‹‹ሐበሻ ምቀኛ ነው›› የሚባል ነገር አለ አይደል? ‹‹የሐበሻ ቀጠሮ›› የሚለው ስድብ አነሰንና ምቀኝነትም ተጨመረልን! ለነገሩ ሁሉም ይገልጸናል፡፡ በነገራችን ላይ ሐበሻ ቢራ ለማዘዝ ‹‹እስኪ አንድ ምቀኛ አምጣ‹‹ የሚሉ አሉ ሲባል ተባራሪ ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ ምቀኛ የተባለው እንግዲህ ቢራው ሳይሆን ‹‹ሐበሻ›› የሚለውን ስም ስለያዘ ሕዝቡን ነው፡፡ አዎ ምቀኞች ነን፡፡
ለምን ተባልን ብሎ መደንፋት ነገሩን ከሀቅነት አያወርደው እንግዲህ (ከቻሉ አለመሆን ነው) የሐበሻ ቀጠሮ የሚለው ስድብ በትክክል ይገልጸናል፡፡ 3፡00 ላይ የተባለ አንድ ስብሰባ 4፡00 እና 5፡ 00 ላይ የምንገኝ አይደለን እንዴ? ታዲያ ይሄ እንዴት አይገልጸንም?
መቼስ እንግዲህ ነገርን ነገር አይደል የሚያነሳው? አንድ መጥፎ ድርጊት ተፈጽሞ ‹‹የእገሌን ህዝብ አይወክልም›› የምትባል ነገር ትገርመኛለች፡፡ አንድ መጥፎ ድርጊት ሲከሰት ከቦ ‹‹ሰልፊ›› ፎቶ ሲነሳ የነበረ ህዝብ እንዴት ነው የማይወከለው? ድርጊቱን አለማውገዝና አለመከላከል እኮ ከተሳታፊነት አያንስም! ለማንኛውም እሱን እንተወው!
ስለምቀኝነታችን እና አልኩባይነታችን እናውራ፡፡ በዚህ ሳምንት ያጋጠመኝን አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ፡፡ ከቤቴ (ማለቴ የተከራየሁት) አካባቢ እንጀራ የምገዛቸው ሴትዮ አሉ፡፡ እንዲያው እግረ መንገዴን ልናገረውና ሴትዮዋ በዕድሜ ገፋ ያሉ ናቸው፡፡
እንዲህ በዕድሜ ገፋ ያሉ እናቶች ንጹህ እንጀራ እንደሚሸጡ ከዚህ በፊት ከአንዴም ሁለቴ አጋጥሞኝ ስለነበር ምርጫዎቼ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ርህራሄያቸውና ትህትናቸው ቀልቤን ይገዛዋል፡፡ ዋጋ ሲጨምሩ ራሱ ተጨንቀው ተጠበው ነው የሚናገሩ፡፡ አንዳንዶቹ እኮ በቁጣ ነው የሚጨምሩት፡፡ ወደህ ሳይሆን በግድህ ትገዛታለህ የሚል ፊት ነው ያላቸው፡፡
እናላችሁ አንድ ቀን ማታ እንጀራ የምገዛቸው ደንበኛዬ ጋ ስደርስ አንዲት ልጅ የያዘች ሌላ እናት (ወጣት ናት) ለሴትዮዋ የምክር ናዳ (ለእኔ ናዳ ነበር) ታወርዳለች፡፡ ከዚያ በፊት ምን እንዳለቻቸው ባላውቅም እኔ የደረስኩባቸው ምክሮች፤ ‹‹ሌላ ቦታ ሰባት ብር እና ስምንት ብር እየተሸጠ አንቺ (አንቺ ነበር ያለቻቸው) አምስት ብር ትሸጫለሽ! እንጀራሽ ደግሞ ጤፍ ብቻ ነው….›› ወዲያውኑ የምክሩ ጥቅል ሀሳብ ገባኝ፡፡ በቃ በአጭሩ ዋጋ ጨምሪ ወይም እንጀራውን ምናምንቴ ነገር ጨምሪበት ነው፡፡ የሚያስቀው እኮ ዋጋ ለመጨመር የሚሯሯጡት ባለምናምንቴዎች ናቸው (ድሮስ ከአጭበርባሪ ምን ይጠበቃል)
የውስጤን በውስጤ ይዤ የተጨመረውን ዋጋ ጨምሬ ልገዛ ሁለት እንጀራ ይስጡኝ አልኳቸው፤ ሰጡኝ፡፡ ጨምር ካሉኝ ልጨምር ወስኜ የተለመደውን አሥር ብር አውጥቸ ስሰጣቸው ‹‹ከነገ ጀምሮ ስድስት ብር ነው›› አሉኝ፡፡ እሺ ብየ ሄድኩ፡፡ በነገው ማታ ብቻቸውን ነው ያገኘኋቸው፡፡
ትንሽ አወራን፡፡ እንደነገሩኝ እንዲህ እየሸጥሽ አያዋጣሽም፤ ወይ ዋጋ ጨምሪ ወይም ሥራውን ተይው ብለው እንደመከሯቸው ነገሩኝ፡፡ እንዲያውም ሌላ ቦታ ሰባት እና ስምንት ብር ሆኗል አሉ እያሉ ነገሩኝ፡፡ ሥራውን ከሚተውትና የእንጀራውን ጥራት ከሚቀንሱት ዋጋ ቢጨምሩ እንደሚሻል ነግሪያቸው ሄድኩ፡፡
ወደቤት ስገባ ብዙ ነገር እያሰብኩ ነበር፡፡ ይሄ በጣም ቀላል እና ተራ ምሳሌ ነው፡፡ ይሄ ችግር ግን እስከ ትልልቅ ጉዳዮች ድረስ ያለ ነው፤ ባህሪያችንን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ አገር ያወደሙ ትልልቅ ሙስናዎች የተሰሩት በእንዲህ አይነት ሰዎች ነው፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚለው አባባል ነገሩን ግልጽ ለማድረግ አጋዥ ይሆነናል፡፡ አንድ ባለሥልጣን ገና ሲሾም ከጓደኛና ከዘመድ አዝማድ የሚሰጠው ምክር ‹‹በል እንግዲህ እወቅበት›› የሚል ነው፡፡ ‹‹አትንከርፈፍ፣ ብልጥ ሁን! አትሞኝ›› ይሉታል፤ በአራድኛው ደግሞ ‹‹ፋራ እንዳትሆን›› ተብሎ ይመከራል፡፡ እነዚህ ሁሉ ምክሮች በግልጽ ቋንቋ ሲቀመጡ ‹‹ስረቅ፣ ዝረፍ፣ ሌባ ሁን!›› ማለት ናቸው፡፡
ልብ በሉ እንግዲህ! ይሄው ህዝብ ደግሞ ‹‹ሌባ ባለሥልጣን ሁላ!›› እያለ ይሳደባል (ግራ የገባን እኮ ነን!) በእኛ በኩል መንገድ አልተሰራም እያለ መንገድ ይዘጋል፣ እኛ ጋ ኤሌክትሪክ የለም እያለ የኤሌክትሪክ ገመድ ይበጥሳል፤ እንግዲህ ምን አይነት ባለሥልጣን ነው የሚሻለን? ባለሥልጣን ሲሾም ‹‹በል እንግዲህ አገርህን አገልግል! ህዝብ የጣለብህን አደራ በታማኝነት ተወጣ›› ብለን ቢሆን ኖሮ ያ ሁሉ አያጋጥመንም ነበር፡፡
አጉል አልኩ ባዮች ነን፡፡ እንዲህ ብየህ ነበር፤ መክሬህ ነበር ለማለት እንዲያመቸን ብለን እንጂ ጠቃሚና ጎጂነቱን አጥንተን አይደለም፡፡ እዚህ ላይ የሴትዮዋን ገጠመኝ ላንሳው፡፡
እንጀራ የሚሸጡት ሴትዮ ሥራውን ቢተውት ይጠቀማሉ ወይስ ይጎዳሉ? ግን እንዲህ ካልሸጥሽ ተይው ተብለው ነው የተመከሩ፤ ወይም ደግሞ ሌላ ባዕድ ነገር እንዲጨምሩበት እየተመከሩ ነው። እንዲህ አይነት ጨዋ ሰው ሲኖርም ጨዋነቱን አናደንቅም ማለት ነው፡፡ አልኩ ለማለት ብላ 7 እና 8 ብር አለቻቸው እንጂ በዚያ አካባቢ ከስድስት ብር በላይ የለም፡፡ ግደለም የዋጋው ነገር ይሁን! ሴትዮዋም መጎዳት የለባቸውም፤ ግን ለምን የሌለ ነገር ይወራል? ሌሎችም እኮ የጨመሩ በእንዲህ አይነት አሻጥር ነው፡፡
የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ መሃይምነት እና ምቀኝነት ነው። ድህነት የእነዚህ ውጤት ነው፡፡ ምቀኝነታችን ይሄው እርስበርስ መጠላለፍ ነው፤ ለወገናችን ተንኮል ማሰብ ነው፤ እኛ የምናስበው አንሶ ሌሎች ተንኮል እንዲያስቡ ማነሳሳት ነው፡፡
ነገራችን ሁሉ በዛፎች ተረት ይመሰላል፡፡ ‹‹ከእኛው የወጣ ጠማማ ነው የፈጀን›› ያሉትን ታውቃላችሁ አይደል? ዛፎች እንዳይቆረጡ ተስማምተው ህብረት ጀመሩ፡፡ ዳሩ ግን ሲያዩ መጥረቢያ ላይ ያለው እጀታ ከእነርሱ የወጣ ነው፡፡ ‹‹ከእኛው የወጣ ጠማማ ነው›› አሉ ይባላል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
ዋለልኝ አየለ