ተወልደው ያደጉት ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ከአምቦ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቶኬ አካበቢ ነው፡፡ እኚህ የገበሬ ቤተሰብ ያፈራቸው ታዋቂና አንጋፋ ፖለቲከኛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞ ስሙ ራስ መስፍን ስለሺ አሁን ደግሞ ጮኬ እየተባለ በሚጠራው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በአምቦ አጠቃላይ የተከተተሉ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በ1965 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መግባት ችለዋል፡፡ ገና የስምንትኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ የጀመረው ለመብትና ለነፃነት ዋጋ የመክፈል ፅኑ ፍላጎት ዩኒቨርስቲ ሲገቡም ፍላጎታቸውን በትምህርት ያግዙት ዘንዳ ምርጫቸውን ፖለቲካ ሳይንስ አደረጉ፡፡
ግና እንዳሰቡት የትምህርት ህይወታቸው አልጋ ባልጋ አልሆነላቸውም፤ በአገሪቷ ላይ ተፈጥሮ በነበረው ፖለቲካዊ ችግር ምክንያት ከአንድም ሁለት ጊዜ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም ከአዲስ አበባ እስከ ኔዘርላንድ ድርስ በመሄድ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እስክ ዶክትሬት አሳድገዋል፡፡ በተለይም ላለፉት 28ዓመታት የመንግስትን ህፀፅ ነቅሰው በማውጣትና በጥበባዊ መንገድ እያዋዙ በማቅርብ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል፡፡
ከፖለቲካው ጎን ለጎንም ራሳቸው በተማሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዛሬ ድርስ በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ለኦሮሞ ህዝብና ፍትህን ላጡ ዜጎች ዘብ በመቆም በግንባር ቀደምትነት የሚነሱት እኚህ የፖለቲካ ምሁር ታዲያ በቅርቡ በውጭና በአገር ውስጥ ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸውና አድናቆዎቻቸው መኖሪያ ቤትና ዘመናዊ መኪና ተበርክቶላቸዋል፡፡
የዛሬው የዘመን እንግዳችን የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ መሪ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከዚህ ቀደም ስለእርሳቸው ያልተወሩ ቁምነገሮችን ያጫውተውናል፡፡ ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስቲ ውይይታችንን የልጅነት አስተዳደጎ አሁን ላሉበት የፖለቲካ ህይወት ምንአይነት አስተዋፅኦ እንደነበረው በማስታወስ እንጀምር?
ፕሮፌሰር መረራ፡- ከሁሉም በላይ ሁለት ነገሮች ናቸው ወደ ፖለቲካ ህይወት እንድገባ ግፊት ያደረጉብኝ ብዬ አምናለሁ። አንደኛው የቤተሰቤ ሁኔታ ነው። በተለይም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳልገባ አባቴ መሞታቸውን ተከትሎ የአባቢው ባላባቶች ተመሳጥረው አባቴ ትተው የሄዱትን ሰባት በሬዎች አስወሰዱብን። ስለዚህ ትምህርቴን ትቼ የምገባበት ሌላ የተሻለ አማራጭ ስለሌለኝ ትምህርቴን አጥብቆ ወደመያዘ አዘነበልኩ።
ከዚያ ደግሞ በልጅነት ህይወቴ ውስጥ ቀላል ያልሆነ ድህነት ቤተሰቤ ላይ ስለተጫነ ባለጊዜዎች የሚያደርጉትን ተፅዕኖ መታገል እንዳለብኝ ፖለቲካ ውስጥም ሳልገባ ይሰማኝ ነበር። ከዚያ በኋላ ስምንተኛ ክፍል እንደገባሁ የተማሪዎችን ንቅናቄ እደግፍ ነበር። ከዚያ ጀምሮ በአንድ በኩል ትምህርቴን ሳልተው በሌላ በኩል ደግሞ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ እሳተፍ ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላም ያንን ትግሌን ቀጠልኩበት። ከዚያ አብዮቱ ከመጣሁ በኋላ የመኢሶን አባል ሆኜ ቀጠልኩ።
አዲስ ዘመን፡- የመጀመሪያ ዲግሪዎትን ሲማሩ ትምህርቶን ለማቋረጥ የተገደዱባቸውን አጋጣሚዎች እስቲ ይንገሩኝ?
ፕሮፌሰር መረራ፡- እንዳልኩሽ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከገባሁ በኋላ ሁለተኛ አመት ላይ ሆኜ አብዩቱ መጣ። በዚህ ምክንያት ደርግ ሁለት አመት እድገት በህብረት ዘመቻ ስለላከን ትምህርቴን ለማቋረጥ ተገደድኩ። ከዚያ መልስም ሁለተኛና ሶስተኛ ዓመት ከተማርኩ በኋላ እኔ አባል የነበረኩበት የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ/መኢሶን/ የተባለ ድርጅት የተወሰነ ጊዜ ከደርግ ጋር ይሰራ ነበር።
እኔም የድርጅቱን ስራ በተወለድኩበት አምቦ አካበቢ ለማቀናጀት ትምህርቴን አቋርጬ ተልኬ ለግማሽ አመት እንደቆየሁ ታላቅ ወንድሜን ጨምሮ 11 ሰዎች ተገደሉ። ከዚያም እኔ ለሰባት አመታት በተለየዩ የደርግ ፅህፈት ቤቶች ታሰርኩ። ከዚያ እንደወጣሁም ዲግሪዬን ጨርስኩ። በመቀጠልም ግብፅ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪን ተማርኩ። ከዚያም ኔዘርላንድ በሚገኘው ኢንስቲትዩት የዶክትሬት ዲግሪዬን ሰርቻለሁ። ከዚያ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሆኜ ቀጥያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በጣም ለጋ እድሜ ላይ ሳሉ ወደ ፖለቲካው መስመር መግባቶ በልጅነት ጊዜ በሚገባ ተጫውተው እንዳያድጉ እንቅፋት አልሆነበዎትም?
ፕሮፌሰር መረራ፡- ልጅ ሆኜ ትንሽ ፈረስ ጉግስ እሞካክር ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ትምህርቱን አጥብቆ መያዙ የግድ ስለነበርና ቅድም እንዳልኩት ሌላ አማራጭ ስላልነበረኝ ከሌሎቹ ልጆች በተሻለ ሁኔታ አጥብቄ መያዝ ነበረብኝ። በዚያ ምክንያት እንደማንኛው ልጅ እንደልቤ ተጫውቼ ለማደግ አልቻልኩም። ሌሎች ስፖርቶች ላይም አላዘወትርም። መመልከት እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ዶክተር መራራ አግብተዋል?
ፕሮፌሰር መረራ፡- ገና በእቅድ ላይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ምነው አልዘገዩም?
ፕሮፌሰር መረራ፡- እስከዛሬ ሌሎች ስራዎችን ስሰራ ስለቆየሁ አሁን ገና በማቀድ ላይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ግን በዚህ ምክንያት አጣሁት ብለው የሚቆጩት ነገር የለም?
ፕሮፌሰር መረራ፡- ያው ተገድጄ ብቻ ሳይሆን የራሴም ምርጫ ስለሆነ ትኩረት ነበር የምሰጠው ሌሎች ነገሮች ነው። ለምሳሌ ትምህርቴን ከዲግሪ እስከ ዶክትሬት ድረስ መጨረስ አለብኝ ብዬ አምን ነበር። ከዚያ ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ስገባ እሱም የራሱ ውጥረቶች ነበሩት። በዚያ ምክንያት ነው የቆየሁት። እናም ብዙውን ጊዜ የህይወት ምርጫ እኛ እንደፈለግነው አይሄድም፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የሚቀድሙ ነገሮች ስለነበሩ ነው እስካሁን ሳላገባ ቆይቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ማህበራዊ ሕይወት ላይስ እንዴት ኖት?
ፕሮፌሰር መረራ፡- በአብዛኛው ሰው ሲሞት እደርሳለሁ፥ ሲታመም እጠይቃለሁ፤ ሰርግ ስጋበዘም እሄዳለሁ። ከጎዳኞቼ ጋር ቡና እጠጣለሁ። በተቻለኝ አቅምና ጊዜ በማህበራዊ ህይወት ላይ እሳተፋለው። ስለዚህ በአጠቃላይ ማህበራዊ ህይወት ላይ ያለኝ ተሳትፎ መካከለኛ የሚባል ነው።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኛው የአምቦ ነዋሪ ለእርሶ ልዩ ፍቅር እንዳለው ይጠቀሳል፤ የትውልድ ስፍራዎ እዛ መሆኑ ነው ወይስ ለአምቦ ህዝብ ምን የተለየ ነገር ስላደረጉ ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፡- እኔ እንግዲህ በአምቦ ህዝብ ዘንድ በሁለት ነገሮች እታወቃለሁ ብዬ አምናለሁ። አንደኛው በትምህርቴ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የምታወቅ መሆኔ ሲሆን በተማሪ ንቅናቄ ውስጥ መሳተፌ ደግሞ ሁለተኛው በተለየ መንገድ እንድታወቅ አድርጎኛል ብዬ አምናለሁ። ከዚያ ደግሞ ወደ ሰፊው የትግል ህይወት እስካሁን ከአምቦ ያለመራቄ በነዋሪው ዘንድ የጎላ እውቅና እንዲኖረኝ ምክንያት ሆኖኛል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ዘመን ታስረዋል፤ እስቲ የሁለቱን ጊዜያት የእስር ሁኔታ ያነፃፅሩልኝ?
ፕሮፌሰር መረራ፡- አንቺም እንዳልሽው በደርግ ዘመን ለሰባት አመት፤ በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ አንድ አመት ከሁለት ወር ታስሪያለሁ። ለእኔ በብዙ መልኩ ከደርግ ጊዜ በላይ የኢህአዴግ የእስር ሁኔታ የከፋ ነው። እኔ ያየሃቸው አሰቃቂ ተግባራት የኢህአዴግ የእስር ሁኔታ በጣም አሳዛኝ የሚባል ነው። ለምሳሌ ብጠቅስልሽ በደርግ ዘመን ያልነበረውና አሰቃቂ የሚባለው ተግባር ሰዎች የማኮላሸት ተግባር ነው።
በጣም የማዝነውና ግራ የሚገባኝ ነገር ኢህአዴግ ለምን ከደርግ መማር እንዳልቻለ ነው። በተለይ ደግሞ ከተፈታው በኋላ በአጋጣሚ ጀርመን ሄጄ የሂትለርን አሰቃቂ ተግባራት በሚዩኒክ ከጎበኘሁ በኋላ የኢህአዴግ የሚለየው ሰውን ከነነብሱ አለማቃጠሉ ብቻ መሆኑን ለመገንዘብ ችያለሁ። እናም በእኔ እምነት በኢህአዴግ እስር ቤቶች የሚፈፀሙት በደሎች ከሂትለር ጋር የሚወዳደር እንጂ የሚያንስ አይደለም። ስለዚህ ከደርግ በብዙ ነገሮች ይከፋል ብዬ ነው የማስበው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ከእርስቤት ጋር ተያይዞ እርሶ አንድ ወቅት ላይ የኢህአዴግ ባለስልጣናትን ወደፊት ሌሎችን በአሰሩበት እስርቤት መግባታቸው ስለማይቀር እንዲያፀዱት የሰጡት ምክር አዘል ንግግር ዛሬ ላይ ያ እውን መሆኑ አንዳንዶች እንደ ትንቢት ይቆጥሩታል። እርሶ ግን ያ ሁኔታ መፈፀሙ ምን ስሜት ይፈጥርበዎታል?
ፕሮፌሰር መረራ፡- በተለይ አቶ በረከት ያሳዝነኛል። ምክንያቱም ብዙዎን ግዜ የኢትዮጵያን መንግስት በመወከል ከእኛ ጋር ይጨቃጨቅ ስለነበር ነው፡ እንደሚታወቀው በእኛ አገር ላለፉት 50 ዓመታት ጠበንጃ ያለው ያስራል፤ ጊዜው ሲመጣ ደግሞ በሌላው ይታሰራል። እና እንደዚህ አይነት ነገሮችን ማብቃት ሲቻልና ሲመጣ እንደ በረከት ያሉ የኢህአዴግ መሪዎች እጣ ፈንታቸው እስር ቤት መሆኑ ያሳዝነኛል። በተለይም እሱ የኢህአዴግ መጥፎ ፊቶች ከሚባሉት ግለሰቦች መካከል አንዱ እንደመሆኑ እሱም የሌላው እጣ ደርሶት መግባቱ ያሳዝነኛል።
አዲስ ዘመን፡- መጥፎ ፊት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፡- መጥፎ ፊት ማለት የኢህአዴግ መንግስት ከሰራቸው ወንጀሎች ከተወሰኑት የህወሓት መሪዎች ቀጥሎ የነበረው አቶ በረከት ነው። ስለዚህ አቶ በረከት ልክ እንደሌሎቹ ባለስልጣናት ባለተራ ስለነበር ለብዙዎች መታሰርና መገፋት አንዱ ምክንያት ነበር። እሱ ባለተራ ሆኖ ሌሎችን በሚያስርበት ስፍራ መታሰሩ ይህች አገር ለዘመናት በፖለቲካ መገፋፋትና መጠፋፋት አስፈላጊ እንዳልሆነ ተገንዝበው የኢህአዴግ ድርጅቶች ከገመድ ጉተታ ወጥተው በእኩል መንፈስ ለውጡን መምራት ይገባቸዋል። ሁላችንም የምንማርበት ይሆናል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ በህዝብ ላይ በደል የፈፀሙና አገር የመዘበሩ ተጠርጣሪ ባለስልጣናት በህግ ተጠያቂ መደረጋቸው ለአገር ሰላም ያለው ፋይዳ ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር መራራ፡- በእኛ አገር ህግ ማስከበር ሳይሆን ትልቁ ችግራችን ፖለቲካችንን ማስተካከሉ ነው። ፖለቲካችን ካልተስተካከለ በጉልበት ብቻ፣ በማሰር በመፍታት ብቻ የማይፈቱ ብዙ ጉዳዮች አሉ። በተለይ ደግሞ የመጠላለፍ ፖለቲካ የመተውና እነዚህን የማስተካከል ስራ ላይ ቢያተኩር ኖሮ የሚደርሱት ችግሮች ይቀንሳሉ የሚል ነገር አለኝ። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስትን የምመክረው ፖለቲካችንን ለማስተካከል ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። በዋናነትም ለአገራችን ብሄራዊ መግባባት መፈጠር የበኩሉን ሚና መጫወት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ነው የሚገነዘቡት? ያሉት መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶች ምንድን ናቸው?
ፕሮፌሰር መረራ፡- ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታታቸው፥ ሃሳብ በነፃነት የመግለጽ መብት በተግባር መረጋገጡ፥ የህግ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ለማሻሻል እርምጃዎች መጀመራቸውና መሰል ጉዳዮች በበጎነት የማያቸው ናቸው። ግን ደግሞ ወሳኝና በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል የምላቸው አምስት ጉዳዮች አሉ። የመጀመሪያው ለውጡን የሚመራው ኢህአዴግ ቢሆንም በስሩ ባሉ አራት ድርጅቶች በአንድ ላይ በለውጡ ጥልቀትና ፍጥነት ላይ አንድ መሆናቸውን እጠራጠራለሁ።
ስለዚህ ይህንን ለውጥ የት አድርሰው ያቆማሉ? እንዴት ይመራሉ? አሁንም ገመድ ጉተታ ውስጥ ናቸውን? ወይስ ከዛ ያለፈና ለመቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጅ ነገር ለመስራት እየሰሩ ነው? የሚለው ነገር አሁንም ጥያቄ ነው። ደጋግሜ እንደምናገረው ትልቁ የዶክተር አብይ ፈተና 100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ መምራት ሳይሆን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ለለውጥ መምራት ነው። ስለዚህ የኢህአዴግ ድርጅቶች ከገመድ ጉተታ ወጥተው በእኩል መንፈስ ለውጡን መምራት ይገባቸዋል።
ሁለተኛው በበርካታ የአገሪቱ አካበቢዎች በተዘዋወሩኩበት ወቅት ህዝቡ ‹‹ለውጡ እኛ ጋር አልደረሰም እባካችሁ ለዶክተር አብይ ንገሩልን›› ብለውናል። ስለዚህ ከዚህ መረዳት የቻልኩት ለውጡ እዚህ አልደረሰም የሚለው ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ ካልተሰጠውና ህዝብ አንድ ቀን ተስፋ ከቆረጠ ሊፈጠር የሚችለው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን ነው። ይህ ጉዳይ ያሳስበኛል። በተለይ ህዝብ ሲዘርፉና ሲያዘርፉ የነበሩት ባለስልጣናት ከቦታቸው አለመነሳታቸው የነበረው ሁኔታ ተመልሶ የማይመጣበት ምክንያት አይኖርም።
ሶስተኛው በየቦታው የሚፈነዱ ግጭቶች ወሳኝ መፍትሄ ካልተሰጣቸውና የህዝብ እምነት እየላላ ከሄደ ወደባሰ አገራዊ ችግር መቀየራቸው አይቀርም። አራተኛው ደግሞ ለውጥ ያመጣው፤ እኛንም ከእስር ቤት ያስወጣው፤ እነዶክተር አብይንም ወደስልጣን ያስመጣው፥ እነግንቦት ሰባትና ኦነግን ወደ አገር ያስገባው ወጣት ዛሬም መፍትሄ አለማግኘቱ ነው። ይሄ ወጣት ለውጥ የሚፈልገው ዛሬ ነው።እንጀራ የሚፈልገው ዛሬ ነው።
ያን ያክል በሚሊዮኖች የሚቆጠረውን ወጣት ህይወት የሚለውጥ ለውጥ አልመጣም። በእርግጥ ጊዜው አጭር ከመሆኑ የተነሳ ብዙ መጠበቅ አይቻልም። ግን አሁንም ለውጡን በተስፋ እየተጠበቀ ያለው ወጣት ካድሬው በጎን እየበላና ከዚህ ቀድም ሲሰራ እንደነበረው እየሰራ የሚቀጥል ከሆነ መልሶ ድንጋይ ወደ መወርወሩ እንዳይገባ ስጋት አለኝ።
የመጨረሻው ተግዳሮት መንግስትና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህችን አገር ወዴት እናድርሳት? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ አጀንዳ አልቀረፁም። ያ ባልተፈጠረበት ሁኔታ የተወሰኑት ወደ ቀኝ ሌላው ወደ ግራ ሲገፋ ይህ ለውጥ ያለ አቅጣጫ መንገድ ላይ ሊቀር ይችላል። እሱ ደግሞ ዋጋ ያስከፍለናል። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ስላሉ ባሉት ተስፋዎች ተመስርተን እየተንቀሳቀስን ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ቀላል ያልሆኑ ፈታኝ የሆኑ አደጋዎች ተጋርጠዋል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከጠቀሷቸው ጉዳዮች በተለይ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያለው አለመግባባት በምን መልኩ ሊፈታ ይገባል ይላሉ?
ፕሮፌሰር መረራ፡- እሱን እንግዲህ እኛ ቀደም ብለንም ለመምከርም ሞክረናል። ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማለት ነው። እንዳውም ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት አዲስ ደም፤ አዲስ ሃይል ወደ መንግስት እንዲገባ ኢህአዴግ መንገድ መክፈት አለበት ብለን ስንሟገት ነበር። አሁንም ለውጡ እዛው ነው የሚሽከረከረው ባይ ነኝ። ውሳኔ የሚወሰነው፥ ድርድር የሚደረገው እዛው ነው። ስለዚህ ካሉበት ሳጥን ውስጥ መውጣትና ማሰብ ይገባቸዋል። እሱን እስካሁን ድረስ አልጀመሩም።
ግን ደግሞ መፍትሄው እሱ ብቻ አይመስለኝም። ምክንያቱም እርስበርስ እየተጓተቱ በመሆኑ ነው። በተለይ ደግሞ ስልጣን ያጣው አካል እኔም ድምፅ አለኝ እያለ የለውጥ አራማጆችን እግር እየጎተተ ከሄደ የታሰበው ለውጥ ከግብ ይደርሳል ለማለት ይከብደኛል። ከዚህ መውጣት የሚቻለው በኢህአዴግ ቁመት ልክ የተሰፋው ጥብቆ ወደ 100ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ መሻገር ሲችል ነው ስለመብቱ መከራከር የሚችለው።
አሁን ግን በአንድ በኩል እነዶክተር አብይ አሉ ይላል፤ ከገፋንም ችግር ላይ ይወድቁብናል ብሎ ይፈራል፤ ዝም ማለቱ ደግሞ የተጨማለቁ ብዙ ነገሮች ይቀጥላሉ የሚል ስጋት ነው ያለው። የሚመጣውም ምርጫ አላስፈላጊ በሆነ መንገድ ሊዘገይ ይችላል፤ ከዘገየ ደግሞ ቀውስ መፍጠሩ አይቀርም።
ስለዚህ ለእኔ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አደገኛ የሆነ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት። ስለዚህ እነዶክተር አብይ እነዚህን ነገሮች በጥልቀትም በፍጥነትም ሊሄዱባቸው ይገባል። አለበለዚያ ቦንብ በፈነዳ ቁጥር እሳት የማጥፋት ስራ የትም አያደርስነም። አጠቃላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ አቅጣጫ ማስያዝ ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የማንነት ወይም የብሄር ፖለቲካ አሁን አገሪቱ ላለችበት ቀውስ የዳረጋት በመሆኑ የሚያስፈልገው የዜግነት ፖለቲካ ነው የሚሉ ሃይሎች ተበራክተዋል። በእዚህ ላይ የእርሶ እምነት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፡- የዜግነት ፖለቲካ ነው የሚያዋጣው ማለት ማንም ይችላል። ግን ይህን የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ ሃይሎች ብዙውን ጊዜ ጥንቃቄ ሲጎላቸው ይስተዋላል። አሁንም ይህንን ጉዳይ በአግባቡ ካልያዙት የሚመጣው አደጋ ሊከፋ ይችላል።በእኔ እምነት የዜግነት ፖለቲካንም ሆነ የብሄር ፖለቲካን የሚከተሉ ሃይሎች ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ህዝብ ነገ ሊሰጣቸው በሚችለው መጠን ካልገፉ በስተቀር አጉል የሆነና ፖለቲካውን ሊጎዳ የሚችል፣ አገሪቷን ለሌላ አደጋ ሊያዘጋጅ የሚችል ውጥረት ውስጥ ነው የሚገቡት።
እዚህ ጋር ለማንነት ልሙት የሚል ወገን አለ፤ ይህ እያለ የጎሳ ወይም የዘር ፖለቲካ አያስፈልግም ብሎ አንዳንድ ቦታ ሲሄድ ድንጋይ ሊወረወርበት ይችላል። እስከጠበንጃ ድረስ ይዘው ቢመጡበት ምን ሊያደርግ ነው? ስለዚህ እኔ የምለው ሁሉንም በልኩና በሚዛኑ ማካሄድ ይገባል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፡-እነዚህ የብሄር ፖለቲካ የሚያራምዱ ሰዎች ምንአልባት ከዜግነት ፖለቲካ ከሚያራምዱት የተሻለ ድጋፍ ሊኖራቸው ይችላል። «የሚያስፈገው የዜግነት ፖለቲካ ነው» ስትይ በጨዋ ቋንቋና በሰለጠነ መንገድ ካልሆነ በስተቀር የሌሎችን አስተሳሰብ «የዘርና የጎሳ ፖለቲካ ነው» ካልሽ ምንአልባት ህብረተሰቡ እንዳንኳሰስሽው የሚቆጥር በመሆኑ ዋጋ ሊያስከፍልሽ ይችላል።
ምክንያቱም ስያሜው ብቻውን የሚያራምዱትን አካል ሊጎዳ የሚችልበት አጋጣሚ በመኖሩ ነው። አደጋም አዝሎ ሊመጣ ይችላል። ስለዚህ መጠንቀቅ ይገባቸዋል ባይ ነኝ። አለበለዚያ ኢትዮጵያዊነትን አስተምራለሁ ብሎ ማንም ቢነሳ «እሱ ማን ነውና እኛን ስለኢትዮጵያዊነት የሚያስተምረን?» የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።
ለምሳሌ ባለፈው ትምህርት ቤት በዘር ተደራጀ ሲባል ወጣቶች እንዳለ ወጥተው የጀነራል ታደሰ ብሩ ትምህርት ቤት ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። እኚህ ሰው እንግዲህ በኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያላቸው ናቸው። በተጨማሪም ባንክ በዘር ይደረጃል ተብሎ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ላይ
በማግስቱ ድንጋይ ወረወሩ። ስለዚህ ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብን ወደ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ሊከት ይችላል። ኢህአፓና መኢሶንም በተመሳሳይ ወጣቱን ወደማይሆን መንገድ መሩት እነሱ ራሳቸው መልሰው ተጎዱበት። ያንን በህይወታችን ያሳለፍነውን ችግር መድገም አይገባንም ባይ ነኝ።
ስለዚህ ተከባብረን የመቻቻል ፖለቲካ እንፍጠር ፤ ማንም ሰው በፈለገው የመደራጀት መብቱ ሊከበርለት ይገባል፤ ይህ ሲሆን የተሻለች ኢትዮጵያ ልትፈጠር ትችላለች። ግን «የእኔ መንገድ ብቻ ነው መንግስተ ሰማይ የሚያደርሰው» ወደሚል ቅስቀሳ ውስጥ ከተገባ ወደማንወጣው አደጋ ውስጥ ነው የምንገባው።
አሁን ህብረተሰቡ ቅስቀሳውን ነው ያልወደደው። ምንአልባት ቅስቀሳው ከዚህ ቀደም ከነበረው በላቀ መልኩ የፖለቲካ ሃይሎች በማይፈልጉት ጊዜና መንገድ አላስፈላጊ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ግጭት ውስጥ ሊከት ይቻላል። ስለዚህ የዜግነት ፖለቲካቸው መብታቸው ነው። ግን ሲያራምዱ በጨዋና በሰለጠነ ቋንቋ ነው ሊሆን የሚገባው።
በግልፅ ለመነጋገር ያህል ወደ ቤቴ መጥተህ ስደበኝ ብሎ የሚቀበል ህዝብ አይኖርም። ስለዚህ እየተሳደቡ ሰው ቤት መሄድ ተገቢ አይደለም። እዛም ያሉትና አብረው በሰላም የሚኖሩትም ህዝቦች ማወክና ወደማይፈለግ መንገድ ወደ ግጭት እንዲገቡ መንገድ መክፈት ነው።
አንዳንዶቹ ጓደኞቼ ስለሆኑ ብዙውን ጊዜ ከዚህ አይነት አስተሳሰበ እንዲወጡ እመክራቸዋለው። ምንአልባት ንግገሮችን ስሜት ቀስቃሽ በማድርግ የተወሰነ ተከታይ ማስከተል ይቻል ይሆናል ግን ከዚያ ያለፈ ውድ ዋጋ የሚያስከፍል የፖለቲካ ጫወታ ውስጥ ነው የሚያስገባን።
አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል ግን የብሄር ፖለቲካ አራማጆች አሁን ላለው መደፍረስ ምክንያት ናቸው እየተባለ ይወቀሳሉ። እርሶ በዚህ ወገንስ ላሉት የሚሰጡት ምክር የለም?
ፕሮፌሰር መረራ፡- እሱን እንግዲህ ለመመለስ እኔ ብዙውን ጊዜ እንደምለው «ቡዳው ማነው?» የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ። ይህ ባልተለየበት ሁኔታ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይቸግረኛል። ዞሮ ዞሮ ግን ለሁሉም የማስተላልፈው መልዕክት ሌላ አገር የለንም ያለን አገር አንድ ነው የሚል ነው። በዚህ ላይ ኦነግም ሆነ ግንቦት ሰባት መስማማት አለባቸው።
ማንኛው ፖለቲካ የሚሰራው በዚሁ አንድ አገር ላይ ነው። ዲሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት ለመፍጠር ከዚህች አገር የተሻለ የለንም። እዚህ ላይ ተስማምተን በመቻቻል ፖለቲካ ህዝቡ የፈለገውን እንዲመርጥ መፍቀድ አለብን። በጨዋ ቋንቋ በሰለጠነ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎቻችንን ብናደርግ ይመረጣል።
በተመሳሳይ የብሄር ፖለቲካ የሚያራምዱ አካላት እነዚህ ነፍጠኞችና ትምክህተኞች የድሮው ስርዓት ናፋቂዎች ናቸው ወደሚለው ከሄዱ የሚፈጥሩት ችግር ተመሳሳይ ነው የሚሆነው።
ጨዋነት ከሁሉም ነው የሚጠበቀው። ስለዚህ ቅድም እንዳልኩሽ ቡዳው ማን እንደሆነ እስከምንለይ ድረስ ከሁሉም አቅጣጫ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በተለይ ህዝብን በማይሆን እና በማያስፈልግ ሁኔታ ግጭት ውስጥ አስገብቶ እሳቱ ሁሉንም ሲያቃጥል መልሶ ማልቀስ አስፈላጊ አይደለም። ፖለቲካችን መሰልጠን አለበት። ለዚህ ደግሞ የሁላችንም ሃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫው እየተቃረበ ነው፤ አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ መካሄድ አለበት ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር መረራ፡- የእኔ እምነት በተያዘለት ጊዜ ምርጫው መካሄድ አለበት የሚል ነው። ይህንን ለማለት ያስገደደኝም ሁለት ትላልቅ ስጋቶች ያሉኝ በመሆኑ ነው። አንደኛው ለውጥ የሚባለው ነገር ወደታች አልወረደም፤ ሁለተኛው የቀበሌና የወረዳ ምርጫዎች እስካሁን አለመካሄዱ ህዝብ ባልመረጣቸው ሰዎች እየተመራ ባለበት ወቅት ምርጫ ማራዘሙ የከፋ ችግር ያመጣል ብዬ ስለማስብ ነው።
ለእኔ እስኪመች ድረስ ብሎ ጊዜ መውሰድ ህዝብ ስህተት ሲሰራ መጠየቅ የምንችልበት ሁኔታ አይኖርም። ስለዚህ ህዝብን ወደዚያ ሁኔታ መግፋቱ አስፈላጊ አይደለም። ሌላው ስጋቴ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ይኖረናል ወይ? የሚለው ነው። ህዝብ ባልመረጠው አካል ነው እየተገዛ ያለው። ኢህአዴግ ባለፈው ምርጫ በምን መልኩ ስልጣኑን እንዳራዘመ እየታወቀ አሁንም ምርጫው ይራዘም ማለት ላልፈለግነውና ላልጠበቅነው ችግር ሊያስገባን ይችላል።
በተለይም ወጣቱ ለውጥ የሚፈልገው አሁን ነው። የምርጫውን መራዘም አልታገስም ካለ ይህ ወጣት ማነው ሊያሳምነው የሚችለው? ስለዚህ ኢህአዴግ በዚህ ጉዳይ ላይ ደጋግሞ ማሰብ አለበት። ይልቁንም ምርጫ ቦርድ የጠየቀውን በጀት ቶሎ ፈቅዶ የምርጫ አስፈፃሚዎችን መዋቅር እና ምልመላ አካሂዶ በተያዘለት ጊዜ ቢያካሂድ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
ዋናው መታየት የሚገባው ውድ ዋጋ የሚያስከፍል የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ እንደሚያስገባን ማወቁ ነው። ይህንን ማድረጉ ብዙ ቅሬታ ያለውን ህዝብ ልብ ሊገዛ ይችላል። የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል ምርጫ መካሄድ ያለበት ለዚህ ህዝብ እንጂ ዝግጅት ያንሰናል ለሚሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሲባል አይደለም። ስለዚህ ይህ የምርጫ ጉዳይ መጥፎ ቁማር እንዳይሆን ስጋት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የእርሶ ፓርቲ ለምርጫው ምንአይነት ዝግጅት እያደረገ ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፡- አቅማችን የፈቀደውን ያህል እየሰራ ነው። በአሁኑ ወቅት ስልጠና ውስጥ ገብተናል።ውይይቶችም እያካሄድን ነው የምንገኘው። እርግጠኛ ነኝ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ዝግጅት እያደረግን ነው። ግን አሁን ዋናው ጉዳይ የእኔ ፓርቲ ስልጣን እንዲይዝ ማድረጉ ላይ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጣን ምላሽና ለውጥ እንዲያገኝ ነው።
ማንም የኢትዮጵያ ህዝብ በፍጥነት በመረጠው ሰው እንዲተዳደር እፈልጋለሁ። እንደ አቅሚቲ የታሰርኩትም ለዚያ ነው። ስለዚህ ሁላችንም ተረባርበን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የሚችል ነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ቦርድ በፍጥነት እንዲቋቋም መዋቅሮቹም እስከታች ድረስ እንዲወርድ ማድረግ ይገባናል። ለዚህ ደግሞ የተጠየቀውን ገንዘብ መለቀቅ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ለተሻለ ውጤት አንዳንድ ፓርቲዎች ራሳቸውን አክስመው ወደ ውህደት መጥተዋል፤ የእርሶ ፓርቲ በዚህ ረገድ ምን እየሰራ ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፡- እኛ በመድረክ ደረጃ ብዙ የጠየቁ ፓርቲዎች አሉ። እየሰራንበትም ነው። በኦፌኮ በኩልም ቀደም ብለንም ቢሆን ከሰባት አመት በፊት ነፃ ሆኖ ከሚንቀሳቀስ ፓርቲ ጋር ውህደት ፈጥረናል። አሁን የምንጠብቀው ከውጭ ከገቡና የኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር ውህደት መፍጠር ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ አስቀድሞ አካሄዳቸውን መቃኘትና በምርጫ ቦርድ መመዝገባቸውን ማጤን ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ምንአልባት እንደ ኦነግ ካሉ ፓርቲዎች ጋር ከተዋሃዳችሁ መድረክ ከሚመራበት መርህ አንፃር አብሮ መሄድ ያስችላል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር መረራ፡- መድረክ መድረክን ሆኖ ይቀጥላል፤ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም እንፈልጋለን፤ ለዚህም አስፈላጊውን አስተዋፅኦ እያበረከትን ነው የምንገኘው። ከኦፌኮ አኳያ ምንአልባት ኦነጎችም በዚህ ትብብር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ኦነግና የእኛ ፓርቲ አሁን ባለው ሁኔታ በፍጥነት ውህደት ይፈጥራሉ የሚለው ሃሳብ ምንአልባት ሰዎች የራሳቸውን ምኞት ነው የሚገልፁት። ኦነግና እኛ ግን የፖለቲካ ግጭት ውስጥ መግባት አንፈልግም። እነሱም ይጠነቀቃሉ እኛም እንጠነቀቃለን።
አዲስ ዘመን፡- እንጠነቀቃለን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፡- የምንጠነቀቀው የፖለቲካ ግጭት እንዳንገባ ሲሆን አሉታዊ በሆነ መንገድ አንዱ ባንዱ ላይ የመቀስቀስና ሰዎችን የመሻማት ግጭት ውስጥ አንገባም ማለት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ኦነግ ገና በምርጫ ቦርድ አልተመዘገበም። ግን አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ የትም ቦታ ስብሰባ ስናደርግ ይመጣሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ህዝቡ ራሱ በጋራ ሁለታችንንም ይጠራናል።
ይህ አብሮ መስራት ከተባለ አዎ አብረን እየሰራን ነው። ግን በፖለቲካ ድርጅት ደረጃ በዚህ በዚህ ጉዳዮች አብረን እንሰራለን ብለን አጀንዳ ያስቀመጥናቸው ጉዳዮች የሉም። የሚሰሩ መሰራት አለባቸው። በግልፅ ቋንቋ ኦነግና ገዢው ፓርቲ ጨምሮ መነጋገር አለብን ብለን ከሁለቱም ጋር ተወያይተናል።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫው ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ ይቀጥላል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር መረራ፡- ምርጫ መቼም አሜሪካም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ ይሰረቃል፤ ከዚህ በኋላ ምርጫ ለመስረቅ የሚፈልግ ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቋዋሚ ፓርቲ ኢትዮጵያን ለማጥፋት እና ለማመስ የሚፈልግ ከሆነ እብድ ነው የሚል እምነት አለኝ። ከጨዋታ ወጥቶ በጠበንጃም ሆነ በሌሎች መንገዶች የህዝብ ድምፅ እዘርፋለሁ፤ ሰርቄም ስልጣን ላይ እወጣለሁ የሚል ሰው ወይ ደደብ መሆን አለበት ወይ አገርን ለማጥፋት ከራሱ ስልጣን ውጭ ማየት የማይፈልግ የታወረ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ይልቁንስ በተቻለ መጠን በተረጋጋ ሁኔታ ወደ ምርጫው እንድንገባ የኢትዮጵያ ህዝብ የፈለገውን እንዲመርጥ መፍቀድና ለዚህም ዝግጁ ለመሆን ሁላችንም መወሰን አለብን።
አዲስ ዘመን፡- የእርሶ ፓርቲ ወጣቶችን ወደ አመራር ለማምጣት ምን አስቧል?
ፕሮፌሰር መረራ፡ – መጀመሪያውኑ እኛ ወጣቶችን ወደፊት የ ማ ም ጣ ት ች ግ ር የ ለ ብ ን ም ፤ ቀ ድ መ ን እየሰራንበት ያለ ጉዳይ ነው፤ ወጣት ሊግ አለን፤ የሊጉ ሃላፊዎች የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ አሉ፤ ሁሉም የየራሱ ድርሻ አለው። «እነሱም ይጎዱናል» በሚሉት ደረጃ አይደለም ያሉት። የቦታ ጥበትም የለብንም። ወጣቶችም እንዳያድጉ የምናፍንበት ምክንያት የለንም። በ1997 ዓ.ም ምርጫ እንኳ የኛ ተወዳዳሪዎች ከ90 በመቶ በላይ ወጣቶች ነበሩ።
ድርጅታችን ከ20 ዓመት በላይ ተሸክሞ እዚህ ያደረሰው ወጣቱ ነው። ቄሮው እኮ ነው ስለኛ የታገለውና ከእስር ያስፈታን። ከዚህ በላይ ቦታ ከፈለገ እኛ የምንከለክለው አይሆንም። በአገርም ደረጃ ለውጥ ያመጣው ወጣቱ ሃይል ነው። ከዚህ ወጣት ጋር መጣላት የሚፈልግ የፖለቲካ ድርጅት እብድ ነው ። ይልቁንስ እነ እገሌን እንፈልጋለን እነ እገሌን አንፈልግም የሚሉበት ደረጃ በመድረሳቸው ተፅእኖ ሊመጣ የሚችለው ከእነሱ እንጂ ከእኛ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- ዶክተር አብይ ከዚህ ቀደም በመንግስት የተንገላቱና የታገሉ ሰዎችን ወደ ስልጣን ማምጣቱ ለአገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳር ምን አንድምታ አለው? እርስዎስ የቦርድ አባል ሆነው በሚያገለግሉበት ኢቢሲ ለውጥ እንዲመጣ ምን እየሰሩ ነው?
ፕሮፌሰር መረራ፡- አሁን ያልሻቸው ነገሮች ጠብታዎች ናቸው። አጠቃላይ የመንግስት ፖሊሲን የሚቀይሩ አይደሉም። እሱ የሚሆነው ቅድም እንዳልኩሽ ሰፊው መንገድ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ሊመራ የሚችል ብሄራዊ አንድነት መንግስት ካልተቋቋመ እኔም ሆንኩ ሌሎች የተገፉ ሰዎች በሃላፊነት ላይ መሰየማቸው ብዙም ለውጥ አያመጣም። ይህ ማለት ግን እንደ ቅመም እዚህም እዚያም መግባታቸው ለፖለቲካው ምህዳር መስፋት እንደ መልካም ጅምር የሚታይ ነው። ግን ወሳኝነት ያለውና የአገሪቱን ፖለቲካ አቅጣጫ ይቀይራሉ የሚል ግምት የለኝም።
የኢቢሲ የቦርድ አባል ከሆንኩ በኋላ ምን ሰርተሃል ላልሽው አስተዋፅኦ ለማለት ይቸግረኛል። ምክንያቱም አራት ስ ብ ሰ ባ ዎ ች ብቻ ነው እስካሁን የተሳተፍኩት። በእነዚህ ስብሰባዎች ገና ፕሮግራም ቀረፃና እቅድ ላይ ብቻ ነው የተወያየነው። አሁንም ቢሆን የመንግስት ቁጥጥር ያለበትና ገና ከተፅእኖ ያልተላቀቀ በመሆኑ በሚፈለገው ፍጥነት ነፃና የሁሉም ድምፅ የሆነ የመገናኛ ብዙሃን ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ይህን ደግሞ እኔ ብቻ ሳልሆን ያሉት ባለስልጣናትም ሳይቀሩ ጠንቅቀው ያውቁታል።ይህንን ለማስተካከል በቀላሉ እየተካሄደ አይመስለኝም፤ ኢቢሲ ብቻውን ደሴት መሆን አይችልም። በአጠቃላይ የአገሪቱ ፖለቲካ መቀየር ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ በተለይ የምክር ቤት አባል በነበሩበት ወቅት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊንም ሆነ ሌሎች ባለስልጣናትን በንግግርዎ መሃል በነገር ሸንቆጥ እያደረጉ የሚፈልጉትን መልዕክት በማስተላለፍ ይታወቃሉ።ይህ የተለየ ባህሪዎ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር መረራ፡- ይህ ልምድ አንድም ከተፈጥሮ ሊመጣ የሚችል ነው በሌላ በኩልም በአስተዳደግ የሚዳብር ነው ብዬ አምናለው። በተለይ ከማነባቸው መፃሃፍትና መልዕክት ለህዝብ በተሻለ መንገድ ለማቅረብ ከሌሎች ከሚወሰዱ ልምዶች የሚመነጭ ሊሆን ይችላል። በተለይ በምክር ቤት ቀልድ መሰል ቁምነገሮችን ጣል ማድረግ ይገባል ብዬ አምናለሁ።
ምክንያቱም በደረቁ ከማቅረብ ይልቅ እያዋዙ ማቅረብ ሰዎች በቀላሉ እንዲረዱት ያደርጋል። ይህ የእኔ የቆየ ባህሪ ነው። እኛ በነበርንበት ወቅት ቢያንስ ቢያንስ የህዝብን ብሶት እናቀርብ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን የኢህአዴግ ፓርላማ ብቻ ስለነበር የህዝብ ጥያቄ የሚቀርብበት መድረክ አልነበረም ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- የተጣበበ ጊዜዎትን አብቃቅተው ከእኛ ጋር ቆይታ በማድረግዎ በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር መረራ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
ማህሌት አብዱል