ስውሯ እጅ በዓድዋ!

ስውር እጅ፣ ለማንም ሰው የማትታይ፤ አርበኛውን በጥበብ መንፈስ የምትሰውር። ይህቺ ምትሀት በኢትዮጵያ አርበኞች ዘንድ ነበረች። ለመሆኑ ማናት?፤ እስቲ ለአፍታ እናሰላስላት…በዓድዋ ጦርነት፤ በዱር በገደሉ ሁሉ እየገባች ከአርበኛው ጋር ወድቃ ስትዋደቅ፤ ወግታ ስታዋጋ የነበረችው ይህች ተዓምረኛ እጅ እራሷ ጥበብ ነበረች። እሷም እንዲህ ነበር የምትለው “እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፤ ወንድም እህት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፤ ሀገር የሞተች እለት ወዴት ይደረሳል!”

የዓድዋ ድል ሲወሳ፣ የአርበኞች ድል ሲነሳ ኪነ ጥበብ ከተረሳች ነገሩ ሁሉ ተበላሸ። ዓድዋ የቆመበት መሰላል ዘመናዊ የጦር መሳሪያ አሊያም ቴክኖሎጂ ሰራሽ መከላከያ አልነበረም። አንድና አንድ ከአርበኛው ዘንድ የነበረው ነገር የጥበብ እንፋሎት፤ ስውር የኃይል ሚዛን ብቻ ነበር። በእጅ የጨበጡት የጦር መሳሪያ ሳይሆን በልብ ያነገቡት ጥበብ ዘራሽ ወኔና የሀገር ፍቅር ብቻ። ይህ የጥበብ ውለታ እንዴት ይረሳል ብንልም፤ እውነታው ግን ተረስቷል። አሊያም ተዳፍኖ እንዲቀር ተደርጓል። በዓድዋ ሰማይ ላይ፤ የኪነ ጥበብ ውለታ በጦርነቱ ወቅት ብቻ አይደለም። ከዚያም በኋላ የዓድዋ ስሜት ሳይበርድ ሳይባረድ እንደነበረው ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬም ድረስ ከነሙሉ ወዘናው እንዲቆይ በማድረጉም ጥበብን የሚስተካከላት የለም።

የዓድዋ ትውስታ በስሜት ማዕበል እንዲንጠን እያደረገ ያለው ነገር ምንድነው? ብለን በመጠየቅ ግራና ቀኝ፤ ኋላና ፊት ብንዞር የምናገኛት ይህችኑ ጥበብን ነው። “ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ” ቢሉ፤ ስለዚህ የኪነ ጥበብ ምትሀት በወቅቱ ከነበሩት አርበኛ አባቶች አፍ ብንሰማውማ እንዴት ያለ የአዕምሮ ልቀትና የጥበብ ብስለት የነበራቸው እንደነበር በቅጡ እንረዳው ነበር። የስውሯን እጅ አደገኝነት እራሱ ፋሽስቱ በአንክሮ ተመልክቶታል።

መጀመሪያ አካባቢ የኢትዮጵያ አርበኞች እንዲያ በግጥምና በአዝማሪው ቅኝት ሲነሆልሉ፤ ሲሸልሉና ሲፎክሩ፤ ቀረርቶውን እየነፉ በጠላታቸው ላይ ሲደነፉ፤ በንቀት ተመልክቶ እንደ እብደት ቋጠሮ ሲስቅ ሲሳለቅባቸው ነበር። ነገሩንም ከቁብ አልቆጠረውም። ይህን ደህና አድርጎ የተረዳው ከሽንፈቱ ማግስት ነበርና ከዓመታት በኋላ ተመልሶ ለዳግም ወረራ በመጣበት ወቅት፤ የበቀል ክንዱን ካሳረፈባቸው ስፍራዎች አንዱ የኪነ ጥበብ መንደር ውስጥ ነበር። ከወደ መርካቶ አካባቢ በነበሩ ቁጥራቸው በውል ባይታወቅም ከ 120 በላይ የሆኑ አዝማሪያንን ሰብስቦ፤ በአንድ ጀንበር ጨፍጭፏቸዋል። በአጋጣሚ የሆነ አይደለም፤ ጥበብ እያታለለች ያጠጣቻቸውን፤ የያኔውን መራራ የሽንፈት ገፈት፤ ጠረኑ ከስሜት አፍንጫቸው ላይ ሽው እያለ በአዕምሯቸው ሲመላለስ ስለነበረ ነው። በዳግም ወረራቸው ወቅት በቀልና ጭካኔን ከእልህ ጋር በጥብጠው የሞትን አሲድ ከአዝማሪዎቹ ፊት ላይ ደፉት። እናስ ከዚህ ተግባራቸው በላይ ለጥበብ ነቃሽ ሆኖ የሚቀርብ ምን አለና።

በጥበብ ቤት፤ በኪነ ጥበብ ጓዳና ሳሎን ዓድዋን የማናገኝበት አሊያም ደብዝዞ የሚታይበት አንድም ስፍራ አናገኝም። ዓድዋ ላይ ጥበብ ነበረች ከማለት፤ ዓድዋ እራሱ ጥበብ ነበር ማለቱ ይቀላል። ትዕይንቱ በራሱ የመድረክ ላይ ትወናና የአንድ የመጽሐፍ ድርሰት እንጂ የገሀድ ታሪክ የማይመስል ነው። ታዲያ ይህ ዓድዋ የሌለበት ኪነ ጥበብ የት አለና…በሙዚቃው ገበታ፤ በቲያትሩ መሶብ፤ በግጥሙ አቁማዳ፤ በልብወለዱ ሰፌድ፤ በስዕሉ ትሪ…በሁሉም ቦታ ዓድዋ ከነመንፈሱ አለ። ምናልባትም ቅር ሊለን የሚችል አንድ ነገር ቢኖርም ከፊልሙ ዘርፍ በአቅም ውስንነት የተነሳ እንደታሪክ ሊቀመጥ የሚችልና ከምንም ጋር ሳይቀየጥ እራሱን ችሎ የተሠራ የሙሉ ጊዜ ፊልም አለመኖሩ ነው።

ከዓድዋ ታሪክ ላይ ተቀንጭበው የተሠሩ አጫጭር ፊልሞች በርከት ብለው ልናገኝ እንችላለን፤ ዘጋቢ ፊልሞችንም እንዲሁ። ነገር ግን በገጸ ባህሪያቱ መሪነት የዓድዋን ሙሉ የታሪክ ትዕይንት ሊያሳየን የሚችል ፊልም እስካሁን ብቅ አለማለቱ ነው። ዓድዋ እንደታሪክ ግዝፈቱ፤ በአንድ ሰዓት ከ45 ደቂቃ አሊያም በ2 ሰዓታት የእይታ ጊዜ ብቻ የምንቋጨው አይደለም። ገቢሮቹ ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው። በዚህም እጅግ በበርካታ ምዕራፎችና ክፍሎች የታጨቀ ተከታታይ ፊልም ሊወጣው የሚችል ነው። እንሥራው ቢባል ከሚያስፈልገው የሰው ኃይልና ከገንዘብ እንዲሁም ከቴክኖሎጂ አንጻር ነገሩ ፈታኝና የማይሞከር ቢመስልም የማይቻልና ተስፋ ቢስ ግን አይደለም። ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድምና ይህ ለፊልሙ ዘርፍ ባለሙያዎች ሁሉ ትልቁ የቤት ሥራ ነው።

እግረ መንገዳችንን ወደዚህ ሀሳብ ሾልከን ገባንበት እንጂ ዋነኛው ርዕሰ ጉዳያችን ፊልሙ አይደለምና ወደ ጦርነቱ አውድማና ኪነ ጥበብ እንመለስ፡፡

ኧረ ለመሆኑ በዓድዋው የጦር አውድማ ጥበብ እንዴትስ ስውር እጇን አስገባች? ለዚህች ጥበብ የልባቸውን በር ከፍተው ነይ ግቢ ሲሉ ያስገቧት የመጀመሪያው ሰው አጼ ሚኒልክ ነበሩ። ጥበብ ሀገር ምድሩን ሞልታ በየሕዝባቸው ልብ ውስጥ ማደሪያዋን ስለመስራቷ አውቀውት ነበርና የመጀመሪያውን የእናት ሀገርህን አድን ጥሪያቸው በራሱ ኪናዊ ለዛን የተላበሰና ስሜት ቀስቃሽ፤ የሀገር ፍቅርን የሚያሟሽ ነበር። ጊዜው ጭጋጋማውም የክረምት ወራት አልፈው የሀገሬው ሕዝብ “ እዮሃ አበባዬ… መስከረም ጠባዬ!” የሚልበት ነበር። ከፈካችው ፀሐይ በታች የሚነፍሰው አየር ግን እንዲህ አልነበረም። የሐምሌ ነሀሴው፤ የጳጉሜው ጭጋግ ሲገፍ፤ ሌላኛው የፋሽስት ጭጋግ 22 ሺህ የሰለጠኑ ወታደሮችና በዘመኑ አሉ የተባሉ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ጭኖ ኢትዮጵያን ሊወር፤ ከኢትዮጵያ ደጅ ላይ ከትሟል።

ከላይ ታቹ ያኮበኩባል። ይህን የወራሪውን ድግስ የተመለከቱት ንጉስ አፄ ምኒልክ ያሰላስሉና መላውን ይዘይዱት ገቡ። ከዚያም 1888 ዓ.ም መስከረም ሰባት ቀን ወደ እንጦጦ ማርያም ደብር ወጡ። ጠላት ለሞቱ ለደገሰው ድግስ ቀባሪውን አርበኛ ጠሩለት።

አጼ ሚኒልክ፤ ስሜት ኮርኳሪውንም የጥበብ ነጋሪት እያስጎሰሙ እንዲህ ሲሉ አወጁ “ድንበር የሚገፋ፣ ኃይማኖት የሚያጠፋ-ተወኝ! ብለው እያደር እንደ ፍልፈል አፈር የሚገፋ ጠላት መጥቷልና፤ የአገሬ ሰው እስከ ዛሬ ያስከፋሁህ አይመስለኝም፤ እኔንም አስከፍተኸኝ አታውቅምና ዘመቻ በየካቲት ስለሆነ _እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ” በማለት ወደ ክተት ዘመቻው እንዲገባ ለሚወዳቸው ሕዝባቸው መልዕክቱን ሰደዱለት። የሚመጣውም ለንጉሡ ዙፋን ብሎ ሳይሆን ለራሱ ሲል መሆኑን እንዲያውቅና እንዳይቀር ሲሉ ደግሞ የሕዝባቸውን የልብ ትርታ ያውቁታልና በማያስነካው መጡበት። ሀገሩን ለሚወድ ስለ ሀገሩ፤ እርስት ያለው ስለ እርስቱ፤ ትዳር ያለው ስለ ሚስትና ልጆቹ፤ በኃይማኖቱ የማይደራደረውም ስለ ኃይማኖቱ ሲል ጠላቱን እንዲዋጋ ፍም እሳቱን ከቆሰቆሱት በኋላ በመጨረሻም ከሁሉ ወጥቶ አንድ ለቀረው “ወስልተህ የቀረህ እንደሆን… ማርያምን አልምርህም!” በማለት ከልቦናው አቆራኙት።

ይህን ሰምቶ የቀረ አልነበረም። ለቁጥር የሚታክት፤ ለአይንና ለጆሮ የማይታመን ሕዝብ፤ ከአራቱም አቅጣጫ፤ ጨርቄን ማቄን ሳይል ከእጁ የገባውን አፈፍ አድርጎ ይተም ጀመረ። ያውም ነጭ በነጭ፤ የክት ልብሱን ለብሶ ለሠርግ እንጂ ለሞት ድግስ የሚሄድ እስከማይመስል ድረስ በአንዳች ኃይል ተሞልቷል፡፡

ጥበብም ይሄኔ ነበር፤ ቁጣው የነብር የመሰለውን ጥቁር ሕዝብ ተመልክታ፤ እኔስ ለምን እቀር ስትል በሶምሶማ እየተከለች ወደ ዘመቻው መግባቷ። ስውሩን እጅ ታምረኛውን መዳፏን፤ በእያንዳንዱ አርበኛ የልብ ደም ስር ላይ ቀረጸችው። አርበኛው ያንን የሚያህለውንና በዘመናዊ ጦር ታጥቆ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለውን የፋሽስት ጦር ለመውጋት ቀርቶ ለመመከት እንኳን የሚሆን መሳሪያ ከእጁ አልነበረም። እርሱ ዘንድ የነበረው ነገር ቢኖር የሀገር ፍቅር፤ ወኔ፤ ጀግንነት፤ የልብ እሳትና መለኮሻው ጥበብ ብቻ ነበር።

ታዲያ ይህን ይዞ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ሞት ካነገበ ፋሽስት ጋር ለመጋጠም መወሰን እብደት አይደል? ፈረስ ላይ ተቀምጦና ለአደን የሚጠቀማትን የእጅ ጦር ይዞ፤ ከፊት ወደቆመው ታንከኛና መድፈኛ መገስገስ፤ ይሄስ ምን ይሉታል? ፋሽስቶቹ እራሳቸው እየተሳለቁ፤ “እኚህስ እብድ ናቸው” ብለውታል። ላዩን ለተመለከተማ እውነትም የእብደት ጥግ ይመስል ነበር። የሀገሬው ጀግና ግን ሙያ በልብ ብሎ፤ ከልቡ የታጠቀውን ማንም አላየም። ሞት የጎረሰው፤ የታንክ አፈሙዝ ከግንባሩ ተደግኖ እያየ፤ እሱ ግን እረቂቁ የጥበብ ኃይል ሰይፈው ባለችው ቁጥር፤ አይኑን ጨፍኖ በሀገሩ ፍቅር በተሰወረው ልቡ እየተመለከተ፤ ያ ሁሉ የተሰለፈው የጠላት ወታደር እንደ ገብረ ጉንዳን፤ ታንክና መድፉም እንደ ርችት መስሎ ይታየዋል። እናም ጎራዴውን ይዞ እየፎከረና እየሸለለ አንድ ወደፊት ይሄድና እልፍ ዘርሮ ይመለሳል። ለሀገሩ ሲል ሞትም ሕይወት ስለመሆኑ፤ በጥበብ ያደረች ነብሲያው ነግራዋለችና ስለምንም አይፈራም ነበር። ከአርበኛው ውስጥ ያለው ክብል የጥበብ ኒውክሊየር ቦንብ እየፈነዳ ጠላትን ይረመርመው ቀጠለ።

በጦሩ አውድማ የአዝማሪያኑ የወኔ ጦማር ገዘፍ ያለ ነበር። ጀግና ሲሞት፤ ጀግና እየተኩ ይበልጥ ያጀግኑታል። “ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፤ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ።” እያሉ ሲዋድሱ የሰሙት ባልቻ አባ ነፍሶ፤ ስውሯ እጅ ሄዳ የልብ ግርግዳቸውን ብትኮረኩር ጊዜ፤ እሳቱን ለኩሰው ሄደው የሰላቶውን ጦር የአመድ ክምር አደረጉት። በእያንዳንዱ የጠላት መውደቅ ውስጥ ስውሯ ጥበብ የወለደችው፤ የኪነ ጥበብ መርፌ ነበረበት። ይህን ጉድ የተመለከተ ነጭ ሁሉ፤ “ኢትዮጵያውያን፤ ቀድሞም ለጦርነት የተፈጠሩ ሕዝቦች ናቸው” ሲል በራሱ አንደበት መስክሮላታል፡፡

ጦርነት ማለት የታንክና የመድፍ ኳኳት ብቻ አለመሆኑንም የጦር ልሂቃኑ አርበኞቻችን በሚገባ አስተምረውታል። እንግዲህ ሰላቶውን ምን ይዋጠው…የሀፍረት ሸማውን እንደተከናነበ፤ ጅራቱን እንደተመታ ውሻ ጭራውን ቆልፎ ተመለሰ፡፡

ዓድዋ ትላንት ዓድዋ ዛሬ

ከጥበብ ታዛ በታች ዓድዋ ትላንት ዓድዋ ደግሞ ዛሬም ናት። ትላንት ባዶ እጁን ለወጣው ጀግና አርበኛ ስንቅ የነበረው ኪነ ጥበብ ዛሬም ደሙ አልቀዘቀዘም። በክረምቱ ከአዋሽ እስከ በሽሎ ወንዙ ሁሉ ሲሞላ፤ ባህሩን ከፍላ ዓድዋን ያሳለፈችው ያቺ ስውር የጥበብ እጅ፤ ዛሬም በበጋው ክንዷ ሳይዝል ዓድዋን እንደታቀፈችና እንዳዘለች አለች። ማየት ተስኖን አሊያም ላለማየት ፈልገን ካልሆነ በስተቀር ይህ አሁንም ይታያል። ዓድዋን እያወሱ መዘከሩን ኪነ ጥበብ ለአፍታ ዘንግቶት አያውቅም። አብነት ለሙዚቃ፤ የትላንትናው የአርበኞች ወኔና የሀገር ፍቅር ወላፈን ዛሬም ከልባችን፤ በጥበብ እንፋሎት እንዲንቀለቀል ያደረጉ ብዙ ቢኖሩም ሁለቱ ግን በልዩነት የሚነሱ ቁንጮ ናቸው። እነርሱም እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እና ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ) ናቸው፡፡

ሁለቱ ከያኒዎች ትላንትናን እንደዛሬ አድርጎ በማንጎራጎር፤ ዓድዋ ትላንትን ዓድዋ ዛሬ አድርጎ በማሳየት ማን እንደነርሱ ተብሎላቸዋል። ጂጂ “ትናገር ዓድዋ” በሚለው የሙዚቃ ሥራዋ አድናቆትን ብቻም ሳይሆን ልዩ የሆነ የትውስታ አሻራዋን ዓድዋን ከኪነ ጥበብ አዛምዳ አስፍራለች። የየካቲት 23 ቀን የዓድዋ መታሰቢያ የሆነችው፤ ይህቺ ልዩ ቀን እየቀረበች በመጣች ቁጥር “ትናገር ዓድዋ” የጂጂን ድምጽና መልክ ይበልጥ እያጎላች ትመጣለች። በዚህ ሰሞን ይህን ሙዚቃ አለመስማት ቅር ቅር ያሰኛል። ቢሄዱ በመንገድ፤ ቢቀመጡ በወንበር፤ ጆሮ ግን “የተሠጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፤ ሰው ተከፍሎበታል በደምና በአጥንት” የሚለውን ዜማ ሲንቆረቆር ለመስማት ይናፍቃል። በሙዚቃው ውስጥ ያሉ ስንኞች የዓድዋን የመስዋዕትነት ጥግ የሚያሳዩ ናቸው።

ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከነ ክብር ወዘናዋ እንድትኖር የተከፈለው “ዋጋ” በሚል ቃል ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑን ለማመልከት “ሰው ተከፍሎበታል” ስትል ድንቅ አገላለፅና ጠንካራ ቃላት ተጠቅማዋለች።

በዓድዋ ትላንት በዓድዋ ዛሬ፤ የጥበብን እጅ ስሞ ባንዲራዋን የተቀበለው ሌላኛው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ነው። “ጥቁር ሰው” በሚለው ሙዚቃው፤ የዓድዋን ትኩስ ደም ከደማችን አዋህዶታል።

“ዳኘው ያሉት አባ መላ ፊት ሃብቴ ዲነግዴ

ሰልፉን በጦር አሰመረው ፊት ሆኖ በዘዴ”

“ዓድዋ ሲሄድ ምኒልክ ኑ ካለ

አይቀርም በማርያም ስለማለ”

“አባቴ ምኒልክ፤ ድል አርጎ ሰራው የእኔን ልክ

ጊዮርጊስ ፈረሱ ላይ፤ ቆሞ ሳይ ድል ቀናኝ ሳልል ዋይ”

አባቴ ወኔውን ተኮሰው ምኒልክ ጥቁር ሰው” …እያለ ይቀጥለዋል። የዚህን ሙዚቃ የቪዲዮ ክሊፕ ለመሥራት፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠር የሰው ኃይል ተጠቅሟል። ወጪ የተደረገበት የገንዘብ መጠንም የሙዚቃውን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ክብረ ወሰን የሰበረ ነበር። ሥራውን ከልቡ ሠርቶታል። በዓድዋ ትላንት በዓድዋ ዛሬ፤ እኚህን ሁለቱን ፈርጦችን ጨምሮ፤ በግጥምና ስነ ጽሁፉ፣ በስዕሉ፣ በቲያትሩ፣ በሙዚቃው፣ በፊልሙ እንዲሁም በተቀሩት ሁሉ “እናመሰግናለን!” የምንላቸው ብዙዎች አሉን።

ስለ ዓድዋ የባህረ ሀሳብ ረቂቅ ባይዘጋጅለትም የሚለው ግን ይህንን ነው…በጦርነት ውስጥ፤ አሸናፊ ለመሆን ወሳኙ ነገር የስነ ልቦናና የአዕምሮ ረቂቅነት እንጂ የዘመናዊ ጦር ልህቀት አይደለም። ቀለሀና ፈንጂ ከመቀመም ይልቅ የማይታይና የማይጨበጠውን ውስጣዊ መሳሪያ መፈብረክ ብልህነት ነው። ኒውክሊየርና ሚሳኤል ከማስወንጨፍም፤ ስውሯን የስሜት ቦንብ በደም ስር ውስጥ መቅበር ይበልጣል። እናም፤ በዚህ የጦር ታክቲክ በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ አርበኞች ልብ ውስጥ የተሾመችው ጀነራል፤ ጥበብ ነበረች። ጥበብም ግዳጇን በአግባቡ ፈጸመችው። ክብር ለዓድዋ ጀግኖች!! ክብር ለስውሯ የጥበብ እጆች!!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

 አዲስ ዘመን የካቲት 21/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You