ሌላ ዓለም አቀፋዊ ውጥረት

“የመካከለኛው ምሥራቅ የማይጠፋ የእሳት ረመጥ በርዕዮተ ዓለም የሚለኮስ፣ በታሪክ የሚራገብ እና በውጭ ኃይሎች ቤንዚን የሚርከፈከፍበት ነው።”ይለዋል ይህን አደገኛ ቀጣና ታዋቂው ጋዜጠኛ አንሰላሳይና ደራሲ ፋሪድ ዘካሪያ። ከብሉይ እስከ ሀዲስ በተለይ እስራኤል እንደ ሀገር ከቆመችበት ከወርሀ ግንቦት 1948 ወዲህ ወይም ላለፉት 77 ዓመታት የሆነው ይህ ነው። እስራኤል ኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት፣ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሩሲያ ስልታዊ የጦር ጀቶች ላይ ጥቃት ማድረስ እና አጠቃላይ የዩክሬን ራሽያ ጦርነት የዓለምን የግጭት ካርታ ሊቀይር የሚችል ጂኦፖለቲካዊ ትሪያንግል ሊያዋልድ ይችላል።

እነዚህ ክስተቶች ብቻቸውን አይደሉም። እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው። አንድ ላይ ሆነው አዲስ እና አደገኛ የባለብዙ ግንባር ቀውሶች ሊቀፈቅፉ ይችላል። እስራኤል በኢራን ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች ላይ የሰነዘረችው ተደጋጋሚ ጥቃት በቋፍ ላይ የሚገኘውን ቀጣና ይበልጥ ያተራምሰዋል። ኢራን በእነ ሐማስ ሔዝቦላህና በሁቲ ሚሊሻዎች፤እስራኤል በቀጥታ ቀዩን መስመር እየጣሱት ነው።

መካከለኛው ምሥራቅ በእስራኤልና በኢራን እየታመሰ፣አሜሪካ ዓለምን በታሪፍ ናዳ ንግድ ጦርነት በዘፈቀችበት፣ትራምፕ በሎሳንጀለስ የገቡበት ቅርቃር ሳይለይ፣ራሽያ ለዩክሬን አስደንጋጭ ጥቃት የበቀል ርምጃ እየወሰደች ሳለ፤ እስራኤል በኢራን ላይ የወሰደችው ለዓመታት ሲጠናና ሲታቀድ የኖረ መብረቃዊ ጥቃት መካከለኛውን ምሥራቅና የአረቡን ዓለም እየናጠው ነው። ገና ከአሁኑ የነዳጅ ዋጋ አሻቅቧል። የሽርክና ገበያዎች ታውከዋል። ኢራን ከአሜሪካ ጋር እየተደራደረች እያለ ለምን ከጀርባ ተወጋች። ድርድሩስ የማዘናጊያ ስልት ይሆን፤ ወይስ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ትኩረታቸውን ከሰሞነኛው የትራምፕ ቀውስ እንዲያነሱ የተሸረበ ሴራ፤ ወይስ ዓለም ከጋዛ ዘር ማጥፋት ዓይኑን እንዲያነሳ የተፈጠረ አቅጣጫ ማስቀየሪያ፤ መልሱን ለእናንተ ልተወውና ወደ እስራኤል ጥቃት ልመለስ።

እስራኤል 200 ተዋጊ ጀቶችን በመጠቀም በተመረጡ 100 ኢላማዎች ላይ ማለትም በኢራን የኒውክሌር ሥፍራዎች እና የጦር አዛዦቿ ላይ ያነጣጠረ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸሟን የእስራኤል መከላከያ ኃይል አስታወቀ። በእዚህ ከባድ በተባለው ጥቃት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊ ሆሴይን ሳላሚ መገደላቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። እስራኤል ኢላማ ያደረግኩት ወታደራዊ ይዞታዎችን ነው ብትልም፤ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው በቴህራን የመኖሪያ ቤቶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው እና ከተገደሉትም መካከል ሰላማዊ ሰዎች ይገኙበታል።

በኢራን መዲና ቴህራን ከፍተኛ ፍንዳታ እየተሰማ መሆኑ፤የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ሀገራቸው በኢራን የፈጸመችው ጥቃት ‘ኦፕሬሽን ራይዚንግ ላየን’ (ዘመቻ አንበሳው አገሳ) ሲሉ የጠሩት አካል ነው። በተጨማሪም ኢራን ለእስራኤል የሕልውና ስጋት መሆኗን ተናግረዋል። ኢራን በምላሹ በቅርቡ አጸፋዊ የመልሶ ማጥቃት ልታደርስ እንደምትችል የገለጸችው እስራኤል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች።

የኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን፣ሆሴይን ሳላሚ በእዚህ ጥቃት ከተገደሉት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው። የሀገሪቱ የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ የነበሩት የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ፍሬይዱን አባሲ መገደላቸውን፤ፍሬይዱን አባሲ ለኢራን የኒውክሌር ማበልጸግ የአንበሳውን ድርሻ እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል።ሳይንቲስቱ ከእዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2010 በቴህራን ጎዳና ላይ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈው ነበር። ሌላው በእዚህ ጥቃት የተገደሉት የኒውክሌር ሳይንቲስት በቴህራን የሚገኘው የእስላሚክ አዛድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መህዲ ቴህራንቺ ናቸው።

ኢራን አሜሪካ የእስራኤልን ጥቃት ደግፋለች ስትል የከሰሰች ሲሆን፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው እንዳልተሳተፈች ገልጸዋል። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፤ ጥቃቶቹ እንደሚፈጸሙ እንደሚያውቁ ነገር ግን ሀገራቸው በጥቃቱ እንደሌለችበት፤ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ድርድር እንደምትቀጥል ተስፋ እንዳላቸው፤“ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ሊኖራት አይገባም እናም ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመመለስ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።

ኢራን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል የፈጸመችባትን ጥቃት እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርባለች። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱ “ የዓለምን ደህንነት ታይቶ ለማያውቅ ስጋት አጋልጦታል”። የእስራኤል ዋና አጋር አሜሪካ ለጥቃቱ መዘዝ ተጠያቂ እንደምትሆንም ነው ሚኒስቴሩ ያስጠነቀቀው። ጥቃቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለቱም ወገኖች “ከፍተኛ መቆጠብ” እንዲያሳዩ ሲጠይቅ፤ አውስትራሊያ በበኩሏ በእዚህ መልኩ ማገርሸቱ “አስጊ” ነው ብላለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ እስራኤል በኢራን ኒውክሌር ይዞታዎች ላይ ያደረሰችውን ጥቃት አውግዘው፤ ሁለቱም ወገኖች ቀጣናው ወደ ከፋ ጦርነት እንዳይገባ እንዲቆጠቡ ጥሪ አድርገዋል።

ጥቃቱ በኢራን ወታደራዊ እና የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ፤ በስድስት ዋና ዋና ወታደራዊ እና የኒውክሌር ቦታዎች ላይ ጥቃት የሰነዘረችው እስራኤል ተጨማሪ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች እየተባለ ነው:: የእስራኤል ጥቃትን ተከትሎ የአየር ክልሏን የዘጋችው ኢራን ከቀናት በፊት የእስራኤል ምስጢራዊ ሰነዶች በእጇ እንደገቡ ስትገልፅ መቆየቷ ይታወሳል:: ኢራን እስራኤል ከባዱን ዋጋ ትከፍላለች የሚል ማስጠንቀቂያ ስትሰጥ፤ እስራኤል በበኩሏ ጥቃቱ ሊቀጥል እንደሚችል አስጠንቅቃለች:: የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሁሴን ሳላሚ በእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት ተገደሉ። ዋና አዛዡ በቴህራን መገደላቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። አዛዡ የተገደሉት እስራኤል ሰኔ 5 ሌሊት ላይ በፈጸመችው ጥቃት ነው።

ኔታንያሁ በቪዲዮ መግለጫቸው “ የኢራን ኒውክሌር ስጋት እስኪወገድ ድረስ ይህ ዘመቻ ለበርካታ ቀናት ይቀጥላል”። አክለውም እስራኤል “ለእስራኤል ሕልውና የኢራንን ስጋት ለመቀልበስ ያለመ ወታደራዊ ዘመቻ” መጀመሯን ገልጸዋል። የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ታስኒም እንደዘገበው ከሆነ፤ “ የእስራኤል ጥቃቶች በኢራን ዋና ከተማ የሚገኙ በርካታ የመኖሪያ ሕንፃዎችን ያነጣጠሩ ሲሆን፤ ይህም የንጹሐንን ሞት አስከትሏል” ብሏል። በረራዎች በኢማም ኮሜይኒ ዓለም አቀፍ የቴህራን አውሮፕላን ማረፊያ መታገዳቸውን ኤጀንሲው አክሏል።

እስራኤል በኢራን የፈጸመችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ፤ ኢራን ከ100 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖቾችን) ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ። የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጄኔራል ኤፊ ደፍሪን፤ የእስራኤል ከተሞችን ለመምታት ዒላማ አድርገው የተወነጨፉትን ድሮኖች ለማምከን እየሠራን ነው ማለታቸውን ኤቢሲ ዘግቧል። የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በኢራን ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል የአየር ክልል ተዘግቷል፤ የጆርዳን አየር ክልልም በተመሳሳይ መዘጋቱ ነው የተገለጸው።

እስራኤል ከባድ ነው የተባለውን የአየር ላይ ጥቃት በኢራን ላይ መፈጸሟን እና ጥቃቱ በኢራን ወታደራዊ እና የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል። በስድስት ዋና ዋና ወታደራዊ እና የኒውክሌር ቦታዎች ላይ ጥቃት የሰነዘረችው እስራኤል፤ ተጨማሪ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች ተብሏል። በእስካሁኑ ጥቃት የኢራን ሪቮሊሽነሪ ጋርድ ኃላፊ የሆኑት ሁሴን ሳላሚን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የጦር መሪዎች እና ስድስት ሳይንቲስቶች መገደላቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የእስራኤል ጦር በኢራን የተለያዩ አካባቢዎች የኒውክሌር ኢላማዎችን ጨምሮ ከአስር በላይ የሚሆኑ ወታደራዊ ኢላማዎችን መምታቱን ይፋ አድርጏል። ጥቃት ከተሰነዘረባቸው ቦታዎች መካከል በሀገሪቱ መሐል በሚገኘው ናታንዝ የኢራን ዋና የዩራኒየም ማበልጸጊያ ተቋም ይገኝበታል። የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ እንዳሳየው፤ ይህ ተቋም በጥቃቱ ስለመመታቱ ምስሎችን አስደግፎ አሳይቷል:: በእርግጥ ይህ ተቋም የዩራኒየም ጋዝን ለማበልጸግ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች የሚሠሩበት በመሆኑ ከመሬት በታች የተገነባ ነው:: ይሁን እንጂ ይህ ተቋም ከጥቃቱ አለመትረፉ የእስራኤል ጥቃት እጅግ ከባድ እንደነበር ማሳያ ነው ይላሉ ባለሙያዎች::

የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በቴህራን ዙሪያ ቢያንስ 6 ወታደራዊ ካምፖች እንዲሁም የወታደራዊ አዛዦች መኖሪያ ቤቶች መመታታቸውን አስነብቧል:: እንዲሁም በርካታ የመኖሪያ ሕንፃዎች መጎዳታቸውን የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ ዘግቧል። ይህን መረጃ የሚያጠናክረው ደግሞ፤ የኢራን ጦር ኃይሎች መሪዎች መገደላቸውን የኢራን መንግሥት ቲቪ ማረጋገጡ ነው። የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ሆሴን ሳላሚ፣ የኢራን ጦር ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጀነራል መሐመድ ባገሪ በእዚህ ጥቃት መገደላቸው እየተዘገበ ነው:: ቢያንስ ስድስት የኒውክሌር ሳይንቲስቶችም በእዚህ ጥቃት እንደተገደሉ እየተገለጸ ነው::

የኢራን የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት የቀድሞ መሪ ፌሬይዶን አባሲ እና ቴህራን የሚገኘው ኢስላሚክ አዛድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መሐመድ መህዲ ቴህራቺ እንዲሁ መገደላቸውን የኢራን መንግሥት ቲቪ ገልጿል። ኢራን በእስራኤል ግዛት ላይ የምትሰነዝረው የአጸፋ ምላሽ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የኢራን አብዮታዊ ዘብ አስጠንቅቋል። ኢራን የደረሰባትን ጥቃት ተከትሎ የሀገሪቱ መሪ አያቶላ ሰይድ አሊ ካሚኒ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ማስጠንቀቂያውን አውጥቷል።

አያቶላ በመልዕክታቸው፤ ኢራን የአጸፋ ምላሿ ከባድ እና “እስራኤልን የሚያጸጽት” ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። ይህን ንግግር ተከትሎ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ለእስራኤል “አስከፊ” ምላሽ በመስጠት በፈጸመችው ጥቃት እንድትጸጸት ያደርጋል ማለቱን የኢራን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል አቦልፋዝል ሸካርቺ ኢራን “ከባድ” አጸፋዊ ርምጃ እንደምትወስድ ተናግረዋል። ብርጋዴር ጀነራሉ እስራኤል ሌሊቱን የፈጸመችው ጥቃት በአሜሪካ ድጋፍ መሆኑን በመግለጽ ሁሉም “ የእጃቸውን ያገኛሉ” ብለዋል።

የእስራኤል ጦር በኢራን የተለያዩ አካባቢዎች የኒውክሌር ኢላማዎችን ጨምሮ ከአስር በላይ የሚሆኑ ወታደራዊ ኢላማዎችን መምታቱን ይፋ አድርጏል። እስራኤል በኢራን የፈጸመችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ፤ ኢራን ከ100 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።

እስራኤል የኢራን የኒውክሌር ሳይንቲስቶችን እና የጦር አዛዦችን ስለገደለችባት ጥቃት የምናውቀው በሚል ቢቢሲ ባጋራው መረጃ፤ እስራኤል የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ማዕከል ላይ ያነጣጠረ ነው ያለችውን ጥቃት ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ በመላው ኢራን በከፍተኛ ሁኔታ ፈጽማለች። በእዚህ ጥቃት የሀገሪቱ ጦር ኃይሎች አንደኛው ኃያል ቅርንጫፍ የሆነውን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ሆሴይን ሳላሚ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲሁም ስድስት የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መገደላቸውን የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ዘግቧል። ሕጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎችም በእዚህ የእስራኤል ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል። ቢቢሲ እነዚህን ዘገባዎች በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

ኢራን በምላሹ 100 ያህል ድሮኖችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን እና ሁሉም መክሸፋቸውን የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል። በኢራን መዲና ቴህራን ፍንዳታዎች የተሰሙት በሀገሬው ሰዓት አቆጣጠር ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ ሌሊት 9፡30 ገደማ ነው። የኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን በቴህራን የሚገኙ የመኖሪያ ስፍራዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው እና ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን ምሥራቅ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘግበዋል። በእስራኤል ነዋሪዎች በተመሳሳይ ሰዓት የአደጋ ጊዜ የስልክ ማስጠንቀቂያዎች ደርሷቸዋል።

የመጀመሪያው ጥቃት ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ ከዋና ከተማዋ በስተደቡብ 225 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ናታንዝ የኒውክሌር ጣቢያ ፍንዳታ መሰማቱን የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ዘግቧል። የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ፣ ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) የናታንዝ የኒውክሌር ማዕከል ጥቃት እንደተፈጸመበት አረጋግጧል። ኤጀንሲው ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ በናታንዝ ጣቢያ የጨረር መጠን እንዳልጨመረ የኢራን ባለሥልጣናት እንዳሳወቁት ገልጿል። የኤጀንሲው ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ የኒውክሌር ተቋማት በፍጹም ጥቃት ሊፈጸምባቸው አይገባም።

እንደ እነዚህ ዓይነት ጥቃቶች በኒውክሌር ደህንነት፣ በጸጥታ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ አንድምታ አላቸው ብለዋል። ኃላፊው ለቦርድ አባላት በሰጡት መግለጫ፤ “ የኒውክሌር ተቋማትን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ወታደራዊ ርምጃ በኢራን፣ በቀጣናው እና በሌሎች አካባቢዎች ከባድ መዘዝ የሚያስከትል ነው” ብለዋል።

ኔታንያሁ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የኢራንን የኒውክሌር መሣሪያ ፕሮግራም በግልጽ በመጋፈጣቸው” ምስጋናቸውን አቅርበዋል። እስራኤል ለዘላለም ትኑር ! አሜሪካ ለዘላለም ትኑር ! የሚል መፈክር አሰምተዋል። ኢራን ከአንድ ዓመት በፊት ለተፈጸመባት ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ መስጠቷ ይታወሳል። ዘንድሮም ተመሳሳይ ምላሽ እንደምታደርግ ይጠበቃል። ለመሆኑ የአምናው ምላሿ እንዴት ያለ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፋለች። ጥቂቶቹ የእስራኤልን ኢላማዎች መምታት ችለዋል።

ኢራን ባለፈው ሚያዚያ እስራኤል ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን እና የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል። ያ ጥቃት በቀደሙት ጥቂት ወራት ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ሆኗል። የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣናት በጊዜው ጥቃቱ ያለቀ ይመስላል፤ “ለጊዜውም ቢሆን” ከወደ ኢራን ምንም ስጋት የለም ብለዋል። ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም። ሆኖም ኢራን ጥቃቷን የምትቀጥል ከሆነ መዘዙ የከፋ ይሆናል ሲሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ማስጠንቀቃቸው አይረሳም።

ኢራን ወደ እስራኤል 180 የሚጠጉ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን የእስራኤል ጦር በሰዓቱ አስታውቋል። ይህም ከእዚህ በፊት ወደ እስራኤል 110 የሚጠጉ የባለስቲክ ሚሳኤሎች እና 30 ክሩዝ ሚሳኤሎች ከተተኮሱበት የሚያዚያው ጥቃት በመጠኑ የከፋ ያደርገዋል። በእስራኤል ቴሌቪዥን ጣቢያ የተቀረጸ ምስል ምሽት 1፡45 አካባቢ አንዳንድ ሚሳኤሎች በቴል አቪቭ ሰማይ ላይ ሲበሩ ታይተዋል። አብዛኛዎቹ ሚሳኤሎች በእስራኤል የአየር መከላከያ ዘዴዎች እንዲከሽፉ መደረጉን የእስራኤል የደህንነት ባለሥልጣን ገልጾ፤በእየሩሳሌም የሚገኝ የቢቢሲ ዘጋቢ በበኩሉ፤ አንዳንድ ወታደራዊ ካምፖች ተመትተው ሊሆን እንደሚችል እና ሬስቶራንቶች እና ትምህርት ቤቶች ደግሞ መመታታቸውን ገልጿል።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ (አይአርጂሲ) በበኩሉ፤ 90 በመቶ የሚሆኑ ሚሳኤሎች ዒላማቸውን እንደመቱ፤ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ውለዋል ሲልም አክሏል። የአይአርጂሲ ምንጮች በወቅቱ እንዳሉት ከሆነ፤ ሦስት የእስራኤል ወታደራዊ ካምፖች በጥቃቱ ዒላማ ተደርገዋል። በዌስት ባንክ በሚገኘው ኢያሪኮ ከተማ የሚገኘው የፍልስጤም የሲቪል መከላከያ ባለሥልጣን በበኩሉ፤ በኢራን የሚሳኤል ጥቃት አንድ ሰው መሞቱን አስታውቋል። የከተማውን አስተዳዳሪ ሁሴን ሃማኤልን ያነጋገረው ኤኤፍፒ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ከሆነ፤ ግለሰቡ የሞተው በሮኬት ስብርባሪዎች ተመትቶ ነው። የእስራኤል ባለሥልጣናት ግን በደረሰው ጥቃት ምንም ዓይነት ከባድ ጉዳት እንዳልደረሰ ቢገልጹም፤ የሀገሪቱ የሕክምና ባለሙያዎች ግን ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።

ኢራን ለምን እስራኤልን አጠቃች?

ጥቃቱ የተሰነዘረው እስራኤል አንድ ከፍተኛ አዛዧን እና በአካባቢው በኢራን የሚደገፉ የሚሊሻ መሪዎችን መግደሏን ተከትሎ መሆኑን አይአርጂሲ ገልጿል። ይህም ከቀናት በፊት በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ የተገደሉትን የሄዝቦላህ መሪ የሆኑት ሀሰን ናስራላህ እና የአይአርጂሲ አዛዥ የሆኑት አባስ ኒልፎሮሻን የሚመለከት ነው። በሐምሌ ወር ደግሞ ቴህራን ውስጥ የሐማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ መገደላቸውንም ጠቅሷል። እስራኤል ከሃኒዬህ ሞት ጀርባ መኖሯን ባትቀበልም፤ ተጠያቂ እንደሆነች በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል በወቅቱ እንደተናገሩት ከሆነ፤ የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜህኒ የሚሳኤል ጥቃቱ እንዲፈጸም በቀጥታ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ኢራን እስራኤልን የሚቃወሙ ቡድኖችንም ለዓመታት ስትደገፍ ቆይታለች። ኢራን የሕልውናዋ ስጋት መሆኗን እስራኤል ታምናለች። በቴህራን ላይ ድብቅ ዘመቻዎችን ለዓመታት ስታካሂድ ቆይታለች። የኢራንን የአጸፋ ጥቃት እስራኤል በአይረን ዶም አክሽፋለች። እስራኤል የተራቀቀ የአየር መከላከያ ዘዴዎችን ትጠቀማለች። ከእነዚህ ውስጥ በጣም የሚታወቀው አይረን ዶም ነው። በሐማስ እና በሄዝቦላ የሚተኮሱትን የአጭር ርቀት ሮኬቶችን ለማጨናገፍ በሚል የተሠራ ነው። ከኢራን የተሰነዘረውን ጥቃት ለመከላከል ጥቅም ላይ ውሏል።

ሌሎች ሀገሪቱ ያሏት “ላቅ ያሉ” የመከላከያ ሥርዓቶች የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለማክሸፍ ጥቅም ላይ ውለዋል። እንዲሁም በአሜሪካ እና በእስራኤል በጋራ የሚመረተው የዳዊት ወንጭፍ (ዴቪድስ ስሊንግ) ከመካከለኛ እስከ ረዥም ርቀት የሚጓዙ ሮኬቶችን እንዲሁም የባለስቲክ እና የክሩዝ ሚሳኤሎችን ለማክሸፍ ጥቅም ላይ ይውላል። የረዥም ርቀት የባለስቲክ ሚሳኤሎች ለመከላከል ደግሞ እስራኤል አሮው 2 እና አሮው 3 የተባሉ ሥርዓቶችን ትጠቀማለች።

በዓለም ላይ በኢራን እና በእስራኤል መካከል ያለውን ጠላትነት ያህል የመረረ እና የከረረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት የሉም ቢባል ማጋነን አይሆንም። በእዚህም የተነሳ ሁለቱ ሀገራት በቀጥታ እና በእጅ አዙር አንዳቸው ሌላኛውን ለመጉዳት ሲጥሩ ቆይተዋል። የኢራን መሪዎች ጠላት የሚሏት እስራኤል ከምድረ ገጽ እንድትጠፋ እንደሚሹ በይፋ ከመናገር አልፈው በቅርበት ሰላም የሚነሷትን ቡድኖች ሲደግፉ ቆይተዋል። የእስራኤል ፖለቲከኞችም እንደ ዋነኛ ስጋት የሚመለከቷትን ኢራን ሳትቀድማቸው ለመቅደም በሚል ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጥቃት ይፈጽሙባታል።

እስራኤል ቁልፍ የምትላቸውን የኢራን ወታደራዊ ዒላማዎችን፣ ባለሥልጣናት እና ሳይንቲስቶችን አድብታ ስታጠቃ፤ ኢራን ደግሞ በእስራኤል ዙሪያ በሚገኙ ሀገራት ውስጥ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ሰላም ስትነሳት ቆይታለች። ከእነዚህም መካከል የፍልስጤሙ ሐማስ፣ የሊባኖሱ ሔዝቦላህ፣ የየመኑ ሁቲ ቡድኖች በኢራን እየተደገፉ ጥቃቶችን በእስራኤል ላይ የሚፈጽሙ ናቸው። በተለያዩ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ፣ የሥልጠና እና የትጥቅ ድጋፎችን ከኢራን እንደሚያገኙ ይነገራል። ቡድኖቹ ባሉባቸው ሀገራት ውስጥ ካላቸው የፖለቲካ እና ወታደራዊ ተሳትፎ ባሻገር ዋነኛ ዒላማቸው እስራኤል መሆኗን በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ያመለክታሉ። ከሁለት ዓመት በፊት ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመው ድንገተኛ እና ከባድ ጥቃት የእስራኤልን እስካሁን ያልተቋረጠ መጠነ ሰፊ የአጸፋ ጥቃትን አስከትሏል።

ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You