‹‹የካፒታል ገበያ በግልም ሆነ በመንግሥት በኩል ያሉትን የፋይናንስ ፍላጎቶችን የሚያሟላ ነው ››

-የኢትዮጵያ ሰነድ መዋለነዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስኪያጅ  ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር)

የካፒታል ገበያ የተለያዩ ጉዳዮችን ያካተተ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በዋናነት መገለጫው የኩባንያ ባለቤቶች ለግለሰቦች ድርሻ የሚሸጡበት አክሲዮን ላይ ያተኮረ መሆኑን ባለሙያዎች ያመለክታሉ፡፡ ከኩባንያ ድርሻ ሽያጭ ባሻገር የብድር ሰነዶች ግብይትን ማለትም የግምጃ ቤት ሰነድ (የቦንድ ሽያጭን)ም ያካትታል፡፡

የካፒታል ገበያ የዓለም ሀገራት ዜጎቻቸው የንግድ ልውውጣቸውን እና ኢንቨስትመንታቸውን ለማስፋፋት ሰፊ ሚና የተጫወተላቸው መሆኑ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከሃምሳ ዓመት በፊት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ በነበረበት ዘመን ጅምሮች የነበሩ ቢሆኑም፤ ደርግ ይከተል በነበረው ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በድጋሚ ማቆጥቆጥ የጀመረው ይኸው የካፒታል ገበያ፤ ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ ሲከናወን ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ደረጃ ሕግ ተበጅቶለት ቁጥጥር እየተደረገበት ወደ ተግባር ሳይገባበት ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በመንግሥት ደረጃ ትኩረት እየተሠጠው በመምጣቱ፤ አዋጅ ወጥቶለታል፡፡ የካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 መውጣትን ተከትሎ ከአንድ ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያም እውን የሚሆንበትን መሥመር እያገኘ መጥቷል፡፡

ገበያው ተዓማኒነት እንዲኖረው እና ኢንቨስትመንቱ እንዲበረታታ በሚል ከአዋጅ በተጨማሪ ፈቃድ የሚሰጥ እና ግብይቱ እንዲሳለጥ የሚያግዝ ተቋምም ተቋቁሟል፡፡ በተቋሙ ሥራ ከሚተዳደሩት መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ሰነድ መዋለነዋዮች ገበያ አንዱ ነው። የእዚህ የኢትዮጵያ ሰነድ መዋለነዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥላሁን እስማኤል ካሣሁን (ዶ/ር) ከተቋሙ መቋቋም ምክንያት ጀምረን፤ የካፒታል ገበያ ምንነት፣ ጠቀሜታውን እና ሌሎችንም ጥያቄዎችን አክለን ያቀረብንላቸው ሲሆን፤ ምላሻቸውን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ስለኢትዮጵያ ሰነድ መዋለነዋዮች ገበያ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የኢትዮጵያ ሰነድ መዋለነዋዮች ገበያ በዚህ ዓመት እንደ አዲስ የታሰበ አይደለም። በፕሮጀክት ቢሮነት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የተቀረፀ ነበር፡፡ የካፒታል ገበያ አዋጅ አንቀፅ 31 ላይ የኢትዮጵያ መዋለነዋዮች ገበያ በመንግሥት እና በግል በጋራ ይቋቋማል ይላል፡፡ አዋጁን ተከትለን ተቋቁመናል፡፡ እኛ የመንግሥትን ሚና ይዘን የግል ኢንቨስትመንትን እንስባለን፡፡

በመንግሥት በኩል ያለው የእኛ ኢንቨስተር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ነው፡፡ ይህ የተቋቋመው ባለፈው ዓመት ሲሆን፤ አብዛኞቹ የመንግሥት እሴት እና እሴቶችን ይቆጣጠራል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ (ኢ አይ ኤች)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ ኢትዮ ቴሌኮምን እና ሲቢኢን እንደባለቤት ያስተዳድራል፡፡ ስለዚህ እኛንም የሚያቋቁመን እርሱ ነው፡፡

የግል ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እስካለ ድረስ መንግሥት ከ25 በመቶ ያልበለጠ እጅ ይኖረዋል። ሌላው ደግሞ የግል ዘርፉ ኢንቨስተር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በኮሜርሺያል ኮድ የምንተዳደር ኩባንያ ነን ማለት ይቻላል፡፡ ፍቃድ የመስጠትን እና ቁጥጥር የማካሔድን ሥራ የሚያከናውነው የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን እና እኛ እንለያያለን።

የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ተቆጣጣሪ ነው። እንደብሔራዊ ባንክ ማለት ነው፡፡ እኛ ደግሞ እንደንግድ ባንክ ነን ማለት ይቻላል፡፡ በመንግሥት ድጋፍ ብንቋቋምም የምንተዳደረው እንደግል ድርጅት ነው፡፡ በግልፅ የተቋቋምነው በኅዳር 2016 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ አሁን የቦርድ ዳይሬክተር አለ፡፡ ሠራተኞችን እየቀጠርን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ዋናው ሥራችሁ ምንድን ነው?

ዶ/ር ጥላሁን፡- ካፒታል የሚፈልጉ ተቋማት ወደ ኢንቨስተሮች ወርደው ካፒታል ይሰበስባሉ፡፡ ኢንቨስተሮቹ ማለትም ሰነደ መዋለነዋዩን የሚገዙት፤ አንደኛው መዋለ ነዋይ አክሲዮን ነው፤ አክሲዮኖችን ይገዛሉ፡፡ ሌላ ሰነደ መዋለነዋይ ደግሞ ቦንድ ነው። ሌላኛው ደግሞ የግምጃ ቤት ሰነድ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ኢንቨስተር ከገዛ በኋላ ወዲያው ትርፍ (የሚያገኘው ፈሳሽ ገንዘብ) የለውም፡፡ ለምሳሌ ቀደም ሲል አንድ የግምጃ ቤት ገዢ ሰነድ እስከሚያተርፍ ልጠብቅ ካለ 360 ቀን፣ ወይም 90 ቀን መቆየት ግድ ይለዋል፡፡ ቦንድ ከሆነ እስከ ቦንዱ ማጠናቀቂያ፣ አክሲዮን ከሆነም ትርፉ በአክሲዮን የትርፍ ክፍፍል እስከሚደርሰው ይጠብቃል፡፡

ከድሮ ጀምሮ አሜሪካን ውስጥ ወይም ያደጉ ሌሎች አገሮች ላይ ሰዎች አክሲዮን ይሻሻጡ ነበር። ይሻሻጡ የነበረው ገበያ ዛፍ ጥላ ሥር፣ ካፍቴሪያ ወይም አንድ ሆቴል ውስጥ ሆነው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ በ1960ዎቹ አካባቢ ብሔራዊ ባንክ እየተቋቋመ በነበረበት ጊዜ፤ አክሲዮን ገበያ ፈጥረው ብሔራዊ ባንክ ውስጥ ሰዎች ይገበያዩ ነበር፡፡

አሁን ደግሞ እኛ ኤሌክትሮኒክ የመገበያያ መድረክ እየፈጠርን ነው፡፡ ከሌላ ሰው ላይ ብዙ ሺህ ሰዎች አክሲዮን መግዛት እና መሸጥ ይፈልጋሉ። የእኛ አሠራር ሰዎች ወደ ኤሌክትሮኒክ ገበያ መጥተው ሰነድ መዋለ ነዋዮችን እንዲሻሻጡ ያስችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ጉዳያችን ዝውውር (liquidity) መፍጠር ነው። አንዱ ሻጭ ሌላው ገዢ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ማዘጋጀት ነው ብለን መውሰድ እንችላለን።

ከዚህ በፊት ቦንድንም፣ የግምጃ ቤት ሰነድንም ሆነ አክሲዮንን መሐል ላይ ለመሸጥ የሚፈልግ ግብይት የማካሔጃ መንገድም ሆነ ቦታ አልነበረውም፡፡ አሁን ግን አንዳንዶች ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ በቴሌግራም እና በኋዋትስአፕ የሚሻሻጡበት አካሔድ አለ፡፡ ይህ ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ ሲሆን፣ አንደኛ ውድ ነው፤ ሁለተኛ አደጋ አለው፡፡ በአጠቃላይ ግን የሰነደ መዋለነዋይ ገበያ ተቋም ማለትም የእኛ ተቋም ሥራ ይህንን ገበያ ያደራጃል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉንም አክሲዮኖች እና ቦንዶችን ከወረቀትነት እና ከቁስ አካልነት ወደ ቁስ አልባ አካልነት እንቀይርና ኤሌክትሮኒክ መዝገብ ውስጥ እናስቀምጣቸዋለን፡፡ ከዛ ኢንቨስተሮች መግዛት እና መሸጥ ሲፈልጉ፤ እንደማንኛውም ገንዘብ እንደማስተላለፍ ይሆናል ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ይሔ ለማን ምን ይጠቅማል?

ዶ/ር ጥላሁን፡- ዋናው ሰዎች ተደፋፍረው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይረዳል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ኩባንያዎቹ ባለሥልጣኑ ጋር መጥተው የኢንቨስትመንት መግለጫቸውን ያስመዘግባሉ፡፡ ከዛ ሕዝብ ጋር ወርደው አክሲዮን ይሰበስባሉ፡፡ ሕዝቡ አክሲዮን ከገዛ በኋላ ደግሞ፤ መሸጥ እና መግዛት የሚፈልግ ወደ እኛ ይመጣል ማለት ነው፡፡ ሰዎች ወደ እኛ ገበያ የሚመጡት በአገናኝ አማካኝነት ነው። ነገር ግን በዚህ ዘመን በተንቀሳቃሽ ስልክ አፕልኬሽን እና ዌብሳይቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ገበያው ላይ መጥተው በአገናኛ አባላቸው በኩል በተንቀሳቃሽ ስልካቸው መግዛት እና መሸጥ ይችላሉ፡፡

ስለዚህ ዋናው ሥራችን ለሁሉም ሰው በሚያመች መልኩ የአክሲዮን ገበያ ዝውውር (ስቶክ ኤክስቼንጅ)ን መፍጠር ላይ እናተኩራለን፡፡ የሰነድ መዋለነዋዮች ገበያ የአክሲዮን ገበያ ዝውውር ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከማስቻል በተጨማሪ፤ ለዋናው ገበያ የተሳለጠ ግብይት ለመፍጠር ሰፊ አስተዋፅኦ አለው። ስለዚህ ኩባንያ ነን። ፍቃድ የሚሰጠን ባለሥልጣኑ ነው፡፡

የገበያ ጉዳይ ሲነሳ ለጊዜው ቢያንስ ሦስት ገበያዎች አሉን፡፡ አንደኛው የአክሲዮን ገበያ ነው፡፡ በእዚህ ውስጥ ከፍተኛ አቅም ያላቸውን የምንዘረዝርበት ዋና መድረክ ይኖራል፡፡ ከእዛም ለአነስተኛ እና ጥቃቅን ኩባንያዎች የምናገበያይበት አነስተኛ ቦርድ ይኖራል። ሁለተኛው ደግሞ የዕዳ ሰነዶች ገበያ፤ የቦንድ ገበያ ይኖራል፡፡

ከመንግሥት አንፃር ስናየው የመንግሥት ቦንድ ለምሳሌ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ የሚገዙት ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ይኖራሉ፡፡ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ከገዙ በኋላ ከእነርሱ በቀላሉ ማንኛውም ሰው ከሞባይሉ ላይ እንዲገዛ እና እንዲሸጥ ዕድል እንሠጣለን፡፡ ስለዚህ ይህንን የዕዳ ሰነዶች ገበያ ላይ ዜጎች ተሳትፈው መግዛት ከቻሉ መንግሥትም ከውጪ ብድር እና ድጋፍ ላይ ከማዘንበል ይልቅ፤ በሀገር ውስጥ ፋይናንስ በጀቱን ለማሟላት ምቹ ሁኔታን ያገኛል ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ንብረቶች ላይም ዜጎች በቀላሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ዕድል ይፈጠራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የካፒታል ገበያ ሥርዓት መርሑ ምንድን ነው?

ዶ/ር ጥላሁን፡- ዋነኛው የካፒታል ገበያ ሥርዓት መርሑ በመንግሥት ደረጃ የፋይናንስ ምንጩ ምንድን ነው? ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ግብር ይሰበስባል፤ ከዚያም አገልግሎት ይሠጣል። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የምንተዳደረው ከግብር በሚገኘው ገቢ ብቻ አይደለም፡፡ በዘንድሮ ዓመት እንኳ ቢታይ በጀታችን ከ800 ቢሊዮን አልፏል። የታክስ ገቢያችን ግን ግማሹንም አይሸፍንም፡፡ ስለዚህ እርሱን ለማሟላት የውጪ ብድር እና ድጋፍ ከዛ ደግሞ አንዳንዴ የብሔራዊ ባንክ ብድር ላይ በመመሥረት በጀቱ እንዲሟላ እናደርጋለን፡፡

ከበጀት ጉድለት በተጨማሪ በሌላ በኩል ያልተሟላ የጊዜው ጥያቄ እና የሕዝብ ፍላጎት አለ፡፡ በቀላሉ ፍላጎትን ማሟላት አለመቻል፤ ወይም ክፍተት አለ፡፡ የካፒታል ገበያ ሥርዓት ጥቅሙ ያንን ክፍተት ለመሸፈን ያግዛል፡፡ ስለዚህ መንግሥት እስከ አሁን ቦንድ ሲሸጥ ወይም የግምጃ ቤት ሰነድ ሲሸጥ ብዙ ተሳታፊ አልነበረውም፡፡ አሁን የተሳታፊዎቹን ቁጥር ማስፋት ይቻላል፡፡

አንድ ተቀጣሪ የግምጃ ቤት ሰነድ ገዝቶ ላያውቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሺህ ወይም አምስት ሺህ ብር ባንክ ያስቀምጥ ይሆናል፡፡ ባንክ ተቀምጦ ሰባት በመቶ ወለድ ከመሰብሰብ ይልቅ፤ አሁን ለግምጃ ቤት ሰነድ መንግሥት አስር በመቶ ይከፍላል፡፡ በተጨማሪ ከግብር ነፃ ነው፡፡ ስለዚህ ባንክ ገንዘብ የሚያስቀምጥ ሰው የግምጃ ቤት ሰነድ መግዛት ይሻለዋል፡፡ ኩባንያዎች፣ ውጪ ያሉ ዜጎችም ሆኑ ኢንቨስተሮች አክሲዮን መግዛትም ሆነ በሽያጩ ላይ መሳተፍ ይችላሉ። በመንግሥት በኩልም አስፈላጊነቱን ስንመለከት የተጠራቀመ የረዥም ጊዜ የፋይናንስ ፍላጎትን ለማሟላት ዕድል ይሰጣል፡፡ ተቋሙ ኢንቨስተሮችን ያመጣል፤ መንግሥት ሰነዶችን ያቀርባል፡፡ ስለዚህ ያ ፍሰት ተሳትፎን ያበረታታል፡፡

በሌላ በኩል የግል ዘርፉም ከፍተኛ የፋይናንስ ክፍተት አለበት፡፡ ነጋዴዎች የሚሠሩት ግማሹን ከኪሳቸው፣ ግማሹን ከባንክ ብድር ወይም ከግለሰቦች ብድር ነው፡፡ ያም ሆኖ ከአስር ዓመት በላይ የሚመለስ የረዥም ጊዜ ብድር የሚያበድራቸው የለም፡፡ ባንኮች የሚያበድሩት ለአጭር ጊዜ ነው፡፡ ምክንያቱም ባንኮች ዋና ምንጫቸው ተቀማጭ ነው፡፡ አስቀማጩ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘቡን አምጡ ሊላቸው ይችላል። ስለዚህ ለሃያ እና ለሠላሳ ዓመት ለድርጅት ገንዘብ አያበድሩም፡፡ ስለዚህ ይሔኛው የመዋለነዋዮች ገበያ ለዚህ መፍትሔ ይሰጣል፡፡

ኩባንያዎች አሁን የተሻለ ገንዘብ የማግኛ አማራጭ ይኖራቸዋል፡፡ የካፒታል ማርኬት ጥቅሙ ይሔ ነው። ባለሃብቶቹ አክሲዮን ሲገዙ በሚቀጥለው ዓመት አምጡ ብለው አይጠየቁም፤ ሻጮቹም ግዴታቸው የትርፍ ክፍፍል እንዲዳረስ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ በኩል አክሲዮን ገዢዎች ደግሞ፤ እንደባለአክሲዮን ሆነን የድርጅቱ ዕድገት ላይ ሚናችንን እንድንወጣ ዕድል ይሰጣል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ የግል ዘርፉ ያለበትን የፋይናንስ ክፍተት ያሟላል፡፡

አንዳንዴ ደግሞ የግል ድርጅቶች መሥራት ያለባቸው በጣም ለሀገር አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህም የረዥም ጊዜ ብድር ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የኃይል ማመንጫ፣ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የወረቀት ፋብሪካ ላይ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ እንፈልጋለን፡፡ ግን ደግሞ እነዚህ ላይ ለመሠማራት ከፍተኛ ፋይናንስ ያስፈልጋል፡፡ ትርፋቸውም በአንድ እና በሁለት ዓመት የሚታይ ላይሆን ይችላል፡፡ ከባንክ ተበድረው ሥራውን ለማከናወን ይከብዳቸዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ በኩልም ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

አሁንም ቢሆን ብዙዎቹ ባንኮች የተቋቋሙት አክሲዮን ሽጠው ነው፡፡ በአጭር ጊዜ አትራፊ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በረዥም ጊዜ ግን አትራፊ ናቸው። ስለዚህ ዋና ጥቅሙ በግልም ሆነ በመንግሥት በኩል ያለ የረዥም ጊዜ የፋይናንስ ፍላጎትን ማሟላት ነው። ግለሰብም ቢሆን ሁል ጊዜ ገንዘብ ያለው ሰው ሪል እስቴት ብቻ ገዝቶ አይችልም፡፡ በሌላ በኩል አነስተኛ ኢንቨስተሮች ሪል እስቴት መግዣ ገንዘብም ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ለልጆቻችንም ሆነ ለእኛ በረዥም ጊዜ ትርፍ የምናገኝበት ኢንቨስትመንት ስንፈልግ አቅም ካለን ሆቴል እንገነባለን። አቅም ከሌለን ደግሞ ሆቴል ከሚገነባ ሰው ጋር የአንድ ሺህ ብርም ሆነ የአምስት ሺህ ብር ድርሻ እንገዛለን። ይህን ማድረጋችን ለራሳችንም ሆነ ለኢንቨስተሮችም ጥቅም አለው፡፡ ስለዚህ ዋና ግቡ ይህ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል? የሕግ ድጋፉና ያሉ ክፍተቶች ምን ይመስላሉ?

ዶ/ር ጥላሁን፡- አሁን ወዳለው አሠራር ከመምጣታችን በፊት በዋናነት ዛሬ ላይም ቢሆን ትንሽ ወደ ኋላ ብንቀርም ወደ 400 ሺህ አካባቢ ሰዎች የአክሲዮን ድርሻ እንዳላቸው ይገመታል። 30 ባንኮች እና 18 ኢንሹራንሶች የተቋቋሙት በአክሲዮን ማኅበር ተደራጅተው ነው፡፡ 400ሺውም ባለአክሲዮኖች የፋይናንስ ፈሰስ ይፈልጋሉ፡፡ እርሱን የማዘመን ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ያንን ለማድረግ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ተቋቁሟል፡፡ ስለዚህ እነርሱ መመሪያ እያወጡ ነው፡፡ መመሪያው ለእኛ ፈቃድ የሚሰጡበት፣ ለአገናኝ አባላት ፍቃድ የሚሰጡበት፣ ለኢንቨስትመንት ባንኮች ፍቃድ የሚሰጡበት መንገድ ላይ ያተኮረ ነው። ስለዚህ የሕግ እና የፖሊሲ ዝግጅት አካባቢ ብዙም ክፍተት የለም፡፡

ዋናው ክፍተት፤ የኢንቨስተር የዕውቀት ደረጃ እንዲሁም አክሲዮን ሽጠው ኩባንያ የሚሆኑበት ሁኔታ ውስን መሆን ነው፡፡ ስለዚህ የተቋማትን አቅም ማጎልበት ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ በእኛ ድርጅት እንዲገበያይ የሚፈቀድለት ድርጅት ኦዲት የሆነ የፋይናንስ ሪፖርት ያስፈልገዋል። ምክንያቱም የምናገበያየው አክሲዮን የግድ ተዓማኒነት ያለው መሆን አለበት፡፡ የኮርፖሬት ማረጋገጫ መመዘኛዎችን ማሟላት ይጠበቅበታል። ያ ደግሞ ከዜሮ የሚነሳ አይደለም፡፡ አሁን ላይ ትንሽ እንቅስቃሴዎች አሉ። ግን ደግሞ ብዙ ክፍተቶች አሉ። ብዙ ርቀት መጓዝ ያስፈልጋል። አካውንቲንግን የሚያጠና እና የሚያዘምን ቦርድ ተቋቁሟል፡፡ ስለዚህ እነርሱ ብዙ የማሻሻያ እና የድጋፍ ሥራ እየሠሩ ነው። እኛ ቅድሚያ መደገፍ አለብን። ሌላውም መደገፍ አለበት፡፡ በኩባንያዎቹ በኩል ዝግጁነት ይጠይቃል፡፡

ሌላው ክፍተት ደግሞ ኢንቨስተር፤ የሚገዛውን ማወቅ አለበት፡፡ የግምጃ ቤት ሰነድም ሆነ ቦንድ እንዲሁም አክሲዮን ምንድን ነው? የእኔ መብቶች ምንድን ናቸው? ጥቅሙ ምንድን ነው? ከሌላ ኢንቨስትመንት ይሔ በምን የተሻለ ነው? በምን ይለያል? ለእኔም ለሀገሬም ምን ያህል ይጠቅማል? የሚለውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ ትምህርታዊ ሥራ መሠራት አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ያለው ክፍተት እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ጥላሁን፡- በእርግጥ በቴክኖሎጂ በኩልም ክፍተት ይኖራል፡፡ ነገር ግን ዋናው ጉዳይ ግለሰብ ጥቅም እስካገኘበት ድረስ ወደ ቴክኖሎጂውም ሆነ ወደ አክሲዮን ግዢ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ሁኔታውን እየተከታተለ ባንክ ከማስቀመጥ፣ ሕንፃ ወይም መሬት ከመግዛት የተሻለ ነው ብሎ አወዳድሮ ይመጣል፡፡ ስለዚህ የእኛ ሥራ ዓላማው ግብ እንዲመታ ማስቻል ነው፡፡

የእኛ ሥራ ቴክኖሎጂን በተከተለ መልኩ አንድ ሰው የኢንቨስትመንት መጠኑ አነስተኛ ሆኖ በቀላሉ መግዛት እንዲችል እና እንዲሸጥ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ሺህ ብርም፣ አምስት ሺህ ብርም ሆነ አስር ሺህ ብር ያለው ሰው ድርሻ መግዛት እንዲችል እናደርጋለን ስንል፤ በዋናነት ገበያውን የሚያገናኙ አካላት ይህንን ሥራ ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ‹‹አምስት ሺህ ብር አለኝ፤ ድርሻ መግዛት እፈልጋለሁ›› ሲል የት መግዛት እንደሚችል አገናኛ አካላት ያማክሩታል፡፡ እነዚህ አገናኞች ፍቃድ እየወሰዱ ነው፡፡ ፍቃዳቸውን ሲጨርሱ ደግሞ በቴክሎጂም ሆነ በሌላው መልክ ላይ ሥልጠና ይወስዳሉ፡፡

ስለዚህ ዞሮ ዞሮ በቀጣይ ከፍተኛ የመማር እና የማስተማር ሥራ መሠራት አለበት፡፡ እኛም የራሳችንን ሚና እንወጣለን፡፡ ነገር ግን ሰው ስለተማረ ብቻ ኢንቨስት አያደርግም፤ ማበረታቻ ይፈልጋል፡፡ ማበረታቻው ካለ ሰው ራሱን ለመማርም ለማስተማርም ዝግጁ ይሆናል። ይህ ማለት ግን እንደዚሁ ግር ተብሎ የሚደረግ ግብይት አለ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያታዊ የሆነ ውሳኔ እንዲወስን ማስቻል አለብን፡፡

ሁለተኛ ከቴክኖሎጂ አንፃር ልምምዱ አለ፡፡ ለምሳሌ ምን ያህል ሰው የሞባይል ዋሌት ተጠቃሚ ነው? ቢባል በጣም ብዙ ሰው እየተጠቀመ ነው፡፡ የእኛ ገበያ ሥራው የሚሆነው ያንን ማስቻል ነው። ሰው በእጅ ስልኩ አክሲዮኖችን በቀላሉ ማየት እና ለምን እንደሚገዛቸው እስከገባው ድረስ የመግዛት እና የመሸጥ ውሳኔን ለመወሰን ቀላል እናደርግለታለን። ይህ ሲታይ እንደውም ሌሎች አገሮች ላይ ድሮ ከነበረው አካሄድ የእኛ የተሻለ ዕድል አለው፡፡ ብዙ ሰው ዘመናዊ የእጅ ስልክ (የስማርት ፎን) ተጠቃሚ ነው፡፡ በስልክ በኩል ብዙ መረጃ ያገኛል። ስልክ ለመጠቀም ርካሽ ነው፡፡ ቢያንስ ኢንተርኔት ለማየት ለማንበብ እና መረጃ ማግኘት እንዲችል እንሠራለን፡፡

በተጨማሪ በቀጣይ የዲጂታል አካዳሚ ይኖረናል። ሰዎች እያዩ በነፃ መጥተው ኮርሶችን የሚወስዱበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ከፋይናንስ ጀምሮ፤ የግል ፋይናንሳቸውን በተመለከተ እንዲሁም ቁጠባ ምንድን ነው? ለምን እቆጥባለሁ? ምን ያህል እቆጥባለሁ? ከቆጠብኩ በኋላስ ገንዘቤን ምን ላድርገው? የተሻሉ አማራጮች ምን አሉ? የካፒታል ገበያን የአክሲዮንንም ሆነ የቦንድን ገበያ ምንነት በተመለከተ የማስተማር ሥራን እንሠራለን። ያው ነገር ግን እንደተባለው ክፍተቱ አለ፡፡ ነገር ግን መሠረታዊው ጉዳይ የማበረታቻ ሥርዓቱን መፍጠር ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን ከተቋቁማችሁ በኋላ ምን ሠራችሁ?

ዶ/ር ጥላሁን፡– ከተቋቋምን ገና ሦስት ወር አካባቢያችን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በዚህ ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ወይም በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ መስከረም ሲጠባ ገበያውን በይፋ እናስጀምራለን፡፡ ስለዚህ ለእርሱ ከመንግሥት ካፒታል አግኝተናል፡፡ የግል ዘርፉን ካፒታል እያሰባሰብን ነው፡፡ ይሔንን በወር እና በሁለት ወር ውስጥ እናጠናቅቃለን። ማስታወቂያ እያወጣን ሰው እየቀጠርን ነው፡፡ በቢሮ በኩልም የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቢሯችንም ይሆናል፡፡ ስቱዲዮ ያለበት ወለል የገበያ ቦታ ይሆናል፡፡

አሁን ሲስተም እየገዛን ነው፡፡ ዋና የገበያ ማካሔጃ ሲስተም በሚቀጥለው ሁለት እና ሦስት ወር ውስጥ መዘርጋት እንጀምራለን፡፡ አገናኝ አባሎቻችንን ማሠልጠን እንጀምራለን፡፡ ኢንቨስተር የማስተማር ሥራ በንቃት እንሠራለን፡፡ ይሔ ሁሉ አዲስ የተጀመረ ወይም በሁለት ወር ውስጥ የተሠራ ሥራ ቢመስልም፤ ነገር ግን ቀደም ያሉ የተጀመሩ ሥራዎች ነበሩ፡፡ የሥራ ዕቅድ እና የፋይናንስ ናሙናዎችን እንዲሁም ሕጎችን የማዘጋጀት ሥራዎችን ቀድመን ስላጠናቀቅን ግፋ ቢል በስምንት ወር አብዛኛውን ሥራ እናጠናቅቃለን። ዞሮ ዞሮ ክረምቱን ካሳለፍን በኋላ የግብይት ሥራው መጀመሩ አይቀርም፡፡

አዲስ ዘመን፡-ቀድማችሁ ያሰባችሁት እና ችግር ሊሆንብን ይችላል ብላችሁ የገመታችሁት ምንድን ነው ?

ዶ/ር ጥላሁን፡- ከላይ እንደገለፅኩት የካፒታል ገበያ ምንድን ነው? እንዴት ለእኔ ይጠቅመኛል? ብሎ መረዳት እና ቶሎ ከእኛ ጋር በፍጥነት በመሔድ በኩል በግል ዘርፎች ላይ ትንሽ ክፍተት አለ፡፡ አንደኛው እርሱ ነው፡፡ ሁለተኛው የሠለጠነ የሰው ኃይል ችግር ነው። ትንሽም ብንሆን ሥራው ሲካሄድ 60 እና 70 ሰዎች ሆነን እንጀምራለን፡፡ ነገር ግን በዘርፉ ላይ የሠራ የሠለጠነ የሰው ኃይል የለም፡፡ ስለዚህ ሰዎችን አምጥቶ ማሠልጠን እና ማስተማር ይጠይቃል፡፡ ይህ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለባለሥልጣኑም ወደ ፊት ደግሞ አገበያይ ለሆኑት ባንኮች ሊያጋጥማቸው የሚችል ችግር ነው፡፡

እነርሱም ያንን ለማድረግ ብዙ ሥልጠና እየወሰዱ ነው፡፡ ለምሳሌ የእኛ ቡድን በንግድ ምክር ቤት በኩል ሲ አይ ኤስ የሚባል ሥልጠና ይወስዳል፡፡ በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በኩልም ሥልጠና እየተሰጠ ነው። ያም ሆኖ ሰው በራሱ ዝግጁ ልሁን ብሎ ማሰብ አለበት። መገናኛ ብዙኃንም ከባለሥልጣኑ ጋር ሆነን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥልጠና እንስጥ ብለን እየሞከርን ነው። የኢኮኖሚ ወይም የፋይናንስ ጋዜጠኝነት (ቢዝነስ ጆርናሊዝም) ላይ እንሠራለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ በሀገር ደረጃ የሚያመጣው ለውጥ ምን ያህል ይሆናል?

ዶ/ር ጥላሁን፡- መመዘኛችን ለአንዳንድ ሰዎች ወይም ኩባንያዎች የሚሆነው መጀመሪያ ከኪሳቸው ወይም ከባንክ ተበድረው ማግኘት ያልቻሉትን፤ ሀገር አቀፍ የሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፉ ዕድል ከሰጠ ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ ሃሳብ ይዞ በትክክል ቢተገበር ለሕዝብ አዋጭ የሆነ ምርት በመንግሥትም ሆነ በግል ዘርፍ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ቦንድ ሽጦ መንገድ ሊሠራ ይችላል፡፡ አዋጭ እስከ ሆነ ድረስ ለሁሉም ጥሩ ይሆናል። የግል ዘርፉም በራሱ አቅም ማድረግ ከሚችለው በላይ ሃሳብ አፍልቆ አክሲዮን ሽጦ ፕሮግራም ቀርፆ ድህነትን መቅረፍ ከቻለ ዋነኛው መለኪያችን እርሱ ነው፡፡

የካፒታል ገበያ በጣም አነስተኛ የሆኑ ታዳጊ ሀገራት ላይ ብዙም ሚና የለውም እየተባለ ይተቻል። ነገር ግን አፍሪካ ላይም ቢሆን ጥሩ ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ኬኒያ ነበር። ኬኒያ ላይ የናይሮቢ ገበያ ላይ ብዙ አክሲዮን ሽጦ ካፒታል ሰብስቦ እዛም የሚፈለገውን ፕሮግራም ተግብሮ ለእኛ የሚበቃ ገንዘብ ይዞ መጥቷል፡፡ አትርፎ ኢትዮጵያ ላይ ደግሞ ኢንቨስት እያደረገ ነው፡፡ 100 ሚሊዮን ብቻ ሳይሆን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ላይ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ካፒታል ገበያ ታዳጊ አገር ላይ እንኳ እንደዚህ ዓይነት ኢንቨስትመንቶች እንዲሳኩ ማድረግ ይችላል፡፡

በዓለም ላይ ደግሞ ሰፋ ያለ ነው፡፡ እያንዳንዱ ምርት ከአክሲዮን ጋር ተገናኝቷል፡፡ ለምሳሌ የምንገለገልባቸውን እያንዳንዱን ቁሳቁስ ስናይ ከአክሲዮን ገበያ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ለምሳሌ ጋዜጠኛ የሚቀዳበት የድምፅ መቅጃ ሶኒ ቢሆን በካፒታል ገበያ ያደገ የሶኒ ኩባኒያ ነው። የምንጠቀመው ስልክ አይፎን ቢሆን የአፕል ኩባንያ ነው። እያንዳንዳቸው በካፒታል ገበያ ያደጉ ናቸው፡፡ ትንንሽ ጋራዥ ውስጥ የቤተሰባቸው ቤት ውስጥ እየሠሩ የነበሩ ሰዎች፤ ሃሳቦቻቸውን ለሰዎች ሽጠው ካፒታል ሰብስበው ሰው ቀጥረው ሃሳባቸውን መተግበር ችለዋል። ከሀገራቸው አልፈው እኛን እያገለገሉ ነው፡፡ እነርሱ እንደዛ ካደረጉ፤ እኛ ለራሳችን እንዴት እናንሳለን? ዋናው ጉዳይ ይሄ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለግለሰብም ሆነ ለአገር አልፎ ተርፎ ለዓለም የሚጠቅም ነገር ሊያስገኝ የሚችል ለፈጠራ እና ለዕድገት የሚያመች፤ የካፒታል ገበያ ኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር አልዘገየም?

ዶ/ር ጥላሁን፡- ፖለቲካው ተቀያይሯል፡፡ ለምሳሌ በንጉሡ ጊዜ ወደ 17 አካባቢ ኩባንያዎች ነበሩን፡፡ ወንጂ ስኳር፣ አንበሳ ከተማ አውቶቡስ፣ ሳባ ጠጅ፣ አቢሲኒያ ባንክ እና ሌሎችም አክሲዮን ሽጠው ተደራጅተው ነበር። ይህ በ1904 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ ነገር ግን ደርግ ሲመጣ የአክሲዮን ካምፓኒዎች ተወረሱ፡፡ ስለዚህ ድራሻቸው ጠፋ፡፡ ከዛ ለውጥ በኋላ በአክሲዮን ገበያ ደረጃ መረጃም ባይደራጅ አክሲዮን እየሸጡ ማደራጀት ተጀምሮ ነበር፡፡ ለምሳሌ አዋሽ ባንክ በ1994 ዓ.ም አካባቢ ተደራጅቷል፡፡ ስለዚህ ቀደም ማለት ይቻል ነበር፡፡ ለምሳሌ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በ1990 አካባቢ ጀምረው ነበር፡፡ ቢያንስ የሥርዓት ለውጡን ተከትሎ ማስተግበር ይቻል ነበር። አሁንም ያው ቢዘገይም ከመተው መተግበር ይሻላል፡፡ ብለን ጀምረነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ፡፡

ዶ/ር ጥላሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You