በ1990 ዓ.ም የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የዜጎች መሠረታዊ መብት መሆኑን ይጠቁማል። በትኩረት አቅጣጫውም ኅብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሰራበት አካባቢ በባህላዊ ስፖርቶችና በስፖርት ለሁሉም ተሳትፎውን የሚያጎለብትበትም ሁኔታ ይመቻቻል። ከአፈጻጸም ስልቶቹ መካከልም በመሥሪያ ቤቶች አካባቢ ከሠራተኛ ማህበራት ጋር የአሠራር ቅንጅት በመፍጠር በሥራ አካባቢ እንዲሁም በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፍ ማድረግን ያካትታል። ከተሳትፎ ባለፈ የስፖርት ቡድኖችን በማቋቋም ማወዳደርንም ያበረታታል።
ይህም ሠራተኛውን በአካልና በአእምሮ በማብቃት አምራች ከማድረግም ባለፈ ማህበራዊ ግንኙነትን በማጠናከር፣ እርስ በእርስ በማስተዋወቅና በማቀራረብ አብሮ መስራትን ያጠናክራል። በመሆኑም በተለያዩ ዓለማት ሠራተኞች በስራቸው ላይ እያሉ ለደቂቃዎች አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲነቃቁ እንዲሁም የተለያዩ የእርስ በእርስ ውድድሮችን ያዘጋጃሉ። በኢትዮጵያም የመንግሥት ሠራተኞችን የሚያሳትፍ ዓመታዊ የስፖርት ውድድር በማዘጋጀት፤ ሠራተኛው አእምሯዊና አካላዊ ጤናውን ከመጠበቅ ባለፈ የመዝናኛና የእርስ በእርስ ግንኙነቱን ያጎለብትበታል።
ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከሚካሄዱ ዓመታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የፌዴራል ተቋማትን የሚያሳትፈው የስፖርት ለሁሉም መርሀ ግብር ነው።
ለአንድ ወር በሚዘልቀው ውድድር በተለያዩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ ሠራተኞችን የሚያፎካክር ሲሆን፤ ‹‹ስፖርት ለሁሉም ለሁሉም ስፖርት›› በሚል መሪ ሃሳብም ይታጀባል። በልዩ ልዩ ክንውኖች ከየካቲት 14/2016ዓ.ም መካሄድ የጀመረው ፌስቲቫሉ እስከ መጋቢት 24/2016 ዓ.ም ድረስ ከ25 በላይ ተቋማትን እንደሚያሳትፍ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አዘጋጁ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን ጨምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ጤና ሚኒስቴር፣ ማዕድን ሚኒስቴር፣ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ… ከተሳታፊ ተቋማቱ መካከል ይገኙበታል።
ውድድሩ የተለያዩ አዝናኝ ጨዋታዎችን ጨምሮ አምስት የስፖርት ውድድሮች ይካሄዱበታል። እነዚህም እግር ኳስ፣ ቮሊቦል፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቼዝ እና ዳርት ናቸው። በውድድሩ መክፈቻ ዕለት በውድድሩ አዘጋጅ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና ኢትዮ ቴሌኮም መካከል የእግር ኳስ ውድድር የተከናወነ ሲሆን፤ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መለያየት ችለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረገው ይህ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላም በሀገር አቀፍ ደረጃ የመንግሥት ተቋማት የስፖርት ለሁሉም ውድድርን ለማከናወን ታቅዷል። ውድድሩን አስመልክቶም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ ሠራተኛው ጤናማ፣ ምርታማ እና ግንኙነቱም ውጤታማ ሳይሆን ሀገር የምትፈልገውን የእድገት ደረጃ ማስመዝገብ የማይቻል መሆኑን ይጠቁማሉ።
የፌዴራል ተቋማት የስፖርት ውድድር በሙያተኞች እየታገዘ ላለፉት 16 ዓመታት ቢካሄድም የዘንድሮው ግን በተለያዩ ሀገራዊና ወቅታዊ ሁኔታዎች ውስጥ የሚደረግ በመሆኑ የሚጠበቀውን ያህል ተሳታፊ አልተገኘም። ይህን መሰል ውድድሮች በዓለም አቀፍ ስፖርት መርህ ውስጥ ስፖርት ለሁሉም በሚል ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም በስፖርት ልማት መርሆችና የስፖርት ፖሊሲ ውስጥ ኅብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሰራበት አካባቢ በስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ታስቦ ይሠራል።
ይህ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የሆነው የመንግሥት ሠራተኞች ውድድር ውጤታማ የሥራ ክንውን እንዲኖራቸው የሚያግዝ ነው። ይኸውም የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሁሉም ተቋማት ተግባር መሆንም ይገባዋል። ከዚህ ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመላው ኢትዮጵያ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የስፖርት ውድድር ለማካሄድ በተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። ዘንድሮም የሁሉንም ክልሎችን ያሳተፈ ውድድር ለማከናወን በትኩረት የሚሠራ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም