላይ በማዋል አንድ ማሳለጫ በአይሲቲ ፓርክ የሚቋቋም መሆኑን አመላክተዋል።

‹‹የሰዓት ፕሮቶኮል እና ኢንተርኔት ፕሮቶኮል ቨርሽን 6 /IPV6/ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የለም›› ያሉት አቶ ዳንኤል፤ የሰከንዶች ልዩነት ትልቅ የገንዘብ ኪሳራ የሚደርስ መሆኑን ይገልጻሉ ። ይህን ግን አብዛኞቻችን ትርጉም አንሰጠውም ። ሌሎች ሀገሮች ጊዜን ወደ ገንዘብ የሚቀይሩ ብዙ ሥራዎችን ሰርተው ከአንድ እስከ አስራ ሁለት የኢንተርኔት ማሳለጫ ያላቸው ሀገሮች አሉ ። በእኛ ሀገር የሌሉት እንዳሉ ሆነው ያሉትንም ቢሆን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ። የቴክኖሎጂ አቅም ብዙ መሥራት እየቻልን ሳንጠቀም እየቀረ ነው›› ይላሉ።

የተሠሩት ሥራዎች እስካሁን በሀገራችን የሌሉ ናቸው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ እነዚህን መጠቀም ባለመቻላችን ፈጣንና ከፍተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት እንዳልተቻለ አመላክተዋል።

ፕሮጀክቱ በቀጣይም ሀገሪቱን በሳይበር ደህንነት የተጠበቀ ኢንተርኔት ኔትወርክ ማሳለጫን ተግባራዊ የሚያደረግ መሆኑን ጠቁመው፤ ለኢንተርኔት የሚወጣው ከፍተኛ ወጪን በማስቀረት ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ፍጥነት ባለው የኢንተርኔት ኔትወርክ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚሰራ መሆኑን አመላክተዋል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን  የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You