የመምህራን እጥረትና የትምህርት መሰረተ ልማት ችግር

ልማት በየፈርጁ ነው። የሰው ኃይል ልማት፣ መሰረተ ልማት ወዘተ እያለ እንደሚሄደው ሁሉ የመምህራን ልማትም እንደ ሌሎቹ ሁሉ በጥብቅ ከተያዙትና የሚመለከታቸው አካላት የዕለት ተዕለት ክትትል ከሚያደርጉባቸው እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው።

የመምህራን ልማት በይዘቱም ሆነ አቀራረቡ ዓለም አቀፍ ገፅታ ያለው ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የትም አገር ያለና እየተተገበረ ያለ ነው። በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን ጉዳዩ ልዩ ትኩረትን ከማግኘቱም በላይ የተሻለ ትውልድን ከመፍጠርና ዘመኑን ያገናዘበ ትምህርትን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በቀላሉ ሊታለፍ የማይችል ሆኖ ተገኝቷል።

ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የትምህርት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው አንድ ቦታ ብቻ አይደለም፤ ወይም በሰሜን እና በደቡብ ብቻ አይደለም ችግሩ ያለው። በምስራቅና ምዕራብም የተወሰነ አይደለም። ከማዕከላዊው የዓለማችን ክፍል ጀምሮ በአራቱም ማዕዘን ትምህርትና ጥራቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ የዓለምንም የጋራ ጥረት እየጠየቀ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የመምህራንን ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ሲመጣ አይታይም። ለዚህ ማሳያው ደግሞ እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ 50 በመቶ በመጨመር ከ62 ሚሊዮን በመስፈንጠር 94 ሚሊዮን (11.6 ሚሊየን በቅድመ አንደኛ ደረጃ፤ 32.6 ሚሊየን በአንደኛ ደረጃ፤ 20.7 በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ፤ 15.7 ሚሊየን በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ፤ እና 13.1 ሚሊየን በሶስተኛ ደረጃ) ላይ ደርሷል።

ምርጥ ስርአተ ትምህርት አላት የምትባለውንና በመምህራን ልማት የማትታማውን አሜሪካ ስንመለከት አጠቃላይ የመምህራኖቿ ቁጥር 4 ሚሊዮን 007 ሺህ 908 ሲሆን፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ተመዝግበዋል።

በዚያው ልክ ደግሞ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ 81 ከመቶ የአንደኛ ደረጃ፤ 78 ከመቶ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ሙያው ከሚፈልገው ዝቅተኛውን ደረጃ የያዙ ናቸው። ከሰሀራ በታች ያለውን ሲታይ ደግሞ 65 ከመቶ የመጀመሪያ፤ 51 ከመቶ ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ዝቅተኛውን መስፈርት ይዘው ይገኛሉ።

በዚሁ በጥር ወር ይፋ በሆነው የዩኔስኮ ጥናት ላይ እንደተመላከተው፣ ጥናቱ ከተካሄደባቸው አገራት አንዷ በሆነችው አሜሪካ 163,650 (5 በመቶ) አካባቢ የሚሆኑ መምህራን ከሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ውጪ በማስተማር ላይ ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ መምህራን ያለ ሙያቸው ማስተማራቸው ብቻ ሳይሆን አጫጭር ስልጠና እንኳን ያልወሰዱና ሰርተፊኬት ሳይቀር የሌላቸው መሆናቸው ነው።

መረጃው እንደሚለው እ.ኤ.አ በ2030 በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት 69 ሚሊዮን አዳዲስ መምህራን ያስፈልጋሉ። የሴት መምህራን ቁጥር ዝቅተኛ በሆነባቸው፣ ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት በዚሁ ዓመተ-ምህረት የተያዘውን ግብ ለማሳካት 15 ሚሊዮን መምህራንን መቅጠር ግዴታቸው ነው። ከእነዚህ አሃዞች ውስጥ ኢትዮጵያ የድርሻዋን መውሰዷ የግድ ነውና ጉዳዩን አርቆ ማየት አያስፈልግም።

አንድ UIS (2016)ን ጠቅሶ ለንባብ የበቃ ሰነድ እንደሚያመለክተው ዓለማችን ከፍተኛ የሆነ የመምህራን እጥረት ያለባት ሲሆን፣ በተለይ ከሰሀራ በታች ያሉት አገራት ከልክ በላይ ለችግሩ ተጋልጠው ይገኛሉ። እንደዚሁ ጥናት ግኝት ከሆነ በቀጠናው በሚገኙት አገራት ያሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 70 ከመቶ የሚሆኑት በከፍተኛ የመምህራን እጥረት የተጎዱ ሲሆኑ፤ በእነዚሁ አገራት የሚገኙ 90 ከመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለከፍተኛ የመምህራን እጥረት ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ። ይህ ማለት አሁን ካሉት በተጨማሪ የሰለጠኑና ብቃት ያላቸው መምህራን እንደሚያስፈልጉ ነው።

በአፍሪካ ያለው ሁኔታ ደግሞ ከዚህም በላይ ያስደነግጣል። በአሁኑ ሰዓት አንድ አራተኛ የመጀመሪያ ደረጃ፤ ከሁለተኛ ደረጃ ደግሞ 50 በመቶ የሆኑት ብቻ በመምህርነት ሙያ ሰልጥነው በማስተማር ተግባር ላይ ያሉ ናቸው። ይህም “አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግዴታ የሆነውን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን እ.ኤ.አ በ2030 እውን ማድረግ ካለባት አህጉሪቱ በሙያው የሠለጠኑ 17 ሚሊዮን መምህራን የምታስፈልጓት መሆኑ፤ እነዚህ መምህራንም ብቃትና ጥራት ብቻ ሳይሆን፣ ብቃትና ጥራታቸውን ተከትሎ ጥሩ ደመወዝና ምቹ የሥራ አካባቢዎች የሚያስፈልጓቸው መሆኑ ነው።

የ26 ስቴቶች አቃፊ፣ ከዓለም ሰባተኛና 214 ነጥብ 3 ሚሊዮን (እ.ኤ.አ በ2021 ጥናት) ሕዝብ ቁጥር ወዳላትና ደቡብ አሜሪካዊት ወደ ሆነችው፤ እንዲሁም፣ ዓለም በጥቅጥቅ ደን ባለቤትነቷ ወደሚያውቃት ብራዚል ስንሄድም የመምህራን በተለይም የእንግሊዝኛ መምህራን እጥረት በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ሲሆን፤ ምክንያቶቹ የንግድ መስፋፋት፣ የቱሪዝም ሴክተሩ መበልፀግና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ የእነዚህና ሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል መፈለግ ትምህርትን እጅጉን አስፈላጊ አድርጎታል። በመሆኑም፣ የመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤ ዲግሪ) ያለው ሲበዛ ተፈላጊና ዘና ብሎ በሚኖርባት ብራዚል ከፍተኛ የመምህራን እጥረት፤ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የመምህራን ልማት አስፈላጊነት ይስተዋላል።

በቂ መረጃ በሚገኝባቸው አገራት፣ የመምህራንን አጠቃላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሙያዊ ደረጃን በተመለከተ አገራት የተዘረዘሩ ሲሆን፣ በቻይና፣ ግሪክ፣ ቱርክ እና ደቡብ ኮሪያ መምህራን ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ላይ ሲገኙ፤ በጣሊያን፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ብራዚል እና እስራኤል ደግሞ በተቃራኒው ደረጃ ላይ ናቸው።

አውሮፓዊቷ ሉክሰምበርግ ለመምህራን የተሻለ ደሞዝ (አንድ የባችለር ዲግሪ ባለቤት ገና ሲቀጠር በዓመት €67,000 (US $70,323.20) ይከፈለዋል) በመክፈል ከዓለም የመጀመሪያዋና ፊት መሪ ስትሆን፤ ከአፍሪካ “ጥሩ ከፋይ″ (በዓመት ከ$22,000 እስከ $46,000) በሚል የተመደበችው ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ነች። ሉክሰምበርግ አንድ መምህር 30 ዓመት ካገለገለ ደሞዙ €119,000 (US $124,902.40) ሊደርስ የሚችልባት አገርም በመሆኗ እስካሁን አቻ አልተገኘላትም።

“ታላቁ መምህር” የሚል ማኅበራዊ ማዕረግን ካገኘው ሶቅራጥስ ጀምሮ ከበሬታን በተመለከተም እንደዚሁ የተደረጉ ጥናቶች ያሉ ሲሆን፤ በጥናቶቹ ላይ ሰፍሮ እንደሚነበበው ከሆነ ቻይና መምህራን በከፍተኛ ደረጃ (መቶ ከመቶ) የሚከበሩባት አገር ስትሆን፣ ማሌዥያም 93 ከመቶ መምህራን የሚከበሩባት አገር በመሆን በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ይህንን እዚህ ማቅረባችን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የመስሪያ ቤታቸውን የ6 ወራት የስራ አፈፃፀም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀሙስ የካቲት 7/2016 ዓ∙ም ባቀረቡበት ወቅት “የመምህርነት ሙያን የሚቀላቀለው ሰው በእጅጉ እየቀነሰ ነው፤ የመምህራን ጉዳይ የጥራት ብቻ ሳይሆን አሁን በቅርብ ባደረግነው ጥናት ያየነው በቅርብ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የመምህራን እጥረት ይገጥመናል፤ ለዚህ እንደ ምክንያት የተነሳው የደመወዝ ክፍያው ከሙያው ጋር የሚመጥን ባለመሆኑ ነው” ማለታቸውን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው።

የካቲት 1 ቀን፣ 2016 ዓ∙ም በዋና መስሪያ ቤቱ ስብሰባ አዳራሽ፣ መምህራንን እና የትምህርት ቤት አመራሮችን በተመለከተ ስላዘጋጃቸው መመሪያዎች ማስተዋወቅን አስመልክቶ በተደረገ ውይይት ላይ በመጪው ክረምት ባሉበት የትምህርት ደረጃና በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት ስነ ዘዴ ላይ የተመሰረተ፤ “ልዩ የአቅም ማጎልበቻ” ስልጠና በስራ ላይ ላሉ መምህራን ሊሰጥ መሆኑን፤ መመሪያዎቹ የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን የደረጃ እድገት አፈጻጸም፣ የትምህርት ቤት አመራሮች ምልመላ እና ምደባ እንዲሁም የእጩ መምህራን ምልመላ እና መረጣን የሚመለከቱ መሆናቸው በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን እና የትምህርት ልማት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ አሰግድ ምሬሳ ተነግረዋል።

ከዚህ ቀደም “በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ መምህራን ለሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት ብቁ ሆነው እንዲገኙ የሚያስችል የሥራ ላይ ስልጠና በመስጠት የብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ ይደረጋል”።

የመምህራንና ትምህርት አመራሮች ልማት ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደ ተናገሩት ማለቱ የሚታወስለት ትምህርት ሚኒስቴር መመሪያዎችን ከማሻሻል በተጨማሪ የመምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮችን አቅም ለማሳደግ ከላይ በተጠቀሰው መርሀ-ግብር ከ15 እስከ 20 ለሚሆኑ ቀናት “በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች” እንደሚሰጥ የሚጠበቀው ይህ ስልጠና፤ ይበልጡን ትኩረት የሚያደርገው “የሁለተኛ ደረጃ የሳይንስ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርቶች ላይ” መሆኑም ተገልጿል። በሂደት ሁሉንም፣ በየደረጃው ያሉትን መምህራን ሁሉ እንደሚያካትትም እንደዛው ተነግሯል።

700 ሺህ የሚደርሱ መምህራን እንዳሉ በሚነገርባት ኢትዮጵያ መምህራኑ ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ ሰርተፊኬት የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ብሔራዊ ፈተና በማዘጋጀት የመምህራንን አቅም ለመፈተሽ እየተሠራ እንደ ሆነም ከላይ በጠቀስናቸው የስራ ኃላፊ ተገልጿል። ተግባሩ “ኢዱኬሽን ዴቨሎፕመንት ትረስት” እና ከመሳሰሉት ጋር በመተባበር፣ ከ2013 ዓ∙ም አንስቶ እየተከናወነ መሆኑ፤ በ2015 በጀት ዓመት 728 የሚሆኑ ሴት መምህራኖችን ወደ አመራርነት ለማምጣት የሚያስችል ስልጠና መሰጠቱም ተመላክቷል።

እንደ ዶ/ር ሙሉቀን ማብራሪያ ከዚህ በፊት በተሰጡ የሥራ ላይ ስልጠናዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ አምስት ሺህ የትምህርት አመራሮች ስልጠናቸውን አጠናቀው ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ እንደሚለው ባለፉት 30 ዓመታት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ጥራት ወርዷል። ትምህርት የአገር የሉዓላዊነት እሴት መለኪያ መሆኑ እየታወቀ በዚህ ጉዳይ ለዓመታት ተቀልዷል። እርስ በርስ መነጋገር ሁሉ የማይቻልበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል። በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፉ ከ10 ዓመታት በኋላ ትምህርት ቤቶች እንደ አሁኑ የፀብ (የረብሻ) መፍለቂያ ሳይሆኑ የመወዳደሪያና የብቃት ማጎልበቻ ይሆናሉ።

ከዚህ በኋላ እንደ ከዚህ ቀደሙ ዲግሪ እንደ ከረሜላ የሚታደልበትን አሠራር አስቀርቶ፣ በብቃት እና በችሎታ ብቻ ዜጎች ማዕረግ የሚያገኙበት ሥርዓት በዘላቂነት ይዘረጋል። ይህ ለመሆኑ አንዱ ምክንያት ምናልባትም ዋናው የመምህራን ልማትን የተመለከተ ይሆናል በሚል ይመስላል፤ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስርነቀል እርምጃዎችን እየተወሰደ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ቀደም ሲል፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው 124 የትምህርት ክፍሎች ተጨፍልቀው ወደ 56 ዝቅ እንዲሉ የተደረገው ውሳኔ ይጠቀሳል። ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 30ኛውን ዓለም አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ባካሄደበት ወቅት “የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ከአሁን በኋላ በካድሬነት ሳይሆን በብቃታቸው ብቻ የሚመረጡ መሆኑን” አስታውቋል።

በዚህ መሠረት ትምህርት ሚነስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ በብቃታቸውና በችሎታቸው የተመዘኑ 1ሺህ 600 የትምህርት አስተዳዳሪዎች ሥልጠና የተሰጣቸው መሆኑን ተናግሯል። ትምህርት ቤቶችን በግብዓትና በጥራት ከማሻሻል ባሻገር ክህሎት፣ ብቃትና ችሎታ ባላቸው ርዕሳነ መምህራን እንዲተዳደሩ ማድረግ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጿል። የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል በተጨማሪ ተማሪዎቻቸውን በዕውቀት ተወዳዳሪ ማድረግ የሚችሉ መምህራንን ማብቃት ከተያዙ ግቦች መካከል አንዱ መሆኑን አስታውቋል።

በመምህራን ልማት ያለው ችግር እንዳለ ሆኖ በትምህርት ተቋማት መሰረተ ልማት ላይም ተመሳሳይ ችግር ይታያል። የጉዳዩ ባለቤት የሆነውና ባለፉት 30 ዓመታት የትምህርት ጥራት ወድቋል የሚለው ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ እንደተናገረው በኢትዮጵያ ካሉ 50 ሺህ ትምህርት ቤቶች ከፊሉ፣ በጥራታቸው ከደረጃ በታች ሲሆኑ፤ ትምህርት ቤቶቹ፣ አስፈላጊው መሠረተ ልማት የሌላቸው፤ ለመማር ማስተማር ምቹ ያልሆኑ ናቸው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ “በኢትዮጵያ ካሉት 50 ሺ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ71 በመቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ከ86 ከመቶ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ለመማር ማስተማር ሂደት የማይበጅ ከባቢ ያላቸው፣ በጥራታቸውም ከደረጃ በታች ናቸው” የሚለው ተቋሙ፣ በትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አማካኝነት፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ የእነዚህን ትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሳደግ እንደሚያስፈልግና ይህንንም ለማከናወን፣ ሀገራዊ የሕዝብ ንቅናቄ እንደሚጀመር፤ በኅብረተሰብ ተሳትፎ የትምህርት መሠረተ ልማትን ለማሻሻል በሚደረገው ሀገራዊ ንቅናቄ፣ በአምስት ዓመት፣ የሁሉንም ትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል እንደታቀደም አመልክቷል።

ይህ ጽሑፍ፣ እኛም የዓለም አካል ነንና፣ ባለፈው ዓመት ዩኔስኮ፣ ዩኒሴፍ፣ ዓለም አቀፍ ትምህርት (EI)፣ እና ዓለም አቀፍ የስራ ድርጅት (ILO) በጋራ ያዘጋጁት “ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን”ን አስመልክቶ የተቀመረውን መሪ ሃሳብ (“The teachers we need for the education we want: The global imper­ative to reverse the teacher shortage”) መሰረት አድርገን ስንመለከተው ይዞት የተነሳው ሀሳብ ቀላል አለመሆኑን መገንዘብ አይከብድም። በተለይም እጥረት (shortage) በቁጥር ብቻ ሳይሆን በጥራትና አቅምም መሆኑን፤ እሱም መቀልበስ ያለበት መሰረታዊ ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑን ልብ ስንል የጽሑፉ ወቅታዊነትና ተከታታይ ሆኖ የመቆየቱን አስፈላጊነት እንረዳለንና ጉዳዩን አጀንዳ ለማድረግ መጣራችን ተገቢ ነው።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You