የዓድዋ ድል በየዓመቱ ሲከበር ሁሌም ለኢትዮጵያ የአሸናፊነትና የደስታ፤ ለጣሊያን ደግሞ የተሸናፊነትና የሀዘን ጊዜን የሚያስታውስ ነው። በኢትዮጵያውያኑና በመላ ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ የዓድዋ ድል የሚንቦገቦግ የነጻነት ቀንዲል ሲሆን፣ ለጨቋኞችና ለቅኝ ገዢዎች ግን የመሸነፍን መራር ጽዋ የተጎነጨበት ዘመንን የሚያስታውስ እንደመሆኑ ቁጭትንና አግራሞትን የሚያጭር ነው፡፡
እንደሚታወቀው የጥቁር ሕዝቦች ድል የሆነው ዓድዋ፣ ዘንድሮ ለ128ኛ ጊዜ ከነገ በስቲያ በተለያየ መርሃግብር የሚከበር ይሆናል። ይህን ታላቅ ድልን አስመልክቶ አዲስ ዘመን ዓድዋ ላይ የነበረው የአንድነት መንፈስ ዛሬ ላይ ለምን ሊደበዝዝ ቻለ በሚሉና ሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ ከሆኑት ሰማኸኝ ጋሻው ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል። መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፦ የዓድዋ ድልን እንደምን ይገልጻሉ?
መምህር ሰማኸኝ፦ ዓድዋ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታላላቅ የታሪክ እጥፋቶች መካከል አንዱ ነው ብንል ማጋነን አይደለም። የሰው ልጅን የእርስበእርስ ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት መልክ ካስያዙ ክስተቶች መካከል ምናልባት የታላላቅ ሃይማኖታዊ አስተምርሆዎች መነሳት በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል። ምክንያቱም ሃይማኖቶቹ በአስተምርሆዎቻቸው የሰው ልጆችን እኩልነት በመርህ ደረጃ ማስተማር መቻላችው ነው።
የሰው ልጅ እንደሚኖርበት አካባቢና ከወላጆቹ እንደሚወርሰው ዘመን የተለያየ ባህል፣ ወግ እና ልምድ እንዲሁም ቀለም፣ ቅርፅና ቁመና ይኖረዋል። ይህ ነባራዊ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዚህ በተቃራኒ የሰው ልጅ እራሱን “ነጭ፣ ቀይና ጥቁር” በሚል ዘረኛ አስተሳሰብ ይመድባል። በሂደት እሳቤው የሰው ዘርን “ታላቅ” እና “ታናሽ” ብሎ ወደ መክፈል ደረጃ አደገ። ይህ የተዛባ አስተሳሰብ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም፣ በ19 እና 20ኛው ምዕት ዓመት ላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። እዚህ ላይ አውሮፓ ወለድ የሆኑት የጆርጅ ሄግል እና የቻርለስ ዳርዊንን ዘረኛ አስተሳሰቦችን ማስታወስ በቂ ይሆናል። ሁለቱ የወቅቱ ልሂቃን “ነጭ” የተባለውን “ዘር” የተሻለ የሰው ዘርና የተሻለ ባሕል ባለቤት እንደሆነ ይስማማሉ። ይህ እሳቤ እየዳበረ በመሄዱ “ጥቁር” የሰው ዘር ለባርነት ብቻ የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ በ19ኛው ምዕት ዓመት በባርነት አጋዙት። እዚህ ላይ በታሪክ “የአትላንቲክ የባሪያ ንግድ (Atlantic Slave Trade)” የሚባለውን ክስተት ማስታወስ በቂ ነው።
በአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ምክንያት አፍሪካውያን ጉልበታቸው ብቻ ሳይሆን እውቀታቸውም ወደ አውሮፓ ተሰደደ። ይህ ክስተት በአውሮፓ የሀብት ክምችት (Capital accumulation) እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ (Technological Enovation) እንዲከሰት አደረገ። ስለዚህ በአፍሪካውያን ባሮች የተገነባው ካፒታሊዝም በሂደት የኢንዱስትሪ አብዮትን ወለደ። በአውሮፓ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ፤ ለፋብሪካዎች ግብአት የሚሆን ጥሬ እቃ እና የሸቀጥ ማራገፊያ ቦታ አስፈለገ። አውሮፓውያን ይህንን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ወደ ኢምፔሪያሊዝም (Living on the cost of other) ደረጃ አሳደጉ። በዚህ ፅንሰ ሀሳብ ከተስማሙ በኋላ አፍሪካውያንን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ህጋዊ መሰረት ማስያዝ ስለነበረባቸው በጀርመኑ መሪ ኦቶማን ቢስማርክ መሪነት እ.ኤ.አ በ 1884 “የበርሊን ኮንፈረስን” በበርሊን ከተማ አካሄዱ። በዚህ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ለኢጣሊያ ቅኝ ግዛት እንድትሆን ተወሰነላት።
በእርግጥ ኢጣሊያ ቀደም ብላ እ.ኤ.አ በ1885 በእንግሊዝ አጋዥነት የምፅዋ ወደብን ተቆጣጥራ ነበር። እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1882 የአሰብ ወደብን “ሮባቲኒዮ” ከሚባል የጣሊያን የግል መርከብ ኩባንያ ተረክባ ነበር። እነዚሀን ሁለት ወደቦች ቀድማ መቆጣጠር በመቻልዋ፤ በበርሊን ጉባዔ ያቀረበችው ጥያቄ በቀላሉ ተቀባይነት አገኘ። “ሮባቲኒዮ” የተባለው የግል ኩባንያ በበኩሉ፤ እ.ኤ.አ በ1896 በወቅቱ የአፋር ገዢ ከነበረው ሱልጣን ራሂታ በስድስት ሺ ጠገራ ብር የአሰብ ወደብን ገዝቶ ነበር። እነዚህ እንቅስቃሴዎቿ ለቀጣይ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ላቀደችው እቅድ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ቻለ።
እንግዲህ የዓድዋ ጦርነት ማለት በቅኝ ገዥዎች እና ተገዥዎች፣ በወራሪዎችና ተወራሪዎች፣ በነጮችና ጥቁሮች፣ በበዝባዦችና ተበዝባዦች፣ በጨቋኝና ተጨቋኞች፣ በዘረኞችና ፍትህ ናፋቂዎች፣ በሰው ልጆች እኩልነት በሚያምኑና በማያምኑ የሰው ልጆች መካከል የተካሄደ ፍትሃዊ ጦርነት ነው። እኔን እስከገባኝ ድረስ የሰው ልጆችን እኩልነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጦርነቶችን “ቅዱስ” ጦርነቶች ብለን ብንሰይማቸው የሚጎድላቸው ነገር የሚኖር አይመስለኝም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ የኢፌዴሪ መንግስት በዚህ “ቅዱስ” ጦርነት ለተሳተፉ የዓድዋ ጀግኖች የመታሰቢያ ሙዚየም ማስመረቁን አይተናል። ጉዳዩን በአስተውሎት ለተመለከተው ሰው በዚህ ፍትሃዊ ጦርነት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የመታሰቢያ ሙዚየም መሰራቱ እጅግ ይበል የሚያስብል ተግባር ነው። አስቀድሜ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ይህ ድል ለሁሉም ጥቁር ሕዝቦች እኩልነት የተከፈለ የደም ዋጋ ነው። ይህ ታላቅ የሆነው የዓድዋ ድል በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በመላ የአፍሪካ አገሮች እንደ አህጉራዊ የድል ቀን ተደርጎ ሊከበር የሚገባው ታላቅ የታሪክ እጥፋት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። በተጨማሪም የዓድዋ ድል በሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት የሚያምን ማንኛውም የስው ዘር ሊያከብረውና ሊዘክረው የሚገባ ክስተት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን የተመረቀውን የዓድዋ “ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም” እንደ አንድ የታሪክ ምሁር እንዴት አዩት? ፋይዳው ምንድን ነው ይላሉ?
መምህር ሰማኸኝ፡- ይህን ታሪካዊ ጀብዱ ለፈፀሙ ጀግኖቻችን፣ መታሰቢያ ሙዚየም መገንባት መቻሉ ታሪካዊ ጠቀሜታዎች አሉት። የመጀመሪያው ጠቀሜታ ታሪክን ጠብቆ ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ ማስቻሉ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ሲሆን፣ የቱሪዝም ሴክተሩን ማነቃቃት ያስችላል። ሶስተኛው የታሪክ ስበት ማዕከሉን አገራችን ኢትዮጵያ ላይ እንዲቆይ ያስችላል። ኢትዮጵያ ታሪካዊት አገር፤ ሕዝቧም የዚህ ታላቅ ጀብዱ ባለቤት እንዲሁም የነፃነት፣ የጀግንነት ተምሳሌ ሆና እንድትቀጥል ያስችላታል። አራተኛው ደግሞ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው የእርስ በእርስ እና ወንድማማችነት መንፈስ የበለጠ እንዲጠናከር ያደርጋል።
እንደሚታወቀው ዓድዋ በዋናነት የመላ ኢትዮጵያውያን የጋራ ድል ነው። ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ከባዱን የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለውበታል። በዚህ ድል ለተሰው ጀግኖች የመታሰቢያ ሙዚየም ተሰራላቸው ማለት፤ በድሉ ላይ ያላቸው የባለቤትነት ስሜት እንዲጨምር ያደርጋል። ይህ ደግሞ አብሮነትን ያጠናክራል። አምስተኛው ደግሞ የብሔረ መንግስት ግንባታውን ሂደት ያፋጥነዋል። የብሔረ መንግስት ግንባታ ማለት በአንድ ሉአላዊት አገር ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች በዋና ዋና አገራዊ ምልክቶች ላይ የጋራ ግንዛቤና የባለቤትነት ስሜት መፍጠር መቻል ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ እንደምናውቀው የአገረ መንግስት ግንባታው ቀደም ብሎ የተከናወነ ቢሆንም ቅሉ የብሔረ መንግስት ግንባታው ግን የተቋጨ ጉዳይ አይመስልም። በአጠቃላይ የጀግኖቻችን መታሰቢያ ሙዚየም መሰራቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡
አዲስ ዘመን፦ የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ የመላ ጥቁር ሕዝቦች እና የጭቁኖች የነጻነት ምልክት ነው የሚባለው እንዴት ነው?
መምህር ሰማኸኝ፦ ከአድዋ ጦርነት በፊት በነጮችና ጥቁሮች መካከል የነበረው ተፈጥሯዊ ግንኙነት የተዛባ ነበር። ነጮቹ ራሳቸውን እንደ ገዢ ሲቆጥሩ፣ ጥቁሮቹን ደግሞ እንደ ተገዢ ሕዝብ ይቆጥሩት ነበር። ጥቁሮቹ ራሳቸውን የማስተዳደር አቅምና ችሎታ እንደሌላቸው ይቆጥሩ ነበር። በተጨማሪም ጥቁሮች ባህልና ታሪክ አልባ፤ እንዲሁም በተፈጥሯቸው ያልተሟሉ የሰው ዘሮች እንደሆኑ ተደርጎ ይነገር ነበር።
በዚህም ምክንያት ነጮቹ ወደ አፍሪካ አኅጉር በመጡ ወቅት፤ “እኛ ጥቁሮችን ለማስተዳደርና ለማሰልጠን ከአምላክ የተላክን ነን፤ ጥቁሮች የሚኖሩበትን ጨለማ አህጉር ለማሰልጠን መጥተናል” በማለት ሕዝቡን ያደናግሩ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የማጭበርበሪያ ስምምነቶችን ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በመፈራረም አፍሪካን በቅኝ ግዛት ስር ማስገባት ጀመሩ።
እዚህ ላይ ለዓድዋ ጦርነት መከሰት መንስዔ የሆነውን የውጫሌ ሰምምነትን ማስታወስ ግድ ይላል። ይህ ውል በዳግማዊ ምኒልክና በጣሊያን መንግስት ወኪል አንቶሎኒ መካክል የተፈረመ ሲሆን፣ አንቀፅ 17 የያዘው አወዛጋቢ ትርጉም ለጦርነቱ መከሰት የቅርብ መንስኤ ሆኗል። የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በዚህ መልኩ እ.ኤ.አ ከ1870ዎቹ እስከ 1960ዎቹ ከኢትዮጵያ በስተቀር በቅኝ ግዛት ስር አደረጉ።
የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስቶች አፍሪካን ለአንድ ምዕት ዓመት ያክል በዝብዘዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያ የተቃጣባትን ወረራ በተሳካ መልኩ ዓድዋ ላይ እ..ኤ.አ ከ1896 መክታ መልሳለች። በወቅቱ ነጭ እንደ አውራ ዘር (Master race) በሚቆጠርበት ወቅት አሸንፎ ለሌሎች አገሮችና ሕዝቦች አርዓያ መሆን መቻል ታላቅነት ነው። ይህንን የተዛባ ታላቅ ትርክት መስበር የቻለች ብቸኛዋ አገር ኢትዮጵያ ናት፤ ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ቀድማ ያበሰረች አገር ናት።
ከዓድዋ ድል ማግስት በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ የነፃነት ትግላቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ በ1900ዎቹ በታንጋኒካ የተከሰተው የማጅ ማጅ እንቅስቃሴ፤ በ1940ዎቹ በኬንያ የተከሰተው የማው ማው እንቅስቃሴ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የተከሰተው የኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴዎች ታላቅ ማሳያዎች ናቸው። በተጨማሪም ወደ 16 የሚደርሱ የአፍሪካ አገሮች የነፃነት ምልክት የሆነችዋን የኢትዮጵያን ባንዲራ በተለያየ ዲዛይን ለአገራቸው ምልክትነት ተጠቅመዋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ ያስመዘገበችው ድል ለሌሎች አፍሪካውያን አገሮች ትልቅ የነፃነት በር የከፈተ ማርሽ ቀያሪ ክስተት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ብዙዎቹ እንደሚለት፤ የዓድዋ ድል ነጮችን ያስደነገጠ ድል ነው፤ ይህን እርስዎ እንዴት ይገልጹታል?
መምህር ሰማኸኝ፤– እንደሚታወቀው የዓድዋ ድል ታላቅ የታሪክ እጥፋት ያስከተለ ክስተት ነው የምንለው በሁለቱም ማለትም በነጮችና በጥቁር ሰው ልጆች ዘንድ ያሳደረውን ተፅዕኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። በአውሮፓውያን ነጮች ዘንድ ታላቅ ድንጋጤና ስጋት የፈጠረ ክስተት ሲሆን፣ በአፍሪካውያን ጥቁሮች ዘንድ ደግሞ ታላቅ ደስታና ሃሴትን መፍጠር የቻለ ክስተት ነበር። በአውሮፓውያን በኩል፣ ነጮች ይከተሉት የነበረው የተዛባ ትርክት “የነጭ ዘር የበላይነት” መንኮታኮትና እርቃኑን መቅረት የጀመረው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው። ከዚህ ድል በኋላ ኢምፔሪያሊስቶች አፍሪካ ላይ የነበራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥቅሞች መናጋት ጀመሩ። ከኢኮኖሚያዊ ስጋቶች መካከል አፍሪካን ቅኝ በመግዛት፣ ለኢንዱስትሪዎቻቸው ያካበቱት የነበረው የጥሬ ሀብት ሊቋረጥ እንደሚችል የተገነዘቡበት ክስተት ተፈጠረ። ምክንያቱም አፍሪካውያን ነጮችን ማሸነፍ እንደሚችሉ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ መማር ችለዋል። ጥሬ ሀብት የሚዘርፉበት ቦታ ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪ ሸቀጦቻቸውን የሚያራግፉበት ቅኝ ተገዥ አገሮችን ማጣት እንደሚችሉ የተገነዘቡበት ጭምር ክስተት ነው።
በፖለቲካው ዘርፍ ስንመለከት ደግሞ፤ በወቅቱ በአውሮፓውያን ዘንድ ቅኝ ግዛት መያዝ እንደ ክብር መገለጫ ይቆጠር ነበር። በዚህም ኃያልነታቸውን ለማሳየት ከአፍሪካ አገሮች ውስጥ በወረራ መያዝ እንደ ጀብዱ ይቆጥሩታል። እንዲያውም ክብራቸውን ለማሳየት ሲሉ አንዳንዴ የእርስበርስ ፉክክር ውስጥ ሁሉ ይገቡ ነበር። ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ እንግሊዝና ፈረንሳይ ሱዳንን ለመቆጣጠር ፉክክር ውስጥ ገብተው ነበር።
ባሕላዊ ዘርፉን በተመለከተ ቅኝ ገዥዎች የአፍሪካውያንን ባሕልና ወግ በመደፍጠጥ የነርሱን ጭነውባቸው ነበር። በዚህም አፍሪካውያን ማንነታቸውን፤ ታሪካቸውን ተነጥቀው ማንነት አልባ ሆነው ነበር። ይህ ትክክል እንዳልነበር የተረዱት ከዓድዋ ድል ማግስት ጀምሮ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለጥቁር አፍሪካውያን እና በሰው ልጆች እኩልነት ለሚያምን የሰው ዘር ሁሉ መልካም ብስራት የተሰማው በዓድዋ ታላቅ ድል ምክንያት ነበር።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል የሰው ልጆችን እኩልነት ማረጋገጥ እንደቻለች ይነገራል፤ በባርነት ቀንበር ውስጥ የነበሩ ሕዝቦችም የዓድዋ ድል አርዓያ እንደሆናቸው ይታወቃልና ይህ ታላቅ ድል የተገባውን ያህል በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተነግሮለታል ይላሉ?
መምህር ሰማኸኝ፦ ዓድዋ ለሰው ልጆች በተለይም ደግሞ ለአፍሪካውያን ያስገኘውን ጠቀሜታ ያህል ተዘክሯል ብዬ አላምንም። እንዲሁም ለድሉ ግንባር ቀደም ባለቤት የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ እራሱ የሚጠበቅባትን ያህል ትኩረት አልሰጠችም ነበር። ዛሬ ላይ የዓድዋን 128ኛ ዓመት እያከበርን ብንሆንም ቅሉ ይህን ሁሉ ዓመታት ዓድዋ በስሙ የሚጠራ አንድም ብሔራዊ ተቋም አልነበረውም። ታሪክ የተሰራባቸው የዓድዋ ተራሮች ዛሬም ምንም አይነት መሰረተ ልማት የላቸውም፤ ለጥናትና ምርምር፤ ለቱሪስት መስዕብ ሊውሉ የሚችሉ ተቋማት ዛሬም አይስተዋሉም።
በተመሳሳይ አፍሪካውያን ድሉ የጋራቸው መሆኑን ተገንዝበው ታሪኩን የሚመጥን ስራ ሲሰሩ አይስተዋሉም። ዛሬም ድረስ ለዓድዋ መታሰቢያ ሊሆኑ የሚችሉ የጥናት ማዕከሎች በአፍሪካ አገሮች አይስተዋሉም። ይህ የራስን ታሪክ ከማቃለል፤ የተከፈለውን መስዋዕትነት ካለመረዳት እንዲሁም ታሪካዊ ፋይዳውን በአግባቡ ካለማወቅ የሚመነጭ ይመስለኛል። በእርግጥ ከቅኝ ግዛት ዘመን በኋላ በአፍሪካ የተመሰረቱ መንግስታት ከአዲሱ ቅኝ ግዛት አስተሳሰብ (Neocolonialism sentiments) ነፃ የወጡ ናቸው ብዬ አላምንም። አሁንም ድረስ በድሮ ቅኝ ገዥዎቻቸው ተጽዕኖ ስር በመሆናቸው ለዓድዋ የሚሰጡት ትኩረት እጅግ ያነሰ እንዲሆን አድርጎታል።
በታሪካዊ የጥናት ዘርፉም ቢሆን ዓድዋ የድሉን ግዝፈት ያህል ተጠንቷል ብዬ አላስብም። ለምሳሌ በዓድዋ ጦርነት ላይ ስነህይወታዊ ጦርነት (Biological war) በኢትዮጵያ ላይ ተፈፅሟል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ፋሽስት ኢጣሊያ ”አባ ሰንጋ” በተባለ የከብት በሽታ የተጠቃ ከብት በምፅዋ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ከፍተኛ ጉዳት አድርሳለች። በዚህ የተነሳ በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ በታሪክ “ክፉ ቀን” የተባለው ዘመን እ.ኤ.አ ከ1889 እስከ 1892 ተከስቶ ነበር። ይህ ክስተት ኢትዮጵያውያንን ክፉኛ ከመጉዳቱም በላይ ኢጣሊያ አገራችንን ለመውረር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አስባ የፈፀመችው እኩይ ሴራ ይመስለኛል። ነገር ግን እስካሁን በጥናት ተደግፎ ሊቀርብ አልቻለም።
አዲስ ዘመን፦ ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን አንድነት ትልቅ መሰረት የሆነና ጥልቅ ትርጉም ያለው ነው፤ ዛሬስ ልክ እንደ ዓድዋው ጊዜ ያንን የሚመስል አንድነት አለ? የዓድዋን ድል ለከፍታችን መነሻነት የማንጠቀመው ለምንድን ነው?
መምህር ሰማኸኝ፦ ኢትዮጵያውያንን አንድ ከሚያደርጉን ታሪካዊ ክስተቶች ውስጥ ዓድዋ የአምበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ነገር ግን የዓድዋ ዘመን ትውልድ የአንድነት መንፈስ በዛሬው ትውልድ ላይ ጎልቶ አይታይም፤ ይህ ደግሞ የራሱ መሰረታዊ ምክንያቶች አሉት። በእርግጥ የዛሬው ትውልድም በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የማያወላዳ አቋም እንዳለው በተለያዩ ሀገራዊ ጥሪዎች ላይ በተግባር አሳይቷል። በቅርቡ እንኳ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ አሰጣጥ ላይ አንድነቱን አሳይቷል። ሆኖም ግን ክቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ያልተለመዱ፤ ለአብሮነታችን እንቅፋት የሚሆኑ ድርጊቶች ሲከሰቱ ይስተዋላሉ።
ዓድዋ የጋራ አምድ እንደመሆኑ መጠን እንደ ዓድዋ ጀግኖች አባቶቻችን የአንድነት ማሰሪያ ፅኑ ቃልኪዳን ልናደርገው ይገባ ነበር። ነገር ግን በፊት ለፊት ጦርነት ዓድዋ ላይ የተሸነፉት ኢምፔሪያሊስቶች ስልታቸውን በመቀየር ሊያግባባን በማይችል የፖለቲካ ሪዕዮትዓለም ውስጥ ከተቱን። በሽንፈታቸው ጥርስ የነከሱት አውሮፓውያን፤ ኢትዮጵያን በምን መልኩ ማፍረስ እንደሚችሉ ዘዴ ከመፈለግ አላረፉም ነበር። ለምሳሌ ባሮን ፕሮቻዝካ የተባለው ፀሀፊ “Abyssinia: The Powder of Barrel” በተሰኘውና በእ.ኤ.አ በ1935 ባሳተመው መፅሀፉ ኢትዮጵያውያን አንድ እንዳይሆኑ አዳዲስ የሀሰት ትርክቶችን ጠቅሷል። ከነዚህ መካከል የ”ብሔር” ጭቆና እንደነበር፤ አገሪቱም ቅኝ መገዛት እንዳለባት፤ ነባር ተቋማት በጠላትነት እንዲፈረጁ አቅጣጫ ሰጥቷል። እንዳለመታደል ሆኖ የ1960ዎች ትውልድ ይህንን የተዛባ ትርክት የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ማዕዘን አድርጎ አስቀጠለው ይህ ዛሬ ያለንበትን ፖለቲካዊ ስብራት ፈጠረ።
በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን ጦር መዝዞ የመጣውን ኃይል ቀደም ብሎ ዶጋሊ ላይ በመቀጠል ደግሞ ዓድዋ ላይ ፊት ለፊት ተጋፍጠን ማሸነፍ ቻልን እንጂ፤ መልኩን ቀይሮ በኛ ሰዎች በኩል የመጣውን የቅኝ ገዥዎች ድብቅ ሴራ ማሸነፍ አልቻልንም። ይህ ደግሞ የዛሬው ትውልድ እንደ ዓድዋ ትውልድ በተሟላ መልኩ በአንድነት እንዳይቆም እንቅፋት የፈጠረበት ይመስልኛል።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያውያን የዓድዋ ልጆች መሆን ያቀተንስ ለምንድን ነው? የዓድዋ ልጆች መሆን እንድንችል ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
መምህር ሰማኸኝ፦ የዛሬው ትውልድ እንደ ዓድዋ አባቶች መሆን ያልቻለው በአስተሳስብ ጦርነቱን መሸነፉ ነው። የግንባር ጦርነቱን በድል ከተወጣ በኋላ ፖለቲካዊ አይዶሎጂካል ጦርነቱን ግን ተሸንፏል። ትውልዱ የራሱ የሆነ አገር በቀል ፖለቲካዊ ተቋማትን ከመገንባትና ከማጠናከር ይልቅ በዴሞክራሲ ሽፋን የተመረዘ ‘አብዮታዊ” ዴሞክራሲን ተከለ። ይህ መልካም የሚመስል ግን ደግሞ አደገኛ የሆነው እሳቤ ተቋማዊ ቅርፅ በመያዝ መሰረታዊ የአብሮነትን መርህ ማናጋት ቻለ።
ወደ አባቶቻችን የአብሮነት ስሜት ለመመልስ ከተፈለገ መነጋገር፤ መወያየትና መደማመጥ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም ሰው ከስሜትና ሆደ ባሻነት መላቀቅ አለበት። መንግስትም ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በሰከነ መልኩ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ግዴታው ነው ብየ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ዓድዋ ልጆች የማንሆን ከሆነ የሚያጋጥመን ምንድን ነው? መፍትሔውስ?
መምህር ሰማኸኝ፦ እንግዲህ ታሪክን የምንመረምር ካለፈው ድርጊታችን ትምህርት ለመቅሰም ነው። ሰዎች በግለሰብም ይሁን በማኅብረሰብ ደረጃ የታሪካዊ ክስተቶች ድምር ውጤት ናቸው። አገርም እንዲሁ የታሪኳ ድምር ውጤት ናት። እንደ አገር ካለፉ ድርጊቶቻችን ትምህርት የማንወስድ ከሆነ፤ የከፋ አደጋ ሊገጥመን ይችላል። በእርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፎ ያውቃል፤ ዛሬ የገጠመውንም ከዓድዋ ጀግኖች በወረሰው ጥበብ ይሻገረዋል ብዬ አምናለሁ።
በመሰረቱ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተጋጭቶ አያውቅም። መሪዎቹ ግን በተለያዩ የውጭና የውስጥ ግፊቶች ምክንያት ሽኩቻ ውስጥ ይገባሉ። በዓድዋ ጦርነት ወቅት፤ ጣሊያን ትከተለው በነበረው የማግባባት ፖሊሲ ምክንያት በትግራይና “መረብ ምላሽ” አካባቢ የነበሩ ገዢዎች ጣሊያንን ሊተባበሩ ሞክረው የነበረ ቢሆንም፤ የጣሊያንን መሰሪ አካሄድ በመገንዘብ ከወቅቱ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ምኒልክ ጋር ታርቀው ጠላትን በጋራ ተጋፍጠው ድልን አውርሰውናል። ዛሬም ቢሆን ሕዝብ እንደ ሕዝብ አልተጋጨም። የችግሩ ምንጭ ዓድዋ ላይ ያሸነፍናቸውን ቅኝ ገዥዎችን ስነ ልቦና ከወረሱት ጥቁር ኮሎኒያሊስት “ምሁራን” ነው። እነርሱም የፖለቲካ ስብራታችን ውጤቶች ይመስሉኛል።
አዲስ ዘመን፦ ዓድዋንና ፓን አፍሪካኒዝምን የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?
መምህር ሰማኸኝ፡– የዓድዋና የፓን አፍሪካኒዝም ግንኙነትን ስንመለከት በቅደም ተከትል የተከሰቱ ተመሳሳይ ዓላማ የነበራቸው ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው። ዓድዋ ቀደም ብሎ የኢምፔሪያሊስቶችን እኩይ ዓላማ ለመመከት እ.ኤ.አ በ1896 የተከሰተ ሲሆን፤ ፓን አፍሪካኒዝም ደግሞ የዓድዋን ተሞክሮ በመቅሰም እ.ኤ.አ ከ1900ዎቹ ጀምሮ መላ ጥቁር አፍሪካውያንን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለማላቀቅ መነሻውን በአሜሪካ ካሪቪያን አገሮች አድርጎ ለመላ ጥቁር ሕዝብ ነፃነት የታገለ ድርጅት ነበር።
የዚህ እንቅስቃሴ ጠንሳሾች በሕንድና አሜሪካ ይኖሩ የነበሩ የጥቁር ሕዝብ ዘሮች ነበሩ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ማርክስ ጋርቬ እና ዱ ቦይስ የተባሉ አፍሮ አሜሪካውያን ይገኙበታል። በተጨማሪም ከአፍሪካ አህጉር ውስጥ ዋና ዋና የፓን ቀደምት አፍሪካኒዝም አቀንቃኞች፤ ዶክተር ዊልሞት ባይደን እና ቢሾፕ ጆህንሰን ከምዕራብ አፍሪካ ይገኙበት ነበር። ቢሾፕ ጆህንሰን፤ ነጮች ክርስትናን በአፍሪካ ለማስፋፋት በሚል ስም የጥቁሮችን ተፈጥሮዊ መብት ምን ያህል እንደሚጥሱ ስለተገነዘበ፤ በጥቁር ሃይማኖታዊ አባቶች የምትመራ ቤተክርስቲያን ለማቋቋም ጥረት ያደርግ ነበር።
ፓን አፍሪካኒዝምን /ፓን ብላክ/ ማለት ሁሉም አፍሪካውያን /ሁሉም ጥቁር ሕዝብ/ እንደማለት ሲሆን፣ ከቅኝ ገዥዎች /ነጮች/ ጭቆና ነፃ ለመሆን የሚደረግ የትግል እንቅስቃሴን ያመለክታል። ፓን አፍሪካኒዝምን በትግሉ ውስጥ በመላው ዓለም የነበሩ ጥቁሮች ሁሉ በንቃት እንዲሳተፉ ያመቻቸ ተቋም ነበር።
ይህ እንቅስቃሴ ከ1900ዎቹ ጀምሮ በአሜሪካና በአውሮፓ የተለያዩ መድረኮችን ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ፤ ከአፍሪካ ወጣት ፖለቲከኞችን በማካተት የነፃነት ትግሉን አፋጥኗል። ከእነዚህ ውስጥ የወቅቱ የናይጄሪያው መሪ ናምዲ አዚኪው፤ የጋናው መሪ ኩዋሜ ንኩርማህ፤ የኬኒያው መሪ ጆሞ ኬኒያታ፣ የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴን በማካተት የአፍሪካ ሕብረት ድርጅትን ወለደ። የአፍሪክ ሕብረት ምስረታ ፅንሰ ሃሳብ እ.ኤ.አ በ1945 በማንችስተር ከተማ በተካሄደው ጉባዔ ላይ ተቀባይነት አገኘ። በሂደትም የአፍሪካ ነፃ አገሮች በአንድ መዋቅራዊ ጥላ ስር ተካተው የፀረ ቅኝ ግዛት ትግሉን ማፋጠን ቻሉ።
በአጠቃላይ ሲታይ፤ የዓድዋ ድል ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መነሻ እንዲሁም ለአፍሪካ ሕብረትና በኋላም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ታሪካዊ ክስተት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
መምህር ሰማኸኝ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤሌያስ
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2016 ዓ.ም