«የበጋው መብረቅ» ጃገማ ኬሎ ቀኝ እጅ ሌንሴ ኬሎ

ጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለስራ ጉዳይ በተገኘሁበት አገጣሚ ነበር ስለ “የበጋው መብረቅ” ጃገማ ኬሎ ቀኝ እጅ ሌንሴ ኬሎ የሰማሁት። በወቅቱ የጃገማ ኬሎ ሴት ልጅ ለጉዳይ ወደ ማኅበሩ ፅህፈት ቤት ጎራ ብላ ተገናኘተን ስንጨዋወት ነበር ስላልተዘመረላት ጀግና አክስቷ ያጫወተችኝ።

በወቅቱ ወንድሟን ብላ የሞቀ ቤቷን ጥላ አምስት ዓመት ጫካ ውላና እድራ የተዋጋችውን የዚህችን ሴት ታሪክ ከማን ልሰማ እንደምችል ስጠይቅ ወይዘሮ ብርቱካን ወንድም አገኘሁ የተባሉ የወይዘሮ ሌንሴ ልጅን ላገኛቸው እንደምችል ተነጋግረን ከእሳቸው ጋር ለመገናኘት በቅተናል።

̋ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ ̋ ነውና ነገሩ ወይዘሮ ብርቱኳን ከእናታቸው እግር ስር ተቀምጠው ሲሰሙ ያደጉትን ታሪክ በዚህ መልኩ አጫውተውናል። መልካም ቆይታ።

ወሩን በውል እንደማያውቁት የሚናገሩት ወይዘሮ ብርትኳን እናታቸው 1911 ዓ.ም በጅባትና ሜጫ አውራጃ ፣ በደንቢ ዮብዲ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ዮብዶ በሚባል ቦታ ከአቶ ኬሎ መወለዳቸውን ይናገራሉ። ገና በአፍላው የልጅነት እድሜያቸው እናትና አባታቸውን በሞት ያጡት የአቶ ኬሎ ልጆች እንደ ማንኛውም ወላጅ አልባ ልጅ ለማደግ ወደየዘመዶቻቸው ተበተኑ። ሌንሴ አክስቷ ጋር ስትሄድ ሕጻኑ ጃገማ ኬሎ ደግሞ አጎታቸው ጋር ይኖር ጀመር።

በሀብት እና በድሎት ያደጉት እነዚህ ልጆች ምንም እንኳን ምቹ ሁኔታ ላይ ባይሆኑም አድገው ለመገናኘት ተስፋን ሰንቀው የዛሬ መለያየታቸውን በናፍቆት እያሰቡ ይኖሩ ነበር። ሌንሴ ለአቅመ ህይዋን ሳትደርስ ገና በአስራ ሁለት ዓመት እድሜዋ ነበር ተድራ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት የሄደችው። በወለጋም የሞቀ የትዳር ህይወት እየመራች እያለች ነበር መለያየታቸው የእገር እሳት የሆነባት እህት ታናሽ ወንድሟ ጃገማ ዕድሜቸው 15 እንደሆነም ማለትም በ1928 ዓ.ም ነበር አገር በጠላት የተወረረችው።

አፍላ ወጣትነት እድሜ ላይ የነበሩት ጃገማ እንደ ሕፃን ውሃ ከመራጨት ይልቅ ጠላትን ጥይት ለመርጨት፤ እንደ ዕድሜ እኩዮቻቸው አፈር ከመፍጨት ይልቅ የጠላትን አጥንት ለመፍጨት ጨርቄን ማቄን ሳይሉ በጠላት ላይ ሸፍተው ጫካ የገቡት። ገና በአፍላ እድሜያቸው የሀገር ወዳድነት ስሜት ከውስጣቸው እየገነፈለ አላስቀምጥ ያላቸው ትንሹ ጃገማ ለታላቅ ገድል ጫካ ገቡ።

በወቅቱ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር የነበረችው የጃገማ ኬሎ ታላቅ እህት ሌንሴ ኬሎ የወንድሟን መሸፈት ስትሰማ ባሏን ፈታ፤ የሞቀ ቤቷን ትታ፤ ወንድሟን ለማገዝ ጫካ ገባች። አግብታ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት ትኖር የነበረችውም ሌንሴ ወንድሟን ለመርዳት ሀብት ንብረቷን ትታ ከወለጋ ወደ ጊንጪ ለማምራት መንገድ ጀመረች። ስንቋን በጀርባዋ ልጇን በሆዷ ተሸክማ የምታመራውን ነፍሰ ጡር ሴት ጣሊያኖች ድንገት መንገድ ላይ ይይዟታል።

አልገዛም ባዩ የሀበሻ ሕዝብ ቆሽቱን ያደበነው ጣሊያን ሴት የለ ወንድ፤ ሕፃን የለ ነፍሰ ጡር ያገኘውን አቅም አልባ እያፈሰ እስር ቤት መክተትን ስራዬ ብሎ ተያይዞት ነበር። ያኔ የወንድሟ ናፍቆት የሀገር መወረር ቁጭት ሲያንገበግባት የኖረችው ይች ሴትም የጣሊያኖቹ የእስር ቤት በትር አርፎባት ለሁለት ወራት በእስር ትቆያለች። እስር ቤት እያለች ልጇን የተገላገለችው ይች ሴት በዛው እስር ቤት የአብራኳን ክፋይ ታጣለች። ይህን ጉዳይ የሰሙት አጎቷ ከጣሊያኖቹ ጋር መልዕክት በመላላክ እንድትፈታ ያድርጓታል።

ቁጭት ቁጭትን እየወለደ ከወንድሟ ናፍቆት፤ የሀገር መደፈር ቁጭት፤ የአብራኳን ክፋይ በእስር ቤት ማጣቷ ተደራርቦ ፍም ያቀፈች አርበኛ ሊያደርጋት ሌንሴ ኬሎ እልህ ከውስጧ እንደ ቋያ እሳት እየተንተገተገ ነበር ወንድሟ የሚመራው የጦር ሰፈር የደረሰችው።

የጀግንነት ደም ውስጣቸው የሚንተከተከው የዚህ ቤተሰብ አባላት፤ ማለትም ሻለቃ ፈንጌሳ ኬሎ፤ ሻንበል ጊዴ ኪሎና ትንሹ የአባ ኬሎ ወንድ ልጅ ጃገማ ኬሎ በአንድ ሆነው ጣሊያንን ሲያርበደብዱ አገኘቻቸው። ይች ሴት ወትሮም መለየያታቸው እንጂ በአንድነት ታሪክ ሰሪ መሆናቸውን ታውቅ ስለ ነበር የራሷን መቶ ሰዎች በማደራጀት ግልጋሎቷን በስፋት መስጠት ጀመረች።

በወቅቱ የጃገማ ኬሎን ወኔ ገና ከጅምሩ የተረዱ ወጣቶችም የእርሳቸውን እግር ተከትለው “እምቢ ለአገሬ” እያሉ በጠላት ላይ ሳያንገራግሩ ሸፈቱ። በዚህም ሳቢያ ጃገማ ኬሎ ገና በአፍላ ዕድሜቸው የ3ሺ500 አርበኞች አለቃ ለመሆን ችለው ነበር።

ያን ጊዜ በምዕራብ ሸዋ የነበረውን የፋሽስት ጦር መግቢያ መውጫ በማሳጣትና ሰቅዞ በመያዝም “የበጋው መብረቅ” የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። አምስት ዓመታትን በፈጀው ጦርነትም በታላላቅ አውደ ውጊያዎች ላይ ጦራቸውን ሰብቀው የተካፈሉት “ጃገማ ዘአንበሳ” ከማሸነፍ በቀር ለአንዴም ቢሆን ሽንፈትን አያውቋትም ነበር።

ጠላትን ድል ነስተው የጠላት ግምዣ ቤት ሰብረው አርበኞችን ባስታጠቁ ቁጥርም እንዲህ ይወደሱ ነበር።

“ገዳይ በልጅነቱ

ዶቃ ሳይወጣ ባንገቱ

ጃጌ ጃገማቸው

እንደ ገጠመ የሚፈጃቸው

አባት እናቱ ከኦሮሞ

ግዳዩን አስቆጠረ ከምሮ ከምሮ” ተብሎ ተገጥሞላቸው ነበር፡፡

ሌንሴ የጃገማን ኬሎ ፀጉር በመስራት፤ ምግብ በማቅረብ አንድም ቀን እንኳን ከጎናቸው ባለመለየት የተሳካና በድል የታጀበ ጦርነት እንዲያካሂዱ አድርጋቸው ነበር።

ስንቁን በአይነት በአይነት በማደራጀት፤ ከጦርነቱ ፈርቶ ሊመለስ ያለውን አርበኛ በሙሉ መሳሪያ በመያዝ ̋እኔ ሴቷ ዘምቼ ሀገር ስትጠፋ ወዴት ትመለሳለህ ? ̋ በማለት በማደፋፈር ሰራዊቱ ሳይበተን በወኔ እንዲዋጋ የጃገማ ኬሎ ቀኝ እጅ በመሆን ስታገለግል ቆይታለች።

የጃገማ ኬሎ ሰራዊት ከሸዋ እስከ ጅማ በመዝመት ጠላት ባዩ ቁጥር ግዳይ እንዳዬ ነብር ወደ ጠላት እየተወረወሩ ጠላትን አስጨንቀዋል። እጅግ አደገኛ የሆኑ የፋሽስት ምሽጎች ሰባብረዋል። በዚህ ወቅትም የሚወድቁ ቁስለኞችን በማንሳት የማከም ስራ፤ ውሃ ለጠማው ውሃ ማጠጣት ድካም ለተሰማው ብርታት መሆን የሌንሴ ኬሎ ተግባር ነበር።

ሌንሴ ወንድሟ እንዳይሞትባት መጠበቁ ታላቁ ኃላፊነቷ ነበር፡፡ ከባድ ወጊያ ተካሄዶ ጦሩ ተበታትኖ እስኪሰበሰብ ድረስ መሳሪያ በመያዝ ከወንድሟ ጋር ጠላትን የምትመክተው እሷ እንደነበረች ይናገራሉ።

ጃገማ ኬሎ ከእነ ደጃች ገረሱ ዱኪ ጋር በመሆን በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አርበኞችን እስከ መጨረሻው ማለትም እስከ 1933 ዓ.ም በመምራት፣ በማስተባበርና ተዋግቶ በማዋጋት ጣሊያንን ቁም ስቅል ነስተው ከኢትዮጵያ ምድር የውርደት ካባ አጎናፅፈው ወደ መጣበት ሸኝተዋል። የእሳቸው ጀግንነት ሲነሳ አንድም ቀን ከአጠገባቸው ያልተለየቻቸው የታላቅ እህታቸው የወይዘሮ ሌንሴ ኬሎ ታሪክም መዘንጋት አይኖርበትም።

ጃገማ ኬሎ ከድል በኋላም በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ምክር ዘመናዊ የጦር ትምህርትን በሆለታ የጦር ትምህርት ቤት እንዲሁም አሜሪካን አገር ድረስ ተጉዘው የተማሩ ሲሆን ወደ አገራቸውም በመመለስ ዕልፎችን ዘመናዊ የጦር ትምህርት ስያስተምሩ ሌንሴ ትዳር በመያዝ ቤተሰብ መስርታ ልጆችን አፍርታለች።

ጃገማ ከግርማዊና ቀዳማዊ አፄ የኃይለ ስላሴ እጅም የሌፍተናንት ጀነራልነትን ማዕረግን የተቀበሉ ሲሆን በንጉሰ ነገስቱም የስምንቱ ጠቅላይ ግዛቶች የሰራዊት ኃላፊ እንዲሆኑ ሲሾሙ ሌንሴ ለወንድማ የነበራት ከባድ ፍቅር ቤቷን አስትቶ እያስኮበለለ ወንድሟ ጋር ሲወስዳት ትዳሩ በፍቺ ይጠናቀቃል። ያኔ ወደ ትውልድ ቀየዋ ጊንጪ በመሄድ እርሻ ታሳርስ እንደነበረ የወይዘሮ ሌንሴ ልጅ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ብርትኳን እንደሚሉት ከጀነራል ጃገማ ኬሎ ታሪክ ውስጥ የሚደንቀኝ የማረኩትን ነጭ የጣሊያን ወታደር መቶ ብር ሸጠዋል። ከእሳቸው መቶ ብር የገዛው ደግሞ ጣሊያኑን 5000 ብር ሽጦታል። ባርነት በቆዳ ቀለም መጥቆር የተነሳ የሚጫን ቀንበር አለመሆኑን ለምዕራባውያኑ ከማስገንዘብ በተጨማሪ አውሮፓውያን ጥቁሮች ላይ የፈፀሙትን በደል በተራቸው በጥቂቱም ቢሆን እየጎመዘዛቸው እንዲቀምሱት ማድረግ የቻሉበት ነው።

ወይዘሮ ብርትኳን እንደሚሉት የጀግና ጃገማ ኬሎ እህት ጀግናዋ ሌንሴ ኬሎ ከግርማዊና ቀዳማዊ አፄ የኃይለ ስላሴ እጅም የተለያዩ ሁለት ኒሻኖችን ተቀብለው ነበር።

ከጦርነት መልስ በትዳር መኖር ያልሆነላቸው ቀሚስ መልበስ የማያውቁት ሌንሴ ኬሎ በሬ ጠምደው በማረስ ልጆቻቸውን ያሳድጉ የነበረ ሲሆን ሰው መርዳት ለተቸገረ መድረስ ተቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን ልጃቸው ይናገራሉ።

ጀነራል ጀጋማ ኬሎም በዛ በልጅነታቸው ወቅት እንደ እናት ተንከባክበው ላቀይዋቸው እህታቸው ውለታ ምላሽ ለጆቻቸውን እየወሰዱ ያሳደጉላቸው እንደነበር የሚናገ ሩት ወይዘሮ ብርትክዋን እሳቸውና ወንድማ ቸውም በአጎታቸው በጀነራል ጃገማ ኬሎ እጅ ማደጋቸውን ያስታውሳሉ።

ዓመታትን ለሀገራቸው ዋጋ የከፈሉ ከሞት ጋር ተናንቀው ነፃነቷን አስጠብቀው የቆዩቱ እናት አርበኛ ሌንሴ ኬሎ ከዚህ ዓለም በሞት እስከሚለዩ ድረስ የራሳቸው መኖሪያ ቤት እንኳን ያልነበራቸው እንደሆኑ ልጃቸው ይናገራሉ።

ትናንትናችንን ስናስታውስ በደማቁ የደም ዋጋ የከፈሉ ለነፃነታችን አንገታቸውን ለሰይፍ ደረታቸውን ለጥይት የሰጡ ጀግኖቻችንን የሚጋባውን ክብር መስጠት ይገባናል ባይ ነኝ። እንደማንም ተራ እቃ በየቦታው ወደቀው የምናያቸው በአንድ ወቅት ለሀገር ባለውለታ የነበሩ አርበኞችና ቤተሰቦቻቸው የት ናቸው ብሎ መመልከት ተገቢ ነው እላለሁ።

ኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ነውና ነገሩ ትናንትን እያከበርን ዛሬ የሚጠበቅብን የወቅቱን የአርበኝነት ተግባር እናከናውን በሚል መልእክት ልሰናበታችሁ ወደድኩ። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You