«የዓድዋ ሙዚየም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድሉ ባለቤት መሆኑን በገሃድ ያሳየ ነው» – ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፡- የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድሉ ባለቤት መሆኑን በገሃድ ያሳየ የታሪክ አምድ ነው ሲሉ የሙዚየሙ ጎብኚዎች ገለጹ፡፡

ሙዚየሙን ሲጎበቨኙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሽኩሪያ መሐመድ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ዘመኑን የሚመጥን ግንባታና ትውልድ ስለታሪኩ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ፋይዳው የጎላ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቅርስ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢፕድ ሰጥተዋል።

ሙዚየሙ ውበትን ብቻ ሳይሆን ታሪክን ይዞ የተሠራ ፕሮጀክት ነው ያሉት ጎብኚዋ፤ ፕሮጀክቱ በድሉ ላይ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ጀግኖች ዕውቅና የሰጠና የድል ባለቤትነትም የሁሉም የሀገሪቷ ሕዝቦች መሆኑን ያመላከተ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ፒያሳ ተወልደው ያደጉበት አካባቢ ቢሆንም እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ፕሮጀክት በአካባቢው አይተው እንደማያውቁ ጠቁመው፤ ከሙዚየሙ ግንባታ በኋላ ታሪክን የሚመጥን ለትውልድ መተላለፍ የሚችል ቅርስ መገንባት መቻሉን አስረድተዋል።

በድሉ ወቅት የነበሩ መሣሪያዎችን ጭምር የያዙና ጦርነቱ በተግባር ምን ነበር የሚለውን ማሳየት የሚችል ሙዚየም ነው ያሉት ጎብኚዋ፤ በሙዚየሙ ውስጥ ያየሁት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተዋደቁበትን የዓድዋ ድል በሚመጥነው መልኩ መቅረቡን ነው ብለዋል። ወይዘሮ ሹክሪያ እንዳስታወቁት፤ የሙዚየሙ ውጫዊ ውበት ለከተማዋ መልካም ገጽታ የራሱን በጎ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችልና ታሪክን በተሻለ መንገድ ለመዘከር የሚረዳ ነው።

ሌላኛው ጎብኚ ወጣት ሳሙኤል እሸቱ በበኩሉ፤ መላው ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ዘርና ጾታ ሳይለዩ ዘምተው ሀገራቸውን ለድል ያበቁበትን የዓድዋ ታሪክ ይበልጥ ዕውቅና እንዲያገኝ የሙዚየሙ ግንባታ ፋይዳው የጎላ ነው ብሏል።

የሙዚየሙ መገንባት የኢትዮጵያ ጦር ዘመናዊውን የጣልያን ወራሪን መርታት የቻለው በሁሉም ኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት መሆኑን ጥበብ በተሞላበት መንገድ ማሳየት ችሏል ሲል ተናግሯል። የሙዚየሙ ግንባታም ዛሬ ላይ የጀግኖቹን ተጋድሎ ማስታወስ የሚችልና የአሁኑ ትውልድም ታሪክን በመልካም እንዲደግም የሚያበረታታ መሆኑን ገልጿል።

የፕሮጀክቱ ግንባታው ደስ የሚያሰኝና ከዚህ ቀደም የቆሻሻ መጣያ የነበረውን ቦታ ወደመስህብነት የቀየረ ጥሩ ፕሮጀክት ነው ብሏል፡፡ ሳሙኤል የሙዚየሙ ግንባታ እንችላለን የሚል መንፈስ የፈጠረና ምን ዓይነት ደማቅ ታሪክ መፍጠር እችላለሁ ብሎ ለራስ የቤት ሥራ የሚያሰጥ ግንባታ ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኘው ወጣት ሁሉ ሊጎበኘው የሚገባ የዘመኑ መስህብ መሆኑን ሳሙኤል ጠቅሷል፡፡  ሌላኛዋ ጎብኚ ጥሩወርቅ ኃይሌ በበኩሏ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከዚህ ቀደም ስማቸው እምብዛም ያልተነሱና ትውልድም ሊያውቃቸው የሚገቡ ጀግኖችን በሚመጥናቸው መልኩ ማውሳት የተቻለበት መሆኑን ተናግራለች።

ለድል መሠረት የጋራ አንድነት ወሳኝ መሆኑን ያነሳችው ጥሩወርቅ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የኢትዮጵያ ድል ብቻ ሳይሆን ጥቁር ነጭን ማሸነፍ ይችላል የሚለውን አስተሳሰብ ለአፍሪካውያን ማጋባት የቻለ በመሆኑ ይበልጥ መዘከር እንደሚገባ አመላክታለች።

አዲስ አበባ ላይ እንደዚህ ዓይነት ታሪክን የሚዘክር ሙዚየም መገንባቱ የትናንትናን አኩሪ ድል ለመዘከርና ዓድዋን በቀጣይ ትውልድ አዕምሮ ሰርጾ እንዲቆይ ለማድረግ ይርዳል ስትል ገልጻለች።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን በማየት ዓድዋን ለትውልድ ማስተላለፍ ይቻላል ያለችው ጥሩወርቅ፤ ልንናገረው የምንችል ትልቅ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነንና ታሪካችንን ስናውቅ ማንነታችንን ማወቅ እንደምንችል ተገንዝቦ መስህቦቹን እያስፋፉ መሄድ ይገባል ብላለች፡፡

ዳግማዊት ግርማ

 

አዲስ ዘመን የካቲት 20 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You