“ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ ወደ ቀደመው ክብርና ዝናዋ ይመልሳታል” ካፒቴን መርሻ ግርማ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አመራር

የዛሬው የዘመን እንግዳችን ካፒቴን መርሻ ግርማ ይባላሉ፡፡ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ እንጦጦ ራጉዔል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ አባታቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው፡፡ እንግዳችን አባታቸውን በሞት የተነጠቁት ሕጻን ሳሉ በመሆኑ አያውቋቸውም፡፡

በወቅቱ ተፈሪ መኮንን ያስተምር የነበረ ወንድም ስላላቸው እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እዛው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስገቧቸው፡ እስከ 12ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ መሆን የሚፈልጉት የባሕር ኃይል ነበር፡፡ ውጥናቸውም ተሳክቶ በ1949 ዓ.ም ባሕር ኃይሉን ተቀላቀሉ፡፡ በወቅቱ ባሕር ኃይል ሰዎችን ሲቀበል ለሁለተኛ ዙር ሲሆን፣ እርሳቸውም የዚያ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ቻሉ፡፡

የዛሬው እንግዳችን ካፒቴን መርሻ የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል ከዛሬ 67 ዓመት በፊት ተቀላቅለው ሀገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፣ በደርግ ዘመን የባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ፤ ቀጥሎም በወቅቱ እርሳቸው ዘንድ ያሉ ወደ 15 የሚጠጉ መርከቦች አዛዥ የሆኑም ናቸው፡፡

እርሳቸው ብዙን ጊዜ ንግግራቸው ፊት ለፊትና እውነት ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም በአለቆቻቸው ዘንድ እንደስጋት ይቆጠራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ እውነት ስለሚናገሩም የመሾም ዕድሉ ጥቂት ለማይባል ጊዜ ሲያልፋቸው ቆይቷል፡፡ አዲስ ዘመንም ዘለግ ላለ ዓመት ኢትዮጵያን በባሕር ኃይሉ ዘርፍ ያገለገሉትን ካፒቴን መርሻ ግርማን ስለቀድሞው ባሕር ኃይልና መሰል ጉዳዮችን አስመልክቶ ቆይታ በማድረግ በእንግዳ ዓምዱ ይዟቸው ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የባሕር ኃይል ትምህርት የተማሩት የት የት ሀገር ነው?

ካፒቴን መርሻ፡- ትምህርቴን እየተማርኩ ሳለ አስብ የነበረው የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል ስለመቀላቀል ነው፡፡ 12ኛ ክፍል እንዳጠናቀቅኩም ለሁለተኛ ዙር ምዝገባ ሲያደርግ የነበረውን ባሕር ኃይል የተቀላቀልኩት ሳላመነታ ነው፡፡ በባሕር ኃይል ኮሌጅም ለሦስት ዓመት ተኩል ተምሬ ለመመረቅ በቃሁ፡፡ በወቅቱ ለሥልጠና እንዲያግዝ የኖርዌይ መርከብ መጥቶ ስለነበር እንደተመረቅሁ ወዲህ ወዲያ ለማለት አልፈለግሁም፡፡ ዘመድ አዝማድም ለመጠየቅ አልወደድሁም፡፡ በቀጥታ ያደረግሁት ነገር ቢኖር እኔም ጨምሮ 16 ከምንሆነው ጋር ያቀናሁት ወደመርከቧ ነው፡፡ በዚያም መርከብ ከሌሎቹ ጓደኞቼ ጋር በመሆን ልምምድ እያደረግሁ በቀጥታ ያቀናሁት ወደኖርዌይ ነው፡፡ በኖርዌይም ባሕር ላይ ለአንድ ዓመት ያህል ሥልጠና አደረግሁ፡፡ በቀይ ባሕር፣ ሜዲትራንያን ባሕር፣ አትላንቲክ ውቂያኖስ ላይ ልምምድ ሳደርግ ቆየሁ፡፡

በኖርዌይ የነበረኝን የአንድ ዓመት ሥልጠናዬን አጠናቀቅሁ፡፡ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላም በቀጥታ ያቀናሁት ወደ እንግሊዝ አገር ነው፡፡ ወደስፍራው ያቀናነው እኔን ጨምሮ አዛዥ የሆኑ ሰዎች ናቸው። በእንግሊዝ የመለማመጃ ማዕከል ስለመሣሪያ፣ ስለናቪጌሽን (የመርከቦችን እንቅስቃሴ የመምራት ጥበብ) እንዲሁም ስለኮሙኒኬሽን ተማርሁ፡፡ እዚያም ልክ እንደኖርዌይ ሁሉ በተመሳሳይ የአንድ ዓመት ቆይታ ነበረኝ፡፡

የእንግሊዝ አገር ቆይታዬን አጠናቅቄ ወደኢትዮጵያ ተመለስኩ፡፡ እንደመጣሁም ሁሉም በተለያየ ቦታ ተመደበ፤ እኔም የሠልጣኞች አስተዳደር ሆንኩ፡፡ ያንን የአስተዳደር ጊዜ እንደጨረስኩ የሄድኩት አነስተኛ መርከብ ላይ ሲሆን፣ የሄድኩትም በምክትል አዛዥነት ነው፡፡

የተሰጠኝን ኃላፊነት ከተወጣሁ በኋላ ያቀናሁት ለድኅረ ምረቃ ትምህርት (Postgraduate) ወደ ሀገረ አሜሪካ ነው፡፡ ከአሜሪካ ስመለስ ምፅዋ የነበረው ኃይል ከምፅዋ ተነስቶ እንደገና ዶንጎላ ላይ ተመሠረተ። በዚያን ጊዜ የእንግሊዛዊው ካፒቴን ቢቲ ምክትል ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ እዛው እየሠራሁ ሳለ የእንግሊዛውን ካፒቴን ቦታ በመያዝ አዛዥ ለመሆን በቃሁ፡፡ በዚያን ጊዜ አዝ የነበረው የመርከብ ብዛት አራት ነው፡፡

ከቆይታ በኋላ እንደገና ወደአገረ አሜሪካ ሳንዲያጎ በማቅናት የማኔጅመንት (Management) ትምህርት ለመማር ቻልኩ፡፡ ከአሜሪካ ቆይታ በኋላ ተመልሼ ወደኢትዮጵያ በመምጣት በናቪጌሽንና ኮሙኒኬሽን (Navigation and Communication) ማለትም የመገናኛ ሥራውን ስሠራ ቆየሁ፡፡ ከዚህ ሥራ በኋላ የሄድኩት ወደ አሥመራ ሲሆን፣ መዳረሻዬንም ያደረግሁት ከአሥመራ 50 ኪሎ ሜትር ራቅ ወደምትለዋ ዶንጎሎ ነው፡፡ እኔ በደርግ ዘመን የባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ ነበርኩ፡፡ ቀጥሎም እኔ ዘንድ ያሉ 15 የሚጠጉ መርከቦችንም በአዛዥነት እሠራ ነበር፡፡

በወቅቱ ምፅዋ ውጊያ በነበረበት ወቅት የመርከቦቹ አዛዥ የነበርኩት እኔ ነኝ፡፡ የዚያን ጊዜ በጦሩ ተከብበን ነበር፡፡ ይሁንና ማንም ወደእኛ ሊጠጋ አልቻለም። በጥይት በመምታት እንዳይገቡ ማድረግ ችለናል፡፡ በዚያን ወቅት ጭነን ያመጣነው ታንኩንም መድፉንም ጭምር ነው፡፡ ከምፅዋ ያመጣነው መሣሪያ ሁሉ ዳህላክ ደሴት እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ ስለሆነም የትኛውም አይነት መሣሪያ ከዚህ የተነሳ በጠላት እጅ ሊገባ አልቻለም፡፡ ምፅዋ የተያዘው መሣሪያ ካወጣን በኋላ ነው፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገር ለመጥቀስ እወዳለሁ፡፡ እኔ ከባሕር ኃይሉ በተጨማሪ ለዚሁ ለባሕር ኃይሉ ስሠራ ወሳኝ የሆነውን የበረራ ትምህርት የመማር ጽኑ ፍላጎት ነበረኝና ወደእሥራኤል አገር አቅንቼ የበረራ ትምህርት ተማርኩ፡፡ ይሁንና ይህን የበረራ ትምህርት መማሬን አየር ኃይል አልወደደውም፡፡ ይሁንና የመማሬ ምስጢር በባሕር ላይ ቅኝት ለማድረግ ያመች ዘንድ ታስቦ እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሥራ ዘመንዎን ያሳለፉት በባሕር ኃይል ውስጥ ነው፤ በመሆኑም ባለፉት ዘመናት በዘርፉ የነበረውን ሒደት እንዴት አገኙት?

ካፒቴን መርሻ፡- በባሕር ኃይሉ ውስጥ ትልቁ ችግር የነበረው በተለይ በደርግ ዘመን የኃላፊነቱን ቦታ ራሱ የባሕር ኃይሉ እንዲወስንበት ከመተው ጣልቃ ለመግባት መሞከሩ ነው፡፡ የነበረው ችግር አዛዡ አለ፤ ከአዛዡ በተጨማሪ ደግሞ ካድሬው አለ፤ የደርግ አባል የሆነ ሠራተኛ አለ፡፡ ከአዛዡ ጋር ያሉት እነዚህ አካላት ችሎታውም ማዕረጉም የላቸውም፡፡ ስለዚህ በደርግ ጊዜ ከጣልቃ ገብነትም አልፎ አብዛኛው በባሕር ኃይሉ ውስጥ ያሉት የደርግ ካድሬዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

እኔ በበኩሌ ግን እንዲህ አይነቱ አካሄድ እምብዛም ስለማይመቸኝም ከካድሬ ጋር መሥራት ደስ አይለኝም ነበር ፡፡ እሺም አልላቸውም፤ አልቀበላቸውም፡፡ እንዲህ በማለቴም ሆነ ያለውን እውነታ ፊት ለፊት ተጋፍጬ ስለምናገር ብዙ ፈተና ደርሶብኛል፡፡ ከመገደልም ተርፌያለሁ፡፡ ምክንያቱም ካድሬነቱን እንጂ ችሎታው የላቸውም፡፡ ስለዚህ ባሕር ኃይል ፖለቲካ አይደለም፡፡ በእውቀት የሚመራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ አሰብ የኢትዮጵያ እንደነበረች ይታወቃል፤ በመሆኑም አሰብ መሰጠት አልነበረበትም በሚል ብዙዎች ይቆጫሉና በዚህ ላይ ስሜትዎ ምንድን ነው?

ካፒቴን መርሻ፡- አሰብ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ከነበረውም የነበረው ከወሎ ግዛት ጋር ነው። ነገር ግን በወቅቱ የነበሩ አካላት ከእጃቸው አወጡት፡፡ ምክንያቱም አሰብ በውሎ ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ የኢትዮጵያ እንጂ የኤርትራ ግዛት አለመሆኑ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ጦር አካባቢውን ለቅቆ ስለሄደ ያዙት፡፡ አሰብን ማጣት ማለት ብዙ ነገራችንን የማጣት ያህል የሚቆጠር ነው፡፡ በብዙዎችም ዘንድ የሚታወቀው ሐቅ በእዛ አካባቢ የሚኖሩት አብዛኞቹ አፋሮች መሆናቸው ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአፄ ኃይለሥላሴና በደርግ ዘመን የነበረውን የባሕር ኃይሉን ሁኔታ ልዩነቱ የሚገለጸው እንዴት ነው?

ካፒቴን መርሻ፡- በደርግ ጊዜ ኦፊሰሮችን ለማቅረብ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ደርግ ሥልጣኑን ከተረከበ በኋላ በኃይለሥላሴ ዘመን የነበሩትን የባሕር ኃይል አካላትን በጥርጣሬ የሚያይ ነበር፡፡

ደርግ ሥልጣኑን ከተረከበ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1970 ዓ.ም አካባቢ እኔ ተይዤ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ አዲስ አበባ ከገባሁ በኋላ ደግሞ አጋጣሚ ሆኖ በመታመሜ ሆስፒታል ገባሁ። በዚያን ጊዜ አዲስ አበባ የነበረውን የባሕር ኃይል ወደ አሥመራ ወሰዱት፡፡ እንደ እኔ አመለካከት ከሆነ እንደዛ መሆን አልነበረበትም፡፡ ይህ ሁሉ የእብደት ሥራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ወደኋላ ላይ ወደመከላከያ ውስጥ ገባሁ፡፡ እዛም ብዙ ሳልቆይ እንደገና ከመከላከያ አንስተውኝ በምክትል አዛዥነት ማዕረግ ወደ ምፅዋ መልሰው ላኩኝ፡፡

በእርግጥ ሰው መመረጥ ያለበት በችሎታው ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በወቅቱ አስቀድሜ ጠቆም ለማድረግ እንደሞከርኩት ደርግ ደግሞ ካድሬ የተባለውን ሁሉ ሾመ፡፡ ደርግ የራሱ የሆነውን ሰው እያመጣ ይህኛው ቦታ ለዚህ ሰው በሹመት ተሰጥቶታል ይል ነበር፡፡ ያኛው ቦታ ደግሞ ለዚያኛው ሰው እያለ የእኔ የሚላቸውን ሲሾም ቆየ፡፡ መሆን የነበረበት በዘርፉ ትክክለኛ እውቀት ያለውና ለሹመቱም ብቁ የሆነ ሰው ነበር፡፡ ነገር ግን ደርግ ያንን ማድረግ አልወደደም፡፡

ምንም እንኳ ደርግ የራሱን ሰው እያመጣ ሹመት እንዲሰጠው ቢያደርግም፤ እኔ ካፒቴን የሆንኩት በዚያው በደርግ ዘመን ነው፡፡ ለቦታው የሚጠይቀውን እውቀት በማሟላቴ ካፒቴን ልሆን ችያለሁ፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ደግሞ ኮማንደር ነበርኩ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ የነበረው የባሕር ኃይል ከሰው ኃይሉ በተጨማሪ የመሣሪያ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

ካፒቴን መርሻ፡– ኢትዮጵያን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በሚመሩበት ዘመን ኃይለኛ ባሕር ኃይል ነው የሚባለው የግብፅ እና የኢትዮጵያ ነው፡፡ በዚያን ወቅት የመን ባሕር ኃይል የለውም፡፡ እኛ በወቅቱ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለጉብኝት ስንሄድ መርከብ አቁመው ነው፡፡ ወደብ አልነበራቸውም፡፡ በወቅቱ እንዲያውም ከተማ ውስጥ ስንቀሳቀስ በከተማቸው ውስጥ የአማርኛ ተናጋሪዎች በርከት ያሉ እንደነበር አስታውሳለሁ። የመንን አልኩ እንጂ እነሶሪያም ሆኑ ሊቢያ በዚያን ወቅት የላቸውም፡፡

ከዚህ አንጻር ሲታይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፡፡ ትልቅነቷ ደግሞ ጠቀሜታው ለእርሷ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ነው፡፡ በጥንት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በቅርብም ለጎረቤት ሀገራት የምታደርገው አስተዋፅዖ በቀላሉ የሚመዘን አይደለም። ሌላው ቀርቶ ደቡብ ሱዳንን ያሠለጠንን እኛ ነን፡፡ ከሠላሙም አንጻር ስንታይ ኢትዮጵያ የሌላውን ሠላም ለመንሳት ይቅርና በሌላ ኃይል አማካይነት የታጣን ሠላም በማስመለስ ረገድ ሚናዋ ላቅ ያለ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የባሕር ኃይሉንም ሆነ የባሕር በሩን አስፈላጊነት እንዴት አዩት?

ካፒቴን መርሻ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሕር ኃይል ያስፈልጋል ማለታቸው መልካም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቀድሞም ቢሆን የባሕር ኃይል የነበራት ሀገር መሆኗ ግልጽ ነው፡፡ ከባሕር ኃይሉ ጎን ለጎን ደግሞ በኢኮኖሚያችንም ማደግ አለብን። ባሕር ኃይሉም ሆነ የየባሕር በሩ ሲታሰብ አብረው መታወስ ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የባሕር በሩን የማግኛ ስልት ነው። ለምሳሌ ኤርትራን መውሰድ እንችላለን፡፡ ኤርትራ የእርሻ መሬት የላትም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ወደቡን እምብዛም አትጠቀምበትም፡፡ ካልተጠቀመችበት በብዙ መንገድ ልታተርፍ የምትችለው የባሕር በርና ወደብ ለኢትዮጵያ በማቅረብ ነው፡፡ በዚህ መላ መጠቀም ብትችል ለእርሷ መልካም ነበር፡፡

የባሕር በር እንዳልኩት ነው፤ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በአህጉሯ ያላት ተሰሚነትም ሆነ ታላቅነት እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ የባሕር በር ደግሞ ሲታከልበት ምን ያህል ልትተልቅ እንደምትችል መገመት አይከብድም፡፡ ደግሞም የብዙ ሕዝብ ባለቤት ናት፡፡

ስለዚህም ባሕር ኃይል ያስፈልገናል፡፡ ቀድሞም ቢሆን የሰጠነው ራሳችን ነን፡፡ በወቅቱ ጅቡቲ የእኛ ነበር፤ ደርግ ወስዶት ቢሆን ኖሮ ችግር አልነበረውም። ጅቡቲንም ምፅዋንም የሰጠነው እንደዚያው ነው። እንዲያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ጥያቄው ተነስቷል፡፡ ተነስቶ ብቻ አይቀርም፤ መልሰን የባሕር በር ማግኘት እንችላለን የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ልዩነታቸው ምንድን ነው? ከባሕልም ከትስስርም አንጻር ሲታይ ልዩነት የለንም፡፡ ለበርካታ ዓመታትም አብረን ኖረናል፡፡ ስለዚህ ለሁለቱም ሀገራት አዋጭው አብሮ መሥራት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የባሕር ኃይሉን ለማቋቋም ከቀድሞው የባሕር ኃይል ሰዎች የተመረጣችሁ ምን ያህል ሰዎች ናችሁ? ያካፈላችሁት ልምድ ምንድን ነው? የተጠራችሁትስ በማን ነበር?

ካፒቴን መርሻ፡– ጥሪው ደርሶን የነበረው ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው፡፡ በእርግጥ ከቀድሞዎቹ የባሕር ኃይል አባላት በመጀመሪያ የተጠራሁት እኔ ነኝ፡፡ ጥሪውም የደረሰኝ በመከላከያ አማካይነት ነው፡፡ በወቅቱ ሊያነጋግረኝ የመጡት ሰው ባሕር ኃይል ማቋቋም እንደሚፈልጉ አጫወቱኝ፡፡ እኔም እንዴት አድርጋችሁ ለማቋቋም ፈለጋችሁ ስል መልሼ ጠየቅኩት፡፡ እርሱም ማቋቋም የምንፈልገው በብርጌድ፣ በጄኔራል እያለ ገለጸልኝ፡፡ እኔም መልሼ ይህ እኮ ጦር ሠራዊት አይደለምና እንዴት ተደርጎ ነው እንደዚያ የሚሆነው ስል አስተያየቴን ሰጠሁ። በጉዳዩ ላይ ተነጋገርን፡፡ ቀጥሎም ሌሎች የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቼን ጭምር ጠሩን፡፡ እኛን ሲጠሩን በወቅቱ በመከላከያ ሚኒስትርነት መሥሪያ ቤቱን ሲመሩ የነበሩት ኢንጂነር አይሻ ሲሆኑ፣ በወቅቱ ስለእኛ የነበራቸው ግንዛቤም በጣም ግሩም ነው፡፡

በመሆኑም ከሚመለከታቸው ጋር ተወያየን፤ የመጀመሪያው ነገር እኛ የዘርፉን መቋቋም ሁኔታ መጀመር የፈልግነው ከስር ነው፡፡ ኦፊሰሮቹ ደግሞ ያንን አልወደዱትም፡፡ በወቅቱ ደግሞ ከባሕር ኃይል ሌላ አማካሪ ነበራቸው፡፡ እንዲያም ሆኖ በወቅቱ የነበሩት ሚኒስትር ስለጉዳዩ እውቀት ነበራቸውና በመምጣታችን እና ለማማከር ዝግጁ በመሆናቸው ደስተኛ ነበሩ፡፡

በወቅቱ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል ክንዱ ገዙ ጋርም ተገናኘን፡፡ እና የሚያስፈልገው ነገር ከማክሮ ጀምሮ እንደሆነ ለመግለጽ ሞከርን፡፡ ይህ ማለት ባሕር ኃይልን ከመሠረቱ፣ ከትምህርት ቤቶቹ፣ ለየማዕረጉ ከሚሰጠው የትምህርት አይነትና ትምህርቱ ለምን ያህል ጊዜ የሚሰጥ ስለመሆኑ ለሦስት ዓመት ሙሉ ካሪኩለም አዘጋጀን፡፡

እኛ በአዲስ መልክ ለተቋቋመው የባሕር ኃይል ከመሠረቱ ጀምሮ በጠቀስኩት ልክ በየደረጃው ለሚሰጠው የትምህርት ዘርፍን ጨምሮ ለሦስት ዓመት የሚሆን ካሪኩለም እናዘጋጅ እንጂ ቀጣይ የሚሆነው ሐሳባቸውን ብዙ አላወቅም፡፡ እንደየዘርፋቸው ግን ብቁ የሚሆን የሰው ኃይል እንዲኖራቸው ስለፈለጉ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ደንብና ሥርዓቱንም (ሬጉሌሽን) ያዘጋጀን ሲሆን፣ እሱን ገና አልሰጠናቸውም።

አዲስ ዘመን፡- ደንብ እና ሥርዓቱን ያልሰጣችኋቸው ባለመጠናቀቁ ነው?

ካፒቴን መርሻ፡- እንደእሱ አይደለም፤ የሠራነውን ሰጥተናቸዋል፡፡ የሚፈልጉንን ያህል ቆይተናል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የማናስፈልግ በመሆናችን በዚያው ቀረን፡፡ በእርግጥ በብዙ ሁኔታ የመከርን ቢሆንም ያዘጋጀነውንም ደንብ ግን አልሰጠናቸውም። ደንቡን ያዘጋጀነው አራት ሰዎች ስንሆን፣ አንደኛውን አጋራችንን ሕይወቱ ያለፈው በቅርቡ ነው፡፡ አንደኛውም ትንሽ አመም አድርጓቸዋል፡፡ እኔ እና ኮሞዶር ጥላሁን መኮንን አለን፡፡ ያጠናቀቅነውም ሁለታችን ነን፡፡ የሠራነው ሰፋ ያለ ደንብና ሥርዓት በመሆኑም ሲጠይቁን ለመስጠት ዝግጁዎች ነን፡ ከዚህ ባሻገር በርካታ ሥራ ሰጥተናቸዋል፤ አማክረናቸዋልም።

አዲስ ዘመን፡- በጽሑፍ ያዘጋጃችሁትን ገና አልሰጣችሁም ማለት ነው?

ካፒቴን መርሻ፡- እሱማ በጽሑፍም ሰጥተናል፡፡ በወቅቱ እንዲያውም መመሪያውን እያዘጋጀን ባለንበት ወቅት ለምሳሌ እነርሱ 30 ሰዎችን አምጥተው ነበር። እኛም ግንዛቤ ሰጠናቸውና ራሽያ ለስድስት ዓመት ትምህርት እንዲማሩ ተላኩ፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ይምጡ አይምጡ አላውቅም፡፡ በወቅቱ ከመሄዳቸው በፊት ግን ገለጻ እንድናደርግላቸው ባዘዙን መሠረት ያለውን ሁኔታ በአግባቡ ገለጻ አድርገንላቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ተምረው መጥተው ከሆነ በዘርፉ መሥራት በሚያስችላቸው ላይ ነው መመደብ ያለባቸው ባይ ነኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት በርካታ አማራጮችን እያማተረች ነው፤ ይሄንን እንዴት ያዩታል?

ካፒቴን መርሻ፡- እኔ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የባሕር በር ታጣለች የሚል አመለካከት የለኝም፡፡ ሁሌም ቢሆን ልቤን የሚሞላው የባሕር በር ታገኛለች የሚለው ሐሳብ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የባሕር በር የግድ ማግኘት አለባት፡፡ ነገር ግን ይህን የባሕር በር ለማግኘት ጥበብ ያስፈልገዋል፡፡ ለምሳሌ ምሥራቅ አፍሪካን ብንወስድ ሱማሊያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ ስምምነት ፈጥረው አብረው መሄድ የሚችሉ አገራት እንደሆኑ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ አማራጩ የየሀገራቱ ስምምነት ነው ባይ ነኝ፡፡

ምፅዋ የኢትዮጵያ ግዛት የነበረ ነው፡፡ በወቅቱ በጣሊያን ይወሰድ እንጂ የእኛ የኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ለምሳሌ ቮሊቢያን ብንወስድ የባሕር በር የሌላት አገር ናት፡፡ ይሁንና አሁንም የባሕር ኃይል አላት፡፡ ስንት ዓመት ሆናት ባሕር ኃይል ካቋቋመች? እስካሁን ግን የባሕር ኃይል ይዞታ አላገኘችም፡፡ አሁን ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በር ሊከፍቱላቸው ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያም እንዲሁ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኘው ደግሞ በጉልበት ሳይሆን ሠላማዊ በሆነ መንገድ ነው፡፡መንግሥት ከሶማሊ ላንድ ጋር የደረሰበትም ስምምነት ሠላማዊነቱን የሚመለከት ነው፡፡

በተለይ ደግሞ በሌላ መንገድ ሌላ አማራጭ ሊሆን የሚችለው ከመሪዎቹ ባሻገር የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝብ ፍላጎቱ ምንድን ነው? የሚለው ጉዳይ መጤን አለበት፡፡ ሕዝቡ አሁንም ቢሆን እንደ አንድ ቤተሰብ የሚቆጠር ነው፡፡ ትግራይና ኤርትራ ልዩነት የላቸውም። የአንዱ አባት እዛ የሌላው እናት እዚህ ነው  ማለት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከወጣው ከዓለም አቀፍ ሕግ አኳያ ያለውን ሁኔታ እንዴት አዩት?

ካፒቴን መርሻ፡- ዓለም አቀፍ ሕጉ አንድ የባሕር በር ያለው አገር ስምምነት ላይ በተመሠረተ ሁኔታ ባሕር ሕግ እንዲያገኝ ይፈቅዳል፡፡ ደግሞም ኤርትራም ሆነች ጅቡቲም ሆነች ሌላው ጎረቤት አገር የኢትዮጵያ ባሕር በር ማግኘት እነርሱኑ የበለጠ የሚጠቅም መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ የአንዱ የጎረቤት ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ለሌላውም ጎረቤቱ የሚተርፍ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ሕጉም ቢሆን ከዚህ አንጻር ሲታይ የሚደግፈው ነው፡፡

ምክንያቱም እንኳን ኢትዮጵያ ይቅርና ቻይና፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎችም ከተለያየ አካባቢ ያውም በብዙ ሺ ኪሎ ሜትር ተጉዘው መጥተው በቀይ ባሕር አካባቢ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም። እንዲያውም ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መልሶ ማቋቋም ወቅት ከፈረንሳይ ሰው ወደ እኛ መምጣት አልነበረበትም የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ፈረንሳዮች ጅቡቲን በቅኝ ሲገዙ የነበሩና አሁንም ድረስ አብረዋቸው ያሉ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም ፡፡

አሁን ቀይ ባሕር ለሁሉም ለአካባቢው ሀገራት ስጋት እየሆነ ነው፡፡ ይሁንና ራሽያ፣ ኢራን፣ ቻይና እና አሜሪካ ሁሉ ባሉበት ኢትዮጵያ የት አለች? ኬንያ አብዛኛው ጊዜ ግንኙነት ያላት ከእንግሊዞች ጋር ነው። ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ልታብር ትችላለች፡፡፡ ሱማሊያ ደግሞ ቀድሞም ቢሆን ለኢትዮጵያም እምብዛም ወዳጅ የምትባል አገር አይደለችም፡፡ ሰለዚህ ቀይ ባሕር ላይ መብቱ እንዳይኖረን ከተደረገ እና የወደብ ተጠቃሚነታችንን ገለል የሚያደርጉ ከሆነ እንዴት እና ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ ብቻ በቂ ነው፡፡

ስለዚህ የባሕር በሩን በስምምነት መርሕም ሆነ በሕግም ጭምር መጠየቅ እንችላል፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መሄድ እንችላለን፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ወደብም ሆነ የባሕር በር የምንሻው በጦርነት አለመሆኑ ነው፡፡ የጦርነት አማራጭ የሚያዋጣ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ማን ከማን ጋር ይገዳደላል? ይህን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ባከበረ መንገድ የሚሠራ ሥራ ውጤታማ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዚህ አጋጣሚ የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖርዎ ይሆን?

ካፒቴን መርሻ፡- ግራም ነፈሰ ቀኝ የባሕር በር ማግኘት አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት። ዳር ድንበሯ ዛሬ ላይ ያለው ሳይሆን እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ የሚዘልቅ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። ስለሆነም ይህች ታላቅ አገር የባሕር በር ማግኘት የግድ ይላታል፡፡ የማግኛ ዘዴው ደግሞ በርካታ ሲሆን፣ ሕጋዊም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ነው። ይሁንና እኛ ማግኘት የምንፈልገው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሲሆን፣ እሱም በመስማማት ነው፡፡

ምክንያቱም ጦርነት መቼም ቢሆን አዋጭ አይሆንም፡፡ በቀጣይም ቢሆነም ማን ወዳጅ ማን ጠላት ነው የሚለውን በአግባቡ መለየት መልካም ነው። ወዳጅ መስለው መሣሪያ የሚሸጡ በርካታ ናቸው፡፡ ስለሆንም ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃና ሠላሟን አስጠብቃ በኢኮኖሚዋ የተዋጣላት ልትሆን ይገባታል፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ከዚህ ጎን ለጎን ራሱ እያለማ እና ለሠላም ዝግጁ እየሆነ መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ካፒቴን መርሻ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You