ዓድዋ ድህነትን ለማሸነፍ የመንፈስ ስንቅ ነው!

የዓድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ተጋድሎና መስዋዕትነት ሀገራችንን ያስከበሩበት ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ አንፀባራቂ የሆነ ድል ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ መታገል እና በጋራ ድል መቀዳጀት የካበተ ልምድ ያለን ሕዝቦች መሆናችን የዓድዋ ድል ትልቅ ታሪካዊ ማሳያ ነው። ጀግኖች አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ድልን አጎናጽፈውናል፤ ለዚህ ክብር ላበቁን አርበኞች ክብር ይገባቸዋል፡፡

ዓድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን የአብሮነት፣ የአሸናፊነትና የጽናት ተምሳሌት ነው። የዓድዋ ድል በኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለሚገጥሙን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ሁሉ መሻገሪያ ድልድይ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ታሪካዊ ኩነት ነው።

ኢትዮጵያዊነታችን የጋራ ማንነታችን ምንጭ ነው። ሉዓላዊነታችንና ነፃነታችን በጋራ የከፈልናቸው መስዋዕትነቶች ውጤቶች ሲሆኑ፣ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባሕል አለመዳበር ደግሞ የጋራ ስብራታችን ነው።

እርስ በርሳቸው ለመታረቅ ተነሳሽነት የሌላቸው “የወዲያ ማዶና የወዲህ ማዶ” ጽንፈኛ የፖለቲካ አቋሞች ለዘመናት ሀገራችንን የጎዱ በመሆናቸው ከስር ከመሠረታቸው መታረም አለባቸው።

ኢትዮጵያ ከድህነት ጋር የምታደርገውን ትንቅንቅ ለአንዴና ለመጨረሻ ለመቋጨት ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን እንደፀጋ በመውሰድ ለጋራ ሀገራችን በጋራ በአብሮነት መቆም መቻል አለብን። ኢትዮጵያውያን በጋራ ሲቆሙ እንደ ዓድዋ አስደማሚና ለዓለም ሁሉ ትንግርት የሆኑ ታሪኮችን ማስመዝገብ እንደሚችሉ አስመስክረዋል። ጀግኖች አባት/እናቶቻችን በዓድዋ የጥቁሮች ሁሉ ቀንዲል የሆነ ድልን አስመዝግበው፣ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ሐረር ግንብ፣ አባጅፋርና የጢያ ትክል ድንጋይን የመሳሰሉ ታሪካዊ ዐሻራዎችን በማኖር ኩራትና ምንዳ ጥለው አልፈዋል።

ኢትዮጵያውያን በዚህ ዘመንም የዓባይ ግድብን ጨምሮ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ ጎርጎራና ሀላላ ኬላን የመሳሰሉ ሀገራዊ ገፅታን የሚቀይሩ ፕሮጀክቶችንና ዓለምን ያስደመመ አረንጓዴ አሻራን በማሳረፍ በአንድ ስንቆም መበልጸግ እንደምንችል አስመስክረናል። ኢትዮጵያዊያን በኅብር ስንቆም አርበኞች ነን ብለን እንድናምን የሚያደርገንም ይህ ነው! ሁሌም በድል ለመራመድና ሀገራዊ የብልጽግና ጉዛችንን ለማረጋገጥ በኅብር ሀገራዊ ገዥ ትርክት የሆነውን ብሔራዊ አርበኝነት ማጽናት ይገባል።

በጋራ ቆመን የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት የምንችልበት እርሾ በእጃችን ላይ አለ፡፡ ልዩነቶቻችንን አጥብበን በማያግባቡን ጉዳዮች ላይ በውይይትና ዕርቅ በመፍታት ነባር እሴቶቻንን በማስቀጠል በሀገራዊ ገዥ ትርክታችን በመግባባት ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማሻገር አለብን፡፡

ዓድዋ ጥሎልን ያለፈው ምንዳ አብሮነትን ክዶ ልዩነቶቻችን ላይ ብቻ ማተኮርን አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ መፈራረጅ ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባሕል ወደ ትብብር ለማሻገር ሕያው የዓድዋ ድል ብዙ ያስተምረናል፡፡

ኢትዮጵያውያን እልፍ አዕላፍ የወል ማንነቶችና ድሎች ባለቤት ነን። በጋራ በትብብር የምንኖርባት አንዲት ውድ ሀገር ኢትዮጵያ ስላለችን የወል ማንነት ያለን ሕዝቦች ነን። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባሕልና ታሪክ ኢትዮጵያዊ በሆነ ሀገር በቀል መነፅር የቃኘ፣ ላለፈው ትውልድ ወረት እውቅና በመስጠት በዚያው ላይ ለመገንባት የቆረጠ፣ የነበሩትንና ያሉትን የፖለቲካ ተቃርኖዎች ከመሠረታቸው በመፍታት ዘላቂ፣ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ቆርጠን መነሳት አለብን።

የዓድዋን ድል ለኅብረብሔራዊ አንድነታችንና ሁለንተናዊ ብልጽግናችን ለማረጋገጥ መጠቀም የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል! እኛም የዛሬ ትውልዶች ለአርበኞቻችን ክብር እየሰጠን ዘመኑን በመዋጀት ከአባቶቻችን ልቀን እንጂ አንሰን እንዳንገኝ የዛሬውን የጋራ ጠላት የሆነውን ድህንትን በማሸነፍ ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን የማስረከብ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል።

የዓድዋን ድል ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መጠቀምና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል። እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ ኢትዮጵያን ወደላቀ ከፍታ ለመውሰድና ታሪኳና ክብሯን የሚመጥን ሁለንተናዊ ከፍታ ለማብሰር የሁሉንም ኢትዮጵያውያን የጋራ አስተዋፅዖ ስለሚጠይቅ ዘመን ተሻጋሪና አካታች የሆነ ብሔራዊ ገዥ ትርክት በመገንባት ለትውልድ ማውረስ ወሳኝ ነው፡፡

የዓድዋ ድል ስኬታማ የሆነው በመላው ኢትዮጵያውያን የተደመረ የአንድነት መንፈስ በመሆኑ አሁንም ሆነ ወደፊት የሀገራችንን ዕድገትና ብልጽግና የምናረጋግጠው አሰባሳቢ በሆነ ብሔራዊ ገዥ ትርክት የወል እውነቶቻችንን እያፀናን በአብሮነት ዋነኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነት ለማሸነፍ በምናደርገው ጉዞ ነው። ለዚህ ደግሞ የዓድዋ ድል ትልቅ የመንፈስ ጥንካሬያችንና ስንቃችን ነው!

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You