«ታሪክን ጠለቅ አድርጎ ለተገነዘበ ሰው ዓድዋ ብዙ ምስጢሮችን ያዘለ ነው»  ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር) የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ

ዛሬ 128ኛው የጥቁር ሕዝቦች ድል በደማቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበርበት ታላቅ ዕለት ነው፡፡ እለቱ ለነጻነት እና ለፍትህ የተከፈለ አንጸባራቂ ድል ከመሆኑ አንጻር እስካሁንም አቻ ያልተገኘለት ሆኖ ዘልቋል። ድሉ የጥቁር ሕዝቦች አንገት ቀና ያለበት፤ ለኢትዮጵያውያንና ለመላ ጥቁር ሕዝብ የማይረሳ ቀንና ታላቅም ኩራት የፈጠረ ነው፡፡ ከዚህ ታላቅ ድል ጋር ተያይዞ አዲስ ዘመን ከተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጎ ተከታዩን አጠናቅሯል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የተመረቀው የዓድዋ መታሠቢያ ሙዚየምን ሲያዩ እንደ አንድ የታሪክ ተመራማሪ ምን ተሰማዎት?

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር)፡- የታሪክ ተመራማሪ እንደመሆኔ የዓድዋ መታሠቢያ ሙዚየም ለምረቃ በመብቃቱ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከታሪክ አንጻር አገራችን እየገጠማት ያለ አወዛጋቢ ነገር ባለበት በዚህ ጊዜ ታሪክ ያለው ተቋም ተገንብቶ ለምረቃ በመብቃቱ ታላቅ ኩራት ነው፡፡ ይህ መሆኑ ለታሪክ ያለንን ክብር እና ለታሪክ መስጠት የሚገባንን አክብሮት መስጠታችንን የሚያንጸባርቅ ሙዚየም ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

የሙዚየሙ ሕንጻ በአንድ በኩል ከ128 ዓመት በፊት በተደረገው ጦርነት ላይ ያገኘነውን ድል ለመያዝ ሲባል የተዘጋጀ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከ128 ዓመት በፊት እና ከ128 ዓመት በኋላ ያለው በተለይ የድህረ ዓድዋ የሚባለው ምን መምሰል አለበት የሚለውን ያጠቃለለ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የዓድዋ ድልን የሚገልጹት እንዴት ነው?

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር)፡– የዓድዋ ድልን ታሪክ ጠለቅ አድርጎ ለተገነዘበ ሰው ዓድዋ ብዙ ምስጢሮችን ያዘለ ነው፡፡ ዓድዋ ለምሳሌ አንድ አራት የጣሊያን ብርጌድና ከመቶ እስከ ሁለት መቶ ሺ የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን ሜዳ ላይ ገጥመው ተዋግተው ኢትዮጵያውያኑ ያሸነፉበት ብቻ አይደለም። ዓድዋ ብዙ ተምሳሌትነት አለው። በገዛ መሬታችን ዓድዋ ላይ ከሩቅ አገር የብስንና ባሕር አቋርጦ የመጣውን ጠላት የተዋጋንበት የእኛን ብቻ ነጻነት ለማስከበር ሳይሆን በዚያች ጊዜ የተንሰራፋውን የቅኝ አገዛዝ ስርዓት የገረሰስንበት ነው፡፡ ጣሊያን ወደአገራችን የመጣው ቅኝ አገዛዙን እኛም ላይ ለመጫን ነበር፡፡ ጣሊያን እኛ ዘንድ የመጣው ሌሎቹን አውሮፓውያኑን ማለትም ጀርመንን፣ ፈረንሳይን፣ እንግሊዝን ለመምሰልም ጭምር ነው፡፡

የዓድዋ ድል የመጣው አውሮፓውያኑ በዚያን ጊዜ ‹‹ካለእኛ ማንም ኃያል የለም፤ እኛ ነጮች ነን›› ባሉበት ጊዜ እና ብዙ የአፍሪካ አገሮችን በቁጥጥራቸው ስር ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ድል ትልቅ ተምሳሌትነቱ ‹‹ቅኝ አገዛዝነት የዘላለም አይደለም›› የሚለውን መልዕክት ማስተላለፉ ነው፣ የዚህ እውነታ የመጨረሻውም የመጀመሪያውም ምዕራፍ የተጻፈበት ነው፡፡

ከዚያም በፊት ሆነ ከዚያ በኋላ ቅኝ አገዛዝን ለማጥፋት ብዙ ንቅናቄዎች ነበሩ፡፡ ዓድዋ ደግሞ ይበልጥ አበረታች ድል ሆናቸው፡፡ ከዚህ የተነሳ ዓድዋ በጣም ትልቅ ድል ነው፡፡ የወቅቱ አሸናፊነት እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በነበረው ርዕዮተ ዓለም የነጭ የበላይነትን ካየነው ከፍ ያለ ነው፡፡

አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ለመሸነፋቸው ምክንያቱ እንግሊዞች ያሏቸው ጠብመንጃ እርሳቸው ስለሌላቸው ነው፡፡ እነ ፊት አውራሪ ገብርዬ በዚያን ጊዜ የነበረው ጠብመንጃ እጃቸው ላይ ስለወደቀ ነው። አጼ ምኒልክ ይህንን ተረድተው የራሳቸውን ፋብሪካ አቋቁመው ባይሰሩትም፣ ከፈረንሳይ፣ ከጣሊያን፣ ከቱርክ፣ ከራሺያ መሳሪያም ጥይትም ገዝተዋል፡፡ ሁሉን ነገር አዘጋጅተው ኢትዮጵያውያኑ በመረጡት ቦታ ሔደው ተዋግተው ድል አድርገው ታሪክ ጽፈዋል፡፡ ከዚህ የተነሳም አጼ ምኒልክ በጣም የታወቁና የተደነቁ ንጉስ መሆናቸውን ዓለም ሁሉ ሊያውቀው ችሏል፡፡

በወቅቱ የተገኘው ድል ያኮራው አፍሪካውያኑን ብቻ ሳይሆን ጥቁር ሕዝቦችን ጨምሮ ብዙዎቹንም ነው፡፡ ካራቢያን ደሴቶች፣ በደቡብ አሜሪካ በቅኝ አገዛዝ ስር የነበሩት ሁሉ ብዙዎቹ ነጻነታቸውን ያገኙት ከዛ በኋላ ነው፡፡ እርግጥ ትግሉን ያካሔዱት ራሳቸው ናቸው፡፡ በጥቅሉ ግን ‹‹ኢትዮጵያ ካደረገችው እኛም እናደርገዋለን!›› በሚል ተበረታትተዋል፡፡

ለኛም የዓድዋ ድል በዓለም ላይ እውቅና አምጥቶልናል፡፡ ከዛ በፊት ግን ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ዓለም የሚያውቃት በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ስሟ ከ40 ጊዜ በላይ በመጠቀሱ ነው፡፡ ይህንን ኢትዮጵያ በመባል የሚታወቀውን ስም ጥቁር አሜሪካውያኑና ካረቢያን ደሴት ውስጥ የነበሩ አፍሪካውያን ተጠቅመውበታል፤ በባርነት ቀንበር ስር በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያኒዝም (ኢትዮጵያዊነት) የሚባል እንቅስቃሴ በመፍጠር ነጻ ለመውጣት ትግል አድርገውበታል፡፡

በዚህም ተመስርተው የራሳቸውን ነጻ የሆነ ቤተክርስትያን ለመመስረት ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ከመታወቅ በተጨማሪ በዓድዋ ድል ለመታወቅ በቃ፡፡ ከዚህ የተነሳ የዓድዋ አስተሳሰብ ዓለም አቀፍ የሆነበት እድል ተፈጠረ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ያልወደቀችበት ምስጢሩ ምንድን ነው ይላሉ?

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር)፡- የእኛ ማሸነፍ እጅግ በጣም ብልህ እና አስተዋይ የሆኑ የአመራር ኃይሎች በመኖራቸው ነው፡፡ እነዚህ አመራሮች ጦሩን አደራጅተውና ዘመቻውን አስተባብረው የመሩ ናቸው፡፡ በተለይ ጠላት ደግሞ ምን አይነት መሳሪያ እንደያዘ፣ ምን አይነት አጃቢ እንዳለውና መሰል የጦር ስትራቴጂያቸውን ሁሉ አጥንተው የመጨረሻ የውጊያ ስልት አውጥተው በመንቀሳቀሳቸውም ጭምር ነው። በወቅቱ ያወጡት ስትራቴጂ አገራችንን ባለማስደፈር የኢትዮጵያን ነጻነት ማስከበር ነው፡፡ የመጣውን ጠላት እንዴት ልንመልሰው እንችላለን በሚል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው፡፡

በወቅቱ አጼ ምኒልክ፣ ወራሪውን ጣሊያን ለመዋጋት የሄዱት በአገር ውስጥ የነበረውን ችግር ከፈቱ በኋላ ነው፡፡ በወቅቱ የበመጨረሻ አስቸግሯቸው የነበሩት የወላይታው ንጉስ ካዎ ጦና ናቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋር ያደረጉት ትግል ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በደጅ ያለው የጣሊያን ወራሪ አንድ ሁለት ሶስት ቦታ ገብቶ ይዞ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ኢትዮጵያ በማበሯ ሊለቅ ችሏል፡፡

በቅድመ ዓድዋ ወቅት የአገር መስፋፋት ነበር። በዚያን ወቅት ግብር እቀበላለሁ ያለ በአገዛዙ ስርዓት ውስጥ ገብቶ አገዛዙ እንዲቀጥል አደረገ፡፡ አሻፈረኝ ያለው ደግሞ ጦርነት ገጥመው ያስገብሩት ነበር፡፡ አጼ ምኒልክ፣ ወደ ዓድዋ የዘመቱት ተስማምቶ የገባውን መግባቱን ካረጋገጡ በኋላ “ድንበር ጠብቅ” ብለው ነበር፡፡

ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ዋናው የማሸነፍ ምስጢሯ፤ የመናበብ ስራ በመኖሩ ነው፡፡ አጼ ምኒልክ አንድ ያደረጉት ነገር ቢኖር ሁሉን በውይይት ማስኬድ በመቻላቸው ነው፡፡ እርሳቸው ኢትዮጵያን ብቻቸውን አልገዙም፡፡ አጼ ምኒልክ የገዙት ከባለሟሎቻቸው ጋር በመሆን ነው፤ በተለይም ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በመሆን ነው። ሰውን በክተት አዋጅ ከኢትዮጵያ ሊያሰባስቡ የቻሉትም በጥበብ ነው፡፡

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ስለኢትዮጵያዊነቱ የተገነዘበው ነገር አለ፡፡ ከቋንቋው፣ ከኃይማኖቱ እና ከዘሩ አልፎ የተገነዘበው ትልቅ ነገር አለ፡፡ አጼ ምኒልክም፣ የክተት አዋጅ ሲያውጁ ለሁሉም በሚገባ ቋንቋ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑም ያንን አዋጅ ተቀብለው ገሚሱ ቤተሰቡን በሙሉ ይዞ፣ ገሚሱ ደግሞ ስንቁን ይዞ፣ ሌላው ደግሞ ያለ የሌለ ንብረቱን ጭምር ይዞ በመዝመቱ ድሉን ሊቀዳጅ ችሏል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩና አንድ ሲሆኑ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዓድዋ የታየ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ትናንት ቅኝ ገዥዎችን በብርቱ ክንዷና ጥበቧ ያሸነፈች አገር፤ አሁን ላይ ድህነት እና ኋላቀርነትን ማሸነፍ ለምን አቃታት? ይህንን ችግር ለመሻገር መፍትሔው ምን መሆን አለበት?

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር)፡- ይህ ዋናውና አንገብጋቢው ጥያቄ ነው ብዬ አስባለሁ። የዓድዋን ጦርነት ድል ማድረግ የተቻለው ጌታውም ሎሌውም፣ ባላባትም አሽከርም አንድ ሆነው ተዋግተው ነው፡፡ ዓድዋ ላይ የተደረገው ድርጊት ኢትዮጵያን ቀይሯታል፡፡ ኢትዮጵያን የቀየረውና ድል የነሳው በተደረገው መስዋዕትነት ነው፡፡ መስዋዕት የሆነው እንዳልኩሽ አሽከሩም ሎሌውም ነውና አሽከሩም በአሽከርነቱ ሎሌውም በሎሌነቱ ሊቀጥል አይችልም፡፡

ድሉን ካገኘን በኋላ ግን ፈጣን በሆነ ሁኔታ ወደፊት መራመድ ነበረብን፡፡ አጼ ምኒልክም ሰብሰብ አሉ፤ መኳንንቱን በያሉበት ሔደው እንዲገዙ አደረጉ፡፡ የጭሰኝነት ስርዓቱም ይቀጥሉ አሉ፡፡ ይህ በመሆኑ አካሄዱ ወደኋላ ጎተተን። ”የነብር ጭራ አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም” በሚል መንፈስ ወደፊት ቀጥለው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ልክ እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ማሊዥያ፣ እንደብራዚልና መሰል አገሮች እንሆን ነበር፡፡ ይህ የእኔ ግምት ነው፡፡

በመቀጠል ኢትዮጵያን የመሩ አጼ ኃይለስላሴን ጨምሮ ሌሎቹም መሪዎች እንደ አጼ ምኒልክ አይነት የየራሳቸው የሰሩት ስራ ይኑር እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አላመጡም፡፡ ደርግም መጣና መሬት ላራሹ አለ፡፡ ይሁንና መሬት ላራሹ ተብሎ፤ መሬት የመንግስት ሆኖ አገኘነው። መሬት የመንግስት ካድሬዎች መጠቀሚያ ሆነ እንጂ አራሹ የመሬት ባለቤት ሆኗል ብለን መናገር አንደፍርም። በመሆኑም በኢኮኖሚ እንዳናድግ የጎተቱን እነዚህና መሰል ምክንያቶች ናቸው፡፡

መንግስት፤ እንደ አንድ አገረ መንግስት አንድ የሆነ ደረጃ ላይ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት። አደገኛ የሆኑ ርምጃዎችንም ሆነ ውሳኔዎችን ማሳለፍ መቻል አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት በለጸጉ የተባሉ አገራት ያንን በማድረጋቸው ነው ዛሬ ላሉበት ደረጃ የበቁበት፡፡

ጣሊያን እንኳ ከዓድዋ ሽንፈት ተምራ 40 ዓመት የጦር መሳሪያዎችን ራሷ ማምረት ጀመረች። አውሮፕላኑን፣ መትረየሱንም ሆነ መድፉን፣ ታንኩንና ሌላውንም የመሳሪያ አይነት አዘጋጅታ በምንም አይነት እኛ እንጂ ኢትዮጵያ ማሸነፍ የለባትም ብላ ለሁለተኛ ጊዜ ኃይሏን አስተባብራ መጥታለች ፡፡

እርግጥ ነው፤ አጼ ምኒልክም ሆኑ አጼ ኃይለስላሴ ብዙ አስገራሚ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ ይሁንና አጼ ኃይለስላሴ ለረጅም ዘመን የባላባት ስርዓት አስከባሪ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የነበሩ ተማሪዎች ስርዓቱ መቀጠል የለበትም በሚል ተነሳሽነቱን ወስደው ስርዓቱ እንዲፍረከረክ አደረጉ፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታዩ ግን መሪዎቻችን ቁጥብ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡

ወደመፍትሔው ሲመጣ የመጀመሪያው ዓድዋን ያሸነፍነው ለምንድን ነው? ከተባለ ጥሩ አመራር ስለነበረን ነው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ የአገር ፍቅር ስለነበረው ነው፡፡ ሕዝቡ አገር ምን ማለት ነው? የሚለውን ተገንዝቧል፡፡ በዚያን ጊዜ አብዛኞቹ የዘመቱትና ሕይወታቸውን የሰውት ደግሞ በእድሜ ደረጃ ሲሰላ ከ18 እስከ 30 የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው። እነዚህም ወጣቶች አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ነጋዴዎች እና በዛ የወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለው ወጣቱ ኃይል በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው? ብሎ መጠየቁ አግባብ ነው፡፡ ምላሹ በጣም ቀላል ነው፤ ምክንያቱም እርስ በእርሳችን እየተናቆርን ነው፡፡ እሱ ደግሞ የሚያሳየን በዚያን ጊዜ 18 ዓመት እድሜ ላይ ያለው ወገን የዓድዋ የክተት አዋጅ ሲታወጅ እንዴት መረዳቱን አገኘ? ከምንም በላይ አገር መቅደም አለባት እንዴት አለ? በዚያ እድሜ ክልል ውስጥ ያለው ያ ሰው ለአገሬ ሉዓላዊነት እሰዋለሁ ብሎ ሲወስን ምን አይነት ብልህነት እና አስተዋይነት ነው? ብሎ ለመጠየቅ የሚያስገድድ ነው፡፡ ምን አይነት የአገር ፍቅር ነው? ማለትም ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያጣነው ያንን ነው፡፡

አሁን ላይ የሌለን ነገር ቢኖር እሱ ነው፡፡ የአገር ፍቅር ምን ማለት ነው? የሚለው ግንዛቤ ከሌለንና የአገር ፍቅር ግድ ብሏቸው መስዋዕት ከከፈሉ ወገኖች ታሪክ መረዳት ካልቻልን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ዝም ብለን በአፋችን አንድነት አንድነት ብንል የምንመኘው አንድነት ሊመጣ አይችልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአብሮነት መቆም ለአገር እድገት ዋና መሰረት ነው፤ በዓድዋ ዘመን የነበረውን አንድነት ወደአሁኑ ትውልድ በማምጣት ለአገር እድገት እንዴት መጠቀም ይቻላል? ከዚህ አኳያ ለወጣቱ ምን ይላሉ?

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር)፡– በዓድዋ ዘመን የነበሩ ሰዎች ከፍተኛ ትዕግስት ያላቸው ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚያን ዘመን ከጥቅምት አንስተው እስከ የካቲት ወር ድረስ በባዶ እግራቸው ተጉዘው፣ የየራሳቸውን ስንቅ ተሸክመው፣ የመዋጊያ ጠብመንጃ አንግበው ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡

በተለይ ሴቶቹ ደግሞ የማብሰያ ቁሳቁስ ይዘው በቀን ስምንት፣ ስምንት ሰዓት ይጓዙ የነበሩ ናቸው። መጓዝ ብቻ ሳይሆን በየደረሱበት ምግብ ማሰናዳቱ ኃላፊነታቸውም ነበር፡፡ አካባቢውን ለቅቀው ሲነሱ እንዲሁ ሁሉንም ቁስ ለረጅም ሰዓት ተሸክመው ይሔዱ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ተግባር ለመፈጸም ከፍተኛ ትዕግስትን ይጠይቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት ስናጤን ደግሞ አሁን ያለነው ትውልዶች በትንሽ ነገር ብዙ ጥቅምን ማግኘት የምንሻ ነን፡፡ የአንድ አገር ሕዝብ ሆነን አንዳችን አንዳችንን የምናየው በጠላትነት ነው፡፡ አንዳችን አንዳችንን ለማጥፋት የምንጠቀምበት ስልት ከዚህ ቀደም ታሪካችንን ውስጥ የሌለ ነው፡፡

እኔ ሳስተውል አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የግል ጥቅሙን አሳዳጅ መብዛቱ ነው። ይህ በግለሰብ ሆነ በቡድን ደረጃ የሚስተዋል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየጎዱን ያሉት እነዚህ ናቸው፡፡ ስለዚህ መረባረብ ያለብን እዚህ ላይ ይመስለኛል፡፡ አሁን አሁን አዲስ ያመጣነው ነገር ቢኖር በብሔር ራስንና ማንነትን መከለል ነው፣ በመካከላችንም የማይገፋ ግድግዳ እየገነባን ነው ማለት ነው፡፡ በጥቅሉ ግን እኔ ሳስበው የጥቅም ፍላጎት ታሪክን ወደማዛባት እያደረሰን እርስ በእርስ እንዳንግባባ እያደረገን ነው፡፡ ጥቅም ፈላጊዎች ደግሞ ሕዝቡን ስሜታዊ እንዲሆን የሚገፋፉ ናቸው፡፡

ሌላው ወጣቱ የሚማረው ትምህርትም መጤን አለበት ባይ ነኝ፡፡ የእኛ ትምህርት ባሕል ተኮር አይደለም፡፡ የራሳችን ታሪክ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ሁል ጊዜ ገልባጮች ነን፡፡ ስንገለብጥ ደግሞ በስርዓት አንገለብጥም። ቋንቋም ስንማር በስርዓት አንማረውም፡፡ የራሳችንንም በስርዓት አንይዘውም፡፡ ስለዚህ የውጭ አገር ዜጎች እየመጡ እየተጫወቱብን ለመሔድ ይሞክራሉ፡፡ እዳ በእዳም የሆንነው ለዚያ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ችግሮችን ስርዓት ባለው መንገድና ትዕግስት ባለው መንገድ መፍታት ይጠበቅብናል፡፡ ሕዝብ ተኮር የሆነ ፖሊሲ እያወጣን ፤ ሕዝቡ ተሳታፊ እንዲሆን እያደረግን መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ዝም ብሎ ስራ ተሰርቶ ሕዝብ መጥቶ እንዲያጨበጭብ ማድረጉ በቂ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ያንን ሁኔታ ማስተካከል ይኖርብናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ትውልዱ የዓድዋን ማንነት እንዲላበስ ምን ማድረግ ይኖርብናል ?

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር)፡– እኛ/ትውልዱ የዓድዋ ማንነት መላበስ ያቃተው ወይም የዓድዋ ልጆች መሆን ያቃተው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው የዓድዋን ድል እንደ ባለቤትነት አለመውሰድ፣ አለመያዝ እና አለመቀበል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከአንድነት ይልቅ የእኔነት መንፈስ በመጉላቱ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በዓድዋ ጊዜ አንድነትና ኅብረት እንደነበረው ዛሬ ላይ ያለመታየቱ ምስጢር የትብብር አለመኖር ነው፡፡ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ የውጭ ጠላት መጣ፤ ያንን የውጭ ጠላት ደግሞ “አገሬን አላስደፍርም” በሚል የክተት አዋጅ ታወጀ፤ በዚያን ሰዓት ከሁሉም አቅጣጫ በመምጣት ጠላትን ድል ማድረግ ተቻለ፡፡ በዚያ የአብሮነት ድርጊታቸውም ኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስ እንዳላቸው ማስመስከር ተቻለ፡፡

አንድነት ላለመኖሩ ዋና ችግር እርስ በእርሳችን ያለመስማማታችንና ያለመግባባታችን ጭምር ነው፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ መሰማራታችን እና ታሪካችን በአግባቡ ያለመገንዘባችን ነው። ታሪካችንን በአግባቡ ብንገነዘብ ኖሮ ቶሎ ወደእርቅና ወደሰላም ብሎም ወደመግባባት እንመጣ ነበር፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት እያየን ያለነው ሽኩቻ ነው፤ ይህ ሽኩቻ ደግሞ የግል ጥቅም ከማሳደድ ፍላጎት የመነጨ እንጂ የአገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም፡፡፡

መፍትሔው ሊሆን የሚችለው፤ የቀድሞ ታሪካችንን ወጣቱ በአግባቡ ይረዳው ዘንድ ግንዛቤ ማስያዝ ነው፡፡ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ድል ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ናቸው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሁሉም አቅጣጫ የመጡና የተለያየ ብሔር እና ኃይማኖት ያላቸው ናቸው፣ የተዋደቁትም ለጋራ አገራቸው ሉዓላዊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነታቸውንም በሚገባ የተገነዘቡ ዜጎች ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው የኢትዮጵያዊነት ግንዛቤ ዛሬ ላይ ግን የተሸረሸረ ሆኗል። ይህ ጉድለት በመሆኑ መሟላት አለበት።

በሌላ በኩል ከመንግስት የሚጠበቀው የአገር ፍቅርን የሚቀሰቅስ፣ የሚያፈልቅና የሚያመነጭ አቅጣጫን ሁል ጊዜ መስጠት መቻል ነው፡፡ በተለይ ዜጋው ከእርስ በእርስ ጦርነት የሚወጣበትን መንገድ ማበጀት የግድ ነው፡፡ ይህንን የእርስ በእርስ ግጭት አካሔድ ማስቆም ከመንግስት የሚጠበቅ ነው። እንዲህ ሲባል ጉዳዩ የመንግስት ብቻ ነው ማለት ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሰላም መስፈን ማሰብ እንዳለበት አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፤ ለሁሉም የምትበቃ ናት፡፡ በመካከል ልዩነት የሚኖር ከሆነ ያንን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ይህም በመወያየትና በመነጋገር ሊከናወን የሚችል ነው፡፡ ልዩነትን በውይይት ለመፍታት መሞከርም ትልቅነት ነው፡፡

አንድነታችን በአንድም ይሁን በሌላ መጠበቁ አይቀሬ ነው፡፡ ሰላም፣ ዋጋ አስከፍሎን ከመምጣቱ በፊት ግን ከወዲሁ አንድነታችንን ብንጠብቅ ተመራጭ ነው፡፡ ያንን መስዋዕትነት ከመክፈላችን በፊት እኛው ራሳችን ለአንድነታችንም ሆነ ለሰላማችን ዘብ መቆም አለብን፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሰላም አገሩን ለመገንባት እና አገሩን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያልምና የሚጥር ነው፡፡ ለዚህ የታሪክ ምስክርነትም አለ፡፡ ሁሉም ጨለማ ነው ብሎ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡

መልካሙ ነገር እንዲመጣ እና ሰላም እንዲሰፍን ዳር ቆሞ መጠበቅ ግን አያዋጣም፡፡ ሁሉም የየበኩሉን ድርሻ መውሰድ ይኖርበታል። ሁሉም ለሰላም ያለውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፡፡ አንድነቱና ኅብረቱ ይመጣ ዘንድም ኃላፊነት ወስዶ የድርሻን መወጣት ያስፈልጋል፡፡

ዜጋው፣ በጦርነት የሚመጣ ሰላም እና አንድነት እንደማይኖር መረዳት ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ጦርነት መልሶ ቁርሾ ውስጥ የሚከትና ቂም የሚያስይዝ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ እየበጠበጠን ያለው ከ30 እና ከ40 ዓመት በፊት የተቋጠሩ ቂሞች ናቸው፤ እዚህ ላይ ብልሆች ልንሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ትዕግስት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ዓድዋ እና ፓንአፍሪካ ኒዝምን የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው ይላሉ?

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር)፡– ዋናው ቁም ነገር ሁለቱም በታሪክ የተሳሰሩ መሆናቸው ነው፡፡ ዋናው ጠቃሚ የሆነው ጥያቄ ለመተሳሰራቸው ምን ማስረጃ አለ? የሚለው ነው፡፡ ዓድዋ የተካሔደው በእኛ በየካቲት ወር ሲሆን፣ በፈረፈንጆች ስናሰላው ደግሞ ያኔ መጋቢት ይገባል፡፡ በእኛ 1888 ዓ.ም በእነርሱ ደግሞ እኤአ 1896 ነው፡፡ እርሱ በተካሔደ በአራተኛ ዓመት እኤአ በ1900 የመጀመሪያ ፓንአፍሪካን ኮንፈረንስ ለንደን ላይ ተካሂዷል። ይህ ኮንፈረንስ ከዓድዋ ድል ጋር ምን ምን ግንኙነት አለው? ይበሉ እንጂ ግንኙነት አለው።

የፓንአፍሪካ እንቅስቃሴ ጥልቀት ሊኖረው የቻለው እና ተፋፍሞ እንደ አፍሪካ አንድነት አይነት ድርጅት ሊፈጠር የቻለው በተለይ ኢትዮጵያ ከ1928 ዓ.ም እስከ 1935 ዓ.ም የጣሊያን ወረራ በተካሄደበት ወቅት ወረራውን በመቃወም የተነሱበትና ከኢትዮጵም ጋር የነበራቸው ቅርበት በጣም የዳበረበት ጊዜ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ፓንአፍሪካኒዝም በጣም ጠንካራ የሆነበት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሁል ጊዜ ተባባሪያችን ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር) ለሰጡን መረጃ ከልቤ ላመሰግንዎ እወዳለሁ፡፡

ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You