አዲስ አበባ፡– በዘንድሮው 1445ኛው የረመዳን ፆም 90 ሺህ ዜጎችን ለማስፈጠርና ማዕድ ለማጋራት መታቀዱ ተገለጸ።
በዘንድሮው 1445ኛው የረመዳን ፆም ወቅት “ኢትዮጵያ ታፍጥር” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ ታፍጥር ቲም፣ ኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያና ፍሎር ዲዛይን ትናንት የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ ስነጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልመሃዲ እንዳሉት፤ የኢፍጣር መርሀ ግብሩ ለሰላሳ ቀን የሚቆይ ሲሆን፤ አቅመ ደካማ የሆኑ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮችን የእለት የምግብ ፍጆታን የመቻል ሥራ ይከውናል ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በንግግራቸው፤ ይህን መርሀ ግብር ለየት የሚያደርገው በክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቁ ጾም የሆነው የአብይ ጾም የሚጀመርበት ወቅት መሆኑ ነው ብለዋል።
ድጋፉ በቀጥታ ስርጭትና ከለጋሽ ተቋማትና ግለሰቦች ከሚሰበሰብ ገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ በበጎ አድራጎት ተግባሩ ላይ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ታፍጥር ቲም የበላይ ጠባቂ ኡስታዝ ጀማል በሽር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ 90 ሺህ በላይ ዜጎችን ለማስፈጠርና ማዕድ ማጋራት ታቅዷል።
በመጪው 30 የረመዳን ቀናት በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በጎዳና ላይ የሚኖሩ ወገኖች እንዲሁም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ፣ በሕክምናና በማረሚያ ቤት ለሚገኙ፣ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ እና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኖች በመለየት ያለ ሃይማኖት ልዩነት ሃይማኖታቸው በሚፈቅደው ሥርዓት የማስፈጠር እና ማእድ ለማጋራት መርሀ ግብር እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ኢፍጣር መርሀ ግብሩ በሕክምና ማዕከላትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ የሚከወን መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአረጋውያን በየቤቶቻቸው የማስፈጠርና ማዕድ የማጋራት ሥራዎች እንደሚከወኑ ጠቁመዋል።
ለዚሁ ድጋፍ የሚውለው ገቢ ከለጋሽ ተቋማት እና ግለሰቦች ለማሰባሰብ የታቀደ ሲሆን፤ ከ72 ሚሊዮን በላይ ገቢ በማሰባሰብ ከ90 ሺህ ሕዝብ በላይ ተደራሽ እንደሚሆን ታውቋል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም