ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሀሳብና ዓላማ ሲሰባሰቡ ጠንካራ የማስተባበር፤ የመምራት፤ የመደማመጥና ፈተናዎችን በአብሮነት የመሻገር ችሎታ እንዳላቸው ያስመስከሩበት ታላቅ የድል ታሪክ ነው። ለኢትዮጵያውያን የአርበኝነት ዓምድ፤ በእሳት ተፈትኖ የነጠረ፣ በወጀብ የማይናወጥ፣ ኅብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የተገለጠበት እና የታነፀበት የብሔራዊ አርበኝነት ምሰሶ ነው ።
የኢትዮጵያውያን አይበገሬነት፤ ጀግንነት፣ ኅብረትና አንድነት በተግባር የተመሰከረበት፤ የብሔራዊነት ምልክት፣ የወል ታሪካችን ዓርማ ነው። ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በወል ተምመው ያስመዘገቡት፤ የጋራ ትናንትን ከነገ ጋር ማስተሳሰሪያ ገመዳቸው ነው። ዛሬን ቀና ብለው መሄድ ያስቻላቸው የአባቶቻቸው የአርበኝነት የተጋድሎ የድል ታሪክ ነው።
ዓድዋ ብዝኃነትን ያከበረ፣ አብሮነት ለሁለንተናዊ ድል ወሳኝ መሆኑን የሚያሳይ ለኢትዮጵያ ክብርና የግዛት አንድነት በተከፈለ የጋራ መስዋዕትነት የተገኘ የኢትዮጵያውያን የወል ድል ነው። ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ በተሰናሰነ የብሔር- ብሔረሰቦች ላብ እና ደም ድምር ውጤት የተገነባችና በወል ጥረቶቻቸው የምትበለጽግ ሀገር መሆኗን ከዚህ የበለጠ ማሳያ የለም።
ኢትዮጵያውያን ከወል ትርክት ይልቅ የተናጠል ትርክቶችን በማጉላታችን አንዳችን ከአንዳችን አላስፈላጊ ግጭቶችንና ጦርነቶችን በማድረግ ተገቢ ያልሆነ መስዋዕትነት መክፈላችን እና አገራችንን ከሥልጣኔ ማማ አውርደን የድህነት ማጣቀሻ ማድረጋችን የማይታበል ሐቅ ነው።
ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ማበብና አጠቃላይ ሀገራዊ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት ይመጣ ዘንድ ከተቃርኖ ትርክት በመላቀቅ ገዥ ብሔራዊ ትርክትን በማጽናት ሀገራዊ መግባባትን ለማዳበር ፀንተን በጋራ መቆም አለብን። በሀገራችን የቂምና የጥላቻ ታሪክ ምዕራፍ እንዲዘጋና በብሔራዊ አርበኝነት የተገነባ ብዝኃነትን ያማከለ አካታች የፖለቲካ ሥርዓት ይኖር ዘንድ ትውል ዱን ከዓድዋ የተሻለ ሊያስ ተምረው የሚችል ነገር የለ ም።
እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ ለመውሰድና ታሪኳንና ክብሯን የሚመጥን ሁለንተናዊ ከፍታ ለማብሰር የሁሉንም ኢትዮጵያውያን የጋራ አስተዋፅዖ ይጠይቃል፡፡ እናም ዘመን ተሻጋሪና አካታች የሆነ ብሔራዊ ገዥ ትርክት በመገንባት ለትውልድ ማውረስ ይገባናል።
የዓድዋ ድል ስኬታማ የሆነው በመላው ኢትዮጵያውያን የተደመረ የአንድነት መንፈስ በመሆኑ አሁንም ሆነ ወደፊት የሀገራችንን እድገትና ብልጽግና የምናረጋግጠው አሰባሳቢ በሆነ ብሔራዊ ገዥ ትርክት የወል እውነቶቻችንን እያፀናን በአብሮነታችን መፅናት ስንችል ነው። ለዚህም የዓድዋ ድል ውጤት መነሻ የዘመቻው መሪዎች፣ ዘማቾችና ሕዝብ ተስማምተው፣ ተቀናጅተውና ተናብበው ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ በጋራ መቆም በመቻላቸው የመሆኑን እውነት በልኩ ልንገነዘበው ይገባል፡፡
ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በሙሉ ወደጎን በመተው ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም የግል ፍላጎቶችን ከሀገር ክብር በታች በማድረግ ወደ አንድ የድል ግንባር ተምመው ለዛሬው ትውልድ ነፃ ሀገር ጥለው አልፈዋል። ጀግኖች አባቶች ይህን ሕያው ታሪክ ለማኖር ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አልነበረም። ይልቁንም በወቅቱ በርካታ ፈተናዎች ነበሩ። ከተፈጥሮ በሽታና ድርድር፣ ከሰው ሠራሽም የውስጥ ባንዳዎች ተግዳሮት ሆነውባቸው ነበር። ሆኖም ለዓላማቸው በመጽናት ፈተናዎችን ተቋቁመው ዛሬ የሚዘከር ለትውልዱም ስንቅ የሚሆን የሚመነዘር ታሪክን ጻፉልን።
እናም ዋናው ቁም ነገር ከዓድዋ ድል አዲሱ ትውልድ ምን ይውሰድ ነው። የነበሩ ድሎችን በመዘከር ብቻ ሳይሆን አሁን ወቅቱ የሚጠይቀውን የአርበኝነት መንፈስ ተላብሶ በአባቶቻችን ደም የከበረችዋን ሀገር በላባችን ማጽናት ያስፈልጋል። በጊዜው የነበሩት ፈተናዎች አይነታቸውን ቢቀይሩም ዛሬም ፈታኞች እና ፈተናዎች አሉ፤ ይኖራሉም።
የዚህ ትውልድ መለኪያ ግን ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር መሰናክሎችን በጽናት በመሻገር ለነገው ስኬት መትጋት ነው። ከጀግኖች አያት ቅድመ አያቶቻችን በወረስነው የብሔራዊ አርበኝነት መንፈስ ፀንተን በኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ከትናንት ይልቅ ነገ ላይ አተኩረን ልንሠራ ይገባል።
በተከፈለልን ዋጋ መኖር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ድሎችን እያስመዘገብን አይቀሬ የሆነውን ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ በመመለስ ጉዞ በድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ በመዝመት የዓድዋን ድል መድገም ይገባል። በፈተና ውስጥም ሆነን በሕዝቦች መከባበርና መፈቃቀድ ላይ የፀናችና የተከበረች ኢትዮጵያን በማስቀጠል የአባቶቻችንን አደራ ለመጭው ትውልድ ማስረከብ ያስፈልጋል።
ከዓድዋ ጽናትን፣ አብሮነትን፤ ትጋትን፣ ብሔራዊነትንና አርበኝነትን ወርሰን በጋራ ቆመን የጋራ ሀገራችንን ወደ ከፍታዋ የመመለስ የአባቶቻችን አደራ እንዳለብን ለቅፅበትም ቢሆን መዘንጋት የለብንም!
አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም