ከዓድዋ ድል ምን እንማራለን?

ሠላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ትምህርታችሁ ላይ እየበረታችሁ ነው አይደል? በጣም ጎበዞች፡፡ መቼም ቅዳሜ እና እሁድ ለእናንተ የተወሰነ እረፍት የምታገኙበት ቀናት ናቸው፡፡ ታዲያ በነዚህ ቀናት እያጠናችሁ፣ ጋዜጣ፣ መጻሕፍትን እያነበባችሁ እንዲሁም በጥቂቱም ቢሆን እየተጫወታችሁ እንደምታሳልፉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ልጆችዬ ለዛሬ ወደ ምናቀርብላችሁ ርዕሰ ጉዳይ ከመግባታችን በፊት እስቲ እንኳን አደረሳችሁ? እንባባል፡፡ መቼም ‹‹ለምኑ?›› እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ትናንት የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም 128ኛው የዓድዋ ድል በድምቀት እንደተከበረ ታውቃላችሁ፡፡ ለዛ ነው እንኳን አደረሳችሁ ያልናችሁ፡፡ ይህ ቀን ለሁሉም ኢትዮጵያውን የተለየ ነው አይደል? ‹‹በሚገባ!›› ምክንያቱም አብዛኛው የአውሮፓ ሀገራት (ነጮች) አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት የከሸፈበት ስለነበር፡፡ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በቁጥጥሩ ሥር አውሎ በቅኝ ለመገግዛት ያደረገው ጥረት የከሸፈበት ቀን በመሆኑ የተለየ ነው፡፡

ልጆችዬ በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በዓድዋ ተራራማ አካባቢዎች በኢትዮጵያ እና በጣሊያን ቅኝ ገዥ ጦር መካከል ጦርነት መካሄዱ ይታወቃል፡፡ አንድ ቀን በፈጀው ጦርነት የጣሊያን ጦር በኢትዮጵያ ተሸንፏል። ይህንን የድል በዓል በማሰብ በተለያዩ መንገዶች ሲከበር እንደተመለከታችሁ ጥርጥር የለኝም፡፡

በዓድዋ ድል ሁሉም ሰው እኩል እንደሆነ ማሳየት ተችሏል፡፡ በቅኝ አገዛዝ ለነበሩት የአፍሪካ ሀገራትም ኢትዮጵያ ምሳሌ ሆና ብዙዎች ከቅኝ አገዛዝ እንዲወጡ መነሳሳትን ፈጥራለች፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩት ዳግማዊ አጼ ምንሊክ እና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ጦርነቱን በመምራት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በተጨማሪም ከአራቱም አቅጣጫ ከደቡብ፣ ከምስራቅ፣ ከሰሜን እና ከደቡቡ የሀገራችን ክፍል የተውጣጡ ጀግኖች ሀገራችን በነፃነቷ እንድትቀጥል እስከሞት ድረስ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡

ልጆችዬ ጣሊያንን ለማሸነፍ ብዙ ዋጋ እንደተከፈለ ተረዳችሁ አይደል ? ስለዚህም ወራሪ የነበረው የጣሊያን ጦር ከሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በተውጣጡ ጀግኖች ለማሸነፍ ተችሏል፡፡ በወቅቱ ጣሊያን ከኢትዮጵያ የምትበልጥ ሀገር ብትሆንም እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በአንድነት እና በሕብረት ሆነን የማይቻል የሚመስል ነገር አድርገናል፡፡ ልጆችዬ ከዚህም መረዳት እንደሚቻለው ማንንም መናቅ እንደማይገባ ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ይህን ያደረገ ሀገር እንደሌለስ ታውቃላችሁ? መልሳችሁ ‹‹አዎ በሚገባ ከአፍሪካ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት!›› እንደምትሉ እተማመናለሁ፡፡

ልጆችዬ ሀገራችን ኢትዮጵያ በነፃነቷ ድርድር የማታውቅ ሀገር እንደሆነች ተገንዝባችኋል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ። በተጨማሪም የአኩሪ ድል ባለቤት ሀገር እንደሆነችም ታውቃላችሁ፡፡ ለዚህ እኮ ነው ልጆችዬ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ታሪክ፣ ባህል፣ እሴት እና የደማቅ ድል ባለቤት እንደሆነች በኩራት የምንነግራችሁ፡፡

ዛሬ እናተን እና እኛ ያለምንም የውጭ ሀገር ተጽዕኖ በነጻነት እንድንኖር የቀደሙት ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ ልጆችዬ ሁሉም የሰው ልጆች እኩል እንደሆኑ ታወቃላችሁ አይደል? ነጭ፣ ጥቁር፣ ደሃ፣ ሀብታም እና የመሳሰሉት ስያሜዎች በመስጠት ይኑሩ እንጂ ሁሉም የሰው ልጅ እኩል ነው፡፡ ታዲያ በዛ ዘመን የነበሩ የአውሮፓ ሀገራት ራሳቸውን የበላይ አድርገው ነበር የሚቆጥሩት፡፡ እኛን ጥቁር አፍሪካውያንን ደግሞ የበታች አድርገው ነበር የሚመለከቱን፡፡ እኛ አፍሪካውያንን ባሪያ እና ተገዢ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም ግን በዓድዋ ምክንያት አልተሳካላቸውም፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ዓድዋ የሁሉም ጥቁር ሕዝብ ድል እና ኩራት ነው፡፡›› የሚባለው፡፡

ልጆችዬ እናንተም ስለ ዓድዋም ይሁን ስለአገራችሁ ታሪክ ለማወቅ ወላጆቻችሁ፣ መምህራን እና ታላላቆቻችሁን ብትጠይቁ እንደሚነግሯችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እናነተም ከወላጆቻችሁ እና ከመምህራን ያወቃችሁትን አኩሪ ታሪክ ላላወቁት በመንገር ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ማስተማር ይገባችኋል፡፡

እናም ልጆችዬ ከዓድዋ ድል ብዙ ነገሮች እንደተማራችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ‹‹ምን ተማራችሁ?›› ተብላችሁ ብትጠየቁ እንኳን መተባበርን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን ለመጥፎ ነገር አለመተባበር፣ ጀግንነት፣ አሸናፊነትም እና ሌሎችን ተምረንበታል ብላችሁ ምላሽ እንደምትሰጡን አልጠራጠርም፡፡ ሌላው ደግሞ ማንም የራሱ ያልሆነውን ነገር መፈለግ እና መሻት እንደሌለበት በሚገባ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ልጆችዬ ዛሬ ታላቁን የዓድዋ የድል በዓል ምክንያት በማድረግ ስለ ድሉ በጥቂቱም ቢሆን አቀረብንላችሁ፡፡ ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ በማድረግ ለዛሬው በዚሁ እንስነባበታለን፡፡ ሳምንት በቸር ያገናኘን፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You