ስትራቴጂው የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን ይረዳል

አዲስ አበባ፡- «ኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ» የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን እንደሚረዳ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በቀጣዮቹ ስድስት ወራት 15 በመቶ ያህሉን የመንግሥት አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የመጀመሪያው ‹‹የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት›› ከሰኞ የካቲት 18 ጀምሮ እስከ የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም «የጋራ ጥረታችን ለዲጂታል ኢትዮጵያችን» በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል። በትናንት ዕለትም የኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ ዎርክሾፕ ተካሂዷል።

የኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ ዎርክሾፕን ያስጀመሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ ስትራቴጂው የመንግሥትን አገልግሎት በዲጂታል የታገዘ እንዲሆን በማድረግ ዜጎች ባሉበት ሆነው የመንግሥትን አገልግሎቶች በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያስችል ጠቁመው፤ የወረቀት አልባ አገልግሎት አሰጣጥ አቅምን ለማጎልበት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በቀጣዮቹ ስድስት ወራት 15 በመቶ ያህሉን የመንግሥት አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

የዲጂታል ተጠቃሚነትን በማስፋት በ2025 ሁሉም የመንግሥት ተቋማት አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ሥርዓት በማሳለጥ የዜጎችን ተጠቃሚነት እንዲያሳድጉ እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ያፋጥናል፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ለማሳካት እና የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማቀላጠፍ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ጉዞ በቴሌኮም የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በሲስተሞች ልማት፣ በአስቻይ ምህዳር ፈጠራ እና በሰው ሀብት ልማት ረገድ ትርጉም ያላቸው ውጤቶች መመዝገባቸውን አመላክተዋል። ከ526 በላይ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ አግባብ ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላለፉት 27 አመታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ከቴክኒክ ሥራ ጀምሮ እስከ አማካሪነት የሠሩት ሊሻን አዳም (ዶ/ር) ፤ ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎት የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀጥታ ባሉበት ለዜጎች፤ ለንግድ ተቋማትና ሌሎችም ተገልጋዮች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ስትራቴጂው በመንግሥት እና በሌሎች በሚመለከታቸው አካላት መካከል ፈጣንና አስተማማኝ የዳታ እና የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር እንደሚያስችል አመላክተው፤ ተቋማት የውስጥ ሥራቸውን በቴክኖሎጂ አስደግፈው በሚገባ እንዲያከናወኑ ማድረግን ያካትታል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች ለማኅበረሰቡ ለማስተዋወቅ ብሎም ዜጎች የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ ለመፍጠር የተሰናዳው ‹‹የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት›› በቀሪዎቹ ቀናት የሳይንስ፤ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲ፣ ወረዳ ኔት፣ ኢ-ኮሜርስ ስትራቴጂ፣ የግል ዳታ ጥበቃ፣ የኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ፣ የመንግሥት የኢንተርፕራይዝ አርክቴክቸር፣ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ፣ የብሔራዊ ዳታ ማዕከል፣ የዳታ አስተዳደር፣ እና ሌሎችም ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምክክሮች ይካሄዳሉ።

የዲጂታል አጠቃቀምን ከማሳደግ ባለፈ ብልሹ አሠራርን ለማስወገድና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማስተካከል ያግዛል የተባለው ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ስትራቴጂ ጥናትና ትግበራ በይፋ ከተጀመረ አንድ አመት አስቆጥሯል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን የካቲት 20 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You