ሕጉ ለማን ለምን ?

መሽቶ በነጋ ቁጥር በመኪኖች አጀብ የሚጨናነቀው መንገድ ዛሬም እንደሌላው ቀን ብሶበታል። ግዜው እየመሸ ነው። በዚህ ሰዓት ከሥራ ወደ መኖሪያው የሚመለሰው ሰራተኛ ይበረክታል። ለጉዳይ ወጣ ያለውም ቢሆን ‹‹ዞሮ ከቤት›› እንዲሉ የመመለሻ ሰዓቱ ይህ ግዜ ነው።

በተወሰኑ ቦታዎች ለአውቶቡሶችና ለሰራተኞች ሰርቪስ ተብለው የተፈቀዱ መንገዶች በዚህ ሰዓት የተሻለ ጉዞ አላቸው። አብዛኛውን ግዜ የትራፊክ ፍሰቱ ለእነሱ መልካም ይሆናል። ብዙዎች የሚቸገሩበት የመጨናነቁ ጣጣ እምብዛም አያገኛቸውም። ይህ የአሰራር ልማድ በሁሉም የከተማው መንገዶች ባይሆንም በተመረጡ አካባቢዎች ተግባራዊ መሆን ከያዘ ቆይቷል።

እንዲህ መሆኑ ከፍ ከሚሉት መኪኖች ግርጌ የሚጓዙ አነስተኛ ተሽከርካርካሪዎች ለሕግ ተገዢ እንዲሆኑ አስችሏል። በዚህ ሰዓት መንገድ ለመሻማት ከመሀል አፈንግጠው ከዳርኛው መንገድ የሚገቡ ቢኖሩ መብት የተሰጣቸው ታላላቆቹ መኪኖች ‹‹በጄ›› አይሏቸውም። እነሱ እንኳን ቢያስገቧቸው ትራፊኮችና የመንገድ ትራንስፖርት ባለሙያዎች አይለቋቸውም። ከተያዙ ደግሞ ‹‹ሕግ ጥሰዋል›› በሚል ቅጣት ያገኛቸዋል ።

በጣም አስገራሚው ጉዳይ ግን በነዚህ መንገዶች ላይ የሚስተዋለው ሕግን የመጣስ እውነት ነው። ሕጉ የሚጣሰው ደግሞ በመንገዱ ላይ በሚዘዋወሩ መኪኖች እንዳይመስላችሁ። በነዚህ የተመረጡ መንገዶች ላይ ሕጋዊ ታርጋ ያልተለጠፈባቸው፣ ትራፊኮችም ሆኑ የመንገዱ ባለሟሎች ያላስተዋሏቸው ሕግን ተጋፊዎች አሉ።

ሕጉን ጥሰው መንገዱን ከሚጋፉት መሀል ዋንኞቹ ጋሪ ሙሉ ሙዝና ፓፓዬ ቆልለው ግዙን የሚሉ ነጋዴዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሁሌም ንግዳቸውን የሚያካሂዱት በእግረኛው መንገድ ላይ አይደለም። ከዋናው ጠርዝ አለፍ ብለው ወደ መኪናው መንገድ ገባ ብለው እንጂ። አስገራሚው ጉዳይ መንገዱን ተጋፍተው ለጉዞ አስጊ የሚሆኑትን ሕግ አልቦ ነጋዴዎች ልብ ብሎ ‹‹በሕግ አምላክ›› የሚላቸው አለመኖሩ ነው። እንደውም አብዛኞች ሾፌሮች ስራቸውን እንደ ግዴታ የቆጠሩት ይመስላል። መንገዱን እንዲለቁላቸው ከማስገደድ ይልቅ በጥንቃቄ እየተካኩ በጎናቸው ማለፍን ልምድ አድርገውታል።

በየቀኑ ደረሰኝ ይዘው የሚቀጣን ሾፌርና መኪናውን ለመያዝ የሚያንጋጥጡ ትራፊኮችና የመንገድ ባለሙያዎችም ስለ እነዚህ ወገኖች ግድ የሚላቸው አይመስልም። መሀል መንገድ ገብተው ከመኪኖች ሲጋፉ፣ የእጃቸውን ለመሸጥ ሲራወጡ እያዩ ዝምታን መርጠዋል።

በአጋጣሚ አደጋ ቢደርስ ሁሌም እንደሚሆነው ተጠያቂው አንድ ወገን ብቻ ይሆናል። እንዲህ ማድረጉ ደግሞ ለማንም ለምንም አይበጅም። እንደ እኔ ሀሳብ ሕግ የሚወጣው ለሁሉም በእኩል ሊሆን ይገባል። አንዱ ወገን ብቻውን በሚፈጥረው ችግር ብዙሀንን ለሚጎዳ አደጋ መጋለጡ አይቀሬ ነውና።

ዛሬ ከተማችን በለውጥ ጉዞ ላይ ነች። በየግዜው አዳዲስ ግንባታዎች ይከወኑባታል። ዘመኑን የዋጁ ድንቅ ሕንፃዎች ይገነቡባታል። እንዲህ መሆኑ ታላቅ ለውጥ ነው። አሮጌው በአዲስ ሲተካ ዘመናዊነት ጎልቶ ሲታይ እሰዬው ያሰኛል። አንዳንዴ ደግሞ ከግንባታዎች ተያይዞ የሚታዩ ችግሮች ጉዳታቸው ይስተዋላል። ካለመጠንቀቅ በሚከሰቱ አደጋዎች ጭምር በርካቶችን ሰለባ ይሆናሉ።

እርግጥ ነው ጥቂት የማይባሉ የሕንጻ አሰሪዎች ግንባታዎቻቸው ላይ ይጠነቀቃሉ። ለሌሎች ደህንነትም ያስባሉ። ይህ እውነታ በርካቶችን ይታደጋልና ምስጋናውን ሊወስዱ ይገባል። የበጎ አርአያነታቸው ጠቀሜታ ለብዙሀኑ ነውና።

አብዛኞቹ ግን ፎቆቻቻው ከፍ ባሉ ቁጥር ስጋታቸው በእኩል ይጨምራል። ብዙ ግዜ ለመንገደኞች፣ለአካባቢው ነዋሪዎችና በዙሪያቸው ላሉ ቤቶች ሲጨነቁ አይስተዋሉም። እንዲህ አይነቶቹ፣ አሰሪዎች በሕንፃዎቻቸው ላይ የደህንነት መጠበቂያ መጠቀምን አያውቁትም። በግልጽ እንደሚስተዋለው የግንባታ ግብአቶቻቸው ለበርካቶች ደህንነት ስጋት ናቸው።

ልብ ብላችሁ ከሆነ በርካቶቹ የከተማችን ሕንጻዎች ግንባታ ለደህንነት ስጋት የተጋለጠ ነው። በአጠገባቸው የሚያልፍ እግረኛ ለአሸዋ፣ ሲሚንቶው፣ ለእንጨትና ሚስማሩ እንደተጋለጠ ይውላል። ከፍተኛ ክብደት ያላቸው ብረቶች፣ ብሎኬቶችና የሴራሚክ ውጤቶች ከላይ ታች የሚመላለሱት በተለየ ጥንቃቄ ተሸፍነው አይደለም።

እንደውም አንዳንዴ በወጉ ያልተገጠሙና ንፋስ ያገኛቸው መስታወቶች ድንገት ወድቀው ይከሰከሳሉ። አወዳደቃቸው ደግሞ በራሳቸው ይዞታ ስር የማይሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ከእነሱ አልፎ በአካባቢው በሚገኙ ሰዎች ላይ የማረፍ ዕድሉ ሊሰፋ ይችላል።

የእነዚህ ሕንጻዎች ግንባታ በገፋ ቁጥር እነሱን የሚፈሩ፣ በሩቁ አይተው የሚሸሹ ይበዛሉ። ከአሁን አሁን ‹‹በላያችን አንዳች ነገር ወደቀብን›› የሚሉቱ እርምጃቸው ሁሉ በመሳቀቅ ይሆናል። ከመንገደኞች ባለፈ በአካባቢያቸው የሚቆሙ መኪኖችም ዋስትና የላቸውም።

አልፎ አልፎ እንደሚታየው በእንዲህ መሰል ስፍራዎች መኪኖች እንዳይቆሙ ማስጠንቀቂያና ቁጣ መሰል ጽሁፎች ይለጠፋሉ። ይህ ብቻውን ግን በቂ የሚባል አይደለም። ማሳሰቢያውን በወጉ እንየው ከተባለ የአንድ ወገንን መብት አክብሮ የሌላውን የሚጋፋ ይዘት ያለው ይመስላል።

በአጋጣሚ ጽሁፉን ሳያስተውል ቀርቶ ችግሩ የሚገጥመው ባለመኪና ቢኖር ስለምን ቆምክ ሊባል አይገባም። ማሳሰቢያው በሆነ አካል በቁራጭ ወረቀት ስለተለጠፈ ብቻ ሕጋዊ ነው ማለት አይደለም። አደጋ አድራሹንም ቢሆን ከተጠያቂነት አያስጥልም።

ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ መንገድን በሰፋፊ ድንኳኖች ዘግቶ ድግስና ጭፈራ ማዘጋጀት እየተለመደ ሄዷል። ይህ አይነቱ ጉዳይ በተለይ ለሆቴሎችና ለመጠጥ ግሮሰሪዎች ምርቃት በሚል ዓላማ የሚካሄድ ነው። ይህ ቆይታውን ከአንድ ቀን በላይ የሚያደርገው የጎዳና ላይ ግርዶሽ እግረኛውን ከመንገድ የሚያስወጣና የብዙሀንን መብት የሚጋፋ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህ ገጽ ላይ የተቀመጡትን ጥቂት ችግሮች ጨምሮ ሌሎችንም ፈታኝ ጉዳዮች መዘርዘርና ማንሳት ይቻላል። ለእንዲህ አይነቶቹ ያልተገቡ ተግባራት የተቀመጠ ደንብና መመሪያ ቢኖር ደግሞ ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል። ይህን እውነታ ለሚመለከታቸው አድርሶም የአደጋ ስጋትን ይቀንሳል።

የመንገድ ላይ የሙዝ ጋሪዎችን ጨምሮ ብዙ ግዜ ትናንሽ የሚመስሉን ጉዳዮች ጎልተው የሚታዩት ችግሩ በተከሰተ ግዜ ነው። ከአደጋዎች በኋላ ደምቀው የሚሰሙ ዘገባዎችም የአንድ ሰሞን ርዕስ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የላቸውም። እንዲህ አይነቶቹን ችግሮች ስናነሳ ሁሌም ለምንና እንዴት የሚል ጠያቂ ባለመኖሩ ችግሮች ሳይቀረፉ መቀጠላቸውን ልብ ልንል ይገባል።

ከዚሁ የግንባታ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚከሰት የመንገድ ላይ ችግርም ፈተናው ተመሳሳይ ነው። ለግንባታቸው ሲሉ መሀል ጎዳናውን ዘግተው እግረኛውን ከመንገዱ ስለሚያስወጡ አካላት አንዳች የሚባል የለም። በዚሁ ሰበብ ችግር ሲያጋጥም ግን እንደተለመደው ወሬው ተናፍሶ የሕጉ ጉዳይ ይዘነጋል።

እነዚህና ሌሎች ጥቃቅን መሰል ጉዳዮች ሁሌም የችግራቸው መዘዝ ከፍ ብሎ ይታያል። በየዕለቱ አብረውን ያሉ እንቅፋቶች ቢሆኑም ግን ልብ ብለን ትኩረት ስንሰጣቸው አይስተዋልም። ከጉዳዮቹ አሳሳቢነት አኳያ በሕጉ በኩል በመመሪያ የታሰረ አፈጻጸም ስለሌላቸውም እንደ ችግር ተይዘው መፍትሄ ሲበጅላቸው አይስተዋልም።

ለእይታና ለጉዳዩ ሚዛንነት ጥቂት የሚመስሉን፤ ችግር ሆነው ሲከሰቱ ግን ጉዳታቸው ጎልቶ የሚታይ እንከኖች ከቁጥር በላይ ናቸው። ጉዳዮቹን በሕግና መመሪያ አስሮ መፍትሄ መሻት ከተቻለ ግን ውጤቱን መልካም ማድረግ ይቻላል። ‹‹ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ›› እንዲሉ የችግር ትንሽ የለውም። በሕግና መመሪያ ማሰሩ ደግሞ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውምና ልብ ሊባል ይገባል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You