እንዴት በሁሉም ዘርፍ ጉራማይሌ ሆንን?

‹‹ብዝኃነት›› የሚለውን ቃል ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ ስለሚጠቀሙት ምናልባትም አሰልቺ የፕሮፖጋንዳ ቃል ሊመስል ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ በፖለቲከኞች ምክንያት ለዘመናት ሲያገለግሉ የነበሩ ቃላት ተደራቢ ትርጉም እንዲይዙ ተደርጓል። መደበኛ ትርጉማቸውን በመርሳት ከፖለቲካ ጋር ብቻ የማያያዝ ልማድ ይዳብራል፡፡ ለምሳሌ፤ በኢሕአዴግ ጊዜ ‹‹ልማት›› የሚለው ቃል አሰልቺ ሆኖ ነበር፡፡ ልማት የሚለውን ቃል ግን የኢትዮጵያ ገበሬ ለዘመናት ሲጠቀመው የኖረ ነው። በተለይም በመስኖ የሚለሙ ነገሮችን ‹‹ልማት›› እያለ ይጠራቸዋል። አርሶ አደሩ ልማት የሚለውን ቃል ያመጣው ልምላሜ ከሚለው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለምለም፣ ለምለሚቱ፣ ለማ… የሚሉ የሰው ስሞች ይወጣሉ፡፡ በአጭሩ ልማት የሚለው ቃል አረንጓዴን፣ ልምላሜን፣ ብዛትን፣ ጥሩ ነገርን የሚገልጽ ነው፡፡

ልማት የሚለውን ቃል ኢሕአዴግ በየመድረኩ ስለሚጠቀመው እየተሰለቸ መጣ፤ እንዲያውም በኋላ አካባቢ ልማት የሚለውን ቃል መጠቀም የካድሬነት መለያ እስከሚመስል ድረስ ቃሉ መቀለጃ ሆነ፡፡ አሁንም ‹‹ብልጽግና›› የሚለውን ቃል ከአሁኑ ገዥው ፓርቲ ጋር በማያያዝ የፓርቲው ብቻ እየተደረገ ነው። ብልጽግና የሚለው አማርኛ ግን ለዘመናት ሲያገለግል የቆየ ነው፡፡ ፖለቲካና ቃላትን በተመለከተ በሌላ ጽሑፍ እንመለስበታለን፡፡

የኢትዮጵያ ብዝኃነት ባሰቡት ቁጥር የሚያስገርም ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ሀገር ብቻ አይደለችም፤ ሁሉንም ሀገር ነች፡፡ የምዕራቡን ዓለም፣ የምሥራቁን ዓለም፣ የዓረቡን ዓለም… ሁሉ በየዓይነቱ የያዘች ናት። በመስከረም ወር ውስጥ እንዳስነበብነው፤ ኢትዮጵያ ማለት በአንድ ወር፣ በአንድ ቀን፣ በአንድ ሰዓት እና በአንድ ደቂቃ ውስጥ እንደ ራስ ዳሸን ተራራ አይነት የሚያንዘፈዝፍ ብርድ ያለባት፣ በዚያው ቅጽበት እንደ ዳሎል ያለ እንደ እሳት ላንቃ የሚገርፍ ሙቀት ያለባት ናት፡፡ በዚች ሰዓት በዚች ቅጽበት ሙቀት ያለባት፣ ብርድ ያለባት ናት፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር አካባቢ ጉም እና ብርድ ያለበት፣ በዚሁ አካባቢ ሸዋ ሮቢት ሙቀት ያለባት ናት። በባሌ ተራሮች፣ በከፋ ዞን ጫካዎች ብርድ ያለባት፣ በድሬዳዋና ጅግጅጋ አካባቢዎች ሙቀት ያለባት ናት። በተመሳሳይ ቀን ደብረ ብርሃን ብርድ ነው፤ አዳማ ሙቀት ነው፡፡ ይህ በተፈጥሮ ያገኘነው ፀጋ ነው፡፡

የሰዎችን ባሕልና ልማድ ደግሞ ልብ እንበል። በእርግጥ ባሕል እና ልማድ ተፈጥሮን መሠረት ሊያደርግ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ግን አዋሳኝ አካባቢዎችንና ጎረቤት ሀገራትንም መሠረት ያደርጋል። በዚህም ምክንያት የሰሜን ኢትዮጵያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የምዕራብ ኢትዮጵያ እና የምሥራቅ ኢትዮጵያ የተለያየ ባሕልና ሥነ ልቦና ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

አካላዊ ገጽታዎቻችንም ከፍተኛ ብዝኃነት ያለባቸው ናቸው፡፡ በጥቅሉ ‹‹ጥቁሮች›› ተብለን ብንጠራም ልክ እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተመሳሳይ ፊትና ጥቁረት ያለን አይደለንም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀይ የቆዳ ቀለም ያለው አለ፣ ነጭ የቆዳ ቀለም ያለው አለ፣ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው አለ፣ ጠይም የቆዳ ቀለም ያለው አለ፡፡ የፊት ቅርጽ የተለያየ አይነት አለ፡፡ በቁመትም ብዝኃነቱ የበዛ ነው፡፡

እነዚህ በተፈጥሮ የተገኙ ብዝኃነቶች ለሰው ሠራሽ ብዝኃነትም ምክንያት የሆኑ ይመስላል። ምንም እንኳን ሀብታም እና ድሃ በሁሉም ሀገራት ቢኖርም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ልዩነቱ የበዛ ይመስላል፡፡ ከአንድ ትልቅ ሆቴል አጠገብ የሚበሉት አጥተው የሚለምኑ የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ብዙ በምቾት የሚኖር፣ ብዙ በስቃይ የሚኖር፤ ብዙ ከልክ በላይ የሚመገብ፣ ብዙ በረሃብ የጠወለገ ያለባት ናት፡፡

በተፈጥሮ የተገኙት ብዝኃነቶቻችን ፀጋዎች ናቸው፤ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትታወቅ የሚያደርጉ የተፈጥሮ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ተፈጥሮንና አካባቢን ተከትሎ የተገነቡት የባሕል ብዝኃነቶቻችንም ውበታችን እና ኩራቶቻችን ናቸው፡፡ በዚያው ልክ የአስተሳሰብና የሥነ ልቦና ልዩነት መፈጠሩም ውበት ነው፤ ተፈጥሯዊ ነው፡፡

አስቸጋሪ እና አደጋ የሆነው ግን የአስተሳሰብ ልዩነቶቻችን መረን የለቀቁ እየሆኑ ነው፡፡ ጫፍና ጫፍ የረገጡ ተፃራሪ አመለካከቶች እየበዙ ነው፡፡ የአመለካከትና አስተሳሰብ ልዩነት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየገነገኑ የመጡት ግን ለሀገር አደጋ የሚሆኑ ናቸው፡፡ የጋራ ታሪክ ላይ፣ የጋራ ሀብት ላይ፣ የጋራ ሀገር ላይ የማይታረቁ የሚመስሉ መካረሮች እየታዩ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ በአንድ የጋራ ታሪክ ላይ በሀሳብ ልዩነት ከመወያየትና ከመከራከር ይልቅ አንደኛው ወገን የማምለክ ያህል ያደንቃል፣ አንደኛው ወገን ከታሪክ ገጽ መፋቅ አለበት ይላል፡፡ በዚህ መሐል የዚያ ታሪክ እውነታ ዋጋ ያጣል ማለት ነው፡፡ ሁለቱም የየራሳቸውን ፍላጎት ብቻ በመከተል ከእውነተኛ ክስተቱ ውጭ ያደርጉታል። ይህ ደግሞ   ሌሎች የተበላሹ ትርክቶችን እየፈጠረ የሌላ ሀገር እና የሌላ አገር ዜጎች የሆንን ያህል ያራርቀናል ማለት ነው። ልዩነታችን የውበት ሳይሆን የጥፋት ይሆናል ማለት ነው፡፡

ከፍተኛ የሆነ የሞራል ልዕልና ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ በዚያው ልክ ግን ከፍተኛ የሆነ የሞራል ዝቅጠት እየታየ ያለውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ለአስከሬን ክብር ያለው ሀገር ያለ አይመስልም፤ በዚያው ልክ ግን አስከሬን በገመድ ሲጎተት እና አስከሬን ሲሰቀል ያየነውም እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነ፡፡ አልጋውን ለእንግዳ ለቆ መሬት ላይ የሚተኛ ሕዝብ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ በዚያው ልክ ግን ከመሬቴ ውጣ የሚል ዘግናኝ ግድያ ያየነውም እዚሁ ነው፡፡

እነዚህኞቹ ልዩነቶቻችን ግን ከውበታዊ ልዩነቶቻችን የመጡ አይደሉም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው ልዩነት ውበት መሆኑን የማይረዱ ፖለቲከኞች በሚነዙት የጥላቻ ስብከት የተገነቡ ናቸው፡፡ ይህ የእገሌ እንጂ የአንተ አይደለም፤ ይህ የአንተ እንጂ የእገሌ አይደለም… የሚል አስተሳሰብ ባላቸው ዋልታ ረገጥ ፖለቲከኞች የተነዛ ትርክት ነው እንዲህ አይነት አጥፊ ልዩነቶችን የፈጠረው።

ይህ ባይሆን ኖሮ በሁሉም ዘርፍ ጉራማይሌ መሆናችን የልዩነት ሳይሆን የውበት ምንጭ ነው። የተፈጥሮና መልክዓ ምድር ልዩነታችን፣ የባሕልና ወግ ልዩነቶችን፣ የአካላዊ ገጽታ ልዩነቶቻችን ሁሉንም ያሟልን እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ደጋውንም ቆላውንም ወይና ደጋውንም ማሟላት መታደል ነው። ጠይሙንም፣ ቀዩንም፣ ጥቁሩንም መያዝ መታደል ነው፡፡ እነዚህን መታደሎቻችንን ግን የአስተሳሰብ ልዩነቶችንም እንደ ውበት በማየት እንድገመው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You