
አዲስ አበባ፡- በጦርነቱ ምክንያት የተበላሹ የኤሌክትሪክ መስመሮች ዘለቄታዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የተጀመረው ሥራ በመጪው ሰኔ መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የትግራይ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች መጠገን እና የእንጨት ምሰሶዎች ወደ ኮንክሪት የመቀየር ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው። ሥራውን እስከ መጪው ሰኔ 30 ድረስ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው።
ሥራው በተወሰነ መልኩ በክልሉ አቅም መጀመሩን የገለፁት ሥራ አስፈፃሚው፤ በዋናነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በጀት መድቦለት የኤሌክትሪክ ጥገና ዝርጋታ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ 16 ሺ የኮንክሪት ምሰሶዎችን ለመትከልና የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። እስከ አሁን አስራ አንድ ሺ ምሰሶዎች በመትከል የኤሌክትሪክ ገመድ ዝርጋታ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። በክልሉ በሚገኙ ሰላሳ ሦስት ወረዳዎች ውስጥ አንድ ሺ ኪሎ ሜትር የማስተካከያ ዝርጋታ እየተሠራ መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህ የመልሶ ግንባታ በፍጥነት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ በጀት እንደተመደበለት አስረድተዋል።
የማስተካከያ ሥራው በዋናት የትራንስፎርመር ዝርጋታ የሚያጠቃልል ቢሆንም ሁሉንም ትራንስፎርመር ለመቀየር ስለማይቻል መካከለኛ ትራንስፎርመር በመጠቀም ጥገናው እስከ ሰኔ 30 ድረስ ተሠርቶ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ሳይቶች አጠቃላይ 38 እንደሆኑ የጠቀሱት ሥራ አስፈፃሚው፤ በዋናነት የአክሱም ሽሬ፣ ዓዲግራት ዕዳጋ ሐሙስ፣ ውቕሮ ፅጌረዳ፣ ማይጨው ዓዲ ሹሁ እና ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንደሆኑ ገልፀዋል። በክልሉ ያጋጠመ የመብራት መቆራረጥ በዘላቂነት እንዲፈታ የመልሶ ጥገና ሥራው ዋና መፍትሔ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ እስኪጠገን ድረስ የመብራት መቆራረጥ ሊያጋጥም እንደሚችል ተናግረዋል።
ሥራውን ለማፋጠን እንደ ዋነኛ እንቅፋት የሆነው የኮንክሪት ምሰሶ እጥረት ሲሆን ቀደም ብሎ የነበረው የበጀት እጥረቱ አሁን ላይ መስተካከሉን ጠቅሰዋል። ትራንስፎርመርና የኮንትራክተር ችግር በዋና ቢሮ በኩል እንዲፈታ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም