ለጋራ ትርክቶቻችን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ብሔራዊ አንድነታችንን እናጠናክር

የአንድ ሀገር ህልውናም ሆነ ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወሰነው በዛች ሀገር ሕዝቦች ነባራዊ እውነታ እንደሆነ ይታመናል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ይህንን ታሪካቸውን ለማስቀጠል በትውልዶች መካከል በሚኖረው ቅብብሎሽ ዙሪያ ሰፊ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ህብረ ብሔራዊነትን የተላበሱ፤የተለያዩ ሃይማኖቶች ፣ ባህሎች እና ማንነቶች ያሉባቸው ሀገራት ሕዝቦች ፣ ዘመናትን የተሻገሩባቸውን እሴቶቻቸውን በተደራጀ መንገድ ለትውልዶች የሚያስተላልፉበትን ተጨባጭ እውነታ መፍጠር ካልቻሉ፤ በየዘመኑ ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶች ሀገራዊ ህልውናቸውን ስጋት ላይ ሊጥሉ ይችላሉ።

በተለይም እንደ ሀገር አጽንተው ሊያቆሟቸው የሚችሉ የጋራ ትርክቶቻቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ፣ እነዚህን የጋራ ትርክቶቻቸውን በትውልዶች ልብ ፣ አእምሮና መንፈስ ውስጥ መጽናት ካልቻሉ፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸው የማይቀር ነው ።

ይህ እውነታ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት እንደ ሀገር ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሰላምና የመረጋጋት ፈተና ሆኖ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። ከዛም አልፎ ዛሬ ላይ ለጀመርነው አዲስ የለውጥ ጉዞም ዋነኛ ተግዳሮት በመሆን ወደ ኋላ እየጎተተን፤ አለፍ ሲልም የማንነት መደበላለቅ እየፈጠረብን ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድም ለወል ትርክቶቻችን በቂ ትኩረት መስጠት አለመቻላችን፤ ከዛም ባለፈ በትርክቶቹ ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ አለመድረሳችን፤ የትላልቅ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ትርክቶች ባለቤት ሆነን፤ እራሳችንን በዛ ልክ መግለጥ የሚያስችል ማንነት መፍጠር ሳንችል ቀርተናል።

ለዚህ ደግሞ ትልቁ ማሳያ የዓድዋ ድል ነው ።ይህ ድል የቀደሙት አባቶቻችን ለነጻነትና ለፍትህ የከፈሉት ትልቅ አንጸባራቂ ድል ነው። ለድሉ ያበቃን የነፃነትና የአልገዛም ባይነት መንፈስም በጭቆና ቀንበር ውስጥ ለነበሩ የዓለም ሕዝቦች እኩልነትን ያወጀ የነፃነት ማነቃቂያ ደውል ነው። እኛንም እንደ ሕዝብ እና ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የነፃነት ሰንደቅ ያደረገን ነው።

ይህ በብዙ መስዋእትነት በደም የተጻፈ የአባቶቻችን የተጋድሎ ታሪክ፤ ለነፃነትና ለፍትሕ ቀናኢ በሆኑ ሕዝቦች ዘንድ ከፍ ያለ ከበሬታን ቢያጎናጽፈንም፤ እኛ ግን በብዙ መስዋእትነት ለተጻፈው ታሪካችን ተገቢውን ከበሬታ በማጣታችን ባልተገቡ የልዩነት ትርክቶች ባልተገባ የታሪክ ምእራፍ ውስጥ እንገኛለን። ዛሬ ላይ እየተሠራ ያለው ዘርፈ ብዙ ተግባርም ይሄንን የተዛባ ትርክትና ሂደት ለመለወጥና የተባበረ ማህበረሰብን ለመፍጠር ነው።

ዓድዋ እንደ ሀገር ለዘመናት የዘለቀው የሀገረ መንግሥት ታሪካችን ምስጢር አካል ነው። ስለ ሀገር ያለን ፍቅር ፣ ለነፃነትና ለፍትህ ያለን ቀናኢነት ተጨባጭ መገለጫ ነው፤ የትኛውም ዓይነት ልዩነት ብሔራዊ አንድነታችንን ሆነ የሀገረ መንግሥት ታሪካችንን የሚገዳደር አቅም እንደሌለው ያመላከተ ነው።

የድሉ ምስጢር ከሁሉም በላይ በተደመረ ሀገራዊ ማንነት፤ ፈተናዎችን በአሸናፊነት የመወጣት እሳቤ ነው። የዚህ እሳቤ መሰረቱ ጥልቅ የሀገር ፍቅር ፣ ለፍትህና ለነፃነት የተገዛ ማንነት ፣ ለሀገራዊ ነገዎች እና ለመጪው ትውልዶች የተሻለ እጣ ፈንታ ከመሻት የሚመነጭ ትውልዳዊ ኃላፊነት ነው።

ይህ ኃላፊነት የሚመነጨው እንደ ትውልድ ትናንቶችን በተገቢው መንገድ አውቆ ከመረዳት፣ ዛሬን በትናንት መሠረት ላይ በመገንባት ፣ ነገዎችን በጊዜ ሂደት ሙሉነት አጣጥሞና አቻችሎ ማሰብና መንቀሳቀስ ሲቻል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ በየዘመኑ መጥቶ የሚሄደው ትውልድ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል።

የዛሬውን የዓድዋ በዓል ስናከብርም፤እንደ ትውልድ ለትናንት የጋራ ትርክቶቻችን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፤ ብሄራዊ አንድነታችንን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል። ትናንትን በትናንት ዓይን እያየን ፤ በዛሬ መነፅር ልንረዳው ያስፈልጋል ።ለዚህ ደግሞ እንደ ትውልድ ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልገናል።

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You