ፍርድ ቤቱ በያሬድ ዘሪሁን፣ በተስፋዬ ኡርጌና ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ ፓሊስ የጠየቀውን 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።
ተጠርጣሪዎቹ በዛሬው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ነው የቀረቡት።
ፍርድ ቤቱ በያሬድ ዘሪሁን ላይ ከህዳር 26 2011 ጀምሮ ታሳቢ የሚሆን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
እንዲሁም በተስፋዬ ኡርጌ ላይ ፍርድ ቤቱ ከህዳር 24 2011 ጀምሮ ታሳቢ የሚሆን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
ፖሊስ ቀድሞ በተሰጠው ጊዜ ከተጠርጣሪዎች ጋር ተያያዥ የሆነ ማስረጃ እየሰበሰበ በመሆኑና የሚቀረው ስራ በመኖሩ በዋስ ቢወጡ ማስረጃ እንደሚያጠፉ ስለታመነበት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜው ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል ተብሏል።
የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጉዳይ የተመለከተው ፍርድ ቤት ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀን የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለታህሳስ 10 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በተመሳሳይ የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘውን ጉዳይ የተመለከተው ፍድር ቤት ለተጨማሪ ምርመራና ለቀሪ ስራ ማጠናቀቂያ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀን ፈቅዷል።
ይህም ከህዳር 24 ጀምሮ የሚቆጠር ሲሆን፥ ለታህሳስ 4 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በዛሬው የችሎት ውሎ የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ጠበቆች በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ላይ ሃሳብ እናቀርባለን ብለው የነበረ ቢሆንም ሳያቀርቡ ቀርተዋል።
ፍርድ ቤቱ ከሜቴክ ሰራተኞች ጋር ተመሳጥረው ከሁለት የውጭ ድርጅቶች የድለላ ፍቃድ ሳይኖራቸው ከተገዛ 2 ሺህ 500 ትራክተር 15 ሚሊየን ብር ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በተባሉት አቶ ረመዳን ሙሳ ላይ ለፖሊስ 14 ቀን በመፍቀድ ለታህሳስ 10 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሙስና በተጠረጠሩት ጋዜጠኛ ፍጹም የሽጥላ ፣ ትግስት ታደሰ እና ቸርነት ዳና ላይ ፖሊስ ቀደም ብሎ በተሰጠው ምርመራ ጊዜ የሰራውን በርካታ ስራ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። ዘገባው የኤፍቢሲ ነው