‹‹ትውልድ የገጠመውን የሥነ-ልቦና ወረራ የሀገሩን ታሪክ በማወቅ ሊወጣው ይችላል ›› – ልጅ ጀርሚያስ ተሰማ እርገጤ  የፊትአውራሪ ተሰማ እርገጤ ልጅ

ልጅ ጀርሚያስ ተሰማ እርገጤ ይባላሉ። በጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በታሪክ ኃላፊነት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ለሰባት ዓመታት ያህል በኃላፊነት አገልግለዋል። በአሁን ሰዓት ደግሞ የኢትዮጵያን የጀግንነት እና የአርበኝነት ታሪክ ከሚያጠኑ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የጥናት ሥራ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ ።

የዛሬው እንግዳችን ልጅ ጀርሚያስ ተሰማ እርገጤ የቤተሰቦቻቸውን ታሪክ በዓድዋ ታሪክ ለእሳቸው ያለውን ትርጉም እና ወጣት ትውልድ እንዴት አድርጎ የሀገሩን ሉዓላዊነት መጠበቅ ይገባዋል። በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን አካፍለውናል ።

አዲስ ዘመን ፡- የአርበኛ ልጅ እንደመሆንዎ ወደኋላ ተመልሰው የአባትዎን እና የአያትዎን የአርበኝነት ታሪክ ቢነግሩን?

ልጅ ጀርሚያስ፡- ወደኋላ መለስ ለማለት የደጅአዝማች ተሰማ እርገጤ አባት ባሻ እርገጤ በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት የግቢው መቶ አለቃ ነበሩ። የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ለመውረር እና ቅኝ ግዛት ለማድረግ ጦር አሰናድቶ ሲመጣ ከዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በተላለፈው የክተት አዋጅ በታላቁ የዓድዋ ጦርነት ሲዘምቱ የእሳቸው ልጅ የሆኑት የእኔ አባት ስመጥር ቀዳሚ ጀግና ፊታውራሪ ተሰማ እርገጤ በጊዜው ወጣት መኮንን ሆነው በዘመኑ የነበረው ‹‹የጎምላ ደም›› ለየት ያለ የጦር ቡድን ውስጥ መቶ አለቃ ሆነው በቤተመንግሥት ውስጥ አገልግለዋል ።

ሽንፈቱን ያላመነው የጣሊያን ጦር በናቀው የጥቁር ሕዝብ በመሸነፉ ከ40 ዓመታት ያክል ጊዜ ሲሰናዳበት እና ለበቀል ሲዘጋጅ ቆይቶ ተመልሶ ለወረራ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አባቴ ደጅአዝማች ተሰማ እርገጤ በማይጨው ጦርነት ከወንድማቸው እስጢፋኖስ እርገጤ እና ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው ዘምተዋል። በማይጨው ሰፍሮ የነበረው የጣሊያን ጦር ውጊያ በሚያደርግበት ሰዓት በኢትዮጵያውያን አርበኞች እና ተዋጊዎች ሽንፈት እየገጠመው መሆኑን የተረዳው የጣሊያን ጦር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከለውን መርዛማ ኬሚካል በመጠቀም ወደ መሐል አገር መንቀሳቀስ በጀመረበት ወቅት የእኔ አባት ከማይጨው ወደ አዲስአበባ በሚወስደው መንገድ ላይ ጣሊያን አልፎ እንዳይገባ የቻሉትን እንዲያደርጉ፣ ሕዝቡ በቻለው አቅም እንዲከላከል የቀሰቅሱ ነበር።

የአካባቢው ሕዝብም አባቴን የጎበዝ አለቃ አድርገው መረጧቸው። እሳቸውም ‹‹እኔን ከመረጣችሁን እንግዲያውስ እኔ የምላችሁን አድርጉ›› ብለው ሕዝቡን ጠንባበር ዋሻ ከሚባለው ስፍራ ጭራሜዳ ( አይገብር፣ ትርጉሙም ለጠላት አንገብርም ማለት ነው) እስከ ሸዋሮቢት ድረስ ያለውን ስፍራ ሕዝቡ ያለውን መጥረቢያ ያለው መጥረቢያ ጎራዴ ያለው ጎራዴውን ይዞ እንዲሰለፍ አድርገዋል ።

የጄኔራል ባዶሊዮ ጦር በማይጨው ጊዜያዊ ድል አግኝቶ ወደ መሐል ሀገር እየገሰገሰ በቦታው ሲደርሱ የገጠሙት ሲሆን፣ በጦርነቱም 75 ካሚዎን (የጭነት ወታደር) የነጭ ወታደር ተመትቷል። ከዛም በኋላ የጣሊያን ጦርም ወደ አዲስአበባ እንዳይገባ በየደረሱበት መንገድ በመዝጋት የተቻላቸውን አድርገዋል፣ ለዚህም ከአጼ ኃይለሥላሴ ምስጋና ተችሯቸዋል ።

ሽንፈት እየገጠመው መሆኑን የተረዳው ጣሊያን የአየር ላይ ድብደባ ማድረግ ሲጀምር እሳቸውም ሕዝቤን መጨረስህን የማትተው ከሆነ ብለው በምርኮ የያዟቸውን ወታደሮች ላይ እርምጃ በመውሰድ አሳይተዋል። በዚህም ‹‹የጥቁር ጭቃው ተሰማ እርገጤ ነጩን አረደው እንደወጠጤ›› ተብሎ ተገጥሞላቸዋል። በኋላም ጦርነቱ ካበቃ እና ከተረጋጋ በኋላ ንጉሡ ጣሊያኖች ደርሰው እኛን እንዳይዙን መንገድ የዘጋልን ባለውለታ ነው ብለው አመስግነዋቸዋል።

ተሰማ እርገጤ የተሰማቸውን ነገር በቀጥታ ፊት ፊት በመናገርም ይታወቃሉ። ከአምስት ዓመት በቆየው ውጊያ ላይም ዘጠኝ ቦታ ቆስለዋል፤ በፍጹም ጀግንነት ተዋግተዋል ወንድማቸው እስጢፋኖስ ተሰማ እርገጤም በጀግንነት አልፈዋል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ነፃነቷን ታግኝ እንጂ በጎንደር የነበረው የጣሊያን ጦር ምሽግ መሽጎ አልወጣም ነበር እና ከመሐል ሀገር ኃይል ያላቸው አርበኞች እንዲሄዱ ሲታዘዝ ተሰማ እርገጤ በፊታውራሪነት ማዕረግ ሦስት ሺህ በላይ ጦር ይዘው በጎንደር ከሚገኙ ተዋጊዎች ጋር በመመካከር በሦስት ምሽጎች የተቀመጠው የጣሊያን ጦር ምሽጉን ዙሪያውን በቦምብ በማጠሩ ሕዝብ እንዳይጨርስ ከበባ ካደረጉ በኋላ ኢትዮጵያን ሊያግዝ የገባው የእንግሊዝ ጦር ጋር በመሆን ተዋግተዋል ። የጣሊያኑ የጦር መሪም እጄን ለጥቁር አልሰጥም ብሎ እጁን ለእንግሊዞች ሰጠ ።

ፊትአውራሪ ተሰማ እርገጤም የማረኩት መሣሪያ የጀርመን ስሪት ነውና እንግሊዞች መሣሪያውን ለማግኘት ቋምጠዋል ነገር ግን ተሰማ እርገጤ እሱም ከነጭ የማረኩትን ለነጭ አልሰጠም ብለው ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበሩም ። በዚህም ምክንያት የጣሊያን ጦር ሊገድላቸው ሰው አሰማርቶባቸው ነበር ። ፊታውራሪ ከመሣሪያው ባሻገር 80 ሺህ በርሜል የጣሊያን ነዳጅ ማርከዋል።

አዲስ ዘመን ፡- የአርበኛ ልጅ የልጅነት ጊዜው ምን ይመስላል እርስዎስ ከዚህ ታሪክ ምን ተማሩ ?

ልጅ ጀርሚያስ፡- እኔ ለቤተሰባችን አራተኛ ልጅ ነኝ /በአጠቃላይ ሰባት ልጆች ነን/ ከልጅነቴ ጀምሬ ሳዳምጥ አባታችን በባንዳዎች ምክንያት ተገፍተው መተዳደርያ አጥተው በቤታቸው አዝነው የተቀመጡ አርበኞችን በቤታችን አስቀምጠው ይጦሩ ነበር። ከታላቆቼ ጋር ሆነን እነሱ ስር ታሪክ እየሰማን ነው ያደግነው።

አባታችንም በልጅነታችን ውጭ ሀገር ሊልኩንም ፍላጎት አልነበራቸውም። በእረፍት ሰዓታችን ወደ ክፍለሀገር በመሄድ አደን እንድናድን፣ ዒላማ እንድተኩስ ያደርጉን ነበር። በዘጠኝ ዓመቴ ከወንድሜ ጋር ዒላማ ስለማመድ ወንድሜ በጥይት መትቶኝ በንጉሡ እና በአልጋወራሹ አማካኝነት ወደ ውጭ ሀገር ሄጄ እንድታከም ቢሞከርም አባቴ ግን ጣሊያኖች በእጅ አዙር ልጄን ይገሉብኛል ብለው ከልክለዋል። አባቴ በጣም ጠንቃቃ እና የሀገራችንን ታሪክ የምናውቅ ተጋዳይ፣ ጨዋና ሥነ-ምግባር ያለው አድርገው አሳድገውናል ።

ታላቅ የሆነችውን የኢትዮጵያን ታሪክ ነው እየሰማን ያደግነው። ጀግናና አርበኛ ሀብት የለውም ምክንያቱም ባንዳዎቹ ገንዘብ ላይ እና ጥቅማቸው ላይ ሲያሯሯጡ እነሱ ግን ሀገርና ሕዝብን ለማዳን ስለነበረ ዓላማቸው የነበራቸው ቤት እንኳን እየተቃጠለ ነበር ወደ ጦርሜዳ የሚዘምቱት። የሚያሳዝነው ለሀገር ውለታ የሠሩ፣ ሀገርን አላስገዛም ያሉ ጀግኖች የሚገባቸውን ክብር እና ምስጋና ሳያገኙ እንክብካቤ ሳይደረግላቸው አልፈዋል ።

የዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያሉ የጥቁር ሕዝቦችን ጭምር አንገት ቀና ያደረገ የጣሊያን ጦር በገጠመው ሽንፈት ሳቢያ ራሳቸው ጣሊያኖች ( ቪቫ ሚኒልክ ቪቫ ጣይቱ) በማለት እንዲመሰክሩ አድርጓቸዋል። በዚህም ኢትዮጵያውያን የጥቁር ሕዝቦችን ነፃነት በማወጅ ኢትዮጵያ ፋና ወጊ ፈር ቀዳጅ ሀገር አድርገዋታል ።

አዲስ ዘመን ፡- ዛሬ ላይ ያለፉ ታሪኮቻችን የግጭት መንስኤ ሲሆኑ ይስተዋላል። ይህ ከምን የመነጨ ነው ?

ልጅ ጀርሚያስ ፡– ወደኋላ ነገሩን ስንመለከተው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም በጥናት ደረጃ ሰፊ ነው። ኢትዮጵያ ኃያል ሀገር እና ኃያላን መንግሥታት የነበሯት መሆኑ ዳግም በዓድዋ ጦርነት ላይ እስከአፍንጫው ድረስ ታጥቆ የመጣውን ወራሪ ሠራዊት በመዋጋት ዳግም አሳይተዋል። ከዛ በኋላም ቢሆን የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር የሠላም አስከባሪ ኃይል በመባል በዓለም ላይ የታወቀ ጠንካራ ሠራዊት የገነባች ሀገር ሆና በኮሪያ፣ ኮንጎ ላይ በመዝመት ጀግንነታቸውን እና ወዳጅነታቸውን አሳይተዋል።

በዚህን ጊዜ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ገና ከቅኝ ግዛት ባልወጡበት ወቅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት አድርጋለች። ይህም በሌሎች ሀገራት በስጋት እንድትታይ አድርጓታል። የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ላይ ኢትዮጵያ ያበረከተችው አስተዋፅዖ ላቅ ያለ ነው ። በኋላም የአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት መቀመጫው በኢትዮጵያ እንዲሆን በሚሞግቱበት ወቅት ኢትዮጵያን መሪዎች ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው በመሪነት ጊዘያቸው አንድ የሆኑበት ነው ።

ኃያላን የሚባሉ ሀገራት ደግሞ ይህች ሀገር ወደፊት ያላትን ሀብት የመጠቀም ደረጃ ላይ ስትደርስ የምታሰጋ ትሆናለች በማለት የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያነሱ አብዛኛው የታሪክ መዛግብትና መጽሐፎቻችን በሌሎች ሀገራት ዜጎች እና ጸሐፊያን የተጻፉ ናቸው። እነዚህ ታሪኮችም በጥቅሉ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያረጋግጡ አንዳንድ ታሪኮችን በታማኝነት እንደማይጽፏቸው ይገልጻሉ።

ከመደበቅም ባሻገር የሌሎች ጀግኖችን ታሪክ የራሳቸው አስመስለው ይጽፋሉ። በመሆኑም ወደሀገራችን ስንመጣ የዓድዋ ታሪክን ጨምሮ ከዓድዋ በኋላ ያሉ ታሪኮቻችን ራሱ በአግባቡ አልተጻፉም አልተመዘገቡም። ፈረንጆቹ የእኛን ታሪክ ጠንቅቀው ያውቁታል፣ ይገረሙበታል ለኛ ሲነግሩን ግን አሳንሰው ያቀርቡታል ።

ኢትዮጵያ ያላትን ጥንካሬ ሰብረው መግባት ያልቻሉት ጠላቶቿ እንደ አማራጭ የተጠቀሙት የተለያዩ አካላትን እና መልዕክተኞችን ከሀገር ውስጥ አንዳንድ ባንዳዎች ጋር በመመሳጠር ያላትን ሰፊ የሆነ ሕዝብ ቁጥር የባሕል፣ የቋንቋ፣ ልዩነት ተጠቅመው የእርስ በርስ ግጭት፣ መከፋፈል እንዲኖር ማድረግ ነበር። ለዚህም የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሟል። የጎሳ እና የዘር ልዩነት እንዲሰፍን ተደርጎ አንዱ ባንዱ ላይ እየተተቻቸ ኢትዮጵያን ወደኋላ ለመመለስ ብዙ ተሠርቷል ለዚህም ቢሆን ኢትዮጵያን ይህንን በመመከት አንድነታቸውን በተለያየ ጊዜ አሳይተዋል ።

በአሁን ሰዓትም ዋልታ ረገጥ ያልሆነ ጽንፈኛ ያልሆነ ወደ አንዱ ያላደላ ጥናት የሚያደርጉ ታሪክ ጸሐፊዎች ተሰባስበው ጥናት ቢደረግ እና ታሪካችን በኛው ቢጻፍ ጥሩ ነው። በተጨማሪም በዚህ የአርበኝነት ታሪክ ውስጥ ያለፉ ጀግኖች ባለታሪኮች ታሪክን ባለመደበቅ መጋራት ይኖርባቸዋል። ያልተዘመረላቸው ያልተነገረላቸው ጀግኖችን እንዲሁ ፈልጎ ማግኘት ላይም ሊሠራ ይገባል፣ ለዚህም የሚዲያ አካላት ድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል ።

አዲስ ዘመን ፡- ወጣቱ ትውልድ የአያት የአባቶቹን ታሪክ በምን መድገም አለበት፤ የሀገሩን ሉዓላዊነት በምን መልኩ አስጠብቆ ይቆይ ይላሉ ?

ልጅ ጀርሚያስ ፡– አንኳር ጉዳዮችን ብናነሳ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያ በኃይልና በጦርነት የማትቻል ሀገር መሆኗ በተጨባጭ ታይቷል። ሁለተኛ ሕዝቦቿን በዘር በሃይማኖት በመከፋፈል የተደረገ ጥረት ነው አልተሳካም ። አሁን እየሆነ ያለው ሀገሪቱ በውስጧ ያሉ ባሕል፣ እምነት እና የሞራል እሴቶችን፤ ያልተጻፉ ሰውን ሰው የሚያሰኙ ማንነት ያላቸው የሥነ-ምግባር ሕጎች፣ ታማኝነት እና እውነትን ከትውልዱ ልብ እና አዕምሮ ላይ በመፋቅ በቋንቋው፣ እና በራሱ ማንነት የማይኮራ ግፋ ሲልም ሀገሩን የማያውቅ ትውልድ ለመፍጠር ነው ።

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል በምታደርገው ጉዞ ሌሎች ያደጉ ሀገራት ያላቸውን የኢኮኖሚ እድገት ተጠቅመው በማማለል ዜጎቻችን ስደትን አማራጭ እያደረጉ ከራሳቸው እና ከሀገራቸው እየራቁ እንዲሄዱ ነው፤ ማንነታቸውን እንዲረሱ ማድረግ ነው ።

እነዚህን ተግዳሮቶች ለመሻገር ሀገር ተረካቢው ወጣቱ ትውልድ ወደኋላ ተመልሶ የሀገሩን ታሪክ ኢትዮጵያ ምን ያህል ታላቅ ሀገር እንደነበረች እና እንደ ሆነች፤ የአባት የአያቶቻቸውን ታሪክ ማጥናት እና ማወቅ ይኖርበታል። በተለያዩ አጋጣሚዎች/መድረኮች የሚፈጠሩ የልዩነት ምንጭ የሆኑ አጀንዳዎችን በሰከነ መንፈስ የመልካም ሀሳብ ምንጭ ለማድረግ መሥራት አለበት።

ሌላኛው ይህ ትውልድ በቋንቋው በአለባበሱ የሥነ-ልቦና ወረራ ተደርጎበታል። የራሳቸውን ቱባ ባሕል ተጠቅመው የራሳቸውን ፈጠራ በማከል በማዘመን እንጂ ጨርሶ መጣል እና የሌላ ሀገር ባሕል ተከታይ መሆን የለበትም ። የሀገራቸውን ቋንቋ በእኩል ዓይን ተመልክተው ጥንቅቅ አድርገው ማወቅ፤ የሌላውንም ዓለም ቋንቋ ማወቅ እንጂ አደባልቀው እና አፋልሰው መናገር የለባቸው። ታሪካቸውን ካወቁ እና እርስ በእርሳቸው መተባበር ከቻሉ የዚህን ዘመን እየተካሄደብን ያለውን የሥነ-ልቦና ወረራ መመከት እንችላለን ።

አዲስ ዘመን ፡- አመሰግናለሁ

ልጅ ጀርሚያስ ፡- እኔም አመሰግናለሁ

ሰሚራ በርሀ እና መክሊት ወንደሰን

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You