ሀገራችን በበርካታ ድልና የአርበኝነት ታሪኮች በዓለም መድረክ በሰፊው ትታወቃለች። በዚህም ነፃነቷንና ክብሯን በማስጠበቅ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ቀንዲል ነች። ዓለም በቅኝ ገዢዎች ፉክክር በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በገባችበት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ የኖረች ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር መሆኗ በጉልህ ይነሳል። የውጭ ወራሪ ኃይል አገሪቷን ለመድፈር በመጣ ቁጥር ሁሉም ዜጋ ከዳር እስከዳር በመነቃነቅ በአንድነትና በአብሮነት በመሰለፍ ጠላትን አሳፍሮ መልሷል።
የታሪክ ምሑራን ዓድዋን “የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ፣ የመላው ጥቁር ሕዝቦችና የነፃነት ታጋዮች የድል ታሪክ ነው” ይሉታል። የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ መላው አፍሪካውያን ለነፃነታቸው እንዲተጉና አንድነታቸውን እንዲያጠናከሩ መሠረት የሆነ ታላቅ ድል ስለመሆኑም ይናገራሉ። የጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ማሳያም አድርገውም ይወስዱታል።
እኤአ በ1885 ጀርመን አገር በተካሄደው የበርሊን ኮንፈረንስ አውሮፓውያን መላ አፍሪካን በካርታ ላይ የተከፋፈሉትን በተግባር መሬት ላይ ለመቀራመት ጦራቸውን ሰብቀው፣ ስንቃቸውን ጭነውና ትጥቃቸውን አጥብቀው ያካሄዱት ዘመቻና የወረራ ጉዞ የተገታባት ዓድዋ እና እለቷ ዛሬ ድረስ በተገፉ ሕዝቦች ልብ ታትማ በአዕምሮ ውስጥ ተቀርጻ ትኖራለች።
እለቱን አስመልክቶ «ዓድዋን ለዘላቂ ልማትና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ» በሚል በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡትን የዩኒቨርስቲው ማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር በቃሉ ዋቺሶ ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ ዓድዋ ለእኛ ምንድነው? ዛሬስ ትውልዱ ላይ እንዴት ነው ሊንጸባረቅ የሚገባው?
መምህር በቃሉ፦ በዚህ ጉዳይ ሁለት አይነት ብዥታዎች አሉ። አንዱ መዘከር ወይም ደግሞ የትላንትን ብቻ አውስቶ ማለፍ ሲሆን ሁለተኛው ዓድዋ ዛሬ (አሁን) እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ነው። በመሆኑም ትላንት በአያት ቅድመ አያቶቻችን የተደረገው ድርጊት፣ የተከፈለው መስዋዕትነት እና የተገኘው ድል ዛሬ ደግሞ ይህ ትውልድ ምናልባት በደም ባይሆንም፤ ተመሳሳይ መስዋዕትነት የሚከፍልበትና የራሱን አሻራ የሚያስቀምጥበት ሊሆን ይገባል።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ትውልዱ አያት ቅድመአያቶቹ በደማቸው አኩሪ ታሪክ በመሥራት አንገቱን ቀና እድርጎ የሚሄድበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥረውለት አልፈዋል፤ ዛሬ ይህንን በደም የተገኘ ዋጋ በላብ ማጽናት ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ከተባለ ዛሬም በዚህ ትውልድ አዕምሮ ውስጥ ዓድዋን መፍጠር እና “እኔ የዓድዋ ትውልድ ነኝ” ብሎ እንዲያምን ማድረግ ያስፈልጋል።
አሁን በዚህ ወቅት የመደመር ትውልድ ይባላል፡፡ አዎ! ዓድዋ ራሱ እኮ ይደምራል፡፡ በመሆኑም ትውልዱ ትላንትና ክፉም ይሁን ደግ የተደረገው ነገር እኔንም ይገልጸኛል፤ በአያቶቼ አጥንትና ደም ውስጥ ነበርኩ ዛሬ እዚህ ደርሼ ሀገሬን እንድረከብ እነሱ መስዋዕትነት ከፍለውልኛል ብሎ ከመዘከር በላይ በሆነ መልኩ ማክበር ያስፈልጋል።
በመሆኑም ዓድዋን ስናስብ ዝም ብለን ተጨባብጠን አልያም ዘምረን ጀግኖችን አንስተንና ሐውልት አቁመንላቸው ብቻ የምናልፈው ሳይሆን ዛሬ ላይ ቆመን ዓድዋን እያሰብን ለነገ ደግሞ ትዝታ የሚሆን ነገርን ለማሳረፍ ወገብ የሚያጎብጥ አይነት አደራ የምንቀበልበትም ነው።
ሀገራችን ከሰጠችን በላይ መስጠት አለብን፤ ግን ደግሞ እንዴት ባለው መልኩ የሚለውንም በማየት በእናት ለምንመስላት ሀገራችን የሚታይ ሥራንም አስቀምጠን ለመሄድ መዘጋጀት ያለብን ዓድዋን ተንተርሰን ሊሆን ይገባል።
ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ በቀደሙት አባት እናቶቹ ቦታ ራሱን አስቀምጦ እራሱን እንዲጠይቅ ያስፈልጋል። በመሆኑም ትውልዱ አሁንም ቢሆን ከጦርነት የጸዳን ከስጋት ነፃ የሆንን ባለመሆናችን ከልማቱ ዝግጁነት ጎን ለጎን ለተንኳሾች ተገቢ ምላሽን ለመስጠትም የተዘጋጀ ሊሆን ይገባል። በዓድዋ የፈሰሰ ደም አሁንም ድረስ ትኩስ ነው፤ ይህ ዓይነቱ መስዋዕትነት የሚጸናው ደግሞ አሁን ላይ በምንፈጽመው ገድል ነው።
አዲስ ዘመን፦ በዚያ ትውልድ ውስጥ ሆኖ ራሱን የሚያይ ትውልድ እንዲፈጠርስ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጀምሮ ቤተሰብና ሌላውም ምን ዓይነት ተግባራትን ማከናወን አለባቸው ይላሉ?
መምህር በቃሉ፦ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ዓድዋን አስመልክቶ ያዘጋጀውን አይነት መድረኮች ዓድዋንና መሰል ድሎች ፋይዳቸው ምንድ ነው? የሚለውን ለትውልዱ ለማሳየት ጥሩ መንገድ ነው። በተለይም ለእኔ ዓድዋ በነፃነት ተጀምሮ በነፃነት የተጠናቀቀ ከመሆኑ አንጻር፤ ድልና ነፃነቱን በማጉላት እንዲሁም ትውልዱ ተገቢና ትክክለኛ መረጃን እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ጥሩ ጥሩውን ብቻ ሳይሆን የተቆሳሰልንባቸውንም ቦታዎች በማሳየት ለሀገር ተብሎ የተከፈለን መስዋዕትነት በመናገር ትውልዱ አንገቱን ቀና እድርጎ እንዲሄድ፤ ይህ ታሪክ የተሠራው ለእኔም ነው ብሎ እንዲያስብ ማስቻል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው።
ይህንን ታሪክ በትውልዱ ልብ ውስጥ ለማስረፅ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትልቅ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። በነገራችን ላይ ተማሪዎቻችን በምን መልኩ አስረድተን ምን ዓይነት ግንዛቤ ነው የምናስጨብጣቸው? የሚለው በጣም ሊታይ ይገባል፤ በዚህም መጀመሪያ ከመናገራችን በፊት ታሪኩን በአግባቡ መረዳት ከዛም የእኔ ታሪክ ነው ብሎ ወደውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን በራሳችን ታሪክ የተዋረደን፣ የምንሸማቀቅና የምንፈራ ትውልዶች እንሆናለን ።
አዲስ ዘመን፦ የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ድል ነው ይባላል ? በተግባር ግን ይህን ድል ከእኛ አልፈን ሌሎች እንዲደምቁበት ለማድረግ ምን ቢሠራ መልካም ነው ይላሉ?
መምህር በቃሉ፦ እኔ ዓድዋ የጥቁሮች ድል በመባሉ ራሱ ቅሬታ አለኝ፤ ለምን ብትለኝ በዛ ጦርነት ላይ ኢትዮጵያውያን ግንባር ቀደሙን ትግል ያድርጉ እንጂ ወረራውን የሚቃወሙ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች(ነጮች) ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ድሉ የጥቁር ሕዝቦች ካልን እነዛን ለእኛ ሲሉ ዋጋ የከፈሉ የሞቱ የቆሰሉ ነጮችን ክብር ማሳነስ አውቅናም መንፈግ ይሆንብኛል፤ በመሆኑም ዓድዋ የጥቁሮች ድል ነው የሚለው ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ፍትሕና ነፃነት የተደረገ የሰው ልጆች ሁሉ ድል ነው ብንለው የሚሻል ይመስለኛል።
ዓድዋ የማይቻል የሚመስል ነገር ሁሉ ተችሎ የታየበት ያለመደፈር፣ በድልና በነፃነት ራስን አክብሮ ሌሎችንም አክብሮ የመኖር ማሳያ ስለሆነ ከዓለም አቀፍ ድሎች ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው፣ በሆሊውድና በሌሎች ፊልሞች ሊታይ የሚገባው ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ተዘካሪነቱንስ በዛ ልክ እንዲሆን ለማድረግ እንደ ዜጋ ምን መሥራት አለብን ?
መምህር በቃሉ፦ ዓድዋን ለመዘከር ተገናኝቶ አንድና ሁለት ሰዓት ተወያይቶ መሄድ ብቻ በቂ አይደለም። ይህ ትውልድ ወገብ የሚያጎብጥ የቤት ሥራ የተሰጠው መሆኑን ማወቅ ይገባል። በመሆኑም እንደ አገር ትውልዱ ላይ የተጫኑ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም ዓድዋ ደግሞ ከዛ መካከል ተመዞ መውጣት የሚችል በጣም ግዙፍ ድላችን በመሆኑ ይህንን ማሻገር ይገባል። ዓድዋ የማያልቅ የተከማቸ ሀብታችን እንደመሆኑ በየቀኑ እያወጣንና እየመነዘርን ራሳችንን ለማወቅ ለመገንባት አልፎ ተርፎም ትውልድንና ሀገርን ለመገንባት መጠቀም ያስፈልጋል።
ከዝክር ባለፈ ትውልዱ በምን መልክ ይዞት ለቀጣዩ ትውልድ ያሳልፈው? የሚለውን ፖለቲካ፣ ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለይ ተጨማሪ ፋይዳው ላይ መስራት ይገባል። ይህም መከባበራችንን፣ ነፃነታችንን እና ወንድማማችነታችንን ለዓለም ለማሳየትና ለማሳወቅ ትልቅ መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ እኔ የዓድዋ ነኝ ከማለት ይልቅ የልዩነት ትርክቶች እየሰፉ ነው፤ ይህን ከማረም አንጻር ምን መሠራት ይኖርበታል ይላሉ?
መምህር በቃሉ፦ የዓድዋ ታሪክ የዘመናት ርቀቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬም ላይ እንዳለው ሁኔታ የፖለቲካዊና ሌሎች ዝንባሌዎቻችንን ተንትነን፣ ይህ ብሔራዊ ማንነታችን ነው ብሎ መቀበል ያስፈልጋል። ዜጎች ምንም ይሁን ምን ሁልጊዜ በሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ አንድ ሆነን ድሉ የእኔ ነው ብለን መቀበል ይጠበቅብናል።
አንድ ሰው ዓድዋ የእኔ ነው ብሎ ባሰበና በተነሳ መጠን በተሠማራበት መስክ ላይ ትውልዱን በመቅረጽና በማነጽ በኩል የበኩሉን መወጣት ይችላል። ትውልዱ ብዙ የሚጫኑት ዘመን አመጣሽ ችግሮች ስላሉበት አሁን ላይ አጎንብሶ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ትንሽ ብቻ ሥራ ከተሠራበት ታሪኩን በማወቅና በመጠበቅ በኩል ትልቅ ሚና ሊወጣ ስለሚችል በዚህ ላይ ሁላችንም ልንሠራ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
መምህር በቃሉ፦እኔም አመሰግናለሁ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም