አምራች እና ሸማችን ማን ይታደጋቸው?

ባለፈው አርብ በማኅበራዊ መገናኛ አውታር አንድ ቪዲዮ ሲዘዋወር አየሁ። በቪዲዮው ላይ አንድ ወጣት ገበሬ ቲማቲም ስንት እንደሚሸጡ ተጠይቆ 3 ብር እየሸጡ እንደሆነ ተመለከትኩ። የተጋነነ ስለመሰለኝ ብዙም አላመንኩም ነበር። ጉዳዩን ለአንድ የሥራ ባልደረባዬ ነገርኩት፤ 3 ብር መሸጡን እርግጠኛ ባይሆንም ገበሬዎች 8 ብር እየሸጡ እንደሆነ ግን ከቤተሰቦቹ እንዳረጋገጠ ነገረኝ።

ሌላም ማሳያ ልጨምር። ባለፈው እሁድ ሌላ ቪዲዮ አየሁ፤ ይህኛው ደግሞ ደላላ ያጠራቀመው ቲማቲም ተበላሽቶ ሲጣል የሚያሳይ ነው። ብዙ ሰዎች ‹‹ተመልከቱ የደላላን ክፋት! በዘይትና በጤፍ የለመዱትን ምርት የመደበቅ ልማድ በቲማቲም እንደግማለን ብለው ተበላሽቶ አከሰራቸው!›› እያሉ ሰዎች በቀልድም በቁም ነገርም አስተያየት ሲሰጡበት ነበር።

ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ ውስጥ ቲማቲም ጠየቅኩ፤ ምንም እንኳን ከአካባቢ አካባቢ፣ ከንግድ ቤት ንግድ ቤት ቢለያይም 35 ብር አሉኝ። አምራቾች ግን 3 ብር እየሸጡ ነው። ግዴለም! 3 ብር የተባለው ምናልባት የተጋነነ ሊሆን ይችላል እንበልና 8 ብር የሚሸጡትን እንያዝ። ከአዲስ አበባ 300 ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ የሚመረት ምርት በአንድ ኪሎ ብቻ የ27 ብር ልዩነት አለው።

በቀጥታ ገበሬዎች በሚሸጡበት ዋጋ አዲስ አበባ ውስጥ ይሸጥ ማለቴ አይደለም፤ መጓጓዣን ጨምሮ ብዙ ወጪዎች እንዳሉት ግልጽ ነው። ዳሩ ግን ቢያንስ በአንድ ኪሎ ከሦስት አጥፍ በላይ ሲሆን አምራቹም ሸማቹም እየከሰረ መሆኑን ያሳያል።

ብዙው የአዲስ አበባ ነዋሪ ምርት ሲወደድበት ምርት ጠፍቶ ይመስለዋል። ዳሩ ግን ነገሩን የሚያበለሻሸው በመሃል ያለ ደላላ ነው። ቲማቲምን እንደ ማሳያ የወሰድነው ከገጠመኝ ለመነሳት እንጂ በሁሉም የግብርና ምርቶች ተመሳሳይ ችግር ነው ያለው። አምራቹም ሸማቹም እየተጎዱ ነው። በተለይ አምራቹ ገበሬ ላቡን ጠብ አድርጎ አምርቶ አንድ ኪሎ 8 ብር ይሸጣል። የላቡን ዋጋ አያገኝም። ገበሬው ገንዘብ ለማግኘት ያለው ብቸኛ የገቢ ምንጭ ያመረተውን ምርት መሸጥ ነው። ዳሩ ግን ፈጣሪንም ሕግንም የማይፈራ ህሊና ቢስ ደላላ ያጭበረብረዋል። ገበሬውን ‹‹አዲስ አበባ ውስጥ 10 ብር ነው የሚሸጥ›› ሊለው ይችላል። አዲስ አበባ ያለውን ሸማች ደግሞ ‹‹ከገበሬው 20 ብር ነው የማመጣው›› ሊለው ይችላል። የአዲስ አበባ ነዋሪ እና 300 ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ ያለ አምራች ገበሬ የማይተዋወቁ፣ የማይገናኙ ነው የሚመስለው።

አምራቹ ገበሬ ዓመቱን ሙሉ የለፋበትን ምርት ሸጦ የሚፈልገውን ጉዳይ መሸፈን አይችልም። በተመሳሳይ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራው የከተሜው ነዋሪ የሚያገኛትን ገቢ በአንድ ነገር ብቻ ይበትናል። የሀገሩ የጀርባ አጥንት የሆነውን አምራች ገበሬ አመስግኖ እንዳይኖር ደላላ የሚባል ደንቃራ ተጋርጦበታል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የከተሜው ነዋሪ ‹‹ምነው ገበሬዎች እንዲህ ጨከኑ?›› እያለ ሊያማርር ይችላል፤ ገበሬው ከከተሜው ሸማች በላይ እየተጎዳ መሆኑን አያውቅማ!

አንድ ምርት ተወደደ ሲባል የሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ‹‹የምርት እጥረት የለም›› የሚል መግለጫ ይሰጣል። ዳሩ ግን ማንም አያምነውም። እውነታው ግን ገበሬው ያመረተውን ምርት በርካሽ ዋጋ ለደላላ እየሸጠ መሆኑ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት መግለጫ የማይታመንበት ምክንያት በድለላ ሴራው ውስጥ ራሳቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ስለሚኖሩበት ነው፤ ባይኖሩበት እንኳን ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል ስለማያደርጉ ነው። ፍተሻ ተደረገ ተብሎ የተደበቀ ምርት ይገኛል። ይህ በየዓመቱ የተለመደ ነው። ዳሩ ግን የማያዳግም እርምጃ ሲወሰድ እና ዳግም እንዲህ ዓይነት ጥፋት እንዳይሠራ በቂ ክትትል ሲደረግ አይስተዋልም። በዚህም ምክንያት አምራች ገበሬ እና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራው ሸማች በችግር ይሰቃያሉ፣ አልጠግብ ባይ ደላላ ግን ብቻውን ያጋብሳል።

እንዲህ ዓይነት ድርጊት ከፍተኛ ቁጥጥር ካልተደረገበት የመንግሥትን እና የሀገርን ገጽታ ያበላሻል። በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራው ሸማች በኑሮ ውድነት መንግሥትን እና ሀገሩን ያማርራል፤ አምራች ገበሬውም ምርቱን ሸጦ በገንዘቡ ማግኘት ያለበትን አገልግሎትና የፋብሪካ ምርት መግዛት ስለማይችል እሱም በኑሮ ውድነት መንግሥትን እና ሀገሩን ያማርራል። አምራችም ሸማችም በኑሮ ውድነት ይሰቃያሉ፤ በመሃል ተጠቃሚው ደላላ ብቻ ይሆናል ማለት ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚነት ‹‹ምርትን ከገበሬው›› በሚል ቅዳሜና እሁድ በብዙ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የሚከናወን የምርት ሽያጭ ገበያ አለ። ይህ ሊመሰገን የሚገባ እና ብዙዎችን ከአምራቾች ጋር ያገናኘ ነው። ይህ ጥሩ ሆኖ ሳለ፤ ደላሎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ከፍተኛ ቁጥጥር ግን መደረግ አለበት። መንግሥት ደላላን የመቆጣጠር ሥራ ካልሠራ ከኑሮ ውድነት ወቀሳ አይድንም። የኑሮ ውድነትን በድርቅ እና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ማሳበብ መንግሥትን ከተወቃሽነት አያድነውም። ምርት ሳይጠፋ ሸማቹም አምራቹም እየተሰቃዩ ሊኖሩ አይገባም።

በነገራችን ላይ ይህ አሁን ያለንበት ወቅት የመኸር ወቅት ነው። የመኸር ወቅት ማለት ደግሞ የግብርና ምርቶች የሚረክሱበት ነው። ዳሩ ግን የግብርና ምርት የረከሰው ለገበሬው ብቻ ነው፤ ሸማቹ ዛሬም በድሮው ዋጋ (እንዲያውም አንዳንዱ ምርት ጨምሮ) ነው እየገዛ ያለው። በርካሽ እየገዛ ያለው ደላላው ብቻ ነው።

ተማሪ እያለሁ ከአምራች ገበሬዎች የሰማሁት አንድ ትዝብት ብዙ ጊዜ ትዝ ይለኛል። ገበሬው ለአንዳንድ ጉዳዮች ከተማ ቦታ ይሄዳል። ምግብ ቤት ገብቶ ምግብ ያዛል። የሆነ ወቅት ላይ ጤፍ ተወደደ ተብሎ የምግብ ዋጋ ይጨምራል። ትንሽ ቆይቶ የጤፍ ዋጋ ይቀንሳል፤ ዳሩ ግን የምግቡ ዋጋ አይቀንስም። ይህን የሚያጋጥመው ገበሬ ጤፉን በርካሽ መሸጡን እያስታወሰ ‹‹ባለፈው ጤፍ ተወዶ ነው አላችሁ፤ ምነው ጤፉ ሲቀንስ እናንተ የማትቀንሱት? እያለ በቀልድም በቁም ነገርም ይናገራል። ‹‹ኧረ ክፉ ቀን አትጥሩ!›› እያሉ ወቀስ ያደርጋሉ።

የገበሬውን ትዝብት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማረጋገጥ እንችላለን። የሆነ ወቅት ላይ ቲማቲም ተወደደ ተብሎ (እስከ 80 እና 90 ብር ደርሶ ነበር) የቲማቲም ምግቦች ተወደዱ። እነሆ ዛሬ ከግማሽ በታች ቀንሶ እስከ 35 እየተሸጠ ነው። የቲማቲም ምግቦች ግን በዚያው ዋጋ ናቸው። ሲጨምር ይጨምራሉ፤ ሲቀንስ ግን አይቀንሱም።

ከምንም በላይ ግን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የደላላ ጉዳይ ነው። ጥቂት ደላላ ብቻ እየተጠቀመ አምራች ገበሬ እና ሸማች ማኅበረሰብ በኑሮ ውድነት ሊሰቃይ አይገባም!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን  የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You