የጅብ ችኩል …

ይህ ማኅበራዊ ሚዲያ ይሉት ጉዳይ የራሱ ችግር ቢኖረውም ጥቅሙ ደግሞ የዚያኑ ያህል ነው፡፡ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ይሁንና ትኩስ መረጃዎችን ሳያቀብለን ውሎ አያድርም፡፡ ያለውን፣ የጠፋውን፣ የራቀ የመጣውን በእኩል እያራመደ ሰውን ከሰው ያገናኛል፡፡ ዓለምን በሰንሰለት ያቆራኛል፡፡

እንዲህ መሆኑ መልካም ነው፡፡ ማንም ተገቢውን መረጃ በትክክለኛው መንገድ ማግኘትን አይጠላምና። አንዳንዴ ደግሞ መረጃ ከትክክለኛነት ይልቅ ፍጥነት ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ ጉድለቱ ይጎላል፡፡ አጋጣሚውም ከማስደንገጥ አልፎ ከትዝብት መጣሉ አይቀሬ ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ሁነቱን ተጣድፈውና ተሸቀዳድመው የሚልኩ አካላት ሙሉ ትኩረታቸው ፍጥነት ላይ ሲሆን መረጃዎች ይዛባሉ፡፡ መታረም፣ ለአንባቢ መቅረብና መቅረት የሚኖርባቸው ነጥቦችም ይዘነጋሉ፡፡ አንዳንዴ ከእርጋታ ይልቅ ፍጥነት በቀደመ ጊዜ ከስህተት በላይ የሚሆኑ አጋጣሚዎች ሊስተናገዱ ግድ ይላል፡፡

ከሰሞኑ ያስተዋልኩትን አንድ ትዝብት ላጋራችሁ፡፡ በቅርቡ ነው፣ በሀገራችን በርካታ የሥነጽሑፍ ሥራዎችን ያበረከቱልን፣ አንድ ታዋቂ ደራሲ የመሞታቸው ዜና መዘገብ ጀምሯል፡፡ እሳቸው ታላቅ አስተዋጽኦ እንደማበርከታቸው ለማንነታቸው ግብአት የሚሆኑ ማስረጃዎች በየአጋጣሚው እየተነበቡ ነው፡፡

ይህን እውነታ በየአቅጣጫው የሚጽፉ ሰዎች የራሳቸውን አስተያየት ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ኀዘኑን በድንገት የተጋሩ በርካቶች ስሜታቸውን እየገለጹ ስለእኚሁ ታዋቂ ሰው ያላቸውን ስሜት መጥቀስ ይዘዋል፡፡ በድንገት አንድ ጽሑፍ ላይ ዓይኖቼ አተኮሩ፡፡ ስለእሳቸው የሚያወጋ ረዘም ያለ መረጃ ነው፡፡

ጽሑፉ ስለእኚሁ አንጋፋ ሰው ዳጎስ ያለ ሃሳብ ይዟልና በደቂቃዎች በርካታ ሰዎች እየተቀባበሉ አጋሩት። በዚህ መረጃ ውስጥ ስለግለሰቡ ውልደትና

 

ዕድገት፣ ስላበረከቱት የሥነጽሑፍ አስተዋጽኦ፣ ድንቅ ሥራዎቻቸው ለዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ግብአት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንና ይህም በሀገሪቱ የሥነጽሑፍ ዘርፍ ታላቅ ግምት የሚሰጠው ስለመሆኑ ይተነትናል፡፡

እውነቱን ለመናገር ይህ ጽሑፍ በወጉ የተቀመረና በቂ ማስረጃዎችን ያጣቀሰ በመሆኑ ማንም ሳያነበው የሚያልፍ አይሆንም፡፡ የእኚህ ታላቅ ሰው ህልፈት በተሰማ አጭር ጊዜ ውስጥ ይህን መሰሉን ዘገባ ማቅረብ መቻል ደግሞ የሚያስገርምና የሚያስመሰግን ጭምር ነው፡፡

እኔንም ሆነ ሌሎች ልብ ያሉ ሰዎችን ያስገረመን ግን የጽሑፉ መረጃ ጠገብነት ብቻ አይደለም፡፡ የሕይወት ታሪኩ ዘገባ በአግባቡ ተጽፎ እንደተጠናቀቀ የተስተዋለው ስህተት እንጂ፡፡ ጽሑፉ በሕይወት ስለተለዩን የሀገር ባለውለታ ሲያወጋን ቆይቶ በመጨረሻው መስመር ላይ ‹‹ነፍስ ይማር›› ማለት ሲገባው ‹‹ረጅም ዕድሜና ጤና ለታላቁ ደራሲ›› ሲል ይደመድማል፡፡

ከዚህ እውነት መረዳት የሚቻለው ለሚቀርቡ መረጃዎች ከጥንቃቄ ይልቅ ለፍጥነት ቅድሚያ መሰጠቱን ነው፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ ይህን መረጃ በጥልቀት ያላስተዋሉ አብዛኞች የመጀመሪያውን ዝርዝር ብቻ አይተው ለሌሎች ማጋራታቸው ነው፡፡

በሕይወት የሌለን ሰው ረጅም ዕድሜ ያስመኘው ጽሑፍ የቀረበው ብዙዎቻችን እንዳሰብነው በዕለቱ ተጽፎ ሳይሆን ቀድሞ ከተጻፈው መረጃ ላይ በቀጥታ ተወስዶ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ጽሑፉ ጊዜን፣ እውነታንና ወቅታዊ መረጃን ያካተተ አልነበረም፡፡

ወደ ሌላው ትዝብቴ ልሻገር፡፡ አሁንም ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የወጣን መረጃ ይመለከታል፡፡ ዘገባው ሰሞኑን ለአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ወደ ሀገራችን ከመጡት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጋር ይገናኛል፡፡ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ለጉባኤው ተሳትፎ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ በቦሌው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር፡፡

ሰውየው የአንድ ሉአላዊት ሀገር ፕሬዚዳንት እንደመሆናቸው ለማንኛውም የሀገር መሪ የሚደረገው የክብር አቀባበል አልተጓደለባቸውም፡፡ ይህን እውነት ያላስተዋሉ አንዳንዶች ግን በራሳቸው የማኅበራዊ ገጽ ላይ የተሳሳተ መረጃን ለማቀባበል አልዘገዩም፡፡

እንደእነሱ ሃሳብ ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ ያለምን ክብር ከመድረክ ወርደው ሲሄዱ ታይተዋል፡፡ ቆየት ብሎ የወጣው መረጃ ግን እንግዳው እንደተባሉት ሆኖ ከመድረክ ወርደው ለመሄድ ፈጽሞ አልሞከሩም፡፡ አጋጣሚው የሆነው አቀባበሉን ያደረጉላቸው አንድ የሀገሪቱ ሚኒስትር በፕሮቶኮሉ መሠረት ከመድረክ እንዲወርዱ በእጃቸው ምልክት በማሳየታቸው ነበር፡፡

ይህችን አፍታ በካሜራ ዓይን አይተናል ያሉቱ ግን ጉዳዩን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ለማቀናጀት አልዘገዩም። ይህ መረጃ እንዲህ ዓይነቱን ትርጉም አዝሎ በማኅበራዊ ሚዲያው ከተሰራጨ በኋላ ስህተት መሆኑን የተረዱ ሌሎች በግልጽ ተቃውመውታል፡፡

ጥድፊያን ያዘለው ዜና አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን የሚጎዳ ነውና ከፍጥነት በፊት ቆም ብሎ ማስተዋል እንደሚገባ አፅንኦት ተሰጥቶታል። ይህ ‹‹የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል›› ይሉት ዓይነት ዘገባ እንደቀላል ቢታይም የሚያስከትለው ግለሰባዊና ሀገራዊ ጉዳት የዋዛ አይሆንም፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ የማኅበራዊ ገጽ ላይ ተዘግቦ ሰዎች በተዛባ እሳቤ ሲነጋገሩበት የነበረውን አንድ ጉዳይ ላክል፡፡ ዘገባው በሀገራችን አንድ ታዋቂ ሚዲያ ላይ የተዘገበ ነው፡፡ ይህን ዘገባ በራሳቸው ገጽ የለጠፉ አንዳንዶች ደግሞ መልዕክቱን ‹‹ይድረስ›› ሲሉ አጋርተውታል፡፡ በእኔ ግምት ይህ መረጃ ለብዙዎች ትምህርትና ጥንቃቄ የሚበጅ በመሆኑ የተለጠፈ ነው ብዬ አምናለሁ ፡፡

የዘገባው ሃሳብ በአጭሩ የሦስት ዓመት ሕፃንን ከእንግሊዝ ወደ ኬንያ በመውሰድ ስላስገረዘችው እናት የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህች እናት የሦስት ዓመት ሴት ልጇን ኬንያ ድረስ በመውሰድ በማስገረዟ የእስር ቅጣት ተጥሎባታል፡፡ እናት ድርጊቱን የፈጸመችው እሷ ያለፈችበት የሕይወት መንገድ በመሆኑና ባህል ነው ብላ ስለምታምን እንደሆነ አስረድታለች፡፡

‹‹ትክክል ነኝ›› በሚል የፈጸመችው ግርዛት ግን በእንግሊዝ ሕግ መሠረት ወንጀል በመሆኑ የሰባት ዓመት አስራት እንደተፈረደባት ዘገባው ያስረዳል፡፡ ወዳጆቼ! እዚህ ላይ ልብ እንድትሉልኝ የምፈልገው ይህ ዘገባ የግርዛት ጉዳይ መሆኑን ብቻ ነው፡፡

በዜናው የመጀመሪያ መስመር ላይም የሦስት ዓመቷን ሕፃን ወደ ኬንያ በመውሰድ ያስገረዘችው ሴት እስር ተፈረደባት በሚል ተጠቅሷል፡፡ አነጋጋሪው ጉዳይ ግን እንዲህ መሆኑ ላይ አይደለም፡፡ ዜናውን በጨረፍታ ያነበቡና ለአስተያየት የተጣደፉ አንዳንድ ሰዎች የሚሰጡት ሃሳብ ማስገረሙ ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎች ‹‹ያስገረዘችው›› የሚለውን ሃሳብ እንድትይዙልኝ እሻለሁ፡፡ እነዚህ አንዳንድ ያልኳቸው ሰዎች ግን ይህን ቃል በተጻፈው መሠረት ተገንዝበው አላነበቡትም ፡፡ በራሳቸው ጥድፊያ ሞልተው እንዳሻቸው በማድረግ አቀባብለውታል፡፡

አንባቢዎቹ ‹‹ያስገረዘችው›› የሚለውን ቃል ‹‹ያስረገዘችው›› ብለው አንብበውታል፡፡ አንብበው ደግሞ ዝም ብቻ አላሉም፡፡ በጽሑፉ ግርጌ በተቀመጠው የሃሳብ ማስፈሪያ ቦታ ላይ በንዴትና በብሰጭት ተሞልተው ያልተገባ ሃሳብ ተቀባብለውበታል፡፡

አስገራሚው ነገር የእነሱን የንዴት ሃሳብ የሚጋሩ ሌሎች የተሳሳተውን ጽሑፍ ከመነሻው ደግመው ከማንበብ ይልቅ ሃሳቡን እየደገሙና እየተቀባበሉ እሳት ሲጭሩና ነገር ሲያጋግሉ መቆየታቸው ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ የጅብ ችኩልነት ድርጊት አሁንም ከራስ አልፎ ብዙኃንን ለመጉዳት የዘገየ አይሆንም፡፡ ‹‹ከአፍ ከወጣ አፋፍ›› እንዲሉ ሆኖ እንደዋዛ የምንሠራቸው ስህተቶች ስር ሰደውና አጉል ትርጉም ተሸክመው የሚያስከትሉት ጥፋት የበዛ ነውና ጠንቀቅ ብንል ይበጃል፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You