በዓሉን የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን በሚመጥን ደረጃ  ማክበር ይጠበቅብናል

ከቀናት በኋላ ታላቁ የአፍሪካውያን ብሎም የጥቁር ሕዝቦች ድል የሆነው የዓድዋ በዓል በአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ይከበራል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ጥቂት የማንባል አያቶቻችን የሰሩትን ታላቅ ገድል በአግባቡ ማወደስ አቅቶን፤ በበዓሉ አከባበር ዙሪያ ለብሽሽቅና ለስድድብ ቃላት በመምረጥ ስንደክም መታየታችን አንገት የሚያስደፋ ነው።

በመሰረቱ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ክብረ በዓል አከባበር በራሱ ከተጀመረ አንስቶ ወጥነት ባለው መልኩ ሲከበር አልነበረም። ብዙዎቻችን ይህንን ባለማወቃችን ይመስለኛል ሁሌም አዲስ ነገር እንደተፈጠረ ሁሉ በዓመት ለዚያውም ለግማሽ ቀን ለማይሞላ መርሃ ግብር አገር ይያዝ የምንለው። ለዛሬ ጽሁፌም የዓድዋ በዓል እንዲህ ተደርጎ፤ እዚህ ተኩኖ፤ በዚህ መልኩ ብቻ መከበር አለበት ለሚሉ ከዚህ በፊት የነበረውን አካሄድ መረጃ ጠቅሼ ለማቅረብ ወደድኩ።

መረጃውን የማጋራችሁ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት አገልግሎት 127 ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን ምክንያት በማድረግ «የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል አከባበር ታሪክ» በሚል ከተዘጋጀ በራሪ ወቀረቀት ነው። ጽሁፉን ለማዘጋጀት “Memories of the victory of Adwa: A focus on its commemoration (1941- 1999)” በሚል በ2004 በቢንያም ወልደ ገብርኤል የተዘጋጀውን የሁለተኛ ድግሪ ማሟያ ጥናት ጽሁፍ መጠቀማቸውንም አስቀምጠዋል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ለመጀመሪያ ግዜ በይፋ የተከበረው ጦርነቱ በተካሄደ በሰባተኛው ዓመት በ1895 ዓ.ም በቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ነው። በበዓሉ ሁሉም ሀገረ ገዢዎች ጦራቸውን ይዘው ተገኝተዋል። ዳግማዊ ምንሊክ 8000 ሺ ፍሪዳ ጥለው ለ60ሺ ሰዎች ግብር አብልተዋል። 307 ሺ ወታደሮችም ወታደራዊ ትርኢት አሳይተዋል፤ ንጉሱ በየዓመቱ የካቲት ሀያ ሶስት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዕለት ሆኖ እንዲከበር አውጀዋል። ለምን ለማክበር እንዳሰቡ ሲገልጹም “ ፈጣሪ በሰላምና በጤና ጠብቆ ሰባት ዓመት ስላቆየን [ዕለቱን] ላከብረው አቅጂያለሁ። የማከብረው ግን ለጉራ እና ያለኝን ጦርና መሳሪያ ለማሳየት አይደለም ።” የአማርኛ ትርጉም በአዘጋጆቹ።

ከ1895ቱ መታሰቢያ በዓል በኋላ እስከ 1917 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት በዓሉ በምን መልኩ ይከበር እንደነበር ዝርዝር መረጃ የለም። ያም ሆኖ ግን በየዓመቱ በደበዘዘ መልኩም ቢሆን መከበሩን ቀጥሏል። ይከበር የነበረው በጊዮርጊስ ካቴድራል ነበር። ከ1917 እስከ 1920ዎቹ በዚህ ዘመን ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና አልጋ ወራሽ ተፈሪም በበዓሉ ይታደሙ ነበር። በዕለቱ ሥራ ይዘጋል፤ አዲስ አበባም በሰንደቅ ዓላማ ታሸበርቃለች፤ ቀሳውስቱ በዋዜማው ሲቀድሱና ሲፀልዩ ያድራሉ። የ1917 በዓል (29ኛው ዓመተ በዓል) በጣም ደማቅና የምንሊክና የራስ መኮንን ፎቶ ለእይታ እንዲቀርብ ተደርጎ በቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ተከብሯል።

ከጣሊያን ዳግም ወረራ በፊት የመታሰቢያ በዓላቱ ሲከበሩ ስለጦርነቱም ሆነ ስለድሉ ዝርዝር ዘገባ በጋዜጦች አይዘገብም ነበር። (በ1928 እ.አ.አ በኢትዮጵያና በጣልያን መካከል በተፈረመው የወዳጅነት ስምምነት የተጀመረውን መልካም ግንኙነት ላለማደናቀፍ)። ከ1922 ቱ ክብረ በዓል ቀደም ብሎ የዳግማዊ ምንሊክ ሀውልት ተመርቆ እንዲከፈት ተደርጓል። የ1923 ቱን የመታሰቢያ በዓል በሚመለከት በእለቱ ዜና በጋዜጣ አልተሰራም።

እአአ የ1934ቱ የወልወል ግጭት በቀጣይ ዓመታት የነበሩ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ አስተዋጽኦ አድርጓል። በጋዜጦችም ለይ የአድዋን ድል አጉልቶና አስፋፍቶ መጻፍ የአድዋ ጀግኖቻችን ማወደስ እና በተቃራኒው ጣልያንን መተቸት እና መንቀፍ ተጀመረ። ከወረራው በፊት የነበረው የመጨረሻው (የ1927ቱ የመታሰቢያ በዓል በአደባባይ በቀረቡ የጀግንነት ግጥሞች ፉከራና ሽለላ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። ነገር ግን በበዓሉ ላይ ብዙ ሕዝብ አልታደመም ምክንያቱም መዋጋት የሚችለው ሰው ሁሉ ወደጦር ግንባር በመዝመቱ ነው።

ዘመነ ጣልያን ጣልያኖች አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ በተለይ ከዳግማዊ ምንሊክ ታሪክ ጋር የተገናኙ ነገሮችን አውድመዋል። ወይም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከልክለው ነበር። በመሆኑም ጣልያን በኢትዮጵያ በቆየችባቸው አምስት ዓመታት የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል አልተከበረም።

ከነጻነት መልስ (1933 እስከ 1966 ዓ.ም ) የነበረው አከባበር፤ በ1933 ዓ.ም የዓድዋ መታሰቢያ በዓል ለመጀመሪያ ግዜ የሕዝብ በዓል ሆኖ እንዲከበር በሕግ ተደነገገ። በዓሉን ከሃይማኖታዊ ይዘት ማላቀቅ ስላልተቻለ በቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድደራል በጸሎትና በቅዳሴ መከበሩንም ቀጠለ። በእነዚህ ዓመታት በዓሉ መከበሩን ቢቀጥልም የሚያዚያ 27 የመታሰቢያ በዓል “ ማጀቢያ” ሆኖ እንደቆየ የሚገልጹ አሉ።

ለምሳሌ ጋዜጦች በእለቱ ስለ ዓድዋ ድል ቢጽፉም በጽሁፋቸው ግን ዓድዋን ሳይሆን ሚያዚያ 27ን ማጉላትና ለአርበኞች ትግል ትኩረት ሰጥቶ መጻፍ ይንጸባረቅ ነበር። በዓሉ ከ1943 ዓ.ም ጀምሮ በማርሽ ባንድ መታጀብ ጀመረ፤ 21 ግዜም መድፍ ይተኮሳል። ንጉሱ ንግስቲቱና መኳንንቱ ይሳተፋሉ። ንጉሱ በማይኖሩበት አጋጣሚ አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ይገኛሉ።

የ1963 ቱ የመታሰቢያ በዓል (75ኛ በዓል) ልዩ ነበር። ይህም ለመጀመሪያ ግዜ የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ ስነስርዓት በመጀመሩ ከድል በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ግብር ማብላታቸው እና ለመጀመሪያ ግዜ በቀጥታ ከድሉ ጋር ያልተገናኘ (“የአድዋ መንፈስ በሌሎች መስኮችም ድል እንድናደርግ ማገልገል አለበት “ የሚል) መልዕክት እንዲኖረው በመደረጉ ነው።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ክብረ በዓል በደርግ ዘመን 1966 እአሰከ 1983 ዓ.ም፤ የደርግ መንግስት ስልጣን እንደያዘ ሚያዚያ 27 ወደ መጋቢት 28 ተዛውሮ እንዲከበር የዓድዋ የመታሰቢያ በዓል ባለበት እንዲቀጥል በድሉ ስም ጎዳና (የዓድዋ ጎዳና) እንዲሰየምና በዓድዋ ጀግኖች ስም ጎዳና እንዲሰየም ተደረገ። በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በበዓሉ ቀን የተለያዩ ትርኢቶችን ማቅረብ ተጀመረ።

ለመጀመሪያ ግዜ ድሉ ሙሉ በሙሉ አለማዊ ይዘትና ትርጉም ኖሮት እንዲከበር ተደረገ ቦታውም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ወደ ምንሊክ አደባባይ ተዛወረ። የአበባ ጉንጉን ማስቀመጥና የመታሰቢያ ንግግር ማድረግ የበዓሉ ዋና ድምቀት ሆኑ። በየዓመቱ የተለያዩ ወቅታዊ የሆኑ ነገሮችን የሚመለከቱ መሪ መልእክቶች ይለጠፉበትም ነበር።

ከ1967 እስከ 1974 ዓ.ም ባለው ግዜ በዓሉ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በድምቀት ይከበር ነበር። ከ1974 እስከ 1983 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ግን ድምቀቱ ቀንሷል። ይህም የደርግ መንግስት ተቃውሞ እየበዛበት በመምጣቱ እንደ ሊቀመንበሩ ያሉ የበዓሉ የክብር ታዳሚዎች ቀርተው በበታች የስራ ኃላፊዎች እንዲፈጸም በመደረጉ ይቀርቡ የነበሩት ትርኢቶችም እንዲቀሩ በመደረጉ ነው። በ1968፤ 1970 እና 1972 ዓ.ም የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በመስቀል አደባባይ እንዲከበር ተደርጓል። የ1967ቱ ክብረ በዓል ከፍተኛ ሕዝብ የተሳተፈበት ሳይሆን አንዳልቀረ ተዘግቧል።

ድህረ 1983 ዓ.ም የነበረው የአድዋ ድል አከባበር ከፍተኛ የሀሳብ መለያየት የታየበት ነው። በዘመነ ኢሕአዴግ የተከበረው የመጀመሪያው ክብረ በዓል (1984 ዓ.ም) የምንሊክ ሀውልት “ይፍረስ” እና “መፍረስ የለበትም” የሚሉ ሁለት ተቃራኒ ተቃዋሚ ሰልፎች ከተካሄዱ በኋላ በመስቀል አደባባይ እንዲከበር ተደርጓል። በሀሳብ የመለያየትና የመወዛገቡ ነገር እስካሁን የቀጠለ ሲሆን በተለይ በ1988ቱ የ100ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል (centenary) አከባበር ሂደት በስፋት ተስተውሎ ነበር።

በ1984ቱ በዓል ለይ የአዲስ አበባ ጊዚያዊ አስተዳደር የነበሩት አቶ ሙሉዓለም አበበ ምንሊክ አደባባይ በመገኘት የአበባ ጉንጉን ያስሰቀመጡ ሲሆን «የዓድዋ ድል የአንድ ግለሰብ ድል ወይም በጥቂት የጦር መሪዎች የተገኘ ድል ሳይሆን በብሄር- ብሄረሰቦች የተገኘ » ድል እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ለበዓሉ መድፍ የተተኮሰው 12 ግዜ ብቻ ነበር።

ለ100 ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል (centenary) መንግስት የራሱን ትርጉምና መልእክት ይዞ የመጣ ሲሆን በተለይ ደግሞ ድሉ “ የአፍሪካ ድል” ሆኖ እንዲታይ ከፍተኛ ትኩረትና ጥረት ተደርጓል። በዓሉን ለማክበር የተቋቋሙት ሶስት ኮሚቴዎች በየራሳቸው መንገድ ይንቀሳቀሱና ከፍተኛ ውዝግብ እና መካሰስ ውስጥ ገብተው ነበር። የታሰበውን አከባበር በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን በዓሉም በምንሊክ አደባባይ ሳይሆን መገናኛ አካባቢ ባለ አደባበይ ተከብሯል። እ.አ.አ የ1991ዱን የኤርትራ ወረራ ተከትሎ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ተሞክሯል። በኢሕአዴግ ዘመን ከተከበሩት የዓአድዋ ድል የመታሰቢያ በዓላት መካከል በጣም ደማቅ የነበረው የ1991 ዓ.ም ነው። (መከላከያ ሰራዊት ባድሜን ከኤርትራ ነጻ ከማውጣቱ ጋር በመገጣጠሙ)።

በዓሉ በመስቀል አደባባይ እና በምንሊክ አደባበይ የተከበረ ሲሆን ታቦቶችም ወጥተው ነበር። በዚህ ዓመት የተከበረው የመታሰቢያ በዓል ለመጀመሪያ ግዜ በሕዝብ ፍላጎትና ተነሳሽነት የተከበረ እንደሆነም ይነገርለታል። ባጠቃላይ ግን 21 ግዜ መድፍ መተኮስ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጥ፤ በማርሽ ባንድ መታጀብ እና የአርበኞች ሽለላ ሳይቆራረጡ ቀጥለዋል። ዘንድሮም የጎደለውን ሞልተን የተሳሰሳተውን አርመን ሕግና ስርዓትን በጠበቀ መልኩ ከመሰዳደብ እና ከመተቻቸት ወጥተን ያባቶቻችንን የነጻነት ገድል እኛም የነሱ ልጆች መሆናችንን በሚመጥን ደረጃ ማክበር ይጠበቅብናል፤ መልዕክቴ ነው።

በቴዎድሮስ ይርጋ

አዲስ ዘመን የካቲት 21/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You