አድዋ – የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ችቦ

እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ..የአባቶቼ መልክና ቀለም የቀለመኝ። በኢትዮጵያዊነቴ ውስጥ እውነት ናቸው ብዬ ከተቀበልኳቸውና ባስታወስኳቸው ቁጥር ከሚያስደንቁኝ እውነቶች ውስጥ አንዱ የአድዋ ታሪክ ነው። አድዋ የጋራ መደነቂያችን እንደሆነ ባምንም እንደእኔ የሚደነቅበት ስለመኖሩ ግን እጠራጠራለው። ከእውነቴ አንዱን ለማንሳት ያህል አድዋ ለኔ በዓለም ታሪክ፣ በሰው ልጆችም ስልጣኔ ያልተደረሰ፣ እውነት በማይመስል ታሪክ ውስጥ ነጻነት የተጻፈበት የሰው ልጆች ሁሉ የቀና ማለት መለኮት ነው።

ለሰው ልጆችም አስደማሚ የነጻነት ገድል ታሪክ ባለቤቶች ነን። ይሄ ገድል ከአባቶቻችን ወደእኛ እንዴት መጣ፣ ዓለምንስ እንዴት አስደመመ ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ አብሮነትን ነው። አብሮነት ከኃይልና ከብርታት ባለፈ በየትኛውም ዘመን የሀገርና የሉአላዊነት ዳር ድንበር ማስከበሪያ ነው። አድዋ በየትኛውም ምሁራን አንደበት ቢተነተን ይሄን መሳዩን እውነታ ነው የሚፈነጥቅልን። በአባቶቻችን ስልጣኔና ዘመናዊነት እንዲሁም ደግሞ በከባድ መሳሪያ የመጣ ሳይሆን በአንድነትና በወንድማማችነት መንፈስ የመጣ ነው።

ይሄ የአይበገሬነት መንፈስ መቶ ዓመታትን ተሻግሮ እንኳን ቀለሙ ዛሬም አልደበዘዘም። ከሀገር ፍቅርና ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ምንም የማይስተዋልበት ያ የአድዋ ዘመን እኔንና እናተን ሲፈጥር መነሻው ሀገርና ሕዝብ ነበር። ክብርና ነጻነት፣ ሉአላዊነትና አትንኩኝ ባይነት ነበር።

እንደ አድዋ ያለ ዘመን ተሻጋሪ ታላላቅ ታሪኮች ደምቀው የሚታዩት ሕብረት በወለደው ሕዝባዊነት ውስጥ ነው። አድዋን ሻማ አብርቶ፣ ጀግኖቻችንን አስታውሶ ማለፍ ብቻውን ዋጋ አይኖረውም። መንፈሳቸውን ወርሰን፣ እምነትና ጽናታቸው ተጋብቶብን አሁን ካለንበት የቡዳኔ ልክፍት ወጥተን በሕብረብሄራዊነት ስንቆም ነው። ዝክረ አድዋ ዝክረ ኢትዮጵያ፣ ዝክረ አፍሪካ፣ ዝክረ ጥቁርነት ነው። ትርጉም ያለው እንዲሆን ትርጉም ባለው ሀገራዊ አስተሳሰብ ስር መሰባሰብ ያስፈልጋል።

ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያዊነትን ባስቀደሙ በአባቶቻችን ታሪክ የምንጠራ ነን። ታሪክ መዘን እንዲህ ነበርን ብለን የምንኮፈስ። አድዋ ሊያስተምረን የሚችለው ትልቁ ነገር አንድነት በዋጀው ወንድማማችነት ሀገራዊ እና ቀጠናዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ድሎችንም መቀዳጀት ነው። ታሪክ ማውራት ብቻውን አንድን ሀገር ወደፊት አያራምደውም። በእኛ ጊዜ ላይ ዳግማዊ አድዋን የሚፈጥር ልዕለ ሰብ መገንባት ድርሻችን ይሆናል።

ታሪክን በዘመን ስናሰላው መነሻና መድረሻው በዛን ሰሞን ይሆናል። ከመጀመሪያው አድዋ እስከ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ድረስ አርባ ዓመታት በመሀል አሉ። አባቶቻችን ሁለተኛውን የጣሊያን እብሪት ለማብረድ አርባ ዓመት ነው የበቃቸው። ጣሊያን ከዛ ቀድሞ ቢመጣም የማሸነፍና የመመከት ሙሉ ልዕልና ነበራቸው። ለዚህ ምክንያት ሆኖ ከፊት የሚመጣው ደግሞ የሀገር ፍቅርና የነጻነት ጥያቄ ነው።

በአርባ ዓመታት ውስጥ ሁለት አይነት ድሎችን መቀዳጀት ትርጉሙ በምን እንደሚለካ ዛሬም ድረስ አልመጣልኝም። አባቶቻችን በጽኑ ተጋድሎ ሀገር ሲጠብቁና ሉአላዊነትን ሲያውጁ ኖረው ያለፉ ናቸው። እኔና እናንተ ግን መቶ ዓመታት አልፈውን ዛሬም ድረስ በአባቶቻችን የትላንት ታሪክ የምንጠራ ነን። የእኛ አድዋ የታለ? የእኛ አድዋ መቼ ነው የሚጀምረው? መቼ ነው በድህነት ላይ ታሪክ የምንሰራው?

ጎጠኝነት አድዋችንን ሰውሮብናል። በዘርና በጎሳ መቧደናችን ልዕልናችንን ሸሽጎብናል። ከዚህ አስተሳሰብ እስካልወጣን ድረስ የእኛን አድዋ አንደርስበትም። በልባችን ላይ ከትዕቢታችን ቀድማ፣ ከጥላቻችን ቀድማ ኢትዮጵያ ካልመጣች አደጋ ላይ ነን። ከብሔራችን ቀድሞ በነፍሳችን ላይ ኢትዮጵያዊነት ካልነገሰ ታሪክ ከማውራት ባለፈ ታሪክ መስራት አይቻለንም።

የአባቶቻችን አድዋ በኢትዮጵያዊነት ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ያበቃ ነው። የእኛ ታሪክ ግን በእኔነት ጀምሮ በራስወዳድነት ያበቃ ነው። ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት ቀድሞ ደማማቅ ጸዳሎቻችንን አደብዝዞብናል። ጥንተ ከፍታዎቻችን አቧራቸው ረግፎ አንቱታን እንዲያገኙ በዚህ ትውልድ ላይ ኢትዮጵያዊነት ሊለመልም ግድ ይላል።

አድዋ ኢትዮጵያዊነት ቀድሞ ኢትዮጵያዊነት በተከተለበት የወንድማማችነት መንፈስ የተፈጠረ ነው። እንደሀገር የተጀመሩ ብዙ እድሎች አሉን። በማለቅ ላይ ያሉ ትንሳኤ አብሳሪ ጸጋዎች አሉን። እኚህ ሁሉ ወደመሆን እንዲመጡ ለሀገራችን ምቹ የሆነ ተግባቦትና ምክክር ያለበት ፖለቲካዊ ምህዳር ያስፈልገናል።

በጠበበ ፖለቲካ የሰፋ ሀገር ትርጉም የለውም። በሰፋ ፖለቲካ ነው የጠበበ ሀገር የሚገዝፈው። ችግሩ ከሀገራችን ሳይሆን ካለፍንበትና እያለፍንበት ካለው የፖለቲካ ምህዳር ነው። እንደ ፖለቲከኛ ከሰፋን፣ እንደ ሕዝብ ከገዘፍን እንደሀገር የማንበረታበት ምንም ምክንያት የለም። አድዋ የሰፋና የገዘፉ ልቦች ነጸብራቅ ነው።

ይሄ ነጸብራቅም ሀገር አድምቆ አፍሪካ ላይ ተንጸባርቋል። ዓለም ላይ መልህቁን ጥሏል። የፖለቲካ ስፋት..የማኅበረሰብ ግዝፈት ማለት ይሄ ነው። የአባቶቻችን ግዝፈት ነው ጠባቧን ዓለም ያገዘፋት። በአድዋ ማግስት መግዘፍ እንጂ ታሪክ እያወሩ ነበርን መዘከር ትርጉም የለውም።

ከልዩነታችን ሀገራችንን ማስቀደም አለብን። የእኛ አድዋ በዚህ መንገድ ካልሆነ በምንም አይፈጠርም። ዛሬም ድረስ የአድዋ ድል ሚስጥሩ ያልገባቸው አሉ፤ ከዚህ የተነሳ ስለድሉ ምርምር ላይ ናቸው። አንዲት ድሃና ኋላቀር ሀገር፣ ምድር የስልጣኔ ፈርቀዳጅዋን ጣሊያንን ልታሸንፍ ቻለች? በሚል ትካዜ ላይ ናቸው። አድዋ ለእኛ ለጥቁሮች ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ኩራት ነው። የዛኑ ያህል ድሉ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የቁጭትና የውርደት ታሪክ የሆነባቸውም አሉ።

ከአድዋ በፊትና ከአድዋ በኋላ ዓለም ሁለት አይነት ናት። ከአድዋ በፊት ያለችው ዓለም ስለ ጥቁር ሕዝቦች ያላት ምልከታ ሙሉ በሙሉ የተበላሸና ከከሰብአዊ እሳቤ የራቀ ነው፤ ከአድዋ በኋላ ግን ይህ እሳቤ የተገራበት እውነታ ተፈጥራል። ድሉ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነትና የቀና ማለት መለኮት ሆኖ በዓለም አደባባይ ተሰምቷል። አድዋ ለዓለም ጭቁኖች የትንሳኤ ቀን ነው። አድዋ ለዓለም ጥቁሮች የአቢዮት ማግስት ነው።

አሁን ከዚህ የታሪክ ትርክት የሚቀዳ አዲስ አድዋ አዲስ ታሪክ ያስፈልገናል። ደጋግመን ከምናወራው የአባቶቻችን ታሪክ ወጥተን የራሳችንን አድዋ የምንሰራበት ጊዜ ላይ ነን። ከአባቶቻችን ጽናትንና አንድነትን፣ ኢትዮጵያዊነትንም ወስደን በዘርና በጎሳ የቆሸሸችውን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ መማገር አለብን። ካለፈው ዘመን ፍቅርና ወንድማማችነትን ወርሰን በጥላቻና በመለያየት የቆመችውን ሀገራችንን መሰብሰብ አለብን። አድዋን ስንዘክረው መቶ ሀያ ስምንት ዓመት ሆነናል እርግጥ አድዋ ማብቂያ የለውም። ከሰው ልጆች ጋር፣ ከነጻነትና ከክብር ጋር፣ ከሰብዐዊነትና ከጥቁርነት ጋር አብሮ የሚነሳ ገድል ነው።

ከአባቶቻችን እንደተቀበልነው ሁሉ ለልጆቻችን የምናወርሳቸው ሌላ አድዋ ያስፈልገናል። መጪው ትውልድ የአባቶቹንና የአያቶቹን ጥንድ አድዋ እንዲያከብር ዛሬ የእኔና የእናንተን አድዋ መፍጠር አለብን። በድህነትና በኋላቀርነት ላይ፣ በዘረኝነትና በጥላቻ ላይ፣ በጦርነትና በመገፋፋት ላይ አዲስ አድዋ ያስፈልገናል። ሰላምን በመስበክ፣ አንድነትን በማጠንከር፣ በልማትና በእድገት ላይ አዲስ ታሪክ ያሻናል።

ታሪክ ተዐምር አይደለም የሚፈጠረው በፍቅር ነው። ታሪክ የሚጻፈው በአንድነት ነው። ፍቅር ውስጥ የቆሙ ነፍሶች ሁሉ ባለታሪክ ናቸው። በአንድነትና በይቅርታ ውስጥ የጸኑ ልቦች እነሱ የታሪክና የታዐምር ባለቤቶች ናቸው። ታሪካችንን የሰወርነው ብሄር ተኮር እሳቤን ባነገበ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ነው። እድላችንን የደበቅነው ፍቅርን በማያውቅ ጨለማ ልባችን ነው። ዳግማዊ አድዋን ለመፍጠር እንደአባቶቻችን መሆን አለብን።

ዓላማቸውን ወርሰን፣ ሕልማቸውን ተጋርተን በቀናው ጎዳና ላይ መቆም ያዋጣናል። እነሱ የኖሩት ለኢትዮጵያ ነበር የሞቱትም ለኢትዮጵያ ነው። እነሱ ቋንቋቸው አንድነት ነበር በአንድነትም አድዋን ፈጥረው አልፈዋል። የእኛ ቋንቋ ምንድነው፤ እውቀታችንስ ? እኛ ቋንቃችን ተደበላልቋል፤ እውቀታችንም በእኔነት ረክሷል። ተነጋግረን መግባባት ተስኖናል። ከዚህ የተነሳም ለራሳችን ኖረን ለራሳችን መብቃት ያልቻልነው። ለዚህ እኮ ነው አድዋን መሳይ ታሪክ ያልሰራነው። ለዚህም እኮ ነው የምንናፍቃትን ኢትዮጵያ አምጠን መውለድ ያልቻልነው።

ምኞት ተግባር ካልታከለበት ከንቱ ልፋት ነው። በምኞታችን ውስጥ ሆና ልናያት የምንፈልጋት ሀገር አለችን፤ በሀሳባችን ውስጥ ሆኖ እንድናየው የምንፈልገው ሕዝብ አለን። ተግባራችን ግን ሌላ ነው..ጥላቻና ዘረኝነት የሞላው። እኔነትና ራስወዳድነትን የቀላቀለ። በዚህ ማህጸን ውስጥ አድዋ አይኖርም መቼም ቢሆን የለም። ይሄ ማህጸን የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ አምጦ መውለድ አይቻለውም።

ማህጸን ሀሳብ ነው..ማህጸን ምግባር ነው። ማህጸን ፍቅርና አንድነት፣ ይቅርታና ወንድማማችነት ያሉበት ስፍራ ነው። ማህጸን እውነትና ፍትህ፣ እኛነትና ኢትዮጵያዊነት የሚፈጠሩበት ለምለም ቦታ ነው። በዚህ ማህጸን ካልሆነ አድዋንም ሆነ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ አንደርስባቸውም። ማህጸናችን ጥላቻን ጸንሶ ጥላቻን መውለዱ ይብቃው። ማህጸናችን እልኸኝነትን ጸንሶ እልኸኝነትን መውለዱ ይቁም።

ለመነጋገርና ለመግባባት፣ ለመተቃቀፍና አንተ ትብስ አንቺ ለመባባል የሚሆን ማህጸን ያስፈልገናል። አድዋ በዛ ውስጥ ነው።

አድዋ አጥቢያ ነው..የኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የነጻነት ዜማ የሚደመጥበት። የጽናት፣ የሉአላዊነት ቅኔ መወድስ የሚሰማበት..የክብር፣ የሕብር..ደብር። አድዋ ታቦት ነው ኢትዮጵያዊነት የተቀረጸበት የብኩርና ጽላት። ሞት የዋጀው፣ ጉስቁልና ያረታው የማንነት አውድ። አድዋ ዋርካ ነው የኩራት፣ የክብርና የትህትና የነጻነትም የመምሬ አድባር።

አድዋ ተራራ ነው..ትልቅና ጥልቅ የኢትዮጵያዊነት ስጋና ደም። ጽናት እምነትና አሸናፊነት የከተቡት። አድዋ ጌጥ ነው..የመቶ ሀያ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አሸክታብ። የሰማኒያና ከዛ በላይ ብሔረሰብ የኩራትና የልዕልና ምንጭ። የመላው ጥቁር ሕዝብ መታበያ..መመጻደቂያ። አድዋ ይሄን ሁሉ ነው..እኛም ይሄን ሁሉ ነን።

አድዋን የፈጠሩ እነዛ ሻከራ እጆች፤ እነዛ ባዶ እግሮች፤ እነዛ ለነጻነት ቀናኢ ነፍሶች ክብር ይግባቸው። ዛሬ አንዲህ ደምቆ ያየነው በነሱ ነው። እነዛ ለነጻነት ቀናኢ ነፍሶች መስዋዕት ባይሆኑ ባይሞቱልንና ኖሮ እኔም እኔን እናተም እናተን ባልሆንን ነበር። ክብር ይግባቸው ሞተው ያቆሙን እነዛ ነፍሶች።

አድዋ የኢትዮጵያዊነት ቀለም ነው..እንደ አፍሪካ ከፊት የቆምነው፣ እንደ ጥቁር ፊተኝነትን ያገኘነው በዚህ እውነት ላይ ተረማምደን ነው። ኢትዮጵያዊነት ነፃነትን በብዙ መስዋዕትነት አምጦ የወለደ ማህጸን ነው። ኢትዮጵያዊነት የዓለምን ታሪክ የቀየረ ነው።

አድዋ በየትኛውም ዘመን ለሚፈጠር ትውልድ መደነቂያና መገረሚያ ነው። ትውልዱ የአባቶቹን አድዋ እያስቀጠለ የራሱን አድዋ ለመፍጠር ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን መነቃቃት አለበት። በአባቶቻችን አድዋ ውስጥ የራሱን አድዋ ለማየት እንደአባቶቹ ያለ ብርቱ አንድነትና ዓላማ ጽናት ያስፈልገዋል። ቸር ሰንብቱ።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You