ዓድዋን በዘመኑ መንፈስ መግለጥ ይገባል!

የኢትዮጵያ ቀዳሚነት እና ተምሳሌታዊ መንገድ በዘመን የሚታጠር፣ ከሁኔታ ጋር ብቻም የሚገለጽ አይደለም ። ይልቁንም የኢትዮጵያ ስሪት፤ የኢትዮጵያውያንም ተፈጥሯዊ ውቅር ከራስ ባሻገር ለሌሎች በመትረፍ ውስጥ የተቃኘ ከመሆን የሚመነጭ ነው ። ለዚህ ደግሞ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በኩራት ከሩቅም፣ ከቅርብም ያሉ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ከራስ ባሻገር ስለ ሌሎች ደኅንነት፣ ሰላምና ነጻነት የመቆም አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚገለጸው የዓድዋው ድል እና መንፈሱ ነው ። እንደሚታወቀው የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ለአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ስምሪት ቦታ የነፈገችበት፤ እንቢኝ ብሎ ወደ ግዛቷ የዘለቀውን ወራሪም አንገት አስደፍታና አሳፍራ የመለሰችበት፤ በዚህ ተግባሯም ለሌሎች አፍሪካውያንና ጭቁኖች ሁሉ ተስፋን የፈነጠቀችበት ነው።

የዓድዋ ድል እንደ ሀገር መተባበርን፣ በአንድ መሰለፍን፣ ለጋራ ሕልውና በጋራ ቆሞ ዋጋ መክፈልን ብቻ ሳይሆን፤ ውስጣዊ ችግሮችና ልዩነቶች የጋራ ጠላትን በጋራ ሆኖ ለመፋለም እንከን እንደማይሆኑ በተግባር የገለጠ ነው ። ስለ ሀገር ሉዓላዊነት፣ ስለ ሕዝብ ክብርና ደኅንነት ሲባል ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥበት የሰብዕና ልኬትም ያሳየ ነው።

የዓድዋ ድል እንደ አፍሪካ ለቅኝ ግዞት እንቢኝ ማለትን፤ ክብርና ነጻነትን አሳልፎ አለመስጠትን ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለዜጎች ክብርና ነጻነት መሪና ተመሪ በአንድ ልብ መክሮ በጋራ የሚሰለፍበትና ዋጋ የሚከፍልበት እንጂ በሌሎች ችሮታ የማይመጣ ስለመሆኑ ትምህርት የሰጠ ነው።

የዓድዋ ድል ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች የሀገርን ሉዓላዊነት ማጽናት እንደሚቻል፤ ወራሪን ድል ነስቶ ማባረር እንደሚቻል፤ የሰው ልጅ በሰውነቱ ከማንም የማይበልጥ፣ ከማንም የማያንስ መሆኑን በማስረዳት ለነጻነትና ክብራቸው እንዲታገሉ መነሳሳትን ያጎናጸፈ ነው።

የዓድዋ ድል በጥቅሉ ለሰው ልጆች የመቻል፣ የማድረግ፣ በራስ አቅም የመቆም፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች የመትረፍ፣ በሌሎች ፍላጎትና ይሁንታ ስር አለመውደቅ ወይም ለሌሎች ጥቅምና ፍላጎት አለመገዛት፣ ስለ ክብርና ነጻነት ዋጋ የመክፈል ልዕልናን፤ ይሄን ማድረግም የሚያጎናጽፈውን ክብርና ከፍታ ያስተማረ ነው ። ከማስተማር ባለፈም በጭቆና ቀንበር ስር ያሉ ሁሉ ስለ ክብርና ነጻነታቸው ታግለው ነጻነታቸውን ማስከበር፣ ክብራቸውንም ማስመለስ አስችሏቸዋል።

ይሄ አቅምና መንፈስ ከኢትዮጵያ ምድር የወጣ ነው፤ ይሄ ከፍታ ከኢትዮጵያውያን የማድረግ አቅም የመነጨ ነው፤ ይሄ የነጻነት ተጋድሎ ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ነጻነትን አሳልፎ ያለመስጠት ሰብዕና የተወለደ ነው ። እናም የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብርን፤ ዓለምአቀፍ ተቀባይነትና የዲፕሎማሲ ከፍታን ሲያጎናጽፍ፤ ለአፍሪካውያን ወንድሞችና ለመላው ጭቁኖች ደግሞ የነጻነት ችቦን አቀጣጥሏል።

ዓድዋ በትናንት መንፈሱ ይሄን ገልጿል፤ ለዛሬም አቅምና ኩራት ሆኗል ። ነገር ግን ዓድዋ በትናንት መንፈስ ተቃኝቶ ያጎናጸፈው ነጻነት እና ያቀጣጠለው የነጻነት ችቦ፤ ዛሬ ላይ በዛው መልክ ሊከወን አይችልም። ይልቁንም ከፍታው ተጠብቆ በዛሬ መንፈስ ሊቃኝ፤ በዘመኑ ፍላጎቶችና የትግል አውዶች ሊገለጥ ይገባል።

ምክንያቱም፣ የዛሬው ዓድዋ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ የቆየች ሀገርን አጽንቶ ማዝለቅ ነው፤ የዛሬው ዓድዋ የተሟላ ሰላም ያላት ሀገርን እውን ማድረግ ነው ። የዛሬው ዓድዋ እጁን ለልመና ሳይሆን ለሥራ የሚዘረጋ ትውልድን መፍጠር ነው ። የዛሬው ዓድዋ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር መተዋወቅና አብሮ መጓዝ፤ ከዚያም አለፍ ሲል የቴክኖሎጂ ተቀባይ ሳይሆን ፈጣሪ መሆን ነው። የዛሬው ዓድዋ የራስን ፍላጎት በሁሉም መልኩ በራስ አቅም አሟልቶ መገኘት ነው።

ይሄን ማድረግ ሲቻል የትናንቱ ዓድዋ ያጎናጸፈን ነጻነት ምሉዕ ይሆናል ። ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ ነጻነትን ማረጋገጥ ሳይቻል ነጻነት አይኖርም፤ እናም ኢኮኖሚያዊ ነጻነትን ማረጋገጥ የዓድዋን ታሪክ መድገም ነው ። የቴክኖሊጂ ጥገኛ ሆኖ ነጻ ነኝ ማለት አይቻልም፤ እናም የራስን ቴክኖሎጂ አበልጽጎ ጥቅም ላይ በማዋል ዓድዋን ከፍ ማድረግ ይቻላል ።

ከዚህ ባሻገር ዓድዋ የዲፕሎማሲ ከፍታን የፈጠረልን አውድ ነው ። ዲፕሎማሲያችን ደግሞ ለራስ ጥቅም ብቻ ታስቦ የሚከወን አይደለም ። ይልቁንም ለጋራ ተጠቃሚነት መርህ የተገዛ፤ በወንድማማችነት መንገድ ተራምዶ፣ በጎርብትና ልኬት ተቃኝቶ፣ የጋራ ሀብትን በጋራ አልምቶ የመጠቀም ግብን ያስቀመጠ እንጂ።

የዓድዋ መንፈስ ከራስ ባሻገር ለሌሎች መትረፍ ነው ። የዛሬው የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂና ሌሎችም ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ተግባራት ከራስ ያለፈ የወንድምና ጎረቤት ሕዝብና ሀገራትን ጥቅምና ብልጽግናን ማዕከል ያደረጉ ናቸው ። ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት መንገዱም ይሄው ነው። ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ፣ ከቀጣናው፣ ከአህጉሪቷ ብሎም ከሌላው ዓለም ጋር የሚኖራት ትብብርና ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነትና አብሮ በመልማት መርህ የተቃኘ ነው።

ይሄ ደግሞ የትናንቱ ዓድዋ የድል መንገድ ነው ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ነጻ ነኝ ብላ አልተቀመጠችም ። ለጎረቤቶቿ ነጻነት፣ ለአህጉሪቱ ነጻነት፣ ብሎም ለሌሎች ጭቁን ሕዝቦች ነጻነት ሠርታለች፤ አሁንም እየሠራች ትገኛለች። ዛሬም ኢትዮጵያ ለመበልጸግ የምታደርገው ጉዞ የቀደመውን ነጻነት ምሉዕ የማድረግ ሲሆን፤ ከድህነት ወጥቶ ሁለንተናዊ ብልጽግናን በማረጋገጥ ከኢኮኖሚም ሆነ ከቴክኖሎጂ ጥገኝነት ነጻ መሆን እንደሚቻል በማረጋገጥ፤ በዚህም ተምሳሌት መሆንም ነው!

አዲስ ዘመን  የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You