ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ የተካሄዱ የነፃነት ትግሎችን በማነቃቃት ለስኬማነታቸው የሞራል እና የመንፈስ ስንቅ በመሆን ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክታለች፤ ትግሉ ተቋማዊ በሆነ መንገድም እንዲመራም በተለይም የአፍሪካውያንን የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል በማቀናጀት የላቀ ስፍራ አላት።
በወቅቱ ከፍ ባለ ማንነትና አቅም፤ ዝግጁነት የመጣውን የጣሊያን ቅኝ ገዥ ኃይል በዓድዋ ላይ ድል የማድረግ የአሸናፊነት ትርክት፤ ለአፍሪካውያንም ሆነ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚገኙ ጭቁን ሕዝቦች የፍትህና የነፃነት ትግል ትልቅ አቅም የፈጠረ፤ ትግሉ በይቻላል መንፈስ እንዲቃኝ የረዳ ነው።
የአፍሪካውያን የነፃነት ትግል፤ ተቋማዊ አቅም በጠየቀበት ወቅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመስረት ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ አበርክቶ ከፍ ያለና ወሳኝ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት በደማቀ ቀለም የሚተርኩት ተጨባጭ እውነታ ነው። አሁን ላለው ትውልድም የኩራት ምንጭ ነው።
የአፍሪካውያንን ነፃነትም ሆነ የነፃነት ትግሉን ተጨባጭ ለማድረግ፤ በወቅቱ «የሞኖሮቪያ» እና «የካዛብላንካ» ቡድን በሚል ተከፍለው የነበሩትን የአፍሪካ ሀገሮች አዲስ አበባ ላይ በማገናኘትና ልዩነቶችን በማለዘብ ወደ አንድ የጋራ አቋም እንዲመጡ ያደረገችበት የታሪክ ምዕራፍ ለኅብረቱ መመስረት አልፋ እና ኦሜጋም እንደሆነ ይታመናል።
ከዚህም ባለፈ በወቅቱ ያልተቋጩ የነፃነት ትግሎችን በሞራል፤ በሥልጠና እና በሎጅስቲክ በማገዝ ትግሎቹ ስኬታማ እንዲሆኑ ያላሰለሰ ጥረት አድርጋለች። ይህም እንደ ሀገር ለአፍሪካዊ ወንድሞቻችን ነፃነት ያለንን የጸና አቋም እና ከበሬታ በተጨባጭ ያሳየንበት ነው፡፡
ከነፃነት ማግስት ጀምሮ በአህጉሪቱ የተፈጠሩ የሰላም እጦቶችን በድርድር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ከመሆን ባለፈ፤ በተለያዩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሳተፍ የሕይወት ዋጋ በመክፈል ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ሰላም ያለንን አጋርነት በተግባር ገልጸናል።
የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አማካኝነት በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን ዳርፉር፣ ሶማሊያ፣ እንዲሁም በአቢዬ ግዛት የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በአግባቡ ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል፡፡
በተለይም የሶማሊያ ሕዝብ በተለያዩ ወቅቶች በአልሻባብ የሽብር ቡድን የተደቀነባቸውን የጥፋት ስጋቶች ከፍ ያለ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል መታደግ ችሏል። በሰላማዊ ወቅቶችም ለሶማሊያ ሕዝብ ያለውን ወገንተኝነት በተለያዩ የልማት ተግባራት በመሳተፍ በተጨባጭ አሳይቷል። በዚህም የሕዝቡ ምስክርነት አልተለየውም።
ከጉርብትና ባለፈ ከወንድምነት መንፈስ የሚመነጨው የሠራዊቱ ተልዕኮ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች ግንኙነት ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያሸጋገረ፤ ሀገራቱ በጥርጣሪ ከመተያየት ወጥተው በክፉ ቀን ወዳጅነት እና በወንድማማችነት መንፈስ እንዲተያዩ የተሻለ ዕድል መፍጠር አስችሏል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን ወንድም በሆነው የሶማሊያ ሕዝብ ላይ የተፈጠሩ አደጋዎችን ከንፈር በመምጠጥ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የሕይወት መስዋዕት በጠየቁ የግዳጅ ወረዳዎች በማሰለፍ፤ ለሶማሊያ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋት ያለውን አጋርነት በተጨባጭ አሳይቷል።
ይህንን ተጨባጭ እውነታ በማጣመም፤ የሀገራቱን ሕዝቦች በደም የተሳሰረ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ በማደፍረስ፤ በሀገራቱ መካከል አለመተማመን እና ግጭቶችን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች፤ ቀጣናውን በመረበሽ የቀጣናው ሕዝቦች አቅማቸውን አቀናጅተው የልማት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የማድረግ የቆየ ሴራ አካል ነው።
የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ካላቸው የተፈጥሮ ጸጋ አኳያ፤ አሁን ላይ መለያቸው የሆነው ኋላቀርነትና ድህነት የሚመጥናቸው አይደለም፤ ሀገራቱ ያላቸውን የተፈጥሮ ፀጋ አቀናጅተው መንቀሳቀስ ቢችሉ፤ አካባቢው አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ሆኖ ሊከሰት እንደሚችል ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
መልከ ብዙ ከሆኑ ጣልቃ ገብነቶች የተነሳ ይህ እውነታ ተግባራዊ ሆኖ የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ከጠባቂነት ሊወጡ፤ ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመውጣት በብዙ መሻት ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም ስኬታማ መሆን አልቻሉም። ከዚህ ይልቅ ከግጭት አዙሪት ውስጥ ዋጋ እየከፈሉ መኖር ዕጣ ፈንታቸው እየሆነ መጥቷል።
ይህንን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የጀመሩት የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ የሰላምና የልማት መንገድ ወሳኝ አቅም እንደሚሆን ይታመናል። ካለበትም የግጭት አዙሪት ለዘለቄታው በልማት ለመውጣትም ያላቸው አማራጭ ይኸው ነው ።
የአካባቢው ሀገራት ያላቸውን የተፈጥሮ ጸጋዎች አቀናጅተው ሊጓዙበት የሚችለው የልማት መንገድ፤ ዘላቂነት ላለው ሰላምና ልማት፤ ከዚያም አልፎ በአካባቢው ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት ወደላቀ ደረጃ ለማሻገር ትልቅ አቅም ነው። ይህን አቅም እውን ለማድረግ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን የማይሸከም አካባቢያዊ ኅብረት መፍጠር ያስፈልጋል!።
አዲስ ዘመን የካቲት 20 / 2016 ዓ.ም