ላለፉት ስምንት ዓመታት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚደንት ሆነው ያገለገሉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ ስማቸውም ታሪክ አለው። በውጭው አጠራር ሚድል ወይንም በመካከል ላይ ያለው ጆቴ የሚለው ነው ታሪክ ያለው።
እርሳቸው እንደነገሩን፤ አባታቸው ጀግና ይወዱ ስለነበር ለልጃቸው የጀግና ስም አወጡላቸው። በአጋጣሚ ጀግናው ሰው ቤተሰብም ናቸው። እኚህ ጀግና ሰው ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ወይም ሙቲ ጆቴ ነው የሚባሉት። ሙቲ ቃሉ ኦሮምኛ ሲሆን፣ ትርጉሙም ንጉሥስ ማለት ነው። እኚህ ንጉሥ ከነኩምሳ ሞረዳ ጋር በመሆን ወለጋን ያስተዳድሩ ነበር። በወቅቱ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የሀገር አንድነትን ለማጽናት ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት አሻፈረኝ ካሉት መካከል ይጠቀሳሉ።
የኋላ ኋላ ግን ሀገራቸውን ከተለያየ ነገር የጠበቁ ባለውለታ መሆን ችለዋል። ለአብነትም በሱዳን ድንበር በኩል ኢትዮጵያ አጋጥሟት የነበረውን ችግር ገትረው የያዙ ጀግና ናቸው። እርሳቸው ይህን ባያደርጉ ግማሹ የወለጋ ሕዝብ ወደሱዳን የሚገባበት አጋጣሚ ይፈጠር ነበር። በሌላኛው ደግሞ ጣሊያኖች የዓባይን ምንጭ መነሻ ለማወቅ በመጡ ጊዜ ‹‹ንጉሤ ዓድዋ ላይ እየተዋጋ እናንተ የዓባይን ምንጭ መነሻ ለማወቅ መጣችሁ›› ይሏቸውና ርምጃ ይወስዱባቸዋል።
በነዚህና በሌሎች ታሪኮች የሚታወቁት ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ፤ የልጅ ዳንኤል ጆቴ እናታቸው እናት የደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ልጅ ልጅ ናቸው። ወላጅ አባታቸው ደግሞ ጀግና ስለሚወዱ ጆቴ ተብለው እንዲጠሩ ያደርጋሉ። ከጊዜ በኋላ ግን በተለያየ ምክንያት ዳንኤል የሚለውን ስም ለራሳቸው በማውጣት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በሚለው ስማቸው ፀንቶ መጠሪያቸው ሊሆን ችሏል።
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በ1936 ዓመተ ምህረት ነው የተወለዱት። የተወለዱበት አካባቢ ደግሞ ኢሉባቦር ነው። አባታቸው የአካባቢው ገዥ ነበሩ። በወቅቱ ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ለቀው ባለመውጣታቸው ሀገር አልተረጋጋችም። ሆኖም ግን አባታቸው ለሥራ ከሀገር ሀገር ይዘዋወሩ ነበር። በኋላም የከፋ ጠቅላይ ግዛት ተብሎ የሚጠራው ሀገረ ገዥ ሆነው በሹመት ተዛወሩ።
በከፋ ጠቅላይ ግዛት የቆዩት ስምንት ዓመት በመሆኑ፤ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም ሚያዚያ ሃያሰባት በሚባል ትምህርትቤት ገብተው ለመከታተል ችለዋል። በወቅቱ ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት በደርግ ሥርዓት ያስተዳደሩት ኮሎኔል ምንግሥቱ ኃይለማርያምን ጨምሮ በርካታ የወታደር ልጆችም በትምህርት ቤቱ ተምረዋል። ኮሎኔል መንግሥቱ በሁለትና እና በሶስት ዓመት እድሜ ቢበልጧቸው ነው። ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን አባታቸው የዘመድና በኑሮ አቅም ያነሳቸውንም ልጆች በቤታቸው ሰብስበው ያሳድጉ ስለነበር በብዙ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደጉት።
አባታቸው አሁንም አዲስ አበባ ከተማ የሀገር ግዛት ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍንም፣ ለጊዜው በወቅቱ የባላባት ልጆች ብቻ የሚማሩበት መድኃኒያለም ትምህርት ለሶስት ወር እንዲቆዩ ተደረጉ። ከአጭር ጊዜ ቆይታ በኋላ ደግሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርትቤት ገብተው ለአንድ ዓመት ከተማሩ በኋላ ዊንጌት ትምህርት ቤት ገቡ። በትምህርታቸው 10ኛ ክፍል ከደረሱ በኋላ የጤና እክል ገጥሟቸው ለህክምና ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄዱ። በዚያም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ እድሉን አገኙ።
በዩኒቨርሲቲ የመማር እድል ያገኙት ደግሞ በአሜሪካን ሳንፍራሲስኮ ነው። ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ሀገራቸውን ለማገልገል ተመለሱ። ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ ነገሮች እንዳሰቡት ሆነው አላገኙም። ሥራ ለመቀጠርም በወቅቱ ከነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ፈተናዎች ገጥመዋቸዋል። በጊዜ ሂደት ግን በልማት ባንክ በፈተና አልፈው ተቀጥረው ለማገልገል ችለዋል። ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ ነው አሁን በሚመሩት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚደንት ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት።
ከልጅ ዳንኤል ጆቴ ጋር 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ በዓድዋ ዙሪያ፣ ስለሚመሩት ተቋም፣ የዓድዋ ተምሳሌት ስለሆነው ዓድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት አንስተን ተጨዋውተናል።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ እንኳን ለ128ኛ የድል በዓል አደረስዎ፤ ከዓድዋ ጀግኖች ዋና ዋናዎቹን በማንሳት ቀኑን እናስታውስ።
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡– እንኳን አብሮ አደረሰን፤ ስለዓድዋና የዓድዋ ጀግኖች ስናወሳ ታሪኩ በአጭሩ የሚገለጽ አይደለም። ታሪኩ ግዙፍ ነው። ጣሊያን ኢትዮጵያን በኃል ስትወር ኢትዮጵያ በሥልጣኔ ከሚጠሩ ሀገሮች መካከል አልነበረችም። በወቅቱ የነበሩት መኖሪያ ቤቶች እንኳን ከጭቃ የተሠሩ ናቸው። ግን በኃይል ደሀ ሀገር ሊወር የመጣን ፋስሽት ጣሊያንን በተባበረ የሕዝብ ክንድ ወደመጣበት ለመመለስ ችላለች።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩት አፄ ዳግማዊ ምኒልክ ይህችን ደሀ ሀገር ወራሪ ያጋጥማታል፣ ጦርነት ውስጥም እገባለሁ ብለው አላሰቡም። ስለዓለማዊ ሁኔታ መረጃ ይከታተሉ ስለነበር ጀርመን በርሊን ላይ በኢትዮጵያ ላይ የተዶለተውን ለማወቅ ቻሉ። በርሊን ላይ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የተካፈሉ ነጮች አስተሳሰባቸው ግልጽ ነው። አፍሪካን እንደቅርጫ ለመከፋፈል ነበር ምኞታቸውና ፍላጎታቸው።
ጀርመኖች፣ እንግሊዞች፣ ቤልጂጎች፣ ስፓኒሾች፣ ደቾች ቦርቺጊዞች ተከፋፍለው ስር ሰደው እየተነቃነቁ ነበር። በዚህ መካከል ጣሊያን ኤርትራንና የተወሰነውን የሶማሌ ክፍል ይዛለች። ለጣሊያን የለቀቀላት ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ስለሆነች ዋናዋን ኢትዮጵያ እንድትይዝ ነው የተለቀቀላት።
ጣሊያን ደግሞ በዚያን ጊዜ ዘ ግሬት ሮማንያ ኢምፓየር ትባል ነበር፣ እኛ ልክ የአፄ ቴውድሮስንና አፄ ዳግማዊ ምኒልክን ታሪክ እንደምናነሳው ሁሉ ነበር ታሪኩን የሚያወሱት። ጣሊያን ኢትዮጵያን በጦር አሸንፋ በቅኝ ለመያዝ አቅዳ ስትመጣ የኢትዮጵያን የውስጥ ችግር መሠረት በማድረግ ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያ በውስጧ የተለያዩ ችግሮች ነበሩባት።
ከነበረው ችግርም የከፋው ሕዝቦችዋ በረሀብ መጎዳታቸው ነበር። ወረርሽኝ ገብቶ ከብቶችም በጣም አልቀውባታል። በበሽታ የጎዱ ከህንድ ሀገር የመጡ ከብቶች ፤ የኢትዮጵያ ከብቶች እንዲያልቁ ምክንያት የሆነዋል ። ክስተቱ ሆን ተብሎ ሊሆን እንደሚችል ይጠረጠራል። ምክንያቱም ከብቶች ተጎዱ ማለት በበሬ የሚያርሰው የኢትዮጵያ ገበሬ ማምረት ያቆማል። የሚበላ ከሌለ ሰው በረሀብ ይሞታል። ይዳከማል። የተራበ ሕዝብም ለመዋጋት አይነሳም።
በጊዜው የነበሩ መሳፍንቶችም በመካከላቸው ነፋስ ገብቶ ስለነበር ስምምነት አልነበራቸውም። የነርሱ አለመስማማት ገበሬውን አሰልችቶታል። ስለዚህ ሌላ ጦርነት ቢመጣ ለመዋጋት የነበረው ፍላጎት እጅግ አናሳ ነበር። ይህ ሁሉ ችግር እጇን ለጠላት ያለምንም ጥርጥር ለመስጠት የሚያስችላት ጊዜ ነው ። በኃይል ኢትዮጵያን ሊወር የመጣው ፋሽስት ጣሊያን ደግሞ ይህንን የኢትዮጵያን የውስጥ ችግሮች ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ያለምንም ድካም ሰተት ብሎ ኢትዮጵያ መግባት እንደሚችልና በቅኝም እንደሚይዝ እርግጠኛ ነበር ።
ብልሁ የኢትዮጵያ ንጉስ አፄ ዳግማዊ ምኒልክ ግን ጦርነቱን ከሕዝባቸው ጋር ለመወጣት በወቅቱ ምኒልክ ዓደባባይ ላይ ሆነው በአዋጃቸው የጥሪ ክተት እንዲህ ነበር ያሉት። “እኔ ምንም ያጠፋሁት ነገር የለም፣ ያደረኩትም ነገር የለም። ሀገራችንን፣ ኃይማኖታችንን በአጠቃላይ ሁሉ ነገራችንን ሊያጠፋ የውጭ ወራሪ ኃይል መጥቶብናል። አቅም ያለህ በጉልበትህ፣ አቅም የሌለህ በንብረትህና በፀሎትህ ብለው ነበር ለክተት ዘመቻ ሕዝባቸውን የቀሰቀሱት። መሃላውም አልቀረም። የክተት ጥሪውን ተቀብሎ ለማይመጣው ደግሞ ትቀርና ማርያምን ምሬ አልምርህም” ነበር ያሉት። ጉዳዩ የሀገር ስለሆነ ነው ይህን ማለታቸው።
ኢትዮጵያን በኃይል ሊወርር የመጣን ፋሽስት ጣሊያንን ወደ መጣበት ለመመለስ የቀረ ኢትዮጵያዊ አልነበረም ማለት ይቻላል። በወቅቱ ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ ታዛዥ ከነበሩት ራስ መኮንን፣ ልጅ ወይንም ራስ አባተ ቧ ያለው፣ አባመላው፣ ንጉሥ ሚካኤል፣ ደጃች ባልቻ፣ አሉላ አባነጋ፣ ራስ ሚካኤል ይጠቀሳሉ። ከታዛዥነታቸውም በላይ ሀገራቸውን አስበልጠው የሚወዱ ነበሩ። ለምቾታቸው ሳይሆን ለሀገራቸው ቅድሚያ የሰጡ ናቸው።
ራስ መኮንን ከሀረር ነው ጦር አሰባስበው ወደ ግንባር የሄዱት። ንጉሥ ሚካኤልም እንዲሁ ከወሎ ወደ 40ሺ የሚሆን ጦር ይዘው ነበር የዘመቱት። የአፄ ዮሀንስ ልጅ ራስ መንገሻ ዮሀንስ፣ እነራስ አሉላ አባነጋም ጦርነቱን በማካሄድ ስማቸው ከሚነሱት መካከል ናቸው።
በዓድዋው ጦርነት የሴቶች ሚና ከወንዶች ያልተናነሰ ነው የነበረው። ያደርጉ የነበረው ድጋፍ በዚህ በአጭር ጊዜ ቆይታ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። በታሪክ በሰፊው ቢሰነድ ብዙ ሊባልላቸው የሚችሉ ሴቶች አሉ። ከሴቶች ደግሞ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚነሳው እቴጌጣይቱ ድርሻቸው እጅግ ከፍተኛ ነው የነበረው።
ጠላትን ለመዋጋት የዘመተውን ጦር ምሳና እራት በማብላት፣ የቆሰለውን በማከም፣ የደከመውን ደግሞ ለአዝማሪ ግጥም እየሰጡ በማበረታታት፣ ወንዱም፣ ሴቱም በጋራ ለሀገራቸው አንድ ሆነው በመነሳታቸውና ትግሉንም በጋራ በመቋቋማቸው ነው ጦርነቱን በአንድ ቀን ድል ማድረግ የተቻለው።
አዲስ ዘመን፡- ወራሪው ፋሽት ጣሊያን ያሰበው ሳይሳካ ነገሮች የተገላቢጦሽ ሆኖ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአንድ ቀን ድል ተቀናጅተዋል ። ከድሉ በሃላ ያለው እውነታ ምን ይመስል ነበር?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡– ከድሉ በኋላ በሀገር ውስጥ ብዙ ክንውኖች ነበሩ። ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዩዋ ተጠምዳለች። ወራሪው ፋሽት ግን የገጠመውን ሽንፈት አምኖ ባለመቀበሉና ቂምም በመያዙ ዳግመኛ ኢትዮጵያን ለመውረር 40 ዓመት ሙሉ ሲዘጋጅ ነው የነበረው። ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጣም የጣሊያንን ታላቅነት አመጣለሁ ብሎ ነው። በአውሮፕላን የታገዘ ዘመናዊ የሆነ የጦር መሣሪያ ታጥቆ፣ ብዛት ያለው ሠራዊት ነበር ያሰለፈው። የጦር መሪው ደግሞ ሙሶሎኒ ነበር።
በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በመጀመሪያው ጦርነት አምስትና ከዚያ በላይ ቤተሰባቸውን ያጡ ናቸው። የኔንም ብጠቅስልሽ አያቴ ደጃዝማች ስለሺ ከወንድሞቻቸው ጋር በዓድዋ ተዋግተዋል። የመጀመሪያውን ጦርነት ያየና የተሳተፈ ነው ጣሊያን ከ40 አመት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን ለመውረር ሲመጣ የተነሳው። በዳግመኛውም ቢሆን ጣሊያን የቱንም ያህል በዘመናዊ መሣሪያ ቢታጠቅና ብዙ ጦር ቢያሰልፍም በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ሽንፈትን ተከናንቦ ነው ድል የተመታው።
በርግጥ በኢትዮጵያ በኩል በጦርነቱ የተጎዳው ሕዝብ ከፍተኛ የሚባል ነበር። አምስት ዓመት ሙሉ በየጫካውና በየዱሩ ተንገላተዋል። ከታሪክ እንደምንሰማው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ለጠላት አሳልፎ ላለመስጠት ተጋድሎ ሲያደርጉ የፈረስ ሽንት እስከመጠጣት ደርሰዋል። ወራሪው ጣሊያን ኢትዮጵያውያኑ የሚጠጣ ውሃ እንዳያገኙ ወንዞችን ሳይቀር እስከመመረዝ ግፍ መፈጸሙ ጭምር ነው የሚነገረው። በአጠቃላይ የሁለተኛው ጦርነት ለኢትዮጵያውያን ፈታኝ ነበር ።
ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ፈታኝ የሆነውን ጦርነትተቋቁመው የሀገራቸውን ዳር ድንበር ባያስከብሩ ኖሮ ዛሬ ስለዓድዋ የድል ታሪክ አናወራም ነበር። በዚያን ጊዜ የነበረውን ታሪክ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ በኋላ ስላለውም ታሪክ ማውራት ቻልን። ጣሊያኖች ሲወጡ እረዳለሁ በሚል ሰበብ ደግሞ እንግሊዞችም መጥተው ነበር። እነርሱን ደግሞ በዲፕሎማሲ ነው ማስወጣት የተቻለው። አፄ ኃይለሥላሴ ቀድመው ካቢኔያቸውን በማቋቋምና ሚኒስትሮችንም በመሾም ተንቀሳቀሱ።
አዲስ ዘመን፡- ትልቅ መስዋእትነት ተከፍሎበት የተገኘው ድል ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ ትውልድ ተምሳሌት አድርጎት ለሀገሩ በተለያየ መንገድ እንዲያገለግል ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡– አሁን ያለው ትውልድ ቀላል ነው ብዬ አልወስድም። ጥሩ አእምሮ አለው። መሥራትም የሚችል ነው። ሀገር ወዳድም ነው። እንደሀገርም ጠንካራ የሠለጠነ የተገነባ ሠራዊት አለን። ትውልዱ ግን በድህነት ብዙ ፈተናዎችን አሳልፏል። አሁን ላይ ደግሞ ለትውልዱ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮችም እየታዩ ነው። እጅ ላይ ባለው ስልክ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅ እድል አግኝቷል። የሀገሩንም ታሪክ ለማወቅ የሚያስችሉት ነገሮች ምቹ ናቸው። አሁን መጠየቅ ያለበት ድህነትን ለማሸነፍ ምን እንሥራ የሚለው ነው። ኢትዮጵያ በማዕድንም ሆነ በተለያየ ነገር የተፈጥሮ ሀብት አላት። ይህንን ወደ ኢኮኖሚ መለወጥ ያስፈልጋል ።
አዲስ ዘመን፡- የዓድዋ ድል በዓል በየዓመቱ በተለያየ ዝግጅት ከመታወስ አልፎ ቋሚ የሆነ መታወሻ የሚሆን የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በመሀል አዲስ አበባ ከተማ ተገንብቷል። ይህ የመታሰቢያ ፕሮጀክት ያለውን ትርጉምና በጥውልዱ ውስጥ የሚፈጥረውን መነቃቃት እንዴት ይገልጹታል ለእርስዎስ የሰጠዎትን ስሜት ምን ይመስላል ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡– የዓድዋ መታሰቢያ ፕሮጀክት በቅርጹና በይዘቱ ብቻ ሳይሆን፤ በውስጡ በያዛቸውም ታሪካዊ ቁሶች ከዓድዋ ድል ጋር እንዲገናኝ ጥረት የተደረገበት ነው። በተጓዳኝም መዝናኛዎች ተካትተዋል። ይሄ እየተዝናኑ ታሪክንም ለማወቅ እድል ይሰጣል። ይህን ትምህርት ሰጪ የሆነ ፕሮጀክት ወጣቱ ሊጠቀምበት ይገባል ። የያኔውን ኩነት አሁን እርሱ ከሚገኝበት ጋር በማነፃፀር ምን መስራት እንዳለበትም እራሱን እንዲጠይቅ ያስችለዋል። የእኔን ስሜት በተመለከተ፤ እውነት ለመናገር በደስታ አልቅሼያለሁ። ለፕሮጀከቱ እውን መሆን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የታሪክ ቤት ነው ፤ የማህበሩ አባላት በተለያየ ምክንያት በሕይወት የማይኖሩበት ሁኔታ ሊከሰት ከመቻሉ አኳያ ማህበሩን ለማስቀጠል የታሰበ ነገር አለ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡- በእኔ እምነት አንድ ማህበር ወይንም ድርጅት ሊፈርስ የሚችለው እራስ ወዳድ የሆነ አባል ወይንም መሪ ሲኖር ነው። ያለውን ሀብት ለመቀራመት እጅ ሲበዛበት ወይንም ለማጥፋት ዓላማ ተደርጎ ሲሠራ ነው ። በእውነት ለመሥራት ዝግጁ አለመሆንም ሌላው ጥፋት ነው። አሁን ላይ በማህበሩ እየተሠራ ያለው ሥራ ቤቱን በተለያየ መንገድ ማጥራት ነው።
የማጥራት ሥራው በውስጡ የሚሠሩት ሠራተኞች ያላቸው የትምህርት ዝግጅት ጭምር ያካትታል። አመራሮቹ የተማሩ ሰዎች መሆን አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። የትምህርት ዝግጅት ባለው ሰው የሚመራ ከሆነ ክፍተቶችን መቀነስ ይቻላል። እስካሁን ጥሩ እንቅስቃሴዎች እየተደረገ ነው።
ከዓድዋ ድል ጋር በተያያዘ በአርቲስቶችና በተለያዩ ግለሰቦች ተነሳሽነት የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ታሪክ ለማውሳት ጥረት ተደርጓል። ለአብነትም አርቲስት ቻቺ ታደሰ በደቡብ አፍሪካ፣ መድረክ አዘጋጅታ ማህበሩ የተገኘውን መድረክ በመጠቀም ጥሩ ሥራ ተሠርቷል። በኬንያም በተመሳሳይ ድሉን፣ ታሪኩን፣ ጀግኖቹን የሚያስታውስ እና የኢትዮጵያንም ኩራት ከፍ የሚያደርግ ሥራ ለመሥራት ዝግት ተደርጓል። በዚህ መልኩ አፍሪካ ውስጥ መሥራት ተችሏል።
በአሜሪካን ሀገርም እንዲሁ አቶ ጥላሁን የተባሉ የታሪክ አዋቂ የማህበሩም የምክር ቤት አባል የሆኑ ሎሳንጀለስ ላይ ባዘጋጁት መርሃግብር ላይ ማህበሩን ወክዬ ተገኝቼ እንዲሁ ገለጻ አድርጌያለሁ። ይህም በዓለም ላይ በታሪካችን ለመታወቅ ያለውን እድል ጨምሮልናል።
የተጀመረው ሥራ የበለጠ እንዲጠናከርና የተሻለም እንዲሆን በውስጥ በተለይም ማህበሩን የምንመራው ሰዎች በእውቀት ላይ የተመሠረተ አመራር መስጠት ይጠበቅብናል ። ከራስ ወዳድነትም የራቅን መሆን ይጠበቅብናል። ማህበሩን በማቆየት ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ እንድንችል ሥራችን ጥራት ሊኖረው ይገባል። ማህበሩ ዘላቂነት እንዲኖረው ደንባችንንም በየጊዜው ማሻሻል ይኖርብናል። የማህበሩን ሀብት የሚያሳድግ ሥራም መሠራት አለበት። ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነትም አብሮ የሚታይ ነው። የማህበሩን አባላት በተመለከተም መንግሥት የሚሰጠንን ድጎማ በመጠቀም ማህበሩ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው። አዋቂዎች በሕይወት ባይኖሩም ማህበሩ ልጆቹን ይዞ ነው እየሠራ የሚገኘው።
አዲስ ዘመን፡- ማህበሩ የሚተዳደርበት የገቢ ምንጭ በተመለከተና አባላት የሚገኙበትን ሁኔታና ያሉትን አባላት እንዲሁም ማህበሩ በክልሎች ስላለው እንቅስቃሴ ቢገልጹልኝ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡– የማህበሩ አባላት ከ10ሺ በላይ ይሆናሉ። ግን መረጃ ማጣራት ይጠይቃል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ማህበሩ የገንዘብ ድጎማ የሚያደርግላቸው አባላት ሁለት ሺ ይሆናሉ። በሥራቸው የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰብ ሲጨመር ከፍ ይላል። ሁሉም አባላት በገንዘብ ቢታገዙ ጥሩ ነው ግን ገቢ ውስን በመሆኑ ማሟላት አልተቻለም። ይህም መንግሥት ስለሚያግዝ እንጂ በማህበር አቅም ተችሎ አይደለም። ስለዚህ ድጋፉን በእድሜ እና ባላቸው የኑሮ ሁኔታ በመለየት መታገዝ ያለባቸው እንዲታገዙ እየተደረገ ነው ።መንግሥት በፈቀደው ነፃ የሕዝብ የትራንስፖርትና የህክምና አገልግሎቶችም እየተጠቀሙ በመሆኑ በዚህ በኩልም ችግራቸውን ለማቃለል ጥረት ተደርጓል።
በአሁኑ ጊዜ ማህበሩ 14 ያህል ዞን አለው። ይሁን እንጂ በነዚህ ዞን ውስጥ የሚገኙት የአርበኛ ልጆችና ቤተሰቦች ተመዝግበው መረጃ ገና አልተያዘም። እዚህ ላይ አንዱ ችግር ምዝገባ ከተካሄደ ክፍያም አብሮ መፈፀም ይጠበቃል። የአቅም ጉዳይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል።
በአሁኑ ጊዜ አርበኞችም ሆኑ የአርበኞች ቤተሰቦች በተበታተነ ሁኔታ ነው የሚኖሩት። ሰው ሊረዳቸው ቢፈልግ እንኳን አድራሻቸው ምቹ አይደለም። ረዳት የሌላቸውም አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ከውጭ ገንዘብ ይልኩላቸዋል። ነገር ግን ገንዘቡን ተቆጣጥሮ በአግባቡ እንዲጠቀሙ በኃላፊነት የሚያግዛቸው ባለመኖሩ እየተቸገሩ ነው። እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት የአርበኞች መንደር ማቋቋም ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ።
የአርበኞች መንደር ቢመሠረት መንግሥትም ሆነ ግለሰቦች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የማህበሩ አባላትን በቀላሉ ማገዝ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። በዚህ ረገድም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባን እየጠየኩ ነው። ከንቲባዋ ሃሳቡንም የሚደግፉት ይመስለኛል። እስካሁንም ማህበሩን በተለያየ መንገድ እያገዙት ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበርን በመምራትዎ ምን ይሰማዎታል ? ማህበሩን ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲመሩ ምን አስተዋጽኦ አደረጉ? ምንስ ይቀረኛል ይላሉ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ፡- ከውጭ ሀገር እንደመጣሁ ለ17 ዓመታት በልማት ኮሚቴ ውስጥ አገልግያለሁ። በዚህ እና በተለያዩ ሥራዎች ውስጥም እሳተፍ ነበር። በወቅቱ ማህበሩ ውስጥ አለመግባባቶችና የተለያዩ ችግሮች ነበሩ። ይህን የተገነዙቡና ለማህበሩ ተቆርቋሪ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ማህበሩን እንድመራ ጥያቄ ቀረበልኝ። እኔም ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ አላሳለፍኩም፤ ኃላፊነቱን ተቀብዬ ላለፉት ስምንት ዓመታት መርቻለሁ። ከዚህ በኋላ የሁለት መዓት እድሜ ነው የቀረኝ። ከዚያ በኋላ አገልግሎቴ ያበቃል። እስካሁን ምን አሳክተሃል ለተባልኩት ይህን ያህል ሰርቻለሁ ብዬ አፌን ሞልቼ የምናገረው ነገር የለም።
ግን ደግሞ አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ። እኔ ወደመሪነት ከመምጣቴ በፊት አንድ አርበኛ አስር ብር ነበር ድጎማ የሚያገኘው። ድጎማው ወደ 2000 ብር ከፍ እንዲል አድርጌያለሁ። ዞን ላይ የሚገኙት እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ወይንም እንዲችሉ የሚጠናከሩበትን መንገድ እያመቻቸን ነው።
በተጨማሪ የጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት ጥቅማጥቅም አንዱ የመቀበሪያ ሥፍራ ነው። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ቀደም ሲል ሥላሴ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከአርበኞች በስተቀር የሌላ ሰው ቀብር አይፈጸምም ነበር። አሁን ላይ ግን ይህ እየተከበረ አይደለም። በዚህ፣ም ቢያንሰ የነርሱ ተጠቃሚነት ግምት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል።
ከመንግሥት ጋር በመሆንም የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን ነው። መንግሥትም ለማህበሩ ትልቅ እክብሮት እንዳለው በተለያየ መልኩ በሚያደርገው እገዛ ይገለጻል። ከመንግሥት ጋር ከምንሠራቸው ሥራዎች አንዱ የትውልድ ግንባታ ላይ ነው። ወጣቱ ትውልድ የሀገር ፍቅር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከዓድዋ ጀግኖች አባቶች እንዲማር በተለያየ ጊዜ በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ በመገኘት ከማህበሩ የሚጠበቁ ተግባራት አከናውነናል። በተለያዩ ዝግጅቶች ላይም ግብዣ ሲደርግልን አጋጣሚውን ተጠቅመን ጀግኖች አባቶች እንዲታወሱ አድርገናል ።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያንም ስለሀገራቸው ታሪክ እንዲያውቁ ፣ በተለይም በወላጆች ይህንን ሃላፊነት እንዲወጡ የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው። የማህበሩ ህልውናም እንዲረጋገጥ በሚቻለው ሁሉ ጥረት እየተደረገ ነው።
ይህም ሆኖ ግን ብዙ ሥራዎች ይቀራሉ። የማህበሩ ህልውና እንዲረጋገጥ ኃላፊነቱ የማህበሩ ብቻ አይደለም ፤ የሁሉም ዜጋ ነው ። የሚኮራበትን ታሪክ ያስመዘገቡት በዚህ ተቋም ውስጥ በማህበር የተሰባሰቡ ጥንታዊ አርበኞች ናቸው። ማህበሩ የገቢ ምንጭ የሚያገኝበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። በዚህ አጋጣሚ ዜጎች ማህበሩን በሃሳብ፣ በእውቀት፣ በገንዘብ እንዲያግዙ ጥሪ አቀርባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በጣም እናመሰግናለን
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም