የእንስሳት ምርትን ለማሳደግ የመኖ ልማትና ሥነ አመጋገብን ማሻሻል ቀዳሚው እርምጃ ነው። በመኖ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ሙያተኞች በሀገሪቱ እየተበራከቱ የመጡትም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ ሙያተኞች ለዘርፉ እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ሙያተኞቹ ለእንስሳት አርቢው አርሶ አደርና አርብቶ አደር እየፈጠሩ ባሉት ግንዛቤ የተቀነባበረ የእንስሳት መኖ የመጠቀም ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ መጥቷል፡፡
ይሁንና በሀገሪቱ ያለው የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ አቅርቦት ካለው ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር አጥጋቢ አለመሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት በዘርፉ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች በመኖራቸው ነው፡ ችግሮቹ ቢኖሩም ታድያ ያንን በመቋቋም የእንስሳት ምርትና ምርማነትን ለማሳደግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙ አምራች ድርጅቶች አልታጡም፡፡ ከእነዚህ መካከል የተቀነባበረ የእንስሳት መኖ እያቀረበ የሚገኘው እልፍ ማኑፋክቸሪንግና ኮሜርሻል አንዱ ነው፡፡
እልፍ ማኑፋክቸሪንግና ኮሜርሻል እንደ ሀገር በእንስሳት ሀብት ላይ እየተሰራ ያለውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ከሚታትሩ ድርጅቶች መካከል ተጠቃሽ ነው። የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቻላቸው ለገሰ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለና ከእንስሳት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ካለው አርሶ አደር ቤተሰብ የተገኘ ወጣት ነው፡፡ ‹‹ከአርሶ አደር ቤተሰብ እንደመውጣቴ ለእንስሳት ቅርብ ነኝ›› የሚለው አቶ ቻላቸው፤ ተወልዶ ባደገበት በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ዳሞት ላይ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡
ከትምህርት ጎን ለጎን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በግብርና ሥራ የተሰማሩ ቤተሰቦቹን ማገዝ ተቀዳሚ ተግባሩ ነበር፡፡ በዚህም ለግብርና ሥራ እንዲሁም ለእንስሳት ልማት ቅርብ ሆኖ አድጓል፡፡ አርሶ አደር ከሆኑ ወላጆቹ በተጨማሪ በንግድ ሥራ የተሰማሩ ቤተሰቦቹን የማየት ዕድል ገጥሞታል፡፡ ለዚህም ነው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ባጠናቀቀ ማግስት ወደ ሥራ ያቀናው። ‹‹ከትምህርት ይልቅ ወደ ንግድ ሥራ እንዳዘነብል በንግድ ሥራ የተሰማሩት ዘመዶቼ ምክንያት ሆነውኛል›› የሚለው አቶ ቻላቸው፤ ገንዘብ መቁጠር የጀመረው ገና በአፍላ የወጣትነት ዕድሜው ክልል ውስጥ ሆኖ ነው፡፡
ቤተሰቦቹ የተሰማሩት በስንዴ፣ በፓስታና በማካሮኒ ምርት ሲሆን፤ በወቅቱ አብሮ ተባብሮ መሥራት መቻሉ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ መነሻ እንደሆነው ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፤ በወቅቱ አፍላ የወጣትነት ዕድሜ ላይ በመሆኑ ሰርቶ አይደክመውም፡፡ በሁሉም የሥራ ዘርፎች ውስጥ ገብቶ ሠርቷል፡፡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በከፍተኛ ተነሳሽነት ለሚሰራው ሥራ የሚከፈለው ገንዘብ አሳስቦት አያውቅም፡፡ እሱን ያሳስበው የነበረው ልምድ አዳብሮ ዕውቀት ሰንቆ የተሻለ ሥራ በመስራት ከተቀጣሪነት ወደ ቀጣሪነት መሸጋገር ነበር፡፡
ሃሳቡን ዕውን ለማድረግና በተግባር ለመከወን ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የስንዴ ዱቄት ፋብሪካ ውስጥ በሚሰራበት ወቅት የመኖ ወይም የፉሩሽካን ምንነት በሚገባ ማወቅና መረዳት ችሏል፡፡ ለእንስሳት መኖ ግብዓት መሆን የሚችለውን ጥሬ ዕቃ የማወቅ ዕድሉን በማግኘቱ ወደ ሥራው ለመግባት ብዙም አልከበደውም፡፡ ከፋብሪካው የሚገኘውን ተረፈ ምርት የእንስሳት መኖን በማቀነባበር ሥራ ላይ ለተሰማሩ ፋብሪካዎች ሲያቀብል ኖሯል። ይህን መነሻ በማድረግ የሚያውቀውን ሥራ በግሉ ለመሥራት ‹‹ሀ›› ብሎ ጀመረ፡፡
ጅማሬው ከፋብሪካው የሚገኘውን ተረፈ ምርት አሰባስቦ ለመኖ አቀነባባሪ ፋብሪካዎች ማቅረብ ነበር። በዚህ ሥራ ውስጥ ታድያ ብዙ እንደተማረና ተጨማሪ አቅም መፍጠር እንደቻለ ነው የሚያስረዳው፡፡ እሱ እንደሚለው፤ ሥራውን በከፍተኛ ጉጉትና ተነሳሽነት በወጣትነት ሙሉ ልቡ ከላይ ታች ብሎ ሰርቷል፡፡ በብርቱ ጥረትና ትጋት መሥራት በመቻሉም ውጤታማ ሆኗል። ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ ታድያ ከተረፈ ምርት አቅራቢነት ወደ ፋብሪካ ባለቤትነት የተሸጋገረው አቶ ቻላቸው፤ የፋብሪካ ባለቤት መሆን የቻለው በሙሉ አቅሙ መሥራት በመቻሉና መንግሥት ያመቻቸውን ዕድል አሟጦ መጠቀም በመቻሉ እንደሆነ አጫውቶናል፡፡
እሱ እንደሚለው፤ የአማራ ክልል መንግሥት የኢንቨስትመንት ቦታ ውሰዱ በሚል ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ የኢንቨስትመንት ቦታ ወስዷል፡፡ ቦታውን የወሰደው ዱቄት፣ ፓስታና ማካሮኒ ለማምረት ነበር። ይሁንና ወደ ሥራው ከመግባቱ አስቀድሞ የተለያዩ ጥናቶችን አድርጓል፡፡ ባደረገው ጥናትም ከለገጣፎ ጀምሮ እስከ ሰሜን ሸዋ ሸዋሮቢት ድረስ ትላልቅ የእንስሳት እርባታዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ ችሏል። አብዛኞቹ እርባታዎችም የወተት ላምና የዶሮ እርባታዎች ናቸው፡፡ ለእነዚህ እርባታዎችም በቀን ምን ያህል መኖ እንደሚያስፈልግና እያቀረበ ያለው ደግሞ ምን ያህል እንደሆነ መረጃ አሰባስቧል፡፡ ያሰባሰበው መረጃም በአካባቢው የእንስሳት መኖ አቅርቦት እጥረት መኖሩን አረጋግጦለታል፡፡
ይሄን ጊዜ ነው የሥራ ዘርፉን የመቀየር ሃሳብ የመጣለት፡፡ የኢንቨስትመንት ፈቃዱን የእንስሳት መኖ ማቀነባበር በሚል መቀየር የቻለው አቶ ቻላቸው፤ የእንስሳት መኖ የማቀነባበር ሥራውን አስቀድሞ ጥሬ ዕቃ በማቅረብ ያውቀው ነበርና ወደ ሥራው ሲገባ ብዙም አልተቸገረም፡፡ በወቅቱ የተቀነባበረ የእንስሳት መኖ ፋብሪካ በማቋቋም ምርቱን ለአካባቢው አርሶና አርብቶ አደር ለማቅረብ በነበረው ብርቱ ጥረት ወደ ሥራው መግባት ቢችልም በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል፡፡ በዘርፉ ከፋብሪካ ምርቱን ከማቅረብ ጀምሮ ፋብሪካ ውስጥ ወዛደር ሆኖ ፉሩሽካ ላይ እያደረ ያሳለፋቸው ወቅቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡
‹‹እያንዳንዱ ጥረትና ልፋቴ ልምድ ለመቅሰምና ወንድሞቼ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ነበር›› የሚለው ቻላቸው፤ ሥራውን በሙሉ ልቡ ወዶና አክብሮ በብርቱ ትጋት የሚሰራ መሆኑን አጫውቶናል፡፡ ፉሩሽካ ከመሸጥ ጀምሮ አሁን ላይ የተለያዩ የእንስሳት መኖዎችን እያቀነባበረ የሚገኝ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በ65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሰሜን ሸዋ ቡልጋ ከተማ ቱሉፋ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ እየተመረተ ያለውን የእንስሳት መኖ በተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ፋብሪካው ሁሉንም የእንስሳት መኖ አይነቶች እያመረተ የሚገኝ ሲሆን፤ የወተት ላም፣ የበሬ፣ የጥጃ፣ የበግና የፍየል፣ የጋማ ከብቶች፣ የአሳማ፣ እንዲሁም ከአንድ ቀን ጫጩት ጀምሮ የቄብና የእንቁላል ጣይ ዶሮ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የተባለውን መኖ ያቀነባብራል። በአጠቃላይ 15 የሚደርሱና ለማንኛውም እንስሳት ጠቃሚ የሆኑ የመኖ አይነቶችን በማምረት ይታወቃል።
እነዚህን የእንስሳት መኖ ለማዘጋጀት ታድያ በዋናነት የሚጠቀመው ጥሬ ዕቃ ከሀገር ውስጥ ሲሆን፤ እነሱም በቆሎ፣ አኩሪ አተር፣ የኑግ ፋጉሎ፣ የስንዴ ገለባ፣ የለውዝ ገለባ የሱፍና የሩዝ ገለባ ወዘተ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪ ከውጭ እንደ እንስሳቱ አይነት አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ቫይታሚኖችና ኬሚካሎችን ይጠቀማል። በቀን ከ1200 እስከ 1500 ኩንታል የማምረት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ እንደ መኖ አይነቱ ከፍና ዝቅ የማለት ሁኔታ አለው፡፡
እልፍ መኖ ምርቶቹን በተለያየ መጠን የሚያዘጋጅና ማንም ሰው በአቅሙ ገዝቶ መጠቀም እንዲችል የሚያድግ በመሆኑ ከሌሎች የእንስሳት መኖ አቀነባባሪዎች ለየት ያደርገዋል፡፡ የሚሉት አቶ ቻላቸው፤ በተለይም ታች ያለው ገበሬ በቀላሉ ገዝቶ መጠቀም እንዲችል ከአምስትና አስር ኪሎ ጀምሮ ያቀርባል፡፡ ይህም አንድና ሁለት ዶሮ ያለው አርሶ አደር ምርቱን በቀላሉ ገዝቶ መጠቀም ያስችለዋል፡፡
የገበያ ተደራሽነቱን በተመለከተም የእንስሳት እርባታ አለ በተባለበት አካባቢ ሁሉ እልፍ መኖ ይገኛል፡፡ ሸገር ከተማን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ የመሸጫ ሱቆቹ ተደራሽ እየሆነ ይገኛል። መሸጫ ሱቆቹ ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከልም ሆለታ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎ፣ አሌልቱ፣ ደብረዘይት፣ ቃሊቲ፣ ሻሸመኔና መቀሌ ድረስ የገበያ ትስስር ፈጥሯል። ምርቱ በሚቀርብባቸው በእነዚህ አካባቢዎችም እየተዘዋወሩ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉ ሙያተኞች ስለመኖራቸው አስረድቷል፡፡
ለተመጣጠነ እንስሳት መኖ በሀገር ውስጥ ከሚገኘው ተረፈ ምርት በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ ቫይታሚኖችና ኬሚካሎች አስፈላጊ ስለመሆናቸው ያነሳው አቶ ቻላቸው፤ ቫይታሚንና ኬሚካሎቹ የተመጣጠነና የተስተካከለ መኖ ለማግኘት አስቻይ መሆናቸውን ሲያብራራ፤ አንድ እንቁላል ጣይ ዶሮን በአንደኛ ደረጃ ለማምረት በትንሹ 17 የሚደርሱ የግብዓት አይነቶችን መጠቀም የግድ ነው። ለዚህም በዘርፉ የሰለጠኑና የብቃት ሰርተፊኬት ያላቸው ዶክተሮች አስፈላጊ መሆናቸውን በማንሳት ፋብሪካቸውም ይህንኑ መሰረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት ግብርናው ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን በዘርፉ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን አመላክቷል፡፡ አርብቶ አደሩ ስለተመጣጠነ የእንስሳት መኖ እያወቀና እየተረዳ በመጣበትና ተጠቃሚ እየሆነ ባለበት በዚህ ወቅት በዘርፉ ያሉት ችግሮች መቀረፍ ካልቻሉ በሚፈለገው ልክ መጓዝ አይቻልም ባይ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው፤ ተለምዷዊ በሆነው መንገድ ገለባ የበላች ላም በቀን ቢበዛ አምስት ሌትር ወተት ትሰጣለች፡፡ በተመሳሳይ የተመጣጠነ መኖ የተመገበች ላም ከ10 እስከ 15 ሌትር ወተት ትሰጣለች፡፡ ይህንን ገበሬው መረዳት በመቻሉና ውጤት በማግኘቱ መኖ የመጠቀም ፍላጎት ጨምሯል። ነገር ግን ጥሬ ዕቃው በውድ የሚገዛ በመሆኑ የመኖ ዋጋ እየናረ በመሆኑ መፍትሔ የሚያሻው ጉዳይ ነው ይላል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት ግብርና ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን በመግለጽ በተለይም የከተማ ግብርናን ለማስፋት በርካታ ዕድሎችን አቅርቧል የሚለው አቶ ቻላቸው፤ በእንስሳት መኖ ሽያጭ ላይ የነበረውን 15 በመቶ ቫት በማንሳት አርሶና አርብቶ አደሩ የመኖ ዋጋ እንዲቀንስለትና እንዲበረታታ ማድረጉ አንዱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ይሁንና ተረፈ ምርቱን የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች ተረፈ ምርን የሚሸጡበት ዋጋ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ከዚህም ባለፈ ከቦታ ቦታ ዋጋው የሚለያይና አበረታች እንዳልሆነ ጠቅሶ የፋይናንስ አቅርቦትም እንዲሁ ሌላው የዘርፉ ማነቆ እንደሆነ ነው ያመላከተው፡፡
በእነዚህና መሰል ምክንያቶች እንቁላል፣ ስጋና ወተት ማህበረሰቡ በቀላሉ ማግኘት የማይችላቸው የቅንጦት ምግብ እየሆኑ ስለመምጣታቸው የሚናገረው አቶ ቻላቸው፤ ‹‹በተለይም እንቁላል የሀብታም ልጅ ምግብ እየሆነ ነው›› ይላል፡፡ ኢትዮጵያን በመሰለች ለምለም ሀገር አብዛኛው ሕዝብ አርሶና አርብቶ አደር በሆነባት ሀገር፤ በቂ የእንስሳት ሀብት እያለን ዶሮ እያረባን እንቁላል፣ ወተትና ስጋ በቀላሉ ማግኘት አለመቻሉ ቁጭት ሊፈጥርብንና ብዙ ልንሠራ ይገባል ባይ ነው፡፡
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አርሶ አደር ሆኖ ስጋ፣ እንቁላልና ወተት ብርቅ ሊሆንበት አይገባም የሚለው አቶ ቻላቸው፤ ዘርፉ ገና ያልተነካና ያልተሠራበት ዘርፍ እንደሆነም ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፤ በዘርፉ ያለውን እጥረት ለማቃለል መንግሥት በከተማ ግብርና እየሠራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው፡፡ ይሁንና መኖ አቀነባባሪ ፋብሪካዎች የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና ዋጋ ላይ እየገጠመ ያለውን ችግር መፈተሽና መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አመላክቷል፡፡
ፋብሪካው 110 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም አበርክቶው የጎላ ነው፡፡ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ለምርቱ ተጠቃሚዎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ የአርሶ አደሩ ሀብት ንብረት ለሆኑት እንስሳት ነጻ ህክምና ይሰጣል። የተቀነባባረ መኖን በመጠቀም ውጤታማ መሆን የሚስችላቸውን የምክር አገልግሎት ለአርሶ አደሩ ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቅም ለሌላቸው አርሶ አደሮች የዶሮ መኖ በብድር ያቀርባል። አርሶ አደሩም እንቁላል ጣይ ጫጩቶችን በማርባት እንቁላል መስጠት እስኪችል መኖ በብድር ይወስዳል፡፡ ዶሮዎቹ እንቁላል መስጠት ሲጀምሩ እንቁላሉን በመሸጥ ብድሩን መክፈል የሚችልበትን የብድር ሥርዓት ዘርግቶ ከአርሶ አደሩ ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡
መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት በመጠቀም በቀጣይ ግብርናውን የማዘመን ዕቅድ ያለው አቶ ቻላቸው፤ ለገበሬው ቅርብ በመሆን ከእርባታ ጀምሮ እስከ መኖ አቅርቦት የመሥራት ዕቅድና ፍላጎት አለው፡፡ ለአብነትም በዶሮ እርባታ ጫጩት ማቅረብና ጊደሮችንና በሬዎችን ጭምር በማርባት ማደለብ ለሚፈልጉ ዜጎች ከመኖው ጋር ለማቅረብና ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል።
በመጨረሻም መኖ ከሌለ እንስሳቱንም ሆነ የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶችን ማግኘት የማይታሰብ በመሆኑ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ተረፈ ምርቶች በምን ዓይነት ሁኔታ ለገበያ መቅረብ እንዳለባቸው፣ የእንስሳት ዕርባታ ድርጅቶች ለመኖ ማዘጋጃ ፍጆታ የሚጠቀሙባቸውን የሰብል እህሎች ሊያገኙ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከሚመለከተው አካል የሚጠበቅ የቤት ሥራ መሆኑን እያስታወስን አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም