«አፍሪካ ከአውሮፓ ቅኝ ግዛት ነፃ እንድትወጣ የዓድዋ ድል ትልቁን ሚና ተጫውቷል» -ፀጋዬ ዘለቀ (ዶ/ር) በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ

በወቅቱ ሰሜን ሸዋ ክፍለ ሀገር ተብሎ በሚጠራው ጎጃም መስመር ጉለሌ በሚባል ቦታ የተወለዱ ሲሆን፤ ለከተማ ቅርብ አካባቢ ይኖሩ ስለነበር እንደአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ትምህርት ቤት ለመድረስ ብዙ ርቀት መጓዝ አይጠበቅባቸውም ነበር፡፡ በግምት ከአንድ ኪሎ ሜትር ብዙም የማይርቅ መንገድ እየተጓዙ የአንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ከተወለዱበት ቦታ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ፍቼ በማቅናት፤ በፍቼ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ አጎታቸው በቅርብ ርቀት በዛው በፍቼ ከተማ ስለነበሩ፤ ብዙም ሳይቸገሩ የመልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ በቅተዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ሲማሩ ከተፈጥሮ ሳይንስ ቀይረው ማህበራዊ ሳይንስ የተማሩ ሲሆን፤ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ቡኪፒንግ ስለተማሩ ኢኮኖሚክስ የመማር ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት አጠናቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሲቀላቀሉ ምኞታቸው የነበረውን ኢኮኖሚክስ መማራቸውን ትተው፤ የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪያቸውን በታሪክ ላይ አድርገዋል።

የዛሬው የዘመን እንግዳችን ፀጋዬ ዘለቀ (ዶ/ር) ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የሽግግር መንግሥቱ ጊዜ በመሆኑ ኢኮኖሚክስ ብዙም የሥራ ዕድል የለውም የሚል ወሬ ሰሙ፡፡ ሆኖም ለአንድ ዓመት የዩኒቨርሲቲውን የመጀመሪያ የጋራ ኮርሶች ሲማሩ፤ ኦኮኖሚክስን እንደሚማሩ እርግጠኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ግርማ አስፋው የሚባሉ መምህር ስለኢኮኖሚክስ ትምህርት ጥሩነት ተናግረው፤ ነገር ግን ሥራ እንደማይገኝበት፤ አካውንቲንግ የተወሰነ ሥራ እንዳለው መግለፃቸውን ተከትሎ የዛሬው እንግዳችን ሌላ ዘርፍ ለመምረጥ አሰቡ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ የታሪክ መምህር ሲያስተምራቸው በጣም ደስ ይላቸው ስለነበር ወደ ታሪክ ትምህርት አዘነበሉ፡፡ በእርግጥም ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲወጡ፤ በታሪክ መምህርነት ሥራ ማግኘት አይከብድም ነበር፡፡ እንዲያውም በአንድ ዓመት ውስጥ ሶስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና አንድ መምህራን ማሠልጠኛ ተፈልገው እየተጠየቁ ለማገልገል በቁ፡፡ ምርጥ ታሪክ መምህር መሆን ቻሉ፡፡ መጀመሪያ ምስራቅ ባሌ በመምህርነት መሥራት ጀመሩ፤ ብዙም ሳይቆዩ አጋርፋ በድጋሚ ተመደቡ፣ እንደገና ሮቤ የመምህራን ማሠልጠኛ እንዲያስተምሩ ተላኩ፡፡ ከዛ እንደገና ጃራ የሚባል ቦታ እንዲያስተምሩ ተጠየቁ፤ በመጨረሻ ግን ጃራ ለሁለት ዓመት ከቆዩ በኋላ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፡፡

የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፤ ሮቤ መምህራን ማሠልጠኛ የነበረው እና ወደ ሮቤ ኮሌጅ ባደገው ተቋም ለሁለት ዓመት ቆይተው ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተዘዋወሩ፡፡ አሁንም በእዛው በጅማ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሙያ እያገለገሉ እና የተለያዩ የምርምር ሥራዎችንም እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት እና የምርምር ሥራዎችንም የሚያከናውኑት ፀጋዬ ዘለቀ (ዶ/ር) ጋር አጠቃላይ ታሪክን በተመለከተ እንዲሁም ሰሞኑን እየተዘከረ ያለውን የዓድዋ ድል ላይ አተኩረን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡-

 አዲስ ዘመን፡- ታሪክ ምንድን ነው?

ዶ/ር ፀጋዬ፡- ታሪክ በቀላሉ የሚታወቅ እና ተበይኖ የሚቀመጥ አይደለም፤ በጣም ብዙ ማንበብን እና መመራመርን ይጠይቃል፡፡ በትምህርት ላይ በነበርኩበት ወቅት የዓለም፣ የአፍሪካ፣ የኢትዮጵያ ታሪክን ተምሬያለው እጅግ ሰፊ ነው፡፡ የዓለም ታሪክ ሲባል የአውሮፓ ታሪክ ለብቻው እጅግ ሰፊ ንባብን የሚጠይቅ ነው፡፡ እንኳን የዓለም የኢትዮጵያ ታሪክም ባህር ነው፡፡ ታሪክ ላይ ሙሉ ለሙሉ በዘመንም ሆነ በሀገር አውቀናል ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ የዘመናዊ ኢንዱስትሪ ታሪክ ከተባለ ኢኮኖሚው፣ ማህበራዊው እና ሌላ ሌላውም ይጠናል፡፡ እንደዛም ሆኖ ያንን ሙሉ ለሙሉ ማወቅ አይቻልም፡፡ ታሪክ የሰው ልጅ ሰርቶ ያለፈ ጉዳይን በሙሉ ስለሚዳስስ፤ ያንን ማወቅ በጣም ፈታኝ ነው፡፡

በሌላ በኩል በየትኛውም ጊዜ ያለ ታሪክ መረጃ ሙሉ ሆኖ አይገኝም፡፡ ታሪክ ፀሃፊ መረጃዎችን አንብቦ አመሳክሮ፣ የመጀመሪያ መረጃ ሁለተኛ መረጃ እያለ አጣርቶ መፃፍ አለበት፡፡ የእኛ ሀገርን ታሪክ በደንብ ልወቅ ከተባለ የራሳችንን ታሪክ ከአፍሪካ ታሪክ ጋር አመሳክረን፤ በተጨማሪ የፅሁፉን ታሪክ ከአፈ ታሪኩ ጋር አስተሳስረን መፃፍ እና ማንበብ አለብን፡፡ አንድ መጽሐፍ ብቻ ተነቦ አንድን ታሪክ ማወቅ አይቻልም። መመሳከር አለበት፤ ታሪክን ማወቅ ጊዜ የሚወስድ ነው። ይህ በዓለም ደረጃ ፈተና ነው፡፡

እኛ ሀገር ታሪክ ላይ ብዙ ጫናዎች እና የተለያዩ ፈተናዎች አሉ፡፡ እንደሚታወቀው ታሪክን ለታሪክ ባለሙያ የመተው ችግር አለ፡፡ በሌላው ዓለም በእያንዳንዱ ዘርፍ የታሪክ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ትንታኔ የሚሰጡትም የታሪክ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ያደጉ ሀገራት ጠንካራ የታሪክ ማህበርም አላቸው፡፡ ታሪክ ሳይንስ ነው፡፡ ባለሙያዎች ታሪክን መፃፍ ያለባቸው በሳይንሳዊ መንገድ ነው፡፡

ታሪክ የራሱ የአፃፃፍ ዘዴ አለው፡፡ ምናልባትም ፈተና የሆነው በሳይንሳዊ መንገድ እየሔድንበት ባለመሆኑ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪክን የምናይበት መንገድም ሆነ የፖለቲካ ጫናዎች ትልቅ ፈተና ሆነውብናል፡፡ አሁን ግን በሒደት የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማህበርን እስከ ማቋቋም ደርሰናል። ወደ ፊት ብዙ ነገሮች ይስተካከላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ታሪክን በቅጡ ለማወቅ እያንዳንዱ ቅንጣት መታየት አለበት፡፡ ታሪክ ፖለቲካ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ሰፊ ጉዳይ ነው፡፡ የሕክምና ታሪክ ብቻውን በሰፊው ሊጠና ይችላል፡፡ የስፖርትን ታሪክ ብቻ መሥራት ይቻላል፡፡ በእርግጥ እኛ እዛ ላይ አልደረስንም፡፡ ነገር ግን ታሪክ ሰፊ እንደባህር ጥልቅ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከታሪክ ጋር ተያይዞ ብዙ ውዝግብ ባለበት በዚህ ጊዜ የታሪክ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ማህበር ከመቋቋም ባሻገር ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?

ዶ/ር ፀጋዬ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚያጨ ቃጭቁ ታሪኮች አሉ፡፡ እዛ ላይ ባለሙያው ገንዘብ በጣም ቢያስፈልገውም ቢያንስ ማህበሩ በእነዚህ ላይ ምርምር አድርጎ የጠራ ታሪክ እንዲኖር ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡ እንደሚታወቀው ታሪክ ለሀገር ግንባታ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ ታሪክ ያገናኛል፤ የሰው ልጅ ታሪክ ወደ ኋላም እየተጠና ሲቀጥል አንድ መሆናችንን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በእርግጥ ማህበሩ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ቢሠራ ጥሩ ነው፡፡ አሁንም እየሠራቸው ያሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ኮንፈረስም እያካሄድን ነው፡፡ ስፖንሰር የሚያደርጉም አሉ፡፡ ስለዚህ በታሪክ በኩል ጥሩ መስመር ላይ ነን ብዬ አምናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ታሪክ መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የዓድዋ ድል ነው፡፡ ይህ የዓድዋ ድል ታሪክ በዓለም ደረጃ ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው ይላሉ?

ዶ/ር ፀጋዬ፡-የዓድዋ ድል እንደሚታወቀው ጥቁሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት አንፀባራቂው ድል ነው፡፡ ከዓድዋ ድል በፊትም ሆነ በኋላ ተመሳሳይ እና ተወዳዳሪ በዓድዋ ደረጃ ድል አልተገኘም፡፡ በተወሰነ መልኩ በዓለም ታሪክ ውስጥ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ የተመዘገበው ጃፓኖች በራሺያ ላይ የተቀናጁት ድል ነው፡፡ የዓድዋ ድል በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይነት አለው፡፡ ምክንያቱም በዛ ጊዜ ራሺያ ናፖሊዮን ያሸነፈች፤ በሁለተኛውም ሆነ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ሁሉንም ለማለት በሚያስችል መልኩ አውሮፓዎችን ያሸነፈች ነበረች፡፡፤ ሆኖም በኋላ በጃፓን ተሸንፋለች፡፡

የኢትዮጵያው የዓድዋ ድል ደግሞ በዛ ጊዜ እንደሚታወቀው ጥቁር ሕዝብ እንደሸቀጥ የሚሸጥበት እና የባሪያ ንግድ የነበረበት፤ ጥቁሮች የበታች ተደርገው አውሮፓዎች አፍሪካን ለመቀራመት የመጡበት እና አብዛኛው አፍሪካ በእነርሱ እጅ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ የተገኘ ድል በመሆኑ ጥቁሮች በነጮች ላይ ያገኙት የመጀመሪያው ድል ነው፡፡ ሌላው የዓድዋ ድል ላይ ነጮች ጉልበት ያለው የፈለገውን ማድረግ ይችላል ብለው ያምናል፡፡ ይህ በራሱ ልክ እንዳልሆነ ያረጋገጠ ድል ነው፡፡ ሃይል አለን ቢሉም እንደሚሸነፉ በዓድዋ ድል ታይቷል፡፡ ድሉ ጥቁሮች የበታች ናቸው የሚለው ትርክት እንዲሸረሸር አድርጓል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለጣሊያን ወግነው የሚፅፉ የዓለም ዕውቅ ፀሃፊያን እነጆርጅ፤ ‹‹በአፍሪካ አዲስ ሃይል ተነሳ›› ሲሉ ከትበው ነበር፡፡

ይህ በጣሊያን ላይ የተቀናጀነው ድል ምናልባት በኋላም ዘግይተው የመጡትን ፋሺስቶችን ለመምታት እንደዋነኛ ምክንያት ይወሰዳል፡፡ ሌላ መሪ ሲመጣ ለዳግም ወረራ ተዘጋጅተው ከ40 ዓመት በኋላ በሞሶሎኒ በኩል ኢትዮጵያን ሲወሩ፤ ዳግም ተሸንፈዋል፡፡ የዓድዋ ድል ከዓለም አንፃር ሲቃኝ ያመጣው ለውጥ ደግሞ ሄዶ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሳት ዋነኛ ባይሆንም እንደአንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ኢትዮጵያን አስመልክቶ ብዙ የፃፉት በዓለም ደረጃ የታወቁት ፖል የሚባሉት ሰው እንደገለፁት፤ የዓድዋ ድል አውሮፓ በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ያላትን የበላይነት ማጣት መጀመሯን ያመላከተ መሆኑን እና የሃይል ፖለቲካ ማዕከሉ ወደ ሌላ መንገድ እያመራ እንደሚገኝ ያመላክተ ድል ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንዳሸነፈች በዛው ዓመት መጀመሪያ ጣሊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ቆንፂላ ከፍታለች። ከዛ በኋላ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የራሳቸውን ቆንፂላ መክፈታቸው እና ኢትዮጵያ በሃያላን ሀገራት ዘንድ ዕውቅና ማግኘቷ የታወቀ ነው። በዛ ጊዜ ብዙ ነጮች ወደ አዲስ አበባ የመጡበት ጊዜ በመሆኑ ዓመቱ የፈረንጆች ዓመት እስከመባል መድረሱ ተፅፏል፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም፤ አሜሪካን ውስጥ በባሪያ ንግድ ወደ እዛ የሄዱ ሰዎች የጀመሩት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በተጨማሪ የዓድዋ ድል እነርሱንም የበለጠ አነቃቅቷል፡፡ የመጀመሪያው የፓን አፍሪካ ኮንፈረስ ተብሎ የሚጠራው በ1900 ላይ የተካሔደው እና በዊሊያም ሔነሪ ሲልቪስተር ስም ለተሰየመው ኮንፈረንስ ድሉ አንዱ ትልቅ ግብዓት ሆኗል፡፡ ለ1919፣ 1921፣1923 ማንቸስተር ላይ በ1945ም ለተካሔደውም የፓን አፍሪካ ኮንፈረስ ሁሉ ትልቅ ሚና ነበረው። በኋላም ከዳያስፖራው በተጨማሪ አፍሪካ ውስጥ ያሉት እነኩዋሜ ኑኩሩማ ፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ እና ሌሎችም ተሳትፈው አፍሪካ ከአውሮፓውያን ነፃ እንድትወጣ ሲጠይቁም የዓድዋ ድል አንዱ ግብዓት ነው፡፡

ስለዚህ በአጠቃላይ ድሉ አፍሪካ ከአውሮፓ ቀኝ ግዛት ነፃ እንድትወጣ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። ያንን ሁሉ የጠየቁበት ኮንፈረስ ነው፡፡ በኋላም ፓን አፍሪካኒዝም ወደ አፍሪካ ሕብረት ድርጅት፣ አፍሪካ አንድነት እና አፍሪካ ሕብረት ሲሸጋገሩ በሙሉ ከዓድዋ ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ሲታይ ዓድዋ በአፍሪካ ደረጃ የተገኘ ትልቅ ድል ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ጥቁር ከነጭ ጋር እኩል መሆኑን ከማሳየት ባሻገር የዓለምን የፖለቲካ መስመር ቀይሮታል ይባላል፡፡ በእርግጥ ቀይሮታል ለማለት መገለጫው ምንድን ነው?

ዶ/ር ፀጋዬ ፡– በእርግጥ በታሪክ በረዥም ጊዜ የሚገኝ ለውጥ ተብሎ የሚጠራ ውጤት አለ፡፡ ከዚህ አንፃር እንይ ከተባለ ለምሳሌ በኢትዮጵያ አንድ አቢዮት ተነሳ እንላለን፡፡ አቢዮት ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው። የዓድዋም በተመሳሳይ መልኩ ተፅዕኖው በአንድ ጊዜ የታየ ነው ለማለት ያዳግታል፤ ረዥም ጊዜ ይወስዳል። በዛን ጊዜ ለምሳሌ ሃያል ሀገር የሆኑት አውሮፓዎች ራሳቸው ፈረንሳይ እና ራሺያ የኢትዮጵያ ተፃራሪዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ፈረንሳይ ጅቡቲ ላይ ቤዝ ነበራት። ጦርነቱ በዛ በኩል እንዲመጣ ፈረንሳይ ፈቅዳ ነበር። ራሺያም በተመሳሳይ መልኩ ከኢትዮጵያ ጋር በተቃራኒው የቆሙ ነበሩ፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራቸዋል፡፡

በተጨማሪ በአሜሪካን ውስጥም የነማርቲን ሉተር ኪንግ መነሳት በራሱ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ግን አሁንም ገና በአፍሪካ ብዙ ችግሮች እንዳሉ መካድ አይቻልም፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ለሚኖረው የዓለም የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥም ጭምር የዓድዋ ድል ሚና ይኖረዋል ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የትኛውም ሀገር ሕዝብ ዝም ብሎ ቅኝ አልተገዛም፡፡ የተለያዩ ትግሎችን ያደርጉ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ድል አልተጎናፀፉም፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዴት ቅኝ ገዢን ማሸነፍ እና ድል መጎናፀፍ ቻሉ?

ዶ/ር ፀጋዬ፡– እዚህ ላይ ኢትዮጵያውያኖች ድሉን ለማግኘት የነበራቸውን ምቹ ሁኔታ ጣሊያኖች የነበራቸውን ምቹ ሁኔታ ምንድን ነው የሚለው ሲነፃፀር አውሮፓውያን ያለምንም ጥርጥር በዛ ጊዜ የተሻለ የጦር መሣሪያ ነበራቸው።በተጨማሪ ከኢንዱስስሪ አብዮት በኋላ የመጡ በመሆኑ ከእኛ በጣም የተሻለ የጦር መሣሪያ ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ ማክሲም ገን የሚባል ለአፍሪካውያን የማይሸጥ የጦር መሣሪያ ነበር። ጣሊያኖች ያንን መሣሪያ ይጠቀሙ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያኖች መልክዓ ምድሩን ያውቃሉ፡፡ ምናልባትም ግን የመሪዎች ብቃት እና አቅም እንዲሁም አፄ ምኒልክን ጨምሮ የሌሎችም የጦር መሪዎች ሚና ትልቅ ነበር፡፡ በዛ ጊዜ የነበሩት የጦር መሪዎች በጦርነት ውስጥ ተወልደው ያደጉ እንዲሁም ጦርነት ምን እንደሆነ የሚያውቁ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ ድል እንድታገኝ ያደረጋት አንድነቷ ነው፡፡ መላው ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንቀሳቅሰው በአንድነት እዛ ሔደው መዋጋታቸው ኢትዮጵያውያን ድል እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ሁሉንም ሕዝብ በአንድ ላይ መጠራቱ እና ሁሉም መንቀሳቀሱ ድሉ እንዲገኝ አድርጓል የሚል እምነት አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ምን አተረፈች?

ዶ/ር ፀጋዬ ፡– የዓድዋ ትሩፋት ብዙ ነው። ሀገርን ወይም ሀገረ መንግሥትን በመገንባት ላይ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ ማለትም ሉዓላዊነትን ማስከበር ከመቻል እና መንግሥትን ከመገንባት አንፃር የተገኘውን ትሩፋት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ዓድዋ ኢትዮጵያውያን የጋራ ትርክት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከላይ እርሶ እንደገለፁት ዓድዋ በዓለም ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል በጣም ትልቅ ድል ነው፡፡ ነገር ግን በልኩ ለዓለም አስተዋውቀነዋል ብለው ያምናሉ ?

ዶ/ር ፀጋዬ፡-ይሔ ምንም ጥያቄ የለውም ድሉን በማስተዋወቅ በኩል ተገቢውን ሥራ አልሠራንም፡፡ ምናልባት በተለይ የአሁኑ ትውልድ አፍሪካ ውስጥም ሆነ ከአፍሪካ ውጪ ያሉት ድሉን የማያውቁበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ነገር ግን በዛ ጊዜ የተማረው ሕዝብ እና የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች ከእኛ የበለጠ ዓድዋን ያውቁታል፡፡ አሁንም ብዙዎች ከእኛ በላይ ለዓድዋ ቅርብ ናቸው፡፡ አሁንም ከእኛ ይልቅ አሜሪካን ውስጥ ያሉት ጥቁሮች፣ ካረቢያን አካባቢ ጃማይካ ላይ እና ሌሎችም አካባቢዎች ለምሳሌ ብራዚል ውስጥ ይታወቃል፡፡ በመጀመሪያ ብራዚል ውስጥ የነበረው የጥቁሮች ጋዜጣ ‹‹ኦ ሚኒሊክ›› የሚል ነበር፡፡ ዓድዋን በማስተዋወቅ እንደውም እኛ ብዙ ሠርተናል ማለት አይቻልም፡፡ አሁን የተወሰነ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን አሁንም ብዙ ይቀረናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ምን መሠራት አለበት?

ዶ/ር ፀጋዬ ፡- የዓድዋን ታሪክ ለማሳወቅ አሁን ላይ የተጀማመሩ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ ጥናት መደረግ አለበት፡፡ ዓድዋ ላይ ብቻ ሳይሆን ብዙ የተጀማመሩ ታሪኮች ላይ ብዙ ይቀረናል፡፡ የዓድዋ ታሪክ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ምርምሮችን ማድረግ አለብን፡፡ ብዙ ነገሮች ላይ የማንስማማባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በዓድዋ ጀግኖች ራሱ አንስማማም፤ ለምሳሌ ገበየሁ ጎራ ይባል ነበር፤ በኋላ ገበየሁ ጉርሙ ተባለ አሁን ደግሞ ገበየሁ ገብሩ ተባለ ስለዚህ በጀግኖቻችን ስም እንኳ እየተስማማን አይደለም፡፡

የጦር መሪዎች ታሪክ ከስማቸው ጀምሮ አሻሚ ናቸው፡፡ ይሔን ማጣራት ከባድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የ 128 ዓመት ታሪክ የልጅ ልጆቻቸውን አግኝቶ ማጣራት ይቻላል፡፡ የተወለዱበት ቦታ ሔዶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ የታሪክ ተማሪዎች ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ሰዎች መሥራት አለባቸው፡፡ መፅሐፎች አልፎ አልፎ አሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። ሙሉ ታሪኩን የያዘ ሳይሆን ለአንድ ወገን ያደላ ለራስ ብቻ ዕውቅናን የሚሰጥ የራስን ሚና ብቻ ከፍ በሚያደርግ መልኩ የሚደረጉ ትርክቶች ሙሉውን ታሪክ አይነግሩንም፡፡ ሚዛናዊ የሆነ የሁሉንም መሪዎች ቢያንስ የዓድዋን ድል በሚመጥን መልኩ ምርምር ከማካሔድ ባሻገር የጥናት ማዕከላት መቋቋም ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን የተጀመረው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እንደትልቅ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በኋላ ሰፊ ምርምሮች መካሔድ አለባቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ፡፡

ዶ/ር ፀጋዬ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You