ሰላም የሁሉ ነገር ዋስትና ነው። ሰርቶ የመለወጥ፣ ወልዶ የማሳደግ፣ ወጥቶ የመግባት፣ ዘርቶ የማፍራት በአጠቃላይ በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋ አለው። ሰላም ከሌለ ነገ የለም። ስለ ነገ ማሰብም ማቀድም የሚቻለው በሰላም ውስጥ ነው። የሰላምን ምንነት ለመረዳት ሰላም የግጭትና ጦርነት አለመኖር፣ በሰዎች መካከል የመቀራረብ፣ የመግባባትና ግጭቶችን በንግግር የመፍታትና የመምራት ሁኔታን ይመለከታል።
ሰዎች ከራሳቸውና ከአካባቢያቸው ጋር ሰላም ኖሯቸው ለጋራ እድገትና አብሮ መኖር አስተዋጽኦ ካደረጉ ሰላም አለ ማለት ነው። በእያንዳንዱ ሕብረተሰብ ዘንድ ውስጣዊና ውጫዊ ስምምነት ካለ ሰላም አለ ለማለት ይቻላል። ስለዚህ ሰላም ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኑሮ ባሻገር ሰዎች ከሰዎች፣ ከተፈጥሮና ከአካባቢ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ስለሚመለከት ሰላም ሁሉን አቀፍ ይዘት አለው ማለት ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ግጭቶች ሌላ ግጭት እየወለዱ የግጭት አዙሪት ውስጥ ተነክረን ሰላም አልባ ዘመናትን አሳልፈናል። ለዘመናት ሲዘሩ የቆዩ የጥላቻና የመከፋፈል ዘሮች ፍሬ አፍርተው ሕብረተሰባችንን ያስተሳሰሩት ክሮች እየላሉና እየተበጣጠሱ የመጡበትና ግጭት የተንሰራፉበት ስለሆነ ከበድ ያሉ መንገራገጮች ላይ ደርሰናል። በርካታ መስዋዕትነቶችንም እንደሀገር እየከፈልን ነው። ይህም “ምክንያታዊ” ሆነን ሰላምንና የሰላምን መንገድ መውሰድ አማራጭ የሌለው መሆኑን ያሳየናል።
ይህ ሰላማችን በተለይም ባለፉት አባቶቻችን የአንድነትና የመደማመጥ አብሮ የመኖር፤ ጠላትን በጋራ ክንድ ድባቅ የመምታት አቅም ላይ ተመስርቶ ዛሬ ላይ ያጣነውን ሰላም አንመልስ ዘንድ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ምሁራንን የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎችንም በአንድ በማድረግ ” አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ” በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ የትላንቱን ዓድዋ ከዛሬ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናኘት ብዙ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል ። በተለይም ዓድዋ የአንድነታቸን ማሳያ ነው በሚል ዛሬ ላይ ያለንበት አስከፊ የመከፋፈል ሁኔታን የሚለውጡ ሃሳቦችም ተንጸባርቀዋል።
ዓድዋ ኢትዮጵያውያን በዘር በሀይማኖት ሳይከፋፈሉ የእድሜና የፆታ ልዩነት ሳያደርጉ ሆ ብለው በመነሳት እስከ አፍንጫው በዘመናዊ ጦር የታጠቀን የጠላት ሰራዊት ድል የመቱበት ነው። ይህንን የመሰለ ከእኛ አልፎ የዓለም ሕዝብ ያደነቀው ታሪክ ባለቤት ሆነን ሳለን ግን ዛሬ ላይ በመንደርና ጎጥ ተከፋፍለን እርስ በእርሳችን ችግር ውስጥ መግባታችንም ለቀጣዩ ትውልድ አሳፋሪ ገድልን እንደማቆየት ነው የሚሉ ሃሳቦች በስፋት ተንሸራሽረዋል።
እኛም ከውይይት መድረኩ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል በሰላም ሚኒስቴር የመንግስታት ግንኙነት ዴስክ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ግርማ ቸሩ ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ ዓድዋን እንዴትና በምን መልኩ ይገልጹታል
አቶ ግርማ ፦ ዓድዋ ለእኛ ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት ብዙ መድከም አያስፈልግም፤ ምክንያቱም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱ ስም ያህል የዓድዋን ምንነትና ማንነት ጠንቅቆ ያውቀዋልና። ይህ ሁኔታም ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ ታላቅ ድል ከመሆኑ ጋር በተገናኘ ከብዙ ጉዳዮች ጋር አገናኝተንም መመልከት እና መተንተን እንችላለን።
ዓድዋ የኢትዮጵያውያንን አገር ወዳድነት አጠናክሮ ያለፈ ትልቅ ድል ነው። ይህ ድል ደግሞ አሁን ላለው ትውልድ የሚያስተላልፈው ትልቅ መልዕክት አለ፤ በተለይም አባቶቻችን ዘመናዊ የጦር መሳሪያን እስከ አፍንጫው የታጠቀውንና በዘመናዊ ወታደራዊ ስልጠና የተዘጋጀውን ኃይል በነበራቸው ባሕላዊ መሳሪያ በእግራቸው ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተጉዘው በጋማ ከብቶቻቸው ድል የነሱበት ነው። እዚህ ላይ ግን ልብ ሊባል የሚገባው ነገር በወቅቱ ሕዝቡ በቂ ወታደራዊ ስልጠና እንዲሁም ዘመናዊ መሳሪያ አልፎ ተርፎም የሚያስፈልገውን ትጥቅና ስንቅ ማግኘት ባይችልም ቅሉ በነበረው ቆራጥነት እንዲሁም አንድነት ድሉ የኢትዮጵያውያን ሆኗል። ይህ ልዩነትን ወደጎን አድርጎ በአንድነት መትመምና መዝመት ለዛሬው ትውልድ የሚያስተላልፈው መልዕክት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ይህ ትውልድ ከድሉ ሊወስደው የሚገባው ትምህርት ቢኖር እንደ አገር በተለይም በአሁኑ ወቅት አንድ እንዳንሆን እያደረጉን ያለው ተግዳሮት ምንድን ናቸው? የሚለውን መመልከት ይመስለኛል። ለዚህ መልሱ ደግሞ ድህነታችን ነው። ድህነቱ የሚፈጥራቸው ነገሮች ደግሞ እዚህም እዚያም ሰዎች በፖለቲካ ወግነው በቡድን ተለያይተው እንዲጋጩ ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ያኔም የእርስ በእርስ ቅራኔዎች ሳይኖሩ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ አልነበረም ድሉ የመጣውና አሁንም ቅራኔዎቻችን ላይ ትኩረት በመስጠት ቁጭ ብለን ለመወያየት በመሞከርና በተረጋጋ መንፈስ አንድነታችንን ማጠናከር የጋራ የሆኑ ችግሮቻችንን በአንድነት መንፈስ መፍታት የዓድዋ ድል አንኳር መልዕክት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ መንፈስ በተጻራሪ በአንድነት መቆም ለምን ተሳነን?
አቶ ግርማ ፦ የሚገርመው ነገር ያን ጊዜ ለዓድዋ ጦርነት መነሻው የባዕድ ወረራ ነው። ነገር ግን ዛሬ በዚህ መልኩ እርስ በእርሳችን ችግር ውስጥ ለመግባታቸን የውጭ ኃይሎች እጅ የለበትም ለማለት እቸገራለሁ። ውስጣዊ ችግሮቻችን በርካታ መሆናቸው ይታወቃል። እነዛን ችግሮች የምንፈታበት መንገድ ደግሞ በውጪም በውስጥም ላሉ የተለያዩ አካላት መንገድ የሚከፍት በመሆኑ ለችግሩ አጋልጦናል ብዬ አስባለሁ።
በአገራችን ውስጥ የተለያየ የፖለቲካ እሳቤ፣ አመለካከት ያላቸው ብሔሮችና ብሔረሰቦችና የፖለቲካ ኃይሎች አሉ። በነገራችን ላይ እንደዚህ አይነት ሃሳቦችና ፖለቲካዊ አመለካከቶች ቀድሞም ቢሆን አልነበሩም ማለት አይቻልም። አባቶቻችን ብዙ ቅራኔዎች ነበሩባቸው፤ ነገር ግን ሁሉንም ልዩነታቸውን አስወግደው ወደአንድነት ነው የሄዱት። እንደዚሁ ሁሉ አሁንም ለውጭ ኃይሎች ተጋላጭ በሚያደርጉን የውስጥ ችግሮቻችን ላይ ቁጭ ብለን ተነጋግረን መፍታት ላይ ደካማ መሆናችን የፈጠረውን ችግር እንዲሁም ውጤቱንም እያየነው ነው።
በመሆኑም ትውልዱ ሊያደርገው ይገባል ብዬ የማስበው ልዩነቶች ተፈጥሯዊ መሆናቸውን በመገንዘብ ነገር እየመዘዙ ወደግጭት ከመሄድ ይልቅ በችግሮቹ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መወያየት ጥያቄ ያለው የትኛውም አካል ደግም በቀናነት ጥያቄውን የማቅረብ መልስ ሰጪው አካልም በተመሳሳይ ለጥያቄው ዋጋ ሰጥቶ በአግባቡ የመመለስ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ እነዚህ አማራጮች መልካም ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ እንግዲህ ችግሮቻችንን በውይይት ለመፍታት ያስችለናል በማለት እንደ አገር የምክክር ኮሚሽን አቋቁመናልና ይህ ምን ያህል ችግሮችን ለመፍታት አቅም ይኖረዋል ይላሉ?
አቶ ግርማ ፦ የምክክር ኮሚሽኑ መቋቋሙ እንደ አገር ጥሩ አካሄድ ይመስለኛል። በምክክር ኮሚሽኑ አማካይነትም ያሉንን ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች ሁሉ አውጥተን በደንብ ተነጋግረን ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ፈተን አንድነታችንን ለማጠናከር የሚኖረው ሚና በቀላሉ አይታይም።
ዛሬ ላይ እንደ ሀና ማህበራዊ ችግሮቹም ብዙ ናቸው፤ በመሆኑም ወጣቱ እንደ ወጣት ምሁራን የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገር ሽማግሌዎችና ሴቶች በያገባኛል መንፈስ በአንድነት ሆኖ በችግሮቹ ላይ መወያየት ፤ተወያይቶም መፍትሔ ላይ መድረስ ይገባል።
ችግሮቻችንን የዚያ የዚህ እያልን ባለቤት እየሰጠናቸው በሄድን ቁጥር እየሰፉና እየተጋነኑ ከመሄድ ውጪ የሚያመጡት ፋይዳ ስለማይኖር ሁሉም የድርሻውን እየተወጣ መንግስትም የመሪነቱን ሚና እየተጫወተ በአገር ጉዳይ በተለይም አሁን ባለንበት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ ለአብዛኛው ችግሮቻችን ምክንያቶቹ የተዛቡ የታሪክ አረዳዶች ናቸው የሚሉ ብዙዎች ናቸውና የሰላም ሚኒስቴር ያሉትን መዛነፎች ለማስተካከል ምን እየሰራ ነው
አቶ ግርማ ፦ አሁን ላይ እንደ አገር ከማያግባቡን ነገሮች መካከል ያለፈ ታሪክ ሳይሆን ትርክቶቹ ናቸው። ታሪክ ሊለወጥ የሚችል ነገር አይደለም። ማንም ያለፈን ታሪክ ወደኋላ ሄዶ መለወጥ አይችልም ፤ ነገር ግን እነዚያ ኩነቶች ሰዎች ጋር የሚደርሱበት ትርክት እየተዛባ እዚህ አድርሶናል። አሁን እንደ አገር የጀመርነው አገራዊ ምክክር መድረክ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ምክክር መድረኩ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ሁሉ እነዚህ ነገሮች ተነስተው ሕዝብ በሚገባ ተወያይቶባቸው መግባባት ላይ ደርሶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊዘጋ ይገባል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ጉዳዩን ቀደም ብሎም በማንሳት እንደ አገር የማያግባቡን ነገሮች ምንድን ናቸው? በማለት የታሪክ ምሁራንን ከታሪክ አንጻር ያለውን ልዩነት እንዲፈቱ አንድ ላይ የማቀራረብ ስራ ሰርቷል። በሌላ በኩል ደግሞ በፊት አንድ ላይ ተቃራኒ የሆኑና ያልነበሩ ተጻራሪ ሀሳቦችን በታሪክ ትርክት መልክ ሲጽፉ የነበሩ ምሁራንን ሁሉ በአንድ መድረክ በማምጣት በአገር አቀፍ ደረጃ “የታሪክ ምሁራን ማኅበር ” እንዲቋቋም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስራዎች ተሰርተዋል።
አሁን ላይ ማኅበሩ ወጥ የሆነ ታሪክና ትርክት ለመፍጠር ሙከራ እያደረገ ነው። በነገራችን ላይ ይህ ቀላል ነገር አይደለም፤ ተጠናክሮ በሄደ መጠንም ወደ መቀራረብ ወደ አንድነት አንድ ዓይነት ወደሆነ ታሪክ አረዳድ ያስገባናል ።
አዲስ ዘመን ፦ የታሪክ ምሁራን ተሰባስበው በሕዝቡ ውስጥ አንድ ዓይነት የታሪክ አረዳድ እንዲኖር ለማድረግ ጥረት መደረጉም ሆነ የምክክር መድረኩ ችግሮቻችንን በመፍታት በኩል ሊኖራቸው የሚችለው ሚና ምን ያህል ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ግርማ ፦ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ ተቀራራቢ ግንዛቤ እንዲኖረው ማስቻል በአዋጅ የተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ነው። ይህንን ኃላፊነታችንን ለመወጣትም ወጣቶችን ሴቶችን ምሁራንን እንዲሁም ሌሎች ይመለከታቸዋል ያልናቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ በማሳተፍ ስልጠናዎችና የፓናል ውይይቶች እናደርጋለን። ይህ እንግዲህ የምክክር ኮሚሽኑም ከመቋቋሙ በፊት ጀምሮ ሲሰራ የነበረ ስራ ነው። ኮሚሽኑም ከተቋቋመ በኋላ አስፈላጊውን መረጃ እየሰጠን የመነሻ ሃሳቦችን እያበረከትን እንገኛለን። እዚህ ላይ ግን ሊታወቅ የሚገባው ነገር ኮሚሽኑ ገለልተኛ የሆነና በራሱ የሚሄድ መሆኑም ነው።
እንደ አንድ አገራዊ መግባባት ላይ እንደሚሰራ ተቋም ግን በአገራችን ያሉ አለመግባባቶች ለመፍታት በተለይም ያለፈው ታሪካችን ወደፊት ከሚኖሩን የጋራ ሕልሞቻችን ጋር ምን ማለት ናቸው? ያለፉት ታሪኮቻችን ላይ ምን ጥሩ ነገር አለ ? እንዲሁም የትኛው ነው መጥፎ የሚለውን በመለየት ከመለየትም በኋላ ታሪክ ታሪክ ነውና የሚፋቅ የሚሰረዝ ነገር አይኖረውምና ባሉት ሁኔታ ለአገር ግንባታ መዋል በሚችሉበት ሁኔታ መጠቀም ይገባል።
በሌላ በኩልም እነዚህ መጥፎ ፤ ጥሩ እያልን የምንከፋፍላቸውን ታሪኮቻችንን ተምረንባቸው የምናርመውን እያረምን፤ የምናሻሽለውን እያሻሻልን ከጥንካሬው ተምረን ደግሞ ልናስቀጥለው የሚገባውን በዛው ልክ እያስቀጠልን የምንሄድበት አግባብ ሊኖር ይገባል። ’
ከዚህ አንጻር ሴክተራችን ታሪክን በማስተማር በማሳወቅ ብሎም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ፈጠራ ላይ ከፍ ያለ ስራን እየሰራ ነው። በዚህም ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ና ሌሎችም ለአገር ግንባታ የሚጠቅሙ እንደ ዓድዋ ያሉ ታሪኮችን በማንሳት ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዴት ነው ለአገር ግንባታ ብሎም አሁን ከፊታችን የተደቀኑ ችግሮችን ልናልፍ የምንችለው በሚለው ላይ ትኩረት አድርገን በመስራት ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፦ ታሪክን ሃብት አድርገን ችግሩን በትምህርትነት ጥሩ ጎኑን ደግሞ በመልካምነቱ ተቀብለን ለትውልዱ ለማቆየት ከማን ምን ይጠበቃል?
አቶ ግርማ ፦ ይህ እንግዲህ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። በተለይም የታሪክ ምሁራን ሰፊውን ድርሻ መውሰድ ቢገባቸውም እንደ አገርና ሕዝብ ግን ሁላችንም ታሪክ ሁነት በአንድ ወቅት የተከናወነ ነገር መሆኑ ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል።
ታሪክን በዚህ መልኩ ከተቀበልን የተዛቡ ትርክቶቹን ማስተካከል ላይ ብዙ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች ስላሉ እንደ አገር የተቋቋመው የምክክር መድረክ ላይ ሁሉም ሰው በያገባኛል መንፈስ በጠንካራ ሁኔታ ተሳትፎ ሀሳቡንም አቅርቦ በታሪኮቻችን ላይ ተቀራራቢ ትርክት እንዲኖረን ማድረግ ይገባል።
ይህንን በምሳሌ ባስረዳሽ መኪና ሲነዳ በግንባር አልያም በጎን መስታወት ወደኋላ የሚታየው ወደፊት ለመሄድ ነው፤ ሁልጊዜ ወደኋላ አይኬድበትም ። በመሆኑም በመስታወቱ ወደኋላ እያየን ወደፊት በሄድን ቁጥር ያለፍነው መንገድ ምን አይነት ነው? የሚከተለን መኪና ፍጥነቱ ምን ይመስላል? የሚለውንና ሌሎች ነገሮችን ለማየት ነው። ታሪክንም ወደኋላ የምናየው ድክመትና ጥንካሬውን እያስተዋልን ወደፊት ለመጓዝ ነው። እዚህ ላይ ግን ወደኋላ አይተን ችግር ያልነውን ነገር ብቻ እየመዘዝን ዛሬ ላይ የምናመጣው ከሆነ ወደፊት በትክክል ለመሄድ የማንችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሳችንም በላይ አደጋ ውስጥ የሚያስገባ ነው።
ምሁራን ደግሞ እዛም እዚህም ተዛብተው የሚነገሩ የታሪክ ትርክቶችን የማቃናት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ቀጥሎም የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቁን ኃላፊነት የሚወስዱ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ የሕዝቡ ጥያቄዎች ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች በእነሱ በኩል ተቀናብረው ስለሆነ የሚመጡት በተቻለ መጠን እነሱም ታሪክን እያወቁ እንዳላወቁ በመሆን ለራስ ፍላጎት ብቻ በሚመች መልኩ እየተረኩ ሕዝቡን ወዳልሆነ አቅጣጫ ከመምራት መቆጠብ ይገባቸዋል።
አንዳንድ ነገሮቻችን አይነኬ እየሆኑ ነው በተለይም አትንኩኝ ወይም የእኔ ብቻ ነው ትክክል የሚለው ሃሳባችን ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው። ለውጭ ጠላትም እያመቻቸን ነው። ይህንን በመገንዘብ አትንካኝ አልነካህም የሚለውን አስተሳሰብ ከውስጣችን ጠርገን አውጥተን የንግግር የውይይት ባሕል በልዩነቶቻችን ላይ የመነጋገር ሌላውን የመረዳት፤ የመገንዘብ ፤ በእሱ ቦታ ሆኖ የማየት፤ ወጣቶች ሴቶች ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። ከዚህ አንጻር ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን በተለያየ ጊዜ በማኅበረሰብ ደረጃ ሰፋፊ የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ ስራዎችን እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ እንደሚሰሩበትም ተቋም እንደ ግልዎም እንደ አገር የገባንባቸውን ችግሮች ፈትተን፤ ተደማምጠንና ተሳስበን አንድነታችንን አጠናክረን በሰላም እንኖር ዘንድ መልዕክት ቢያስተላልፉ?
አቶ ግርማ ፦ ከሰላም ሚኒስቴር አንጻር የምጠቅሰው አገራችን ላይ በርካታ ፖለቲካዊ፤ ማኅበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉብን። በሌላ በኩል ደግሞ በተዛቡ አረዳዶች ከተለያዩ መንግስታት ሲንከባለሉ ቆይተው ዛሬ ላይ እኛ የተቀበልናቸው የማያስማሙን ታሪኮች አሉን፤ በመሆኑም ትውልዱ አደጋዎቹን በሚገባ መረዳት አደጋዎቹንም ለመሻገር ምንድነው ከእኔ የሚጠበቀው የሚለውን አጽዕኖት ሰጥቶ ማሰብ ይገባዋል።
በሌላ በኩል እኛ ኢትዮጵያውያን እስከ ዛሬ የደረስነውም ፍጹም በሆነ መደማመጥ ፤መከባበር፤ መዋደድና መተሳሰብ በመሆኑ አሁን ላይም ልዩነቶች እንኳን ቢኖሩን የቀድሞ አንድነትና ሕብረታችንን ፍቅራችንን በማሰብ ችግሮችን የመፍቻ መንገዶችን ከማንም ሳንጠብቅ እርስ በእርሳችን ተነጋግረን መፍታት ይገባናል።
በሰላም ሚኒስቴር በኩል አንድነታችንን ለማምጣት ከተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶችን በበጎ ፈቃደኝነት በመመልመል ከአካባቢያቸው ውጪ ሄደው አገልግሎቶችን እንዲሰጡ የማድረግ ስራ አለ። ይህ ስራ ከምናገረው በላይ ውጤት ያመጣ ነው። በታሪክ ትርክት ላይ ያላቸው የተዛባ አስተሳሰብ ከትውልድ ቀያቸው ወጥተው ሌላ ቦታ ሲሄዱ ተቀይሯል። ስለዚህ ይህ ሁኔታ አንዳንድ ችግሮቻችንን እየፈታልን የእርስ በእርስ ግንኙነታችንንም እያጠናከረ ወጣቶቹም በሄዱበት አካባቢ ስራ እየሰሩ ትዳር እየያዙና ቤተሰብ እየመሰረቱ ወደ አንድነቱ እየመጡ በመሆኑ ስራው ውጤታማና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው። ይህ እንደ ሰላም ሚኒስቴር በጥቂቱ የሚሰራ ነው ነገር ግን ሌሎች ሴክተሮች፣ ክልሎች ፣ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሊሰሩበት የሚገባ ነው።
ትውልዱ በጥቃቅን ምክን ያቶች ለሚጠሉንና እድገታችንን ለማይፈልጉ ዱላ አቀባይ ከመሆን ይልቅ ተረጋግቶ አገሩን ማስቀደም ብሎም መሪውን ስለወደደ አልያም ስለጠላ ብቻ ሳይሆን አገሬ ምን ጊዜም የኔ ናት ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ
አቶ ግርማ ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም