የኢትዮጵያ እና የኬንያ ሕዝቦች ግንኙነት ከጉርብትና ባለፈ ዘመናትን በሰላምና በወዳጅነት መንፈስ መጓዝ የቻለ ነው። መተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሠረት ያደረገው የሀገራቱ ግንኙነት ሁሉን አቀፍ እና በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ መዋዥቅ ሳይታይበት ለረዥም ዓመታት የዘለቀ ነው።
የሀገራቱ ሕዝቦች ድንበር ከመጋራት ባለፈ፤ በባህል፣ በቋንቋ እና በታሪክ የተሳሰረ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ታሪክ ባለቤት ናቸው፤ ይህም ክፉ ጊዜያትን ሳይቀር በወዳጅነት እንዲያሳልፉ አቅም ሆኗቸዋል። በቀጣናው ለሚገኙ ሀገራት ሕዝቦች የመልካም ጉርብትና ተምሳሌት እንዲሆኑም አስችሏቸዋል።
በበጎ ህሊና እና በአፍሪካዊ የወንድማማችነት መንፈስ ላይ የተመሠረተው የሁለቱ ሀገራት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት፤ የሀገራቱን ሕዝቦች ወዳጅነትና የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ዛሬ ላይ ወደ አዲስ ታሪ ካዊ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል።
ሀገራቱ አሁን ላይ የጀመሩት አዲስ ታሪካዊ የግንኙነት ምዕራፍ የሀገራቱ ሕዝቦች ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ መስተጋብሮችን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር፤ የዜጎቻቸውን የጋራ ነገዎች ብሩህ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂክ አቅም በመገንባት ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ።
ካለንበት ወቅት፤ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ እውነታ አኳያም፤ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን በሁለንተናዊ መንገድ ለማጠናከር የጀመሩት መንገድና ጉዞ፤ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በጋራ መቋቋም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የተሻለ ዕድል የሚፈጥርላቸው ነው። ከዚህም ባለፈ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን በተሻለ መንገድ ለማስከበር ትልቅ አቅም ይሆናቸዋል።
ሀገራቱ በቅርቡ በአዲስ አበባ ባካሄዱት 36ኛው የጋራ ኮሚሽን የሚኒስትሮች ስብሰባ እና በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የተደረሰበት ስምምነትም የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ እንደሆነም ይታመናል።
ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል የቆየውን ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁሉም መልኩ በላቀ ደረጃ ማስቀጠል የሚያስችል፤ በውጭ ጉዳይና መከላከያ ዘርፎች፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፤ በማኅበራት ዘርፎች ለጋራ ተጠቃሚነት አብረው መሥራት የሚያስችላቸውን ዕድል የሚፈጥር ነው።
በተለይም አሁን ባለንበት ዓለም አቀፋዊ እውነታ፤ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን በተሻለ መልኩ ለማስጠበቅ ከተናጠል ይልቅ በጋራ መንቀሳቀስ እንደ ዋነኛ ስትራቴጂ እየተወሰደ ባለበት ሁኔታ፤ በሀገራቱ መካከል እየታየ ያለው አዲስ የትብብር ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን በተሻለ መልኩ ለማስጠበቅ የሚረዳ ነው።
የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሕዝቦች ሰላምና ልማት ለማስፈን ካለባቸው ተግዳሮቶች አንጻር፤ የሀገራቱ የጀመሩት አዲስ ታሪካዊ የትብብር ግንኙነት በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እና ልማት ለማስፈን አስፈላጊ የሆነውን የመተማመን መንፈስ ለመፍጠር ይረዳል። የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች በሁለንተናዊ መልኩ የጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ተጨባጭ ተሞክሮ መፍጠር ያስችላል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አካባቢያዊ ጸጋዎችን በጋራ በማልማት፤ የጋራ ተጠቃሚነትን በቀጣናው ሕዝቦች መካከል ለማስፈን ለጀመሩት ዘመኑን የሚዋጅ እሳቤ ስኬት የሚኖረው ጠቀሜታ ከሁሉም በላይ የላቀ ነው። ወደ ፊት ለቀጣናው ሀገራት ሕዝቦችም ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ነው።
የሀገራቱ በበጎ ህሊና እና በአፍሪካዊ የወንድማማችነት መንፈስ ላይ የተመሠረተውን የቆየ ግንኙነታቸውን በማደስ የጀመሩት አዲስ ግንኙነት በግጭት፣ በድህነትና በኋላ ቀርነት ለዘመናት ዋጋ ሲከፍል ለቆየው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ፤ አዲስ የብስራት ድምጽ ሆኖ ሊሰማ የሚችል ዘመኑን የሚዋጅና ትውልድ ተሻጋሪ እንደሚሆንም ይታመናል።
ለዚህ ደግሞ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ከበዓለ ሲመታቸው ማግስት በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የተባለለትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸውን ከኢትዮጵያ መጀመራቸውም ሆነ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለሁለት ቀናት መንግሥታዊ ጉብኝት ኬንያ ሲደርሱ በጆሞ ኬንያታ አውሮፕላን ጣቢያ በፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል፤ በቆይታቸው ያደረጓቸው ውይይቶችና በውይይቶቹ የተደረሰባቸው ስምምነቶች የዚሁ ታሪካዊ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2016 ዓ.ም