የንብረት አያያዝን በማዘመን ብልሹ አሰራሮችን ማስቀረት

በመንግስት ተቋማት የሚስተዋለው ዝርክርክና ውስብስብ አሰራር ሀገሪቱን ለከፍተኛ ቸግር ሲዳርጋት ቆይቷል፡፡ በተለይም ያላትን ውስን ሃብት በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ዘመናዊና ቀልጣፋ ሥርዓት መዘርጋት ባለመቻሉ ሀገሪቱ አጠቃላይ በኢኮኖሚ ልማት ለመራመድ የምታደርገውን ጥረት ወደኋላ እየጎተተ ይገኛል፡፡ ለብልሹ አሰራርና ለምዝበራ በር በመክፈቱ ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የእምቧይ ካብ አድርጎታል፡፡

አሁን ላይ ግን ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይግባውና ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት እዚህም እዚያም የሚደረጉ ጥረቶች አሉ። ከሚደረጉት ጥረቶች መካከልም መንግሥት መዋቅር ውስጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም አንዱ ነው። በተለይም የመንግስት ተቋማትን አሰራር ለማዘመን ያስችላሉ የተባሉ በርካታ ሥርዓቶች ከውጭ ተቀድተው ተግባራዊ ቢደረጉም በሚፈለገው ልክ ውጤት ማምጣት አልተቻለም፡፡

ለዚህም የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ቁርጠኛ አለመሆን፤ ከፈፃሚ ቴክኖሎጂን ያለመቀበል ዳተኝነትና ሌሎች ችግሮችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ተደማምረው ጥረቱን አመድ አፋሽ አድርገውታል። ይሁንና አሁን አሁን የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አሰራራቸውን ለማዘመን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ክልል ገንዘብ ቢሮ በፓይለት ደረጃ እየተገበረ ያለው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የንብረት አያያዝና አስተዳደር ሥርዓት ለሌሎች ክልሎች በአብነት የሚጠቀስ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት ከበበው በኦሮሚያ ገንዘብ ቢሮ ግዢና ንብረት አስተዳደር ሪጉራቶሪ ዳይሬክተር የንብረት አስተዳደር የስራ ሂደት መሪ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ ለዘመናት የቆየው ኋላቀርና ዝርክርክ አሰራር ለክልል እድገት ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል። በተለይም ወረቀት ላይ መሰረት ያደረገውና በማኑዋል የሚካሄደው የንብረት አስተዳደርና አያያዝ የክልሉን ኢኮኖሚ አቅም ተፈታትኖት ኖሯል፡፡ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ያለው መዋቅር ዘመኑን የዋጀ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ አመራሩም ሆነ ፈፃሚው የመንግስትን ንብረት እንዳሻው እንዲያወጣ፤ እንዲመዘብርና አላግባብ እንዲጠቀም እድል ፈጥሮለታል፡፡

ይህንን ብልሹ አሰራር ለማስቀረት በሚል የክልሉ መንግስት መመሪያ ከማዘጋጀት ጀምሮ ይሆናሉ ያላቸውን የአሰራር አቅጣጫዎችን በየጊዜው ቢያወርድም መመሪያንና አቅጣጫን ጠብቆ የሚተገበር ባለመሆኑ ችግሩን ማስቀረት እንዳልተቻለ ወይዘሮ ትዕግስት ይናገራሉ፡፡ ‹‹እንደ ክልል በወጣው አዋጅና መመሪያ ላይ ተመስርተን፤ የተሻለ ያልነውን አሰራር ተከትለን በየጊዜው ስልጠና እንሰጣለን፤ ይሁንና በማንዋል የሚሰራው የንብረት አያያዝ ሥራ በመመሪያና በሕጉ መሰረት በተጨባጭ ሲተገበር አይታይም›› ይላሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ በየጊዜው የሰለጠነው የሰው ኃይል ከስራ የሚለቅበትና መሰል ምክንያቶች ተጠቃሽ ቢሆኑም በዋነኝነት ግን መመሪያውን ለመተግበር የአመራሩም ሆነ የፈፃሚ ቁርጠኛ ያለመሆኑ አንዱ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ተጠያቂነት የሚያስከትል የዘመነ አሰራር ያለመኖሩ አብይ ጉዳይ እንደነበር ወይዘሮ ትዕግስት ያስረዳሉ፡፡ በማንዋል ይሰራ የነበረው የንብረት አያያዝና አስተዳደር የተለያዩ ተግዳሮቶች ያሉበት እንደሚፈልገው የመንግስትን ንብረት ሊያስተዳድር አልቻለም ይላሉ፡፡

በመሆኑም አሰራሩን ማዘመን የግድ በማለቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን እና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አዲስ አሰራር መተግበሩን ወይዘሮ ትዕግስት ያመለክታሉ፡፡ ‹‹የንብረት አያያዙን ሊያዘምን የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ ‘ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት ሲስተም’ የሚል አሰራር ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ‹‹የቴክኒክ ስራውን እነዚህ አካላት እንዲሰሩት የስራ አመራሩን ደግሞ በእኛ ሊመራ ተስማምተን ነው ወደ ሥራ የተገባው›› ይላሉ፡፡ በዋናነትም የቢዝነስ መላምቱ ከየት ተነስቶ የት ይደርሳል? እና አዋጭነቱን ቢሮው አስቀድሞ የራሱን ክፍተቶችን ለመለየት መሞከሩን ይጠቅሳሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ረጅም ሂደት፤ ጎታችና ዝርክርክ እንዲሁም ለከፍተኛ የወረቀት ወጪ ይዳርግ የነበረውን አሰራር ያስቀራል የተባለውንና በኮምፒውተር መር ዘመናዊ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት በመጀመሪያ በአስር ክልል ቢሮዎች፤ በአራት ዞኖች፣ በሁለት ከተሞች ፓይለት ሙከራ ተደርጓል፡፡ አተገባበሩ ላይ የተነሱ ክፍተቶችን በመሰብሰብ እንደግብዓት በመጠቀም ወደ እንከን አልባ አሰራር ለመምጣት ጥረት ጠይቋል፡፡

‹‹በቴክኒክ በተደገፈ ሁኔታ ለአመራሮች ለቴክኖሎጂ ቅርብ ለሆኑ ፈፃሚዎች ስልጠናዎችን ስንሰጥ ቆይተናል›› የሚሉት ወይዘሮ ትዕግስት ይህንን አዲሱንና ዘመናዊውን የንብረት አስተዳደር ስርዓት በክልል 53 ቢሮዎች ፤ በ21 ዞኖች፤ በ19 ክልል ከተሞችና 200 በሚደርሱ ወረዳዎች ተግባራዊ መሆን መቻሉን ያመለክታሉ፡፡ ይህ ሲባል ግን በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ከአዲሱ አሰራር ጎን ለጎን የቀድሞውን የማኑዋል አብሮ የሚሰራበት ሁኔታ እንዳለ አልሸሸጉም፡፡ በተለይም የጠፉ ንብረቶች እዲገኙ፤ አልያም ያጠፋው አካል እንዲከፍልና ተጠያቂ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፤ ደቡብ ምዕራብ ሸዋና ምዕራብ አርሲ የተሻለ ውጤት የተገኘባቸው ናቸው፡፡ አሁን ላይ 21ዱም ዞኖች ተግብረዋል፡፡

ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ቴክኖሎጂን ቶሎ ተቀብሎ መተግበሩ ላይ ውስንነት በመኖሩ እንዲሁም በአንዳንድ የክልል አካባቢዎች የፀጥታ ችግር ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ንብረቶች በመውደማቸውና ሥልጠናውንም መስጠት ባለመቻሉ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ከትግበራው በተጓዳኝ በየዘርፉ እንደየሥራ ባህሪው መምራት የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ ስለመሆኑ ያወሱት ወይዘሮ ትዕግስት፤ ‹‹መመሪያው ሲጠናቀቅ ሙሉ ለሙሉ ወደ አዲሱ ስርዓት እንዲገቡ የሚደረግ ይሆናል›› ይላሉ፡፡

‹‹ይህንን የዘመነ የንብረት አያያዝ ተሞክሮ የወሰድነው ከፌዴራል መንግስት ነው፤ በዚህ መሰረትም ስታንዳርድ የሆኑ የንብረቶች ሥም ሲስተሙ እንዲቀበለው ለማድረግ በሁሉም አካባቢ አንድ አይነት አያያዝ እንዲኖር ጥረት ተደርጓል›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ በተለይም በሶስት መደብ በመለየት የክልሉን ንብረቶች የመመዝገብ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በዚያ መሰረት በክልላችን ሁሉም ወረዳዎች እያንዳንዱ ንብረት አንድ አይነት ሥምና ኮድ (መለያ) እየተሰጠውና የጋራ መግባባት ተይዞ ወጥነት ያለው አሰራር ለመዘርጋት ተሞክሯል›› ይላሉ። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን የንብረት አመዘጋገብ ሥርዓቱ ወጥነት የሌለውና ከአንዱ አካባቢ ሌላው የተለያየበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም ሪፖርቶችን እንኳን ለማቀናጀት ፈታኝ እንደነበር ነው ያስረዱት፡፡

እንደ ወይዘሮ ትዕግስት ማብራሪያ፤ በክልሉ አሁን ላይ በዚህ ሶፍትዌር አማካኝነት ንብረቶች የሚመዘገቡ መሆኑ ውስብስብና ዝርክርክ የነበረውን አሰራር ለማስቀረት አግዟል፤ በቀድሞው አሰራር ይባክን የነበረውን ጊዜ፤ ጉልበትና ኃብት ለመታደግም አስችሏል፡፡ በተለይም በትንሽ ኃይል ብዙ ሥራ ለመስራት አግዟል፡፡ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተገዙና በመጋዘን የተቀመጡ የመንግስት ንብረቶች ያለአግባብ ወጥተው የሚጠፉበትን ስርዓት ለማስቀረትም ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ይህም ተጠያቂነትን ለማስፈን ያስችላል ተብሎ ተምኖበታል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም ንብረት ወጥቶ አገልግሎት ሰጥቶ እንዲመዘገብ የሚደረገው በማኑዋል ትልቁ መዝገብ ላይ ነበር፡፡ አሁን ግን ወጪ ስናደርግ በዩዘር ካርድ እንከፍትና እያንዳንዱ ያወጣሁትን ንብረት ሲስተሙ ይመዘግባል። በተጨማሪም ትልቁ መዝገብ ላይም ወስዶ ይመዘገባል፤ እንደአስፈላጊነቱ ከሰራተኛ ወደ ሰራተኛ ማዛወር አልያም ወደ መዝገብ ቤት ወስዶ ይመዘግብልናል፤ ንብረት ወጥቶ ሲገባ ዳግመኛ ለሰራተኛ ሲሰጥ አሮጌ መሆኑን የሚያሳይ ስርዓትም ተዘርግቶለታል›› ሲሉም ስለአዲሱ አሰራር ቅልጥፍና ያብራራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ግን ረጅም ውጣውረድ እንደነበረው አስታውሰውም፤ አሁን ላይ ወዲያውኑ ከነባላንሱ የሚመዘገብበት ሥርዓት መኖሩ በሁሉም ዘንድ መግባባትና ግልፀኝነትን የፈጠረ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በክልሉ በቀደመው አሰራር ለህትመት ብቻ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በየዓመቱ ወጪ ይደረግ እንደነበር ያመለከቱት ወይዘሮ ትዕግስት ይህንን በቴክኖሊጂ የተደረገ አሰራር ሙሉ ለሙሉ መተግበር ከተቻለ ይህንን ወጪ በማስቀረት ለሌላ የልማት ሥራ ለማዋል እንደሚያግዝ ይናገራሉ፡፡ አክለውም ‹‹በማንዋል በምንሰራበት ጊዜ ንብረቶች ካገለገሉ በኋላ ባለቤት አልነበራቸውም፤ አብዛኛው ንብረቶች ሰው ዝም ብሎ እያወጣ ይጠቀምበታል፤ ግልፅነት አልነበረውም፤ አንድ ቢሮ ምን ንብረት አለው? ምን የለውም? በግልፅና በደንብ የተመዘገበ የንብረት አያያዝ ተቀምሮ የተቀመጠ ነገር አልነበረም›› ይላሉ፡፡ አሁን ግን ይህንን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስርዓት ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ ወዲህ የሚሰራውንና ሊወገድ የሚገባውን ንብረት ለመለየት እንዳስቻለ ነው ያብራሩት፡፡

እንደ ወይዘሮ ትዕግስት ገለፃ፤ በክልሉ ያሉ ንብረቶች በተዘረጋው ሶፍትዌር አማካኝነት መመዝገብ ሲጀመር አብዛኛው ንብረት በጥቂት ሰዎች እጅ የተያዘበት ሁኔታ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሁለትና ከዚያ በላይ እንደ ኮምፒውተር ያሉ ንብረቶች በአንድ ሰው ስም ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላው ሰራተኛ ምንም የመስሪያ ንብረት ሳይኖረው ለመስራት እንደሚቸገር ተስተውሏል፡፡ ከሁሉ የባሰው ደግሞ ይህንን የመመዝገብ ሥራ የሚሰሩት ንብረት ክፍሎች ራሳቸው ንብረታቸውን የሚመዘግቡበት ኮምፒውተር የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡

ይሄ የምዝገባ ሥርዓት ከተጀመረ ወዲህ ግን በኦንላይን አማካኝነት ሁሉም በሚያየው መልኩ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ስም ስለሚመዘገብ አላግባብ ንብረት የያዙ ሰዎች በገዛ ፍቃዳቸው ትርፉን እቃ እየመለሱ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ይህ አሰራር የተበታተነው አሰራር እንዲቀናጅና እንዲዘምን በማድረግ ረገድ ሚናው ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ የንብረት ዝርክርክነት እንዳይኖር ከማድረጉም ባሻገር ንብረቱ እንዳይበላሽ፤ ግልፅነት እንዲፈጠር ማድረጉ ይህ ሁኔታ በራሱ አመላካች ነው ባይ ናቸው፡፡

በተመሳሳይም መመሪያ ኃላፊዎች የሚገለገሉበትን መሳሪያ ራሳቸው ፈርመው በስማቸው እንዲወስዱ ቢያዝም በተጨባጭ ግን ሌሎች ከበታች ያሉ ሰራተኞች እንዲወስዱላቸው ያደርጉ ነበር፡፡ ይህም ደግሞ ግልፀኝነት እንዳይፈጠር ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ለብልሹ አሰራር በር ከፍቶ ቆይቷል፡፡ ከመመሪያ ውጪ ንብረቶች ወጪ ሲሆኑ ተጠያቂነትንም ለማስፈን አዳጋች አድርጎት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

‹‹ምዝገባውን ስንጀምር የጠፉ ንብረቶች፤ በገንዘብ ደረጃ መግለፅ ባልችልም ማን እንዳወጣቸው የማይታወቁ በየቦታው የተበተኑ ንብረቶች እንዲሰባሰቡ አድርጓል። አገልግሎት የማይሰጠውን ንብረት አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ችለናል›› ይላሉ፡፡ አብነት አድርገውም ‹‹ወረዳዎች አካባቢ ሞተር ሳይክል በዘፈቀደና በየቦታው ይቆሙ ነበር። ሲመዘገብ ግን ባለቤቱ የጠፋበት ሁኔታ ነበር፡፡ ወረዳዎች አውጥተው መዝግበው፤ ስራውን ለይተው አስጠግነው ወደ ሥራ እንዲገባ አድርገዋል›› ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ንብረቶች በጊዜው ባለመወገዳቸው ብቻ የንብረቱ ዋጋ እንዲወርድ የሚያደርገው በመሆኑ መንግስት ለተጨማሪ ኪሳራ የሚዳረግበት ሁኔታ ነበር። የማያገለግሉ ንብረቶችን በየጊዜው ባለመወገዳቸው ምክንያት የንብረቶቹ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ይህ በኮምፒውተር የታገዘ ሥርዓት መተግበር ከጀመረ ወዲህ ቀድሞ የነበረው የዳተኝነት አመለካከት እየቀነሰ በመምጣቱና ተጠያቂነትን በመስጋት አመራሩም ሆነ ፈፃሚው በሕግና በመመሪያ ለመስራት ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ነው ያብራሩት፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ይህ ቴክኖሎጂ መር አሰራር አሁን ላይ በክልሉ ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር አንዳንድ ተግዳሮቶች አጋጥመዋል፤ በዋናነትም አሁንም ድረስ ቴክኖሎጂን ተቀብሎ ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመራመድ የሚያስችል ቁርጠኝነት ያለመኖር፤ ይህንን ተከታትሎ ለማስፈፀም ያለመቻሉ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር ዛሬም ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በመሆኑም የአመለካከት ችግሩን ለመፍታት ያስችል ዘንድ ቴክኖሎጂን ቶሎ የሚቀበሉትን ሰራተኞች በመለየት ከኃላፊዎች ጋር አብረው እንዲሰለጥኑ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል፡፡ የፀጥታና ሌሎች ችግሮች ሙሉ ለሙሉ መተግበር ከቻለ ምርጥ ተሞክሮውን ወደ ሌሎች ዘርፎች በማሻገር ውጤታማ ሥራ ለመስራት መታቀዱን አመላክተዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን የካቲት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You