በዓድዋ ጦርነት ድል እንዴት ሊገኝ ቻለ?

ኢጣሊያኖች እ.አ.አ በ1888 ከሸዋው ንጉስ ምኒልክ ጋር ለመፈራረም የውጫሌን ውል አዘጋጁ። ኢጣሊያ ኤርትራን ከወረረች በኋላ የተዘጋጀው ይኸው ውል ኢጣሊያ በባሕር ዳርቻ ቅኝ ግዛት ላይ ያላትን ጥያቄ እውቅና እንዲሰጥ ተደርጎ የተመቻቸ ነበር። ውሉ ኢጣሊያ የገንዘብ ድጋፍ እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ቃል የገባችበት የሁለቱንም ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ቢባልም፤ የስምምነቱ አንቀጽ 17ን ጨምሮ ሌሎችም የውሉ አንቀፆች በሁለቱ የሰነድ ቅጂዎች ትርጓሜ ላይ ልዩነት ስለነበራቸው አለመግባባት ተፈጠረ።

በተለይም አወዛጋቢው አንቀፅ 17 በጣልያንኛ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሁሉንም የውጭ ጉዳዮችን በኢጣሊያ ባለሥልጣናት አማካይነት የማካሄድ ግዴታ እንዳለበት የሚያስቀምጥ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያን የጣሊያን መንግሥት ፍቃደኝነት ላይ እንድትመሠረት ያስገድዳታል። የጽሑፉ የአማርኛ ቅጂ ግን ንጉሠ ነገሥቱ ከውጭ ሀገራት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት የኢጣሊያን መንግሥትን ቢሮዎች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይገልፃል። ዳግማዊ ምኒልክም ይህንን እና ሌሎችም የትርጉም ልዩነቶች ሲያውቁ ተቃወሙ፤ ከኢጣሊያን ዲፕሎማቶች ጋር ተጋጩ ።

የቃል ግጭቱን ተከትሎ የኢጣሊያ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ እንደሚገባ እና እንደሚወር አሳወቀ። ይህን ተከትሎ ጦርነት ተጀመረ ። ኢትዮጵያውያን ተበድለናል በሚል ስሜት በአንድነት ተባብረው ከኢጣሊያ ጋር ባካሔዱት ጦርነት ድልን ተቀናጁ ። በዘመኑ ነጭ በጥቁር መሸነፉ የመጀመሪያው አስደማሚ ዜና ነውና ዓለም ተገረመ ። ይህ ድል እንዴት ሊገኝ እንደቻለ፣ ያስገኘው ጥቅም እንዲሁም ወደፊት ድሉን በሚመጥን መልኩ ምን መሠራት እንዳለበት ምሁራን የተለያዩ ትንታኔዎችን ይሰጣሉ ።

የታሪክ እና የባሕል ተመራማሪው አቶ ዓለማየሁ ኃይሌ እንደሚያስረዱት፤ በዋናነት የድሉ መነሻ የሀገሬው ሕዝብ በጋራ እና በጠነከረ አንድነት የውጭ ኃይልን ለመከላከል ያደረገው ዝግጅት ነው ። ንጉሠ ነገሥቱ ከቀኝ ገዢው መልዕክተኛ ጋር ከፍተኛ ክርክር ሲያካሂዱ ብዙ ሕዝብ ያውቅ ነበር ። በዛ ክርክር ንጉሠ ነገሥቱ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሕዝብና በንጉሠ ነገሥቱ ሥር ያሉ ንጉሶችን ቁጭት ውስጥ ጨምሯል ። በየአካባቢው የነበሩ በጉልበትም ሆነ በዲፕሎማሲ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች የተዛመዷቸው እና ያሰባሰቧቸው ንጉሶች፤ ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹ሀገራችን ልትወረር ነው፤ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ሀብት ያለህ በሀብትህ ያቃተህ ደግሞ በፀሎትህ እርዳኝ ።›› በማለት ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ወደኋላ አላሉም ።

መልዕክቱ ከስድስት ወር በኋላ ጥቅምት ላይ ወረሂሉ ድረሱ የሚል ሲሆን፤ በዛ ጊዜ የተመመው ሠራዊት የኢጣሊያን 20 እጥፍ አካባቢ ነበር ። ኢጣሊያ ንጉሶቹ ሁሉ በአንድነት ይዘምቱብኛል ብላ አልገመተችም ነበር ። ነገር ግን ንጉሶቹ ወደኋላ አላፈነገጡም ። የትግራይ፣ የሐረር፣ የአማራ፣ የወሎ፣ የአፋር፣ የኦሮሞ፣ የሸዋ፣ የወለጋ፣ የወላይታ የጉራጌ ሁሉም ሕዝብ እና ንጉሶችም ከንጉሠ ነገሥቱ ጎን ቆሙ። በሌላ በኩል ዕለቱ የጊዮርጊስ ንግስ በመሆኑ ለኢጣሊያ ጦር ‹‹ንጉሠ ነገሥቱ ታቦት ለማንገስ ወደ ቤተክርስቲያን ሄደዋል ።›› የሚል የተሳሳተ መረጃ እንዲደርሰው ተደረገ ። ባሻ አዋሎኣምን የመሳሰሉ ጀግና ሰላዮች የኢጣሊያ ጦር በተሳሳተ መንገድ ከምሽጉ ወጥቶ ለወረራ እንዲነሳ መገፋፋታቸው ለድሉ መገኘት ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ዓለማየሁ ይናገራሉ።

ሌላ በአስራ አንድ ሰዓት ሌሊት የተጀመረው ጦርነት በቀን ስምንት ሰዓት በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተደመደመበት ምክንያት በተለይ ሰሜን አካባቢ የነበሩ ለኢጣሊያ ያደሩ መስለው ኢትዮጵያን የረዱ ሰላዮችም ሆኑ ሀገራችንን አንወጋም ብለው በኢትዮጵያ በኩል ሆነው ኢጣሊያን ሲያስጨንቁ የነበሩ የኤርትራ ተዋጊ ኃይሎችም ሚናቸው ከፍተኛ ነበር ይላሉ አቶ ዓለማየሁ።

የጦር መሪዎች በነጠረ ስትራቴጂ መመራታቸው ያበረከተው አስተዋፅኦ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ መልከዓ ምድሩ የነበረው አስተዋፅኦም የሚናቅ አለመሆኑን ያስረዳሉ። መልከዓ ምድሩ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች የኢጣሊያን ጦር እየከፋፈሉ ለመውጋት እና የጠላት ኃይል ሳይገናኝ ለመደምሰስ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ ጠቁመዋል። በዋናነት መጠቀስ ያለበት ግን የሕዝቡ ተነሳሽነት እና በአንድነት የመዝመት ጉዳይ ነው የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል።

ሌላው የዓድዋ ድልን ምክንያት የሚያብራሩት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ደረጄ እነው (ዶ/ር) ግን በከፊል የአቶ ዓለማየሁን ሃሳብ በመደገፍ እና የተወሰነውን በመቃወም እርሳቸው የድሉ መገኘት ምክንያት ነው ብለው የሚያምኑበትን ያብራራል። ደረጄ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ በወቅቱ ኢትዮጵያ ኢጣሊያንን ታሸንፋለች ብሎ መገመት ቀርቶ፤ ሁለቱን በውትድርና አቅም ማወዳደር አይቻልም ነበር ። ለእዚህ ብዙ መላምቶች ያሉ ቢሆንም፤ በዋናነት ተጠቃሽ የሆነው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በብዛት ጦርነቱ ላይ መሳተፋቸው ነው በማለት ከአቶ ዓለማየሁ ጋር የተመሳሰለ ሃሳብ ሰንዝረዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች እና አጠቃላይ ተዋጊዎች አንድነታቸው በዓለም ተወዳዳሪ እንዳልነበረው አስታውሰው፤ ለምሳሌ የሸዋ፣ የየጁ፣ የጎጃም፣ የሐረርጌ፣ የትግራይ፣ የወሎ፣ የቋራ እና የሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ፈረሰኞች እና ጠመንጃ ብቻ ይዘው የዘመቱት አርበኞች ውጊውን ተናበው በአንድነት ማካሔዳቸው ለድሉ መገኘት ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተ ያብራራሉ።

በተጨማሪነት ግን ከዓድዋ ድል በፊትም ሕዝቡ በተደጋጋሚ በጦርነት ውስጥ ማለፉ ድሉ እንዲገኝ አስተዋፅኦ እንዳለው የሚጠቅሱት ደረጄ (ዶ/ር)፤ የዓድዋ ድል ከመገኘቱ ከሃያ ዓመታት በፊት ጀምሮ ኢትዮጵያ ከግብጾች፤ ከመሃዲስቶች ጋር ጦርነት አካሂዳ አሸንፋለች ። የዶጋሌ ጦርነትን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ሌሎችም ጦርነቶችን ማሳለፋቸው እና ልምድ ያላቸው መሆኑ ለመጣው ውጤት ልምዳቸው ያበረከተው አስተዋፅኦ በቀላል የሚወሰድ አይደለም ይላሉ።

ደረጄ (ዶ/ር) ጨምረው እንደሚገልፁት፤ የወቅቱ የጦር መሪዎች ጣይቱን ጨምሮ እነሃብተጊዮርጊስ እና ባልቻ አባነብሶ ጦርነቱን መምራት ብቻ ሳይሆን እነርሱም በወኔ ጦርነቱ ውስጥ ገብተው መዋጋታቸውም ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል። በተጨማሪ የተዋጊዎቹ ቁርጠኝነትም ተጠቃሽ መሆኑን አስታውሰው፤ የጦር መሪዎቹ ‹‹በጥይት ከጀርባዬ ከተመታሁ ስሸሽ ነውና እንዳትቀብሩኝ አሞራ ይብላኝ፤ ግንባሬን ከተመታ ግን የትውልድ ቦታዬ ቅበሩኝ›› እያሉ ለሚመሯቸው መንገራቸው እንዲሁም፤ አንዱ ቢሞት ማለትም ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ እንደተባለው አንዱ ሌላውን ተክቶ ውጊውን መርቶ በቁርጠኝነት መግፋቱ ለድሉ መገኘት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን አመላክተዋል።

ደረጄ (ዶ/ር) አቶ ዓለማየሁ እና ሌሎችም ቢሆኑ የዓድዋ ተራራ አስተዋፅኦ አለው እንደሚሉ አስታውሰው፤ ነገር ግን ተራራው ጦርነቱን ለማሸነፍ ምቹ ነው ከተባለ የሚሆነው ለሁለቱም ነው። ምክንያቱም እንደውም ተራራውን ቀድመው ይዘው የነበሩት ኢጣሊያዎች በመሆናቸው ኢጣሊዮኖች ማሸነፍ ነበረባቸው። ይሄ የኢትዮጵያን ጀግንነት የሚያደበዝዝ መሆኑን ጠቁመው፤ የድሉ መገኘት ምክንያት መልከዓ ምድሩ ነው ብለው እንደማያምኑ አመልክተዋል።

አቶ ዓለማየሁ የዓድዋ ድል ያስገኘውን ጥቅም አስመልክቶ እንዳስቀምጡት፤ በአንኳርነት ሊጠቀስ የሚችለው የኢትዮጵያን አንድነት በማጠናከር በኩል ያበረከተው አስተዋፅኦ ነው ። የዓድዋ ድል ሰሜኑን ከደቡብ፣ ምዕራቡን ከምሥራቁ ያገናኘ እና ያዋደደ እንዲሁም ኢትዮጵያ ነጭን በማሸነፍ በዓለም ደረጃ የታወቀች እንድትሆን ያደረገ ነው ብለዋል ።

ደረጄ ዶ/ር በበኩላቸው የዓድዋ ድል ትልቁ ትሩፋት ከኢትዮጵያውያን በላይ ከአፍሪካውያን አንፃር ቢታይ የተሻለ ነው የሚሉት እምነት አላቸው ። ምክንያታቸው ደግሞ ኢትዮጵያውያን በድሉ በመጠቀም በኩል ሰፊ ክፍተት እንደነበረባቸው ያብራራሉ። አንደኛው ክፍተት ድሉን የተወሰኑ ግለሰቦች ያመጡት ድል እንደሆነ ብቻ የማስቀመጥ ክፍተት ነበር ። በፆታም ሆነ በብሔር በሁሉም መስክ የተሳተፉትን መዘንጋት እና ድሉን ለአንድ ወገን ብቻ በመስጠት የመበረዝ ችግር እንደነበር ተናግረዋል።

ሴቶች በውጊያ ከመሳተፍ ጀምሮ ቁስለኛን ማንሳት እና ማከም፤ ውሃ ማጠጣት እና ምግብ ማዘጋጀት ሌሎችም ተሳትፎዎችን ሲያደርጉ ነበር። በሌላ በኩል ውጊያው ላይ የተለያዩ ወገኖች ለድሉ መገኘት ሰፊ ሚና ተጫውተዋል። ነገር ግን ድሉ በአንድ ወገን ብቻ እንደተገኘ በማስመሰል ድሉ ላይ ጥላ እንዲያጠላ ተደርጓል የሚል እምነት እንዳላቸው ደረጄ (ዶ/ር) ተናግረዋል። ያም ቢሆን ኢትዮጵያ በዓለም እንድትታወቅ ከማድረግ ጀምሮ ልጆቿ ጀግኖች መሆናቸውንን እና በውትድርና ስኬታማ መሆን የሚችሉ መሆናቸውን ለዓለም ማሳያ ሆኗል ይላሉ።

በኋላም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመበቀል ስትወር በጊዜው በድጋሚ ሕዝቡ የማሸነፍ መንፈስ ኖሮት ለአምስት ዓመታት ሃያ አምስት ሺህ ኢትዮጵያውያን ጫካ ውስጥ ሆነው እንዲዋጉ ጀግኖች በከተማ ውስጥም ግራዚያንን ለመግደል እንዲሞክሩ በማነሳሳት በኩልም ጥቅም አለው ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

ደረጄ (ዶ/ር) እንደሚሉት ድሉ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ሰፊ አስተዋጽኦ ማበርከት ቢችልም፤ በሚገባው ልክ ኢትዮጵያውያን አልተጠቀምንበትም የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ጥቁር የነጭን የቀኝ ግዛት አስተሳሰብ ያሸነፈችበት በመሆኑ መንፈሱ ትልቅ ነው። ድሉን በበቂ መጠን አልተጠቀምንበትም፤ በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ በተቃራኒ በርዘነዋል። ከኢትዮጵያውያን ይልቅ አፍሪካውያን ተጠቅመውበታል። ፓን አፍሪካኒዝምን ከማቀጣጠል ባሻገር አፍሪካውያን በዓለም ደረጃ ቀና ብለው እንዲራመዱ አስችሏል ።›› ብለዋል።

የድሉን ጉዳት አስመልክቶ የታሪክ እና የባህል ተመራማሪው አቶ ዓለማየሁ እንደሚናገሩት፤ ጦርነቱ ኢትዮጵያ ምንም አልተጎዳችም ማለት የማይታሰብ ነው ። በጦርነቱ ወቅት የከብቶች በሽታ ተከስቶ ነበር ። የኅዳር በሽታ፣ ክፉ ዘመን የተባሉ ጊዜዎች ነበሩ ። በበሽታ እና በጦርነቱም ብዙ ሰው አልቋል ። ብዙ ቤተሰቦች ተጎድተዋል ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ አሁን ያላት ግዛት እንዲኖራት እና ወደብ እንዳይኖራት ትልቅ ምክንያት ሆኗል በማለት አብራርተዋል። እንደ አቶ ዓለማየሁ ገለፃ፤ በዛ ጊዜ የአውሮፓ ነገሥታት እነ እንግሊዝ እና እነ ፈረንሳይ የመሳሰሉት ሀገራት ኢጣሊያኖች በታች በኩል ኦጋዴንን ለቀው በልዑል ራስ መኮንን ተደራዳሪነት ወደታች ተመልሰዋል። በመቋደሾ በኩልም ወደኋላ ተመልሰዋል። በኬንያ በኩልም እንግሊዞች ነበሩ። በተለይ ኬንያን ሲገዙ ቦረናን ከፍለው አስቀርተዋል። በሱዳን በኩልም ያለው የድንበር ልዩነት ድሉ ከተገኘ በኋላ መቀመጡ ይታወቃል። ይሄ ሁሉ ከዓድዋ ድል ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

የወደፊቱን አስመልክቶ የሚናገሩት ደረጄ (ዶ/ር)፤ አሁን የዓድዋ ድልን ለመጠቀም እየተሠራ ያለው ሥራ መልካም ቢሆንም፤ ምግብ ካበሰሉት ጀምሮ፣ ጦሩ እንዲበረታ እና በወኔ እንዲዋጋ እየዘፈኑ እየሸለሉ ሲያነሳሱ የነበሩትን ጨምሮ ሌሎቹንም በቀጣይም ማወሳት ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚህ በፊት የነበረውን በመተው የዓድዋ ድል የጋራ ታሪክ መሆኑን በማመን ለአንድነት አንደኛው መጠቀሚያ እንደሆነ ማስቀመጥ ይቻላል ብለዋል። ለምሳሌ የሕዳሴ ግድብ ወደ አንድ እንዳመጣን ሁሉ፤ ዓድዋም ወደ አንድነት እንዲያመጣን ከዚህም በላይ ልንጠቀምበት እንደሚገባ ተናግረዋል ።

የታሪክ እና የባህል ተመራማሪው አቶ ዓለማየሁም ያለፈውን ብቻ እያስታወሱ መኖር ሳይሆን ካለፈው ተምሮ የወደፊቱንም ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል ። የዓድዋ ድል የሚያስተምረን አንድነት ምን ያህል ኃይል መሆኑን ማወቅ እንደሚገባ አመልክተው፤ የአሁኑ ትውልድ ዓድዋ የጥቁሮች የድል ተምሳሌት መሆኑን ከማወቅ ባሻገር የድሉን ታላቅነት ለዓለም ማስተጋባት አለበት ብለዋል ። ሌላው ድሉን በትምህርት ካሪኩለሙ ውስጥ በአግባቡ በማካተት ከታች ጀምሮ ትውልዱ አውቆት እንዲያድግ መሥራት እንደሚስፈልግም ጠቁመዋል።

አሁን ላይ አንዳንድ ማህበራዊ ችግሮች መኖራቸውን በማስታወስ፤ መሪውም ሆነ ተመሪው በመወያየት ወደ ሰላም በመምጣት ተማሪው እንዲማር፣ ገበሬው ወደ እርሻው እንዲሠማራ፣ ነጋዴውም እንዲነግድ፣ ወታደሩም በአግባቡ ግዳጁን እንዲወጣ አንድ በሚያደርጉን እንደ ዓድዋ ድል ዓይነት ታሪኮች ላይ መግባባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You